ታሪክን ወደ ኋላ መለስ ብለን ስናስታውስ አንዳንድ ቀናት ወይም ሳምንታት ወይም ወራት ብዙ የታሪክ ክስተት የተከናወነባቸው ይሆናሉ፡፡ ለምሳሌ የየካቲት እና የግንቦት ወር ብዙ የኢትዮጵያ የታሪክ ክስተት ያለባቸው ናቸው፡፡
ይህን ሳምንት ደግሞ ካየን ብዙ ታላላቅ ጀግኖች የተወለዱበት እና የሞቱበት፣ እንዲሁም የጀግኖችን ሁሉ ታሪክ የሚዘክረው የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር የተመሰረተበት ነው፡፡
ጥር 1 ቀን 1931 ዓ.ም የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ተመሰረተ፡፡ ጥር 3 ቀን 1893 ዓ.ም የጎጃም ንጉስ የነበሩት ንጉሥ ተክለሃይማኖት ተሰማ አረፉ፡፡ ጥር 5 ቀን 1937 ዓ.ም ደግሞ ጀግናው አርበኛ ደጃዝማች በላይ ዘለቀ (አባ ኮስትር) እና ወንድማቸው እጅጉ ዘለቀ ተሰቀሉ (ተገደሉ)፡፡ ጥር 6 ቀን 1811 ዓ.ም ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ቴዎድሮስ ተወለዱ፡፡ ጥር 6 ቀን 1986 ዓ.ም ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ቁልፍ ሚና የነበራቸው ስመ ጥሩው ዲፕሎማት አቶ ከተማ ይፍሩ አረፉ፡፡ ጥር 7 ቀን 1997 ዓ.ም በኮሜዲ ስራዎቹና በበጎ ፈቃድ ተግባራቱ ታዋቂ የነበረው ኮሜዲያን አለባቸው ተካ (አለቤ) አረፈ፡፡
ያሳለፍነው ሳምንት እነዚህን ክስተቶች በተለያዩ ዘመናት አስተናግዶ ነበር፡፡ የአንዳንዶቹ ብዙ የተባለለት ሲሆን የአንዳንዶቹ ደግሞ ምናልባትም ልብ የማይባል ሊሆን ይችላል፡፡ ሙሉ ታሪካቸውን በሌላ አጋጣሚ የምናየው ይሆናል፡፡ የጀግኖችን ታሪክ የሚዘክረውን የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ምሥረታ እና ታሪ ካዊ ክስ ተቶቹን እናስታውስ ፡፡
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር የተመሰረተው ከ84 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 1 ቀን 1931 ዓ.ም ነበር፡፡
ደጃዝማች ከበደ ተሰማ ‹‹የታሪክ ማስታወሻ›› በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ፣ ይህ ማኅበር በአርበኝነት ዘመን በሸዋ ክፍለ ሀገር በ1931 ዓ.ም «የጥንታዊት ኢትዮጵያ የጀግኖች ማኅበር» በሚል ስም ተሠይሞ የተቋቋመ ማኅበር እንደነበርና ዓላማውም የአርበኞችን ክብር በማበረታታትና በየሀገሩ ካሉ አርበኞች ጋር በመላላክ የሚገኘውን ሥራ ፍሬ እርስ በእርስም ሆነ በስደት ላይ ከነበሩት ንጉሠ ነገሥት ጋርም መካፈል እንደነበር ገልፀዋል።
ጥር 1 ቀን 1931 ዓ.ም ባላምባራስ አበበ አረጋይ (በኋላ ራስ)፣ ሻለቃ መስፍን ስለሺ (በኋላ ራስ)፣ ልጅ ግዛቸው ኃይሌ ወንድማማቾቹ ደጃዝማች ፀሐዩ ዕንቁሥላሴ እና ደጃዝማች ተስፋዬ ዕንቁሥላሴ፣ አቶ እምአእላፍ ኅሩይ፣ ደጃዝማች ኃብተ ሥላሴ በላይነህ፣ ደጃዝማች ታከለ ወልደሐዋርያት … በአጠቃላይ 29 ስመ ጥር አርበኞች በተገኙበት በሞጃና ወደራ (ተጉለት)፣ በልዩ ስሙ አንቀላፊኝ ሜዳ፣ ‹‹አንዲት ግራር›› በሚባለው ቦታ ለሀገር ፍቅር ሲባል ማኅበሩ ተመሰረተ፡፡
የፋሺት ጦር ተሸንፎ የኢትዮጵያ ነፃነት ከተመለሰ ከ21 ዓመታት በኋላ፣ በሚያዝያ ወር 1954 ዓ.ም ሌተናል ጀኔራል ነጋ ኃይለሥላሴ ከሥራ ባልደረቦቻቸውና ከሌሎች ሰዎች አገር አፍቃሪዎች ጋር በመሆን ‹‹ጥንታዊት ኢትዮጵያ ሀገራዊ የጀግኖች ማኅበር››ን በታደሰ ሀገራዊ ዓላማና በተሻሻለ ደንብ አቋቋሙት። ይሁን እንጂ ማኅበሩ ከመንግሥት እውቅና ያገኘው ሰኔ 19 ቀን 1956 ዓ.ም ነበር፡፡
ሌተናል ጀኔራል ነጋና ባልደረቦቻቸውም በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ አባላትን መመዝገብ ችለዋል፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ብዙ መሰናክሎችን እያለፈ ዛሬ ላይ የደረሰው ይህ ማኅበር፣ በአሁኑ ወቅት የራስ መስፍን ስለሺ ልጅ በሆኑት በልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ስለሺ እየተመራ ይገኛል፡፡
በ2006 ዓ.ም የታተመውና ‹‹እኔ ለአገሬ›› የተሰኘው የማህበሩ መጽሔት ስለአመሰራረቱ በሰፊው ያስረዳል። ከመጽሔቱ በተገኘው መረጃ፤ የማህበሩ የመጠሪያ ሥያሜ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ይባላል፡፡ ማህበሩ በዚያን ጊዜ በነበሩት ጎበዛዝትና የጎበዝ አለቆች የማስተባበሪያና የመምሪያ አካል ነው፡፡
የጀግኖች አርበኞች መሰባሰቢያና መመሪያ ጥላ የሆነው ይህ ማህበር በሰሜን ሸዋ ተጉለት አውራጃ ለመጀመሪያ ይመሥረት እንጂ ቀስ በቀስ በመስፋፋትና በመጠናከር፤ በእንግሊዝ መንግሥት በመታገዝ በ1933 ዓ.ም የወራሪውን የፋሽስት እብሪተኛ ኃይል በድል አድራጊነት ሚያዚያ 27 ቀን በታላቅ ገድል ድል ተጎናጽፏል፤ መላ አገሪቷ ነፃ ወጥታለች፤ ከዚህ ጣፋጭና አስደናቂ ድል በኋላም ማህበሩ የተቋቋመበትን ዓላማ እንዲያውትና እንዲስማማ አድርጎ መተዳደሪያ ደንቡ ተሻሽሎ ተጠናክሮ ተቋቋመ፡፡ ይህ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር መጀመሪያ አንቀላፊኝ ላይ ሲመሠረት ዓላማው የአርበኞቹን ትግል ለማሥተባበር ነበር፡፡
ማህበሩ ከድል በኋላ እንደገና ሲጠናከርና ሲቋቋም ደግሞ ዓላማ ያደረገው የአርበኝነት ትግሉንና የታጋዮቹን ታሪክ ለመዘከርና ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ፣ እንዲሁም በህይወት ያሉት ጀግኖች አርበኞች የሚደገፋበትን መንገድ ለመፍጠርና አገር ተረካቢው ትውልድ መብቱንና ግዴታውን የሚያውቅበትና የሚረዳበትን ማዕከል የሚያገለግልበትን መንገድ በማሰበም ጭምር ነው፡፡
የጥንታዊ ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ከተቋቋመ በኋላ አሁን ባለበት አራት ኪሎ የራሱን ሕንፃ በማሠራት በየጊዜው ከአርበኞቹ መካከል መሪዎቹን እየመረጠ በዚያው መንገድ ቀጥሏል። ማህበሩ የተቋቋመበትን ዓላማ ይዞ እንዲቀጥልም ይሁን የመታሰቢያ ህልውናውን በህያውነት ለማቆየት የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት የቅርብ ድጋፍና ክትትል እንዳልተለየው የመጽሔቱ መረጃ ያሳያል፡፡
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አንቀላፊኝ ላይ ሲመሠረት በሰብሳቢነትና በአባልነት የነበሩት አባት አርበኞች ቃል ኪዳን ተገባብተው ነበር፡፡ ከቃል ኪዳናቸው ውስጥ የሚከተሉት ይገኛሉ፡፡
‹‹እኛ ከዚህ በታች የመተማመኛ ቃል ፊርማችንን ያደረግን በጥንታዊት ኢትዮጵያ የጀግኖች አርበኞች ማህበር ስንገባ በጥቅምት 23 ቀን 1931 ዓ.ም የወጣውን ደንብ ወደናል፡፡ ግዴታውን ሁሉ እንፈጽማለን፡፡ ምንም ቢቸግረን በዚሁ ደንብ በአራተኛው ቁጥር እንደተፃፈው የመንፈስ ቅዱስ ወንድሞቻችንንና ጓደኞቻችንን አንከዳም፡፡ ሁለተኛ በሦስተኛው እንደተባለው የአገራችንን ነፃነት በማናቸውም ምክንያት ቢሆን ክብሯ የሚጎድልበትን፣ ጓደኞቻችን የሚጎዱበትን አንሠራም፡፡ እራሳችንም ምንም ቢቸግረን ለጠላት አንገባም፡፡
…. በሃያ አንደኛው ተራ ቁጥር እንደተፃፈው የንጉሰ ነገሥቱን መንግሥት መቃወም የለብንም። ይህንን ሁሉ ባንፈጽም የእግዚአብሔር መቅሠፍት ያጥፋን፡፡ ለዚሁም ፈፃሚ መሆናችንን ለማሳወቅ ዋሥ ጠርተናል። ጥር 1 ቀን 1931 ዓ.ም አንቀላፊኝ መንዝ›› ፊርማ መሥራች አባላት (ሹማምንት) የነበሩትም የሚከተሉት ናቸው፡፡
1. ክቡር ራስ አበበ አረጋይ፤ የክብር ሊቀመንበር
2. ባሻ ወልደኪሮስ ገብረመስቀል፤ የሥራ
ሊቀመንበር
3. አቶ ፈለቀ ዳኜ፤ ዋና ፀሐፊ
4. አቶ ደምሴ ወልደአማኑዔል፤ አባል
5. አቶ ደሣለኝ ተክለወልድ፤ አባል
6. አቶ ልሳኑ ሀብተወልድ፤ አባል
7. ልጅ ጸሐይ እንቆስላሴ፤ አባል
8. ልጅ ተሥፋዬ እንቆስላሴ፤ አባል
9. ልጅ ወልደዮሀንስ እምሩ፤ አባል
10. ልጅ ጽጌ ወልደማርያም፤ አባል
ማህበሩ ተመስርቶ፣ ኢትዮጵያም ድል አድርጋ ወራሪው የጣሊያን ፋሽስት ከኢትዮጵያ ተጠራርጎ ወጣ፡፡ ከድል በኋላ ማህበሩ መንግሥታዊ ድጋፍ እየተደረገለት፣ የጀግኖችን ታሪክ እየዘከረ እነሆ ዛሬ ድረስ ቀጥሏል፡፡
ከድል በኋላ አገሩን ላገለገለው አርበኛ ስደተኛና የውስጥ አርበኛ የመታሰቢያ ሜዳለያ ተሰጠ፡፡ ከዚህ ውጭ መንግሥት ለአርበኛው የሚሰጠው የጡረታ ክፍያ ስለሌለ ለጠየቀው አርበኛ መንግሥት ከሚያዝበት መሬት ለአርበኛው ርስት መሬት እንዲሰጠው ተደረገ፡፡
ለአርበኛው መጦሪያው ይሄው መሬቱ ሆነ፡፡ አርበኛው መንግሥት የሰጠውን መሬት አልምቶ ቤት ሰርቶ ለመንግሥት የሚገባውን ግብር እየከፈለ በሰላም መኖር ጀመረ፡፡
በንጉሣዊ ሥርዓቱ በዚህ ሁኔታ የቆየው አርበኛ እና ማህበሩ በ1967 ዓ.ም የመንግሥት ለውጥ ሲከሰት ግን ችግር ገጠመው፡፡ ንጉሣዊ ሥርዓቱን የገረሰሰው አብዮታዊው ደርግ መሬት የመንግሥትና የሕዝብ ነው የሚል አዋጅ አወጣ፡፡ በዚህ የደርግ አዋጅ ምክንያት በቢሮ የተያዘውን ቤት ብቻ በማስቀረት አርበኛው ሁሉ መሬቱንና ንብረቱን ተነጠቀ፡፡ እንዲያውም አንዳንዶቹ መነጠቅ ብቻ ሳይሆን ለሕይወታቸው የሚያሰጋቸው ሁኔታ ሁሉ ተፈጠረ፡፡ እንዲያም እንዲህም እያሉ ለቢሮ ብቻ በቀረችላቸው ቤት ማህበሩን አቆዩት፡፡
ዳግም የመንግሥት ለውጥ ተፈጠረ፡፡ ወታደራዊው የደርግ ሥርዓት ተገርስሶ ኢህአዴግ አገሪቱን ማስተዳደር ጀመረ፡፡ የማህበሩ ሰዎች ከደርግ አንፃር ኢህአዴግን ያመሰግኑታል፡፡ ምክንያቱም በ2001 ዓ.ም አዲስ ሕንጻ ለማሰራት የማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ ወስኖ ወደ ሥራ ተገብቷል፤ ሆኖም ግን ሕንጻው በተለያየ ምክንያት ሲጓተት እንደቆየ መረጃዎች ያሳያሉ። በመጨረሻም ተሳክቶ አሁን ያለውን የአርበኞች ሕንጻ ለመገንባት ተችሏል፡፡
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ጥር 7 ቀን 2015 ዓ.ም