በ16 ክለቦች መጋቢት 18/2012ዓ.ም ህጋዊ ዕውቅና አግኝቶ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር፤ በፕሪሚየርሊጉን እየመራ በርካታ አበረታች ለውጦችን በማሳየት ሶስተኛ ዓመቱን አስቆጥሯል፡፡ ስፖርት በምን መልኩ ገቢ ማመንጨት ይችላል? የሚለውን ጥያቄ በአጭር ጊዜ በመመለስ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን አብሮ የመስራት ስምምነት ከዲኤስ ቲቪ ጋር በማድረግ ለሌሎችም ተምሳሌት መሆን ችሏል፡፡ በሊጉ የሁለት አስርት ዓመታት ጉዞም በርካታ አዳዲስ ነገሮችን በማሳየትም ውድድሩ አንድ እርምጃ እንዲሻገር ምክንያት ሆኗል፡፡ አሁን ደግሞ ያለፈበትን ለመገምገም እንዲሁም መጪውን ጊዜ የሚያመላክተው የልማት ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቷል፡፡
ከክለቦች ጋር በተያያዘ አሁንም በርካታ ክፍተቶች የሚስተዋሉ ሲሆን፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ክለቦች ማሟላት የሚገባቸውን መስፈርት እንዳጓደሉም ዓመታትን ዘልቀዋል፡፡ ይህንን ጨምሮ አክሲዮን ማህበሩ በእስካሁኑ ቆይታው ያሉትን ደካማና ጠንካራ ጎኖች ለመለየት የሚያስችለው ጥናት ተዘጋጅቷል፡፡ ጥናቱም የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ቀርቦ ውይይትም ተካሂዶበታል፡፡ ይህ የግምገማ ጥናት እና ፍኖተ ካርታ እንዲዘጋጅ መነሻ ምክንያቶችም ሊጉ እና የውድድር ስርዓቱ ምን መምሰል አለበት፣ ከግለሰብ እስከ ማህበረሰብ ያለው ሚና፣ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ያለው ግንኙነት ምን ይመስላል እንዲሁም ሊጉን ዘመናዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ምክረ ሃሳቦችን ለማግኘት ነው፡፡
ጥናቱ የተዘጋጀው በባለሙያዎች ሲሆን፤ 1ዓመት ከ6 ወራት ጊዜ እንደወሰደበትም ተጠቁሟል፡፡ በዚህም የ140 ሀገራት ተሞክሮ፣ ከ200 በላይ ሳይንሳዊ ግኝቶች፣ ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ የህግ ማዕቀፎች፣ ድርጅታዊ ሰነዶች እንዲሁም ከ90 በላይ የሚሆኑ ባለድርሻ አካላት እይታ ግብዓት መሆን ችለዋል፡፡ ጥናቱ ከሜዳ ውጭ ባሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን ያደረገ ሲሆን፤ ምክረ ሀሳቦችንም አጠቃሎ የያዘ መሆኑም ጥናቱን ያካሄዱት ዶክተር ጋሻው አብዛ ትናንትና ከትናንት በስቲያ በገለጻቸው ወቅት ጠቁመዋል፡፡
የጥናቱን መካሄድ ተከትሎም የአክሲዮን ማህበሩ ቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ፤ አክሲዮን ማህበሩ ከተመሰረተ ጀምሮ ሊጉን ለማሳደግ የተለያዩ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡ በፕሪሚየር ሊጉ እንዲሁም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ያሉ ችግሮችን ለመመለስ መሰል ጥናቶች ጠቃሚ ናቸው፡፡ በመሆኑም እንደተለመደው ከውይይት በኋላ በተጨማሪ ሃሳቦች ዳብሮ ተግባራዊ እንዲሆን ጥሰት እንደሚደረገ ተናግረዋል። በመሆኑም ከአክሲዮን ማህበሩ ባለፈ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር እንዲሁም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም ለተግባራዊነቱ እገዛ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኋላፊ ባህሩ ጥላሁን፤ አክሲዮን ማህበሩ ሊጉን የማስተዳደር ኃላፊነቱን ከፌዴሬሽኑ ከወሰደ በኋላ ውጤታማ የሆነ ስራ በማከናወን ላይ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ከዚህ ባለፈ በእግር ኳስ ላይ ያተኮረ ጥናታዊ ጽሁፍ በማዘጋጀት ለውይይት በማቅረቡ ምስጋና እንደሚገባውም ጠቁመዋል፡፡ ፌዴሬሽኑን ጨምሮ የባለድርሻ አካላት መሰል ጥናቶች ሊበረታቱ ይገባል ያሉ ሲሆን፤ በእግር ኳሱ ያሉ ችግሮችም እንዲቀረፉ እገዛ እንደሚያደርግ አብራርተዋል። ችግር ፈቺ ጥናቶች ላይ የሚቀርቡ ምክረ ሃሳቦችን ወደ ተግባር ለማስገባትም ፌዴሬሽኑ የድርሻውን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል፡፡
የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በበኩላቸው፣ እግር ኳሱ በዘመናዊ መንገድ አለመመራቱ ውጤታማ እንዳይሆን ያደረገው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ክለቦችም በዓለም አቀፍ እንዲሁም ሀገር አቀፍ መስፈርቶችን አሟልተው ቢደራጁ ጥራት ያላቸው እግር ኳስ ተጫዋቾችን ለማፍራት እንደሚያግዝ ተናግረዋል። በስፖርት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት መሰል ጥናቶች ጠቀሜታቸው የላቀ መሆኑን የጠቆሙት አምባሳደር መስፍን፣፡ ሚኒስትር መስሪያ ቤቱም በዚህ ረገድ እገዛውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ገና ከምስረታው ራሱን ማወቅና ያለበትን ደረጃ መረዳት ላይ ትኩረት አድርጎ ሊጉን የማስጠናት ስራ እንደሰራ የገለጸ ሲሆን ለዚህም ሁለት ነጥብ አራት ሚሊየን ብር ወጪ አድርጓል።
በጥናቱ የሊጉን አጠቃላይ ገጽታ፣ የሊጉ ነባራዊ ሁኔታ፣ ተቋማዊ እሴት፣ የአሰራር ስርአትና የአመራር ሂደት፣ የፋይናንስና የገቢ አስተዳደር፣ የሚወርዱና የሚወጡ ክለቦች፣ የተጨዋቾች ደመወዝ አከፋፈል ሂደት፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና ሊጉ ልዩነትና አንድነትን ተዳሰዋል። በሊጉና በፌዴሬሽኑ መሃል ያለው አንድነትና ልዩነት ላይም ምክረ ሀሳብ ቀርቧል።
ሁለቱም ተቋማት መስመር እንዲሰመርላቸው የሚፈልጓቸውን የዳኞችን አስተዳደር፣ የአሰልጣኞች አስተዳደርና የተጨዋቾች ቅጥርና ዝውውር ላይ መፍትሄ የሚያመጣ ምክረ ሃሳብ የቀረበ ሲሆን ለዚህ ሲባል የ14 አገራትን ልምድ ተመርምሯል። “ዘርፈ ብዙ የግምገማ ጥናትና የልማት ፍኖተ ካርታ” በሚል የተደረገው ጥናት የኢትዮጵያን እግር ኳስ የደረሰበትን ደረጃና ያለበት እውነት እንዲሁም ያለውን ሀብት በተመለከተ የተደረገው ጥናት መፍትሄ የሚያመጣና ችግሮችንም የሚያስወግድ እንደሚሆን ተስፋ ተደርጎበታል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥር 5/ 2015 ዓ.ም