በአገር አቀፍ ደረጃ ትልቅ እንቅስቃሴ ከሚደረግባቸው የስፖርት መድረኮች አንዱ በሰራተኛው መካከል የሚካሄደው ስፖርታዊ ውድድር ነው። በኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) አማካኝነት በየዓመቱ በሶስት የተለያዩ መድረኮች የሚካሄዱ ስፖርታዊ ውድድሮች በርካታ ቁጥር ያለው ተሳታፊ የሚያስተናግዱ ናቸው። የበጋ ወራት ውድድሮች፣ አገር አቀፍ የሰራተኞች ውድድርና ዓለም አቀፉን የሰራተኞች ቀን ሜይዴይን አስመልክቶ የሚካሄዱት ሶስት የውድድር መድረኮች በኢትዮጵያ ረጅም ዓመት ያስቆጠሩ ናቸው። እነዚህ የውድድር መድረኮች የተለያዩ ተቋማትና ድርጅቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞቻቸውን የሚያሳትፉባቸው ቢሆኑም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ 2012 መጋቢት ላይ ከተከሰተ በኋላ ባለፉት ሶስት ዓመታት ተቋርጠው ቆይተዋል። ከነገ ጀምሮ ግን በሰራተኛው የበጋ ወራት ውድድሮች እንደሚቀጥሉ የኢሰማኮ የስፖርት ክፍል አሳውቋል።
የበጋ ወራት ውድድሮች የመክፈቻ መርሃግብር ነገ በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ሲጀመር ከአርባ በላይ የሰራተኛ ስፖርት ማህበራት ተሳታፊ ይሆናሉ። የኢሰማኮ የማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊና የስፖርት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ፍሰሃፂዮን ቢያድግልኝ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ የጤና ሚኒስቴር ያወጣውን ክልከላና መመሪያ ተከትሎ ውድድሮች ተቋርጠው ቢቆዩም ሰራተኛው በያለበት አካባቢ በማህበረሰብ አቀፍ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲሳተፍ ሲደረግ ቆይቷል። አሰልጣኞችም ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ ከአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ፣ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እንዲሁም ከተለያዩ የስፖርት ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የተለያዩ ስልጠናዎችን ሲወስዱና ሰራተኞችን ማህበረሰብ አቀፍ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ሲያሰሩ እንዲሁም ወረርሽኙን በስፖርት እንዲከላከሉ ሲያደርጉ ሰንብተዋል። ከአዲስ አበባ ፐብሊክ ሰርቪስ፣ ከአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን፣ ከአንበሳ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅትና ሌሎች ተቋማትም ጋር በቅርበት በርካታ ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል። የኢሰማኮ ስፖርት ክፍል ለስፖርታዊ ውድድሮቹ የተለያዩ መመሪያዎችን ከማዘጋጀት ጀምሮ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር በርካታ አሰልጣኞች ልዩ ልዩ ስልጠናዎችን እንዲያገኙ ሲሰራ መቆየቱንም አቶ ፍስሃፂዮን አስታውሰዋል።
“የአገራችን የሰላም ሁኔታ ወደ ጥሩ ደረጃ እየተመለሰ መምጣቱን ተከትሎ የሰራተኛው ስፖርት ለወዳጅነት፣ ለሰላምና አንድነት እንደመሆኑ ሰራተኛውን አሁን ላይ ለማንቀሳቀስ ታስቧል” ያሉት የስፖርት ኮሚቴው ሰብሳቢ ስፖርት ድንበር የሌለው የሰላም መድረክ እንደመሆኑ በሁሉም አቅጣጫ ያለውን ሰራተኛ በዚህ ወቅት በውድድሮች አማካኝነት እንዲገናኝ ማድረግ ጥቅሙ የጎላ መሆኑን አስረድተዋል። በዚህም ተቋርጦ የነበረውን የሰራተኞች ስፖርት ውድድር “የሰራተኛው ስፖርት ለጤንነት፣ ለወዳጅነትና ለምርታማነት” በሚል መርህ ከነገ ጀምሮ እንዲቀጥል ተደርጓል። ይህም በስፖርታዊ መድረኮቹ ሰራተኛው የሰላምን መዝሙር እንዲዘምርና እንዲያጠናክር ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ይጠበቃል። “የዓለም ሰራተኞች ማህበር መርህ ተባበሩ ነው፣ የሰራተኛው ትብብርም ድንበር የለሽና ዓለም አቀፍ ነው፣ ሰራተኛውን ብሔር ፆታ የሚለየው አይደለም” ያሉት የስፖርት ኮሚቴው ሰብሳቢ ስፖርትም ይህን የሚያጠናክር ሁነኛ መድረክ በመሆኑ በዚህ ዓመት በሰራተኛው መካከል የሚካሄዱ ውድድሮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
ከነገ ጀምሮ በሚካሄደው የሰራተኞች የበጋ ወራት ውድድሮች ከአርባ በላይ ስፖርት ማህበራት የተውጣጡ ስምንት መቶ ስልሳ ወንዶችና ሁለት መቶ አርባ ስድስት ሴቶች በአጠቃላይ ከአንድ ሺ አንድ መቶ በላይ ተሳታፊዎች በአስር የተለያዩ ስፖርቶች እንደሚፎካከሩ ይጠበቃል። በተለያዩ ስፖርቶች የሚደረጉ ውድድሮች እንደከዚህ ቀደሙ በአዲስ አበባና አካባቢዋ በሚገኙ የተለያዩ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች የሚከናወኑ ሲሆን ሰራተኞችም እርስበርስ ልምድ የሚለዋወጡበት፣ የሚዝናኑበት የራሳቸው መድረክ እንደመሆኑ በውድድር ስፍራዎች በመገኘት ፉክክሮችን እንዲመለከት አቶ ፍስሃፂዮን ጥሪ አስተላልፈዋል። መገናኛ ብዙሃንም ይህን በርካታ ተሳታፊዎች የሚያፎካክር ትልቅ የስፖርት መድረክ በመከታተልና መረጃዎችን ለህዝብ በማድረስ እንዲተባበሩ ጠይቀዋል።
ነገ የሚጀምረው የሰራተኛው የበጋ ወራት ስፖርት ውድድር በሰራተኛው መካከል ከሚካሄዱት መሰል ውድድሮች ትልቁ መድረክ ሲሆን ለስድስት ወራት ያህልም ይቆያል። የዘንድሮው የበጋ ወራት ውድድርም ነገ ተጀምሮ እስከ መጪው ሰኔ አጋማሽ እንደሚቆይ ተጠቁሟል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥር 6/ 2015 ዓ.ም