የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በቻን ዋንጫ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከትናንት በስቲያ ከሞዛምቢክ ጋር አድርጎ 0ለ0 በሆነ ውጤት አጠናቋል። ዋልያዎቹ በዚህ ውድድር በምድብ አንድ ከአዘጋጇ አልጄሪያ፣ ሊቢያና ሞዛምቢክ ጋር መደልደላቸው የሚታወቅ ሲሆን በውድድሩ ረጅም ርቀት ይጓዛሉ ተብሎ ከሚጠበቁ ቡድኖችም ተጠቃሽ ናቸው። ይሁን እንጂ ከሞዛምቢኩ ጨዋታ በኋላ ዋልያዎቹ በውድድሩ ረጅም ርቀት ይጓዛሉ የሚለው ግምት የመሳካቱ ነገር አጠራጣሪ ሆኗል።
ዋልያዎቹ በዚህ የውድድር መድረክ ለሦስተኛ ጊዜ እንደመሳተፋቸው ካለፉት ሁለት የተሳትፎ ታሪካቸው የተሻለ ውጤት ያስመዘግባሉ የሚል እምነት ተጥሎባቸዋል። በተጨማሪም ዋልያዎቹ ባለፈው ግንቦት በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ትልቁን የግብጽ ብሔራዊ ቡድን ከጨዋታ ብልጫ ጋር 2ለ0 ማሸነፋቸው ቻን ላይ የተለየ ትኩረት እንዲሰጣቸው አድርጓል። ምክኒያቱም ያንን አስደናቂ ጨዋታና ድል ፈርኦኖቹ ላይ ማስመዝገብ የቻለው የዋልያዎቹ ስብስብ ከሞላ ጎደል በዚህ የቻን ውድድር ላይ ተካቷል። አማካዩ ሽመልስ በቀለና አጥቂው አቡበከር ናስር በውጪ ሊጎች የሚጫወቱ ተጫዋቾች እንደመሆናቸው በዚህ ውድድር ከዋልያዎቹ ጎን አይሰለፉም። በተረፈ ግን ግብጽን ካሸነፈው ቡድን ዋልያዎቹ ያጡት ወሳኝ ተጫዋች ዳዋ ሆጤሳ ነው። ከዚህ አኳያ ዋልያዎቹ ሞዛምቢክን በቀላሉ ያሸንፋሉ ብሎ ማሰብ ጤናማ ነበር። ያምሆኖ ግን ዋልያዎቹ የምድቡን ቀላል ተጋጣሚ መረብ መድፈር ሳይችሉ ቀርተዋል። ዋልያዎቹ ምናልባትም በዚህ ውድድር የግድ ማሸነፍ ካለባቸው ሞዛምቢክን ነበር። ግን አልሆነም። ይህም በውድድሩ ለመቆየት ያላቸውን እድል ያጠበበ ሲሆን በቀጣይ ሁለት የምድብ ጨዋታዎችም ጫና ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል።
ዋልያዎቹ በሞዛምቢኩ ጨዋታ የነበራቸው እንቅስቃሴ ከቁጥር አንጻር ይገለጽ ከተባለ በኳስ ቁጥጥርና በጨዋታ የበላይነት ጥሩ ነበሩ ብሎ መደምደም ይቻላል። ይሁን እንጂ የገጠሙት እጅግ በጣም የመቀናጀት ችግር ያለበትን ቡድን እንደመሆኑ ግብ ማስቆጠር አለመቻላቸው ዋልያዎቹ ብዙ ችግሮች እንዳሉባቸው አመላካች ነው። ዋልያዎቹ የግድ በውድድሩ ለመቆየት እነዚህን ችግሮች በቀጣይ የምድብ ጨዋታዎች አርመው መገኘት ይኖርባቸዋል።
በቅዳሜው ጨዋታ በተለይም በሁለተኛው ግማሽ ላይ ለቀጣይ ሁለት ጨዋታዎች ዋልያዎቹ ማረም ያለባቸውን ችግሮች ፍንትው አድርገው አሳይተዋል። የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ቡድን የውሳኔ፣ የጉጉት፣ የጨራሽነት ችግሩን በቀጣይ ጨዋታዎች መቅረፍ አለበት።
የአሰልጣኝ ውበቱ አባተን የተጫዋቾች ምርጫ ማክበር ተገቢ ቢሆንም ቡድኑ በሁለቱ ጨዋታዎች የሚያጣውን ነገር ከሞዛምቢኩ ጨዋታ የግድ መማር ይጠበቅበታል። የዋልያዎቹ ሁለቱ ቀጣይ ተጋጣሚዎች መስመር ላይ የተሻለ እንቅስቃሴ በማድረግ አደጋ መፍጠር የሚችሉ ናቸው። የግማሽ ሜዳ አጠቃቀም አቅማቸው ያደገ ነው። ሩጫዎቻቸው እና ረዣዥም ኳሶቻቸውም ለመከላከል እና ለመቋቋም ይከብዳሉ። ይህ ማለት በሞዛምቢኩ ጨዋታ ከሁለቱ ቀጣይ ተጋጣሚዎች አንፃር ደካማ የነበረውን ሞዛምፒክ ሲገጥሙ የፈጠሯቸውን ስህተቶች እና የአጨራረስ ድክመቶች በቀጣዮቹ ሁለቱ ጨዋታዎች እንዲሁ በቀላሉ የሚታዩ ሳይሆን ዋጋ የሚያስከፍሉ ናቸው።
ግብ ጠባቂው ፋሲል ገብረሚካኤልም ሜዳ ውስጥ ያለውን የዕርጋታና የግል ቁጥጥሩን ማሳደግ አለበት። አንዳንድ የሚወስናቸው ውሳኔዎች ቡድኑንም የእሱንም የእግርኳስ ዘመን እድገት የሚቀንሱ ናቸው። በተፈጥሮው ጥሩ ግብ ጠባቂ ነው። ነገር ግን የሜዳ ውስጥ አቅሙን ማሳደግ ይኖርበታል።
የዋልያዎቹ ስብስብ ከዛሬ 15 አመት በፊት ይነሳበት የነበረው የአጨራረስ ችግር ዛሬም አብሮት አለ። ቡድኑ እንደፈለገው ኳስ ይነጥቃል ኳስ ያደራጃል በፈለገው ሰዓት የተቃራኒ ቡድን ክልል ውስጥ ይደርሳል፣ የአንድ ሁለት እንቅስቃሴዎቹም ጥሩ ናቸው፣ ነገር ግን ይሄ ኳስ እና መረብን ካላገናኘ ሶስት ሊገኝ አይችልም።
የወዳጅነት ጨዋታ ጥቅሞች ይሄና መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ ነው። ምክንያቱም ከልምምድ በላይ ጨዋታ የቡድኑን ደካማና ጠንካራ ጎን ያሳያልና።
ሞዛምቢኮች በሁለተኛው አጋማሽ እራሳቸውን ፈልገው አግኝተዋል ማለት ይቻላል። ምክንያቱም ዋልያዎቹ ኳስን መቆጣጠር እንጂ ወደ ጎል ለመቀየር ያላቸው ችኮላ ውጤታማ እንደማያደርጋቸው ተረድተዋል።
በእግር ኳስ ልምድ ወሳኙ ነገር ነው። ለዚህ ነው ልምድ ያስተማራቸውን ተጫዋቾች የየክለብም ይሁን የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች የሚፈልጓቸው። አሰልጣኝ ውበቱ በጉዳት ቡድኑ ውስጥ የሌሉትን እንደ ዳዋ ሆጤሳ ዓይነት ተጫዋቾች የሚተካ አዲስ ትውልድ መመልከት ያለባቸው ወቅትም አሁን ነው። ይህንንም አሰልጣኙ ነገ በሁለተኛው የምድብ ጨዋታ አዘጋጇ አልጄሪያን በኔልሰን ማንዴላ ስቴድየም ሲገጥሙ አስበውበት ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይጠበቃል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥር 8/ 2015 ዓ.ም