የውጭ ንግድ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ነው። የኢኮኖሚ እድገት ቀጣይነት እንዲኖረው የውጭ ምንዛሬ ገቢን በማሳደግ የአገር ኢኮኖሚ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችለው ሥራዎች በመሥራት የውጭ ንግድን /የኤክስፖርት/ በማስፋት በከፍተኛ ደረጃ የማሻሻል ሥራ መሥራት በእጅጉ አስፈላጊ ነው። ኢኮኖሚው በሚፈልገው መጠን ተንቀሳቅሶ ከውጪ ምንዛሬ የሚገኘውን ገቢን ለማሳደግ ወደ ውጪ የሚላኩ ምርቶችን ጥራትን ማዕከል ያደረገ መጠን፣ አይነትና ስብጥር መጨመር እንዲሁም የውጭ ንግድ ስትራቴጂን በማስፋት በይበልጥ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሠራበት እንደሚገባ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ።
የውጭ ንግድ መስፋፋት ከፍተኛ ደረጃ መድረስ የተነቃቃ እና ሳቢ የዓለም ገበያ ፍላጎት መኖር ወሳኝ ነው። ከዚህ ባሻገር ምርቶችን በክምችት የመያዝ አዝማሚያዎችን በመግታት፣ የሕገወጥና ኮንትሮባንድ ንግድ ቁጥጥሩን በማጠናከር፣ የድንበር ላይ ንግድ አፈጻጸሙን ከሕጋዊ አሠራሩ ጋር የማስተሳሰርና የገበያ መዳረሻዎችን በማስፋት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግም መረጃዎች ያመላክታሉ።
በአገራችን ባለፈው በጀት ዓመት የወጪ ንግድ ለማሻሻል የተሰራው ሥራ ለውጥ ያስገኘና የተሻለ ውጤት የተመዘገበበት እንደሆነ ተመላክቷል። በ2015 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ 5 ነጥብ 4 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት የታቀደ ሲሆን፤ ይሕም በ2014 ከተገኘው ገቢ በ30 በመቶ ለማሳደግ የሚያስችል እንደሆነ ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ክትትል ከሚያደርግባቸው ዘርፎች ደግሞ ባለፈው 2014 በጀት ዓመት ከተገኘው 906 ነጥብ 27 ሚሊዮን ዶላር በ28 ነጥብ 19 በመቶ በማሳደግ 1ነጥብ 16 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት መታቀዱንም ነው መረጃው የሚያመላክተው። ለምሳሌ፣ በዘንድሮ በጀት ዓመት 221 ሺ 916 ቶን የቅባት እህሎች በመላክ በ2014 ከዘርፉ ከተገኘው 263 ነጥብ 78 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በ26 ነጥብ 2 በመቶ በማሳደግ 333 ነጥብ 02 ሚሊዮን ዶላር፤ እንዲሁም 274 ሺ 785 ቶን የጥራጥሬ ምርቶችን በመላክ ባለፈው በጀት ዓመት ከዘርፉ ከተገኘው 213 ነጥብ 306 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በ22ነጥብ3 በመቶ በማሳደግ 262 ነጥብ 176 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት መታቀዱን ነው የሚኒስቴሩ መረጃ የሚያመላክተው።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከውጭ ንግድ ሊያገኘው ያቀደውን የውጭ ምንዛሬ በዚህ መልኩ የሚገለጽ ሲሆን፤ ይሄን ከማሳካት አኳያም ባለፉት አምስት ወራት በርካታ ስራዎች መከናወናቸው ተነግሯል። በዚህም በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ በአምስት ወራት ውስጥ ለመፈጸም ካቀደው 1ነጥብ 528 ቢሊዮን ዶላር ማግኘቱን ነው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አቶ መስፍን አበበ የሚኒስትሩ አማካሪ የገለጹት።
በውጭ ንግድ በአምስት ወራት ውስጥ ለማግኘት ከታቀደው 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ውስጥ 1ነጥብ 528 ቢሊዮን ዶላር ማግኘት መቻሉን የገለጹት አቶ መስፍን፤ ይህም የእቅዱን 80 ነጥብ 4 በመቶ ያህል እንደተፈጸመ የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል። በውጭ ንግድ በአምስት ወር ውስጥ የተመዘገበው ውጤት ከዓምና ተመሳሳይ ወቅት አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር የዘንድሮ በጀት ዓመት የአምስት ወራት አፈጻጸም ቅናሽ ማሳየቱን ጠቅሰው፤ የ2014 አፈጻጸም 1ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር አስታውሰዋል። አጠቃላይ የአምስት ወሩ የውጭ ንግድ ገቢ 87 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ እንዳለው ነው አቶ መስፍን የሚገልጹት።
በዘርፉ ስንመለከት ግብርና 85 በመቶ፣ ማኑፋክቸሪንግ 72 በመቶ፣ ማዕድን 36 በመቶ እና ሌሎች ምርቶች 138 በመቶ አፈጻጸም አሳይተዋል። ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አፈጻጸም ጋር በዘርፍ ሲነጻጸር ግብርና 63 ሚሊዮን ዶላር ጨምሯል፤ ማኑፍክቸሪንግ 20 ሚሊዮን ዶላር፤ ማዕድን 142 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ አሳይተዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ክትትልና ድጋፍ የሚያደርግባቸው የግብርና ምርቶች የቅባት እህሎች፣ የጥራጥሬ ምርቶች፣ የብር እና አገዳ እህሎች፣ ጫት፣ እጣንና ሙጫ እና የቁም እንሰሳት ሲሆኑ ለእነዚህም ምርቶች የውጭ ንግድ የግብይት ሥርዓት ተዘርግቶላቸው በግብዓት ሥርዓቱ መሠረት ወደ ውጭ እንዲላኩ በማድረግ ለላኪዎች የተለያዩ ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግ አቶ መስፍን የሚናገሩት።
አቶ መስፍን እንዳብራሩት፤ ከግብርና ዘርፍ የውጭ ንግድ ግብይት የአምስት ወሩ ውስጥ 414 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 272 ነጥብ 8 ሚሊዮን የውጭ ምንዛሬ ገቢ ተገኝቷል። ይህም የቅባት እህሎች፣ የጥራጥሬ ምርቶች፣ የብር እና አገዳ እህሎች፣ የጫት፣ የእጣን፣ የሙጫ እና የቁም እንሰሳት ወደ ውጭ በመላክ የተገኘ ሲሆን፤ አፈጻጸሙን በመቶኛ ሲሰላ 65 ነጥብ 8 በመቶ ነው። የውጭ ንግድ ገቢው ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 272 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር ወደ 99 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ አሳይቷል። በባለፈው ዓመት የውጭ ንግድ ገቢ 371 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደነበር አስታውሰዋል።
የእያንዳንዱ ዘርፍ አፈጻጸም ስንመለከት ከውጭ ንግድ የቅባት እህሎች 69 በመቶ፣ የጥራጥሬ ምርቶች 72 በመቶ፣ ጫት 59 ነጥብ 6፣ የብእርና አገዳ እህሎች 99 በመቶ እና የቁም እንሰሳት 50 ነጥብ 3 በመቶ ማከናወን ተችሏል። ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የቅባት እህሎች የውጭ ምንዛሬ ገቢ 40 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ ያሳየ ሲሆን፤ የጥራጥሬ ምርቶች 3ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ጭማሪ አሳይተዋል። የጫትና የቁም እንሰሳት የውጭ ንግድ ደግሞ ቅናሽ ማሳየቱ ተመላክቷል።
ለውጭ ንግድ የሚላኩ ምርቶች ቅናሽ ማሳየት እንደምክንያት የሚጠቀሱት በርካታ ጉዳዮች መኖራቸውን የሚናገሩት አቶ መስፍን ፤ የአንዳንድ የጥራጥሬ ምርቶች ዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያ መቀዛቀዘ መኖሩን ይገልጻሉ። እንደ አኩሪ አተር እና የማሾ አይነት ምርቶች በዓለም አቀፉ ገበያ መቀዛቀዝ ከታየባቸው ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው። በተጨማሪም በጥራጥሬ እና በጫት ምርቶች እንዲሁም በቁም እንሳሳት የውጭ ንግድ የኮንትሮባንድ ንግድ መስፋፋቱን ጠቁመዋል። አንዳንድ ምርቶች ላይ በተለይ ቀይ ቦለቄ፣ ዝንጉርጉር ቦለቄ እና አኩሪ አተር ምርቶች የዓለም አቀፍ ገበያ ዋጋ የመቀነስ ሁኔታዎች በመታየቱ ምክንያት ገቢውን የተሻለ ያለማድረግ ሁኔታዎች ይስተዋላሉ።
የቅባት እህሎችን ስንመለከት አንዳንድ ምርቶች የኢንዱስትሪ ምርቶች የሚበዙባቸው በመሆኑ የአቅርቦት እጥረት መኖሩን ነው አቶ መስፍን የገለጹት። እንደ ኑግ እና ለውዝ አይነቶቹ ምርቶች በሻጋታ ምክንያት የዓለም አቀፍ አገራት የመግዛት ፍላጎት መቀዛቀዝ የሚስተዋል እንደሆነ ጠቅሰው፤ ዋንኛው የገቢ ምንጭ የሆነው የሰሊጥ ምርት ደግሞ በተበጣጠሰ መልኩ በላኪዎች መያዙ ለውጭ ንግድ ግብይት አቅርቦት እጥረት እንዲከሰት እንዳደረገው አንስተዋል።
አቶ መስፍን እንደሚሉት፤ የጫት ንግድ የድንበር ላይ ጫት ኮታን ሽፋን በማድረግ በኮንትሮባንድ ንግድ መስፋፋቱ በውጭ ንግድ/በኤክስፖርት/ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል። በጫት ምርት ላይ አላስፈላጊ ቀረጥ መበራከት ውጭ ንግድ/ ኤክስፖርቱ እንዳይበረታታ እያደረገ ነው። አንዳንድ አካባቢዎች የኬላዎች መበራከት የጫት ምርት በወቅቱ ወደውጭ እንዳይወጣ እንቅፋት እየሆነ መምጣቱ አመላክተው፤ የኮንትሮባንድ ንግድ ለቁም እንሳሳት የዓለም አቀፍ ገበያ መቀዛቀዝ ምክንያት እንደሆነም ያብራራሉ።
የኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከል ከጉምሩክ ጋር በመቀናጀት የተሰሩ ሥራዎች መኖራቸው የሚናገሩት አቶ መስፍን፤ የድንበር ላይ ኮታዎች እንዲቆሙ በማድረግ ከጉምሩክና ከፌዴራል ፖሊሲ ጋር በመቀናጀት ለመከላከል ጥረት እየተደረገ እንደሆኑ ይናገራሉ። ይህም በመሆኑ በርካታ ለውጦች እየተመዘገቡ ነው ይላሉ። በሌላ በኩል የዓለም አቀፍ ገበያ ዋጋ መቀዛቀዝን ለመከላከል ከኤምባሲዎች ጋር በመሆን የውጭ ንግድ መዳረሻ ከገበያዎች የመለየት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ከላኪዎች ጋር ያለውን ችግሮች በመለየት በችግሮቹ ዙሪያ ላይ የጋራ መግባባት በመውሰድ ኤክስፖርቱ እንዲሻሸል ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። ላኪዎች በገቡት ውል መሠረት ንግዱን እንዲፈጸሙ ለማድረግ የዕለት ተዕለት ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ እንደሆነም አብራርተዋል።
የውጭ ንግድ ላይ የተበራከቱትን ሕገወጦች ላይ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ሥራ እየተሰራ እንደሆነ የሚገልጹት አቶ መስፍን ፤ ይህንን የበለጠ አጠናክሮ በማስቀጠል የተሻለ ሥራ ለመሥራት የሚያስችል ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል። በዚህም ለአብነት ለረጅም ጊዜ በጂቡቲና በሱማሌ ሳይሻሻል የቆየው የጫት ንግድ ዋጋ እንዲሻሻል ተደርጓል። ቀደም ሲል 5 ዶላር የነበረውን የጫት ዋጋ አሁን ላይ ወደ 10 ዶላር እንዲገባ የተደረገ ሲሆን፤ ከዚህም በተጨማሪ ከጅቡቲና ከሱማሌ ጋር የነበረው የንግድ ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችል ሰፊ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል። በአጠቃላይ የውጭ ንግድ እንዲያሻሽሉ የሚረዱ ሥራዎች በማጠናከር እየተሰራ እንደሆነ ነው አቶ መስፍን የሚገልጹት።
በቀጣይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በውጭ ንግድ/ኤክስፖርት/ ላይ ለሚያጋጥሙ ችግሮች ለመፍታት በፖሊሲ መስራት አለበት ያሉት አቶ መስፍን፤ ከክልሎች ጋር በቅንጅት መሥራት ውጭ ንግድ ገበያን በማስፋፋት ኮንትሮባንድ በመከላከል የሚያስችል ሕገወጦች ላይ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ይናገራሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ላኪዎች ግንዛቤ እንዲያገኙ የማድረግ ሥራ የሚሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ በተለይ የኮትሮባንድ መስመሮች ሰፊ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከጉምሩክ ኮሚሽን እና ከክልሎች በመቀናጀት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ከኤምባሲዎች ጋር በመሆን የገበያ መቀዛቀዙን ለማሻሻል የሚያስችል ሥራ እየተሰራ ነው ያሉት አቶ መስፍን፤ ከኤምባሲዎች ጋር በሚሰራ ሥራ ምርቶቹ የሚላኩባቸው አገራት የውጭ ንግድ ግብይት በቀላሉ እና አመቺ በሆነ ሁኔታ ሊካሄድ በሚችልበት ሁኔታ እየተመቻቸ መሆኑ ያስረዳሉ።
የሩቅ ምስራቅና ኤዥያ አገራት በስፋት የውጭ ንግድ የሚከናወንባቸውና ምርቶች የሚላክባቸው እንደሆነ የሚናገሩት አቶ መስፍን፤ የአውሮፓ አገራት እስካሁን የተወሰኑ ምርቶች ወደ ውጭ ያልተላከባቸው ሁኔታዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል። ለዚህም ደግሞ ምክንያቱ የአውሮፖ አገሮች ጥራት ላይ ትኩረት ስለሚያደርጉ መሆኑን ጠቅሰው፤ አገሪቷ ወደ ውጭ የምትልካቸውን ምርቶች ጥራት ማረጋገጥ የሚችል ላብራቶሪ እንደሚያስፈልጋት ይናገራሉ። ከሌሎች አገሮች ጋር በጥራት ለመወዳደር በጥራት እና መሠረተ ልማት በኩል እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ሲጠናቀቁ የመዳረሻ ገበያዎች እየሰፉ እንደሚመጡ አብራርተዋል።
የንግድና ቀጠናዊ ሚኒስቴር የውጭ ንግድ የአሰራር ሥርዓት ባለማወቅ ሕገወጥ ተግባራት እንደሚፈጸሙ የጠቆሙት አቶ መስፍን፤ በዚህ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በየጊዜው እየተሰሩ በመሆኑ ሚዲያው የሚጠበቅ ድርሻ መወጣት እንዳለበት አስገንዘበዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ጥር 3 /2015