ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኮሮና ቫይረስ (COVID-19) ወረርሽኝ እና በሰላም እጦት ምክንያት ብርቱ ፈተና ገጥሞት የቆየው የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ፣ ባጋጠሙት ፈተናዎች ምክንያት ለአገራዊ ምጣኔ ሀብት የሚያበረክተው አስተዋፅዖ በእጅጉ ተቀዛቅዞ ቆይቷል። ከወረርሽኙና በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ከተፈጠሩት የሰላም መደፍረሶች፣ በተለይ ደግሞ በሰሜን ኢትዮጵያ ከተከሰተው ጦርነት፣ በፊት ዘርፉ በጥቅል አገራዊ ምጣኔ ሀብት ላይ የነበረው ሚና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቶ ነበር። በስራ እድል ፈጠራና በውጭ ምንዛሬ ግኝት አገራዊ ምጣኔ ሀብቱን የሚደግፈው ይህ ዘርፍ፣ አገሪቱ በዘርፉ ካላት አቅም አንፃር በአገራዊ ምጣኔ ሀብቱ ላይ ያለው ሚና የሚፈለገውን ያህል ባይሆንም እድገቱ መሻሻል ዕያሳየ እንደነበር አይዘነጋም።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የጎብኚዎችን እንቅስቃሴ በመገደብ፣ በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማትንና ግለሰቦችን ከስራ ውጭ በማድረግ ዓይነት ብዙ ግለሰባዊና ተቋማዊ ምስቅልቅሎች እንዲፈጠሩ አድርጓል። ኮቪድ-19 ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ከጥቂት ወራት በኋላ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ 98 በመቶ ኪሳራ ውስጥ መግባቱን የኢትዮጵያ ሆቴል ባለሙያዎች ማኅበር መግለጹ የሚታወስ ነው። ይህንን ተከትሎም ሆቴሎች የቀጠሯቸውን ሠራተኞች ከሥራ እስከማሠናበት ደርሰው ነበር። ለወትሮው በጎብኚዎች የሚጨናነቁት አንዳንድ አካባቢዎች ‹‹ኧረ የጎብኚ ያለህ!›› ብለዋል። የቱሪዝም ዘርፉ በወረርሽኙ እየተፈተነ በነበረበት ወቅት የተከሰቱት ግጭቶች (በተለይም የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት) ደግሞ የዘርፉን ችግር በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርገውበታል።
በኢትዮጵያ በቱሪስት መስህብነት ከሚያገለግሉ ሀብቶች መካከል ታሪክ፣ ባህልና ተፈጥሮ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ። በታሪክ ረገድ ላቅ ያለ የቱሪስት መነኻሪያ የሆነው የሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በጦርነቱ ምክንያት ያጋጠሙት ፈተናዎች በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድረዋል። ጦርነቱ የቱሪዝም እንቅስቃሴው እንዲቋረጥ ከማድረጉ በተጨማሪ፣ የቱሪዝም መዳረሻዎችና አገልግሎት ሰጭ ተቋማት እንዲወድሙም ምክንያት ሆኗል። በጦርነቱ የሃይማኖት ተቋማትን ጨምሮ፣ በርካታ የቱሪዝም አገልግሎት መስጫ ተቋማት፣ ሙዚየሞችና ሌሎች የታሪክና የባህል ሀብቶች ወድመዋል፤ ተዘርፈዋል። ወረርሽኙም ሆነ ጦርነቱ የውጭ አገራት ጎብኚዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጡ እንቅፋት ከመሆናቸው በተጨማሪ የአገር ውስጥ ጎብኚዎች እንቅስቃሴም ገትተዋል። ጦርነቱ የቱሪዝም እንቅስቃሴው እንዲቋረጥ በማድረግ ከዘርፉ ይገኝ የነበረውን የውጭ ምንዛሬ ከማሳጣቱ በተጨማሪ፣ ኑሯቸውን በቱሪዝም መዳረሻ አካባቢዎች አድርገው በቱሪዝም ዘርፍ የሚተዳደሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ለከፍተኛ ችግር እንዲጋለጡም አድርጓል።
በኮሮና ቫይረስ እና በሰላም እጦት ችግሮች ክፉኛ ተፈትኖ የቆየው የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ በአሁኑ ወቅት ካጋጠሙት ፈተናዎች ለመውጣት በትልቅ ትግል ላይ ይገኛል። ከሁለት/ሦስት ዓመታት በፊት ከነበረው ነባራዊ ሁኔታ ጋር ሲነፃፀር አሁን በተሻለና ቀለል ባለ ሁኔታ ላይ የሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የቱሪዝም ዘርፉ ተመልሶ እንዲነቃቃ እድል የሚፈጥር እንደሆነ ይገለፃል። በእርግጥ ቀደም ሲል የጎብኚዎችን ዝውውር በእጅጉ የጎዳው የወረርሽኙ መስፋፋት በአሁኑ ወቅት ያሳየው መቀነስ፣ የጎብኚዎችን ዝውውር በማነቃቃት የቱሪዝም ዘርፉ እንቅስቃሴ ቀስ በቀስ ቀድሞ ወደነበረበት እንዲመለስ እድል መፍጠሩ አይቀርም። የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍም የዚሁ እድል ተጠቃሚ እንደሚሆን ይጠበቃል።
ሌላው ለኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ መነቃቃት እድል እንደሚፈጥር የሚጠበቀው በዘርፉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሎ ለነበረው ለሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት መቋጫ ይሆን ዘንድ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግሥትና በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት ነው። ስምምነቱ ሰላም እንዲሰፍን በማድረግ አጠቃላይ የዘርፉ እንቅስቃሴ እንዲሻሻል ከፍተኛ የሆነ በጎ አስተዋፅዖ ይኖረዋል። ስምምነቱ ጦርነቱ በአገር ገፅታ ግንባታ ረገድ ፈጥሮት የነበረውን በጎ ያልሆነ መልክ በመቀየር ጎብኚዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ መበረታታትን ይፈጥራል። በዚህም የቱሪስቶች ፍሰት እንዲጨምርና ቆይታቸው ሰላማዊና የተራዘመ እንዲሆን በማድረግ ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ እንዲጨምር ያስችላል።
የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃትን እያሳየ እንደሆነ የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቋል። ከስምምነቱ መፈረም በኋላ ለጉብኝትና ለስራ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የውጭ አገራት ዜጎችና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የገለፀው ሚኒስቴሩ፣ ይህ ሁኔታ በቀጣዮቹ ጊዜያትም እንደሚቀጥል ጠቁሟል። ይህ መረጃ የሚያመለክተው የሰላም ስምምነቱ ትሩፋቶች ገና በጠዋቱ ለቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃት በጎ አስተዋፅዖ ማበርከት መጀመራቸውን ነው።
የሰላም ስምምነቱ የቱሪዝም ዘርፉ በጊዜያዊነት እንዲነቃቃ ከማስቻሉም በላይ ዘላቂ የሆነ እድገት እንዲኖረውም ያግዛል። ቱሪዝም ሰላምን በእጅጉ የሚሻ ዘርፍ በመሆኑ ስምምነቱ ሰላምን በማስፈን የቱሪስቶች ፍሰት በቋሚነት እንዲጨምር እንዲሁም በጦርነቱ የወደሙ የቱሪዝም ተቋማት መልሰው እንዲገነቡ በማድረግ የቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃትና እድገት ቋሚ/ ዘላቂ እንዲሆን ያስችላል።
ሰሞነኛ ሁኔታዎችም ለቱሪዝሙ ዘርፍ መነቃቃት እድል የሚፈጥሩ ተጨማሪ መልካም አጋጣሚዎች ናቸው። በተለይ በጥር ወር በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚከናወኑ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ኹነቶች የዚህ መልካም አጋጣሚ ዋነኛ ማሳያዎች ናቸው። ደማቅ በሆነ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ስርዓቶች የሚከወኑት እነዚህ በዓላትና ጨዋታዎች የጎብኚዎችን ቀልብ የሚስቡና ለብዙ ዜጎች የስራ እድሎችን በመፍጠር ገቢ የሚያስገኙ እንደሆኑ ይታወቃል። ከእነዚህም መካከል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) የተመዘገበው የጥምቀት በዓል ዋነኛው ተጠቃሽ ነው። በዓሉ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በድምቀት የሚከበር ኃይማኖታዊ ክዋኔ ከመሆኑ ባሻገር በበዓሉ ላይ የሚስተናገዱት ልዩ ልዩ ባህላዊ ጨዋታዎች የበዓሉን ድምቀት ከፍ የሚያደርጉ ተጨማሪ ቅመሞች ናቸው። እነዚህ ጨዋታዎች የጎብኚዎችን ቀልብ በመሳብ ረገድ ትልቅ ሚና አላቸው። ስለዚህ እነዚህን ሰሞነኛ ክዋኔዎች በስፋት በማስተዋወቅና ባህልና ስርዓቱን በጠበቀ መልኩ በማከናወን የቱሪዝሙ ዘርፍ እንዲነቃቃ ማድረግ ይገባል። በአጠቃላይ ወቅታዊ ሁኔታዎች (የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መቀነስ፣ የሰላም ስምምነቱ፣ ሰሞነኛ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ክዋኔዎች…) የፈጠሯቸውን መልካም አጋጣሚዎች በሚገባ በመጠቀም በተደራራቢ ፈተናዎች የተጎዳውን የቱሪዝሙን ዘርፍ ማነቃቃት ይገባል።
በተደራራቢ ችግሮች ምክንያት ዘርፈ ብዙ ፈተናዎች የገጠሙት የኢትዮጵያ ቱሪዝም ከገጠመው ችግር እንዲወጣ አስቸኳይ የማገገሚያ ሥራዎችን ማከናወን ያስፈልጋል። ከዚህ አንፃር ጉዳት ያስተናገደውን ማኅበረሰብ በማነቃቃት የማኅበረሰቡ እንቅስቃሴ በፍጥነት እንዲያገግም ማድረግ፣ የወደሙ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን መልሶ ማልማት፣ የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ማበረታታት፣ በቀጣይም የቱሪዝም ዘርፉ የኢንሹራንስ አገልግሎት እንዲኖረው ማድረግ… ይገባል።
ፒያንኪ ዘኢትዮጵያ
አዲስ ዘመን ጥር 2 ቀን 2015 ዓ.ም