የሰርከስ ስፖርት ጅምራቸው በአዲስ አበባ ‹‹አዲስ አፍሪካ ሰርከስ ማህበር›› ውስጥ ነው። ከአስር ዓመታት በላይ አብረው በመስራት ወደ ተለያዩ አገራት በጋራ ጉዞ በማድረግ በስፖርቱ ትርኢቶችን አሳይተዋል። በአብሮነት ቆይታቸው በስፖርቱ ውጤት በማስመዝገብ ወደፊትም ከፍ ብለው አፍሪካን ሊያስጠሩ የሚችሉ ወጣቶች ናቸው።
በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ ላስ ቬጋስ 165 ሚሊየን ዶላር በፈሰሰበት ሰርከስ ዱሶሌ ሾው ላይ ተመርጠዉ ስራቸውን ከሚያቀርቡ ወጣቶች መካካል ናቸው። እነዚህ የሰርከስ ስፖርት ጥበበኞች አራት ወጣቶች ሲሆኑ ለገሰ አባ፣ ብሩክ ሞገስ፣ ወንደወሰን ሽመልስ እና ኤፍሬም ፈቃደ ይባላሉ።
ከአስራ አምስት ዓመታት በላይ ስፖርቱን መስራታቸውን የሚናገረው ብሩክ ሞገስ፣ ወደ ሰርከስ ቡድኑ ከመግባታቸው በፊት ሁሉም በየግላቸው የተለያዩ የሰርከስ ማህበራት ውስጥ ይሰሩ እንደነበር ያስታውሳል። በአንድ ቡድን ውስጥ ተጠቃለው መስራት ከጀመሩ በኋላ አንዳቸው ለአንዳቸው ብርታት በመሆን ራሳቸውን በስፖርቱ በማጎልበት ዛሬ ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሰዋል። “በዚህ አጋጣሚም የቡድን ሥራ ውጤታማ እንደሚያደርግ አይቻለሁ” ይላል ብሩክ ስለ ሰርከስ ቡድኑ ሲናገር። “እኛ ተግባብተን ተናበን እየሰራን ነው። ስራችንን የምንሰራው ስለዚህ አንዳችን ለአንዳችን ድጋፍ ነን ይህ ደግሞ ገና ከፍ ያደርገናል። ሁሉም በአብሮነት ሥራን ባህል ቢያደርግ ውጤታማ ሆነን የፈለግንበት ቦታ መድረስ እችላለን” የሚል እምነትም አለው።
በዚህ ስፖርት ለዓመታት መዝለቁን የሚናገረው ሌላኛው የቡድኑ አባል ወንደሰን ሽመልስ፣ “የምንሰራው በአገራችን ብዙም ያልተዘመረለት ነገር ግን ቢሰራበት በጣም የሚያዝናና፣ ውጤታማም የሚያደርግ ወጣቶችን ከአጓጉል ቦታዎች ከመዋል የሚታደግ ብዙዎች ራሳቸውን የሚፈትሹበት የስፖርት ዘርፍ የሆነውን የሰርከስ ስፖርት ነው” ይላል።
ለገሰ አባ በበኩሉ፤ ሁሉም ሙያ የራሱ የሆነ ሙያዊ ጥበብ እንዳለው ያስረዳል። ሰርከስ ደግሞ ጥበብን ብቻ ሳይሆን ልዩ ትኩረትን፣ አብሮነትንና መናበብን የሚፈልግ ስለሆነ ብዙዎች አይደፍሩትም። በመሆኑም በአገራችን እንደሌሎቹ ስፖርቶች አይነገርለትም ባይ ነው።
በተለያዩ አገራት እየዞርን ትርኢቶችን አቅርበናል የሚለው የሰርከስ ቡድኑ አባል ኤፍሬም፤ በጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያንና ዴንማርክ ጥበባቸውን ማሳየት እንደቻሉ ይናገራል። አሁን ደግሞ በአሜሪካ 165 ሚሊየን ዶላር በላይ የወጣበት ትልቅ መድረክ ላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ለማድረግ ለትርዒቱ ብቁ በመሆናቸው ተመርጠው እየሰሩ መሆኑን ጠቁሟል። ወደፊትም እንደ አህጉር አፍሪካንም እናስጠራለን የሚል እምነት አላቸው።
ይህ የሰርከስ ቡድን አሜሪካ የሚገኝ ትልቅ ተቋም ውስጥ ለመስራትም አጋጣሚውን አግኝቷል። ለዚህ ደግሞ ሰርከሰ ዱ ሶሌ ካምፓኒ የራሱን ለሰርከስ ሾው የሚሆኑ አርቲስቶችን ወደ ተለያዩ አገራት በማምራት ውድድሮችን በማካሄድ መስፈርቱን የሚያሟሉ ሰዎችን ሲመርጥ ቆይቷል። በዚህም ከአፍሪካ ኢትዮጵያ ውስጥ በመገኘት ከተለያዩ የሰርከስ አርቲስቶች ጋር አወዳድረው እነዚህ አራት ወጣቶች መስፈርቱን በማሟላታቸውና የተካሄደውን ውድድር በማሸነፋቸው አሜሪካ ውስጥ ወደሚገኘው ሰርከስ ዱ ሶሌ ካ ተቋም ገብተው በዓለም ላይ ካሉ ትልቁና አስደናቂ በሆነው የሰርከስ መድረክ ላይ ለመስራት ዕድል አግኝተዋል።
ወጣቶቹ የመጀመሪያ የመድረክ ስራቸውንና የተመልካቾችን ግብረመልስ ሲያስታውሱ፣ “በተለያዩ አገራት እንደ አንድ ፕሮፌሽን ስናቀርብ በጣም ደስተኞች ነበርን፤ ምክንያቱም የደከምንበትን ሥራ ለፍሬ ሲበቃ የምናይበት ቀን በመሆኑ። በምናቀርብባቸው ቦታዎች ከተመልካች የምናገኘው አስተያየት አስደናቂ ነዉ፣ ቆመዉም ያጨበጭቡልናል። አክሮባት ሾ ስለሆነም ተወዳጅነት አለዉ አዲስ አበባም ብዙ ሰርተናል” ይላሉ።
እነዚህ ወጣቶች ወደ አሜሪካ በሄዱበት አጋጣሚ ጥበባቸውን ተጠቅመው ኢትዮጵያን በብዙ መንገድ ማስተዋወቅ ችለዋል። በሰርከስ ዱ ሶሌ ተመርጠው የተቋሙ አባል ከሆኑበት ቀን ጀምሮም ይህን ተግባራቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል። በእያንዳንዱ የመድረክ ስራዎቻቸው ላይ ተመልካቾች ኢትዮጵያን እንዲያውቁ ወደ መድረክ በሚወጡበት አጋጣሚ ሁሉ በተለያዩ አርቲስቲክ ስራዎች እያስተዋወቁ ይገኛሉ። ከአፍሪካም ከነዚህ አራት ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ውጭ ይህን እድል ያገኘ የለም።
ወጣቶቹ የሰርከስ ጥበበኞች ምንም እንኳን እነዚህን ስኬቶች ቢቀዳጁም ብዙ ፈተናዎችን ማለፋቸውን ያስታውሳሉ። ይህንን ጥበብ ሲጀምሩ ልምምድ የሚሰሩበት ቦታና አልባሳትም አልነበራቸውም፤ የሚዲያ ትኩረትም አያገኙም ነበር። ” ይህ ደግሞ በሰዓት መጓዝ የነበረብንን ያህል ርቀት እንዳንጓዝ አድርጎናል። ነገር ግን እኛ ደግሞ ትልቅ ራዕይ ይዘን ስለተነሳን ለነበረብን ችግር እጅ ሳንሰጥ ዛሬ ላለንበት ትልቅ ተቋም ውስጥ ለመግባት በቅተናል” የሚሉት ወጣቶች ከእያንዳንዱ ስኬት ጀርባ የተደላደለ ነገር አይኖርምና መክፈል የነበረባቸውን መስዋዕትነት ከፍለው እዚህ ደርሰዋል።
አላማን ለማሳካት ሲባል ትጋት እንደሚያስፈልግ ለወጣቶች የሚመክሩት የሰርከስ ቡድኑ አባላት፣ “በየትኛውም የሥራ ዘርፍ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ለምንም ዓይነት ችግር ሳይበገሩ ዓላማቸውን በማስቀደም ወደኋላ ለሚጎትቷቸው ነገሮች ሳይበገሩ ለህልማቸው ቅድሚያ መስጠት አለባቸው” ሲሉም በየትኛውም ሙያ ውስጥ ያሉ ወጣቶች ካላቸው ጊዜ የተወሰነ ሰዓት ለጥበብ ሙያ ሰጥተው አጓጉል ቦታዎች ላይ ከመዋል ቢቆጠቡ ይመክራሉ። ወጣትነት ብዙ የሚሰራበት፣ የነገ ስንቅ የማዘጋጃ ጊዜ ስለሆነ ለችግር እጅ ሳይሰጡ ጊዜያቸውን በአግባቡ መጠቀም አለባቸው ይላሉ።
“በተለያዩ አገራት መድረኮችን ስናቀርብ በጣም በርካታ የቴክኖሎጂ እውቀቶችን አግኝተናል፣ ይህንን ቴክኖሎጂ በአገራችን ትልቅና ዓለም አቀፍ የሆነ መድረክ በማዘጋጀት ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም እናስባለን” የሚል ህልም ያላቸው ወጣቶች እነሱ የገጠሟቸውን ችግሮች ሌሎች እንዳይገጥማቸው፣ ወደ ኢትዮጵያ የተለያዩ አርቲስቾች መጥተው ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡበት ማዕከል ዘርግተው ትላልቅ መድረኮችን የማዘጋጀት ራእይ ሰንቀው እየተንቀሳቀሱ ነው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥር 3 /2015