ሁሉም ሰው የተፈጠረበት አንድ ትልቅ ዓላማ አላው፤ ለዚህ የሚታደሉት ግን ጥቂቶች ብቻ ናቸው። የሁሉም ስኬቶች መጀመሪያና መጨረሻ ደግሞ እራስን መስሎ መኖር ነው። ከምንም በላይ ስኬታችን ከራስና ከአካባቢ አልፎ ለሀገር መትረፍ ሲችል ደግሞ ይሄ ትክክለኛው የስኬት ጥግ ነው። ለዚህ ከታደሉት ጥቂት ሰዎች መካከል የዛሬው የፋሽን አምድ ርዕሳችን የሆኑት የባህል አልባሳት ባለውለታ አንዷ ናቸው።
ታዲያ ስለፋሽን እያወራን በኢትዮጵያ ባሕላዊ የፋሽን ጥበብ ውስጥ ግዙፍ አሻራቸውን ማሳረፍ ስለቻሉት ስለ እኚህ ታላቅ ሴት ባናነሳ ታሪክና የሠሩት ሥራዎቻቸው ይወቅሱናልና በዛሬው የፋሽን ገጻችን ስለታላቋ የባሕል ልብስ ዲዛይን ሥራቸው ታሪካቸውን አስደግፈን ልናስነብባችሁ ወደድን።
አብዛኛዎቻችን ማለት ይቻላል የባሕል ልብሶቻችን ትዝ የሚሉንና ከየመስቀያው እያወረድን የምንለብሳቸው በበዓላት ቀን ነው። ለእኚህ ሴት ግን የባሕል አልባሳት ከመድመቂያነት አልፎ ልዩ ትርጉም አላቸው። ለእርሳቸው ሁሌም በዓል ነውና በዓመት ለ365 ቀናት በባሕል ልብስ ተውበው፣ ውብ የሆነውን የኢትዮጵያን ባህል ለዓለም አሳይተዋል። ታላቋ፣ የመጀመሪያዋ የሀገራችን የፋሽን ልብስ ዲዛይነርና የባህል አምባሳደር ወይዘሮ ጽዮን አምዶም(እማማ ጽዮን)።
እማማ ጽዮን አንዶም፣ በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ስለሚወደሰው የሌላኛው የሀገር ባለውለታና የጦር ጀግናው አማን ሚካኤል አንዶም ታላቅ እህት ናቸው። የተወለዱት በሱዳንዋ የካርቱም ከተማ ውስጥ ቢሆንም ለሀገራቸው ከነበራቸው ጥልቅ ፍቅር የተነሳ ሁሉንም ነገር ትተው የሴቶችን የባሕል ልብስ ዲዛይን ወደማድረግና ባሕላቸውን ወደ ማስተዋወቅ ሥራ ገቡ።
ስለሀገራቸው ባሕል ለማወቅና ለመጨነቅ የነበራቸው ዕድል በጣም ጠባብ ብትሆንም እሳቸው ግን በመርፌ ቀዳዳ አምልጠው ብዙዎች ትኩረት ወዳልሰጡት የባሕል ፋሽን ፊታቸውን አዞሩ። ሀሳቡ ከብዙ ነገሮች አንጻር ከባድ ቢሆንም ሁሉንም በጽናት ተቋቁመው በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያዋ የሴቶች የባሕል ልብስ ዲዛይነር፣ እንዲሁም እንቁ የባሕል ፈርጥ ለመሆን በቅተዋል።
ብዙዎች የባሕል ልብሳቸውን በመልበስ ለቀናትና ለሳምንታት በተለያዩ መድረኮች ሀገራቸውን ባሕላቸውን አስተዋውቀው ሊሆን ይችላል፤ እሳቸው ግን በሳሎን፣ በጓዳው ለ365 ቀናት በመልበስ ሰለቸኝ ታከተኝ ሳይሉ እድሜ ዘመናቸውን ኖረዋል። ይህንን የሚያደርጉት ከየልብስ መደብሩ ሸምተው ሳይሆን ከቤታቸው ውስጥ በራሳቸው ፈጠራ ዲዛይን እያደረጉ በማዘጋጀት ነበር። ከወጣትነት እስከ እርጅናቸው ለዚህ ዓላማቸው የሚሆን ልዩ ልዩ ዲዛይኖችን በመፍጠርና በመሥራት ያሳለፉት እማማ ጽዮን በየቀኑ በአዳዲስ የባሕል ልብስ ይታዩ ነበርና በዚህ ድርጊታቸው የሚገረሙ ወዳጅ ዘመዶቻቸውም ‹‹እማማ አሁን እኮ እድሜዎ ገፍቶ ጥቁር ሀር ጸጉርዎም ቀለሙን ቀይሮ ጥጥ መስሏል እርሶ ግን ሁሌም በባህል ልብስ ተውበው እንደ ልጅ የሚፈነድቁበት ምስጢር ምንድነው?›› ብለው ሲሏቸው የእሳቸውም ምላሽ “ከቤቴ መሶብ ሙሉ እንጀራ እያለ አመል ካልሆነብኝ በቀር እንዴት ለልመና ጎረቤት እሄዳለሁ፣ ሀገሬ ለኔ አይደለም ለማንም የሚተርፍ የሸማ ጥበብ አላት። ሁሉ ነገር በእጄ እያለ የባዕዱን ከቋመጥኩማ ይሄ ነውር ነው። እንዲያው የፈረንጁን ስለብስ ሰውነቴን ይኮሰኩሰዋል። የባሕል ልብሴን በለበስኩ ጊዜ ግን መንፈሴ ይታደሳል ገና አንድ ፍሬ ልጅ እንደሆንኩ ያህል ይሰማኛል።” በማለት ይመልሱ ነበር።
ይህንን የሚያደርጉበት ዓላማ ለሰዎች አምሮ ለመታየት ወይንም ለመወደስ አልነበረም፤ ይልቁንስ ከጅምር እስከ ፍጻሜ የነበራቸው ዓላማ በሀገር ኩራት፣ በፋሽን ፈጠራና በባሕል ማስተዋወቅ ሥራ ከራስ አልፎ ለሌሎች ምሳሌ መሆንና ሀገራቸውን በራሷ ባሕል ከፍ ማድረግ ነበር። ሕልማቸው ከስሞ አልቀረምና ሀገር በቀል የሆኑ ቁሳቁሶችን በመጠቀም ብቻ የኢትዮጵያ የባሕል አልባሳት በዘመናዊ መልኩ ለገበያ እንዲቀርቡ ያደረጉ የሀገር ባለውለታ ናቸው።
በተለያዩ ጊዜያት ወደተለያዩ ሀገራት ይጓዙ ስለነበረ በሄዱበት ሁሉ የባሕል አልባሳቱን በመልበስ የኢትዮጵያን ውብ ባሕል በተዋበ መልኩ ለማሳየት ችለዋል። በኢትዮጵያ አሁን የሚለበሱትን የሴት ባሕላዊ አልባሳት ሸማኔ ግቢያቸው ቀጥረው፣ ዲዛይን አድርገው እራሳቸው እየሰፉ፣ እየለበሱ ሌላውም እንዲለብስ ትልቁን አስተዋጽዖ አድርገዋል!!!
የእርሳቸው የጥለት ዲዛይን ሥራዎች ዘመን ተሻጋሪና በብዙ የባሕል ተከታዮች ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፉ በመሆናቸው አሁንም ድረስ በባሕላዊ አልባሳት ገበያ ላይ ይገኛሉ። ለእርሳቸው እውቅናና ክብር ሳንሰጥም እየተጠቀምንባቸው ነው።
ለ60 ዓመታት ያህል ከሀበሻ ጥበብ ውጭ ምንም አይነት የፈረንጅም ሆነ ሌላ ልብስ ለብሰው የማያውቁት እማማ ጽዮን የራሳቸው የሆነውን ጽዮን ጥበብን በማቋቋም በመኖሪያ ቤታቸው ሸማኔዎችን ቀጥረው በተለያዩ ዲዛይን ፈጠራዎች እየተጠበቡ አልባሳቱን ያመርቱ ነበር። ታዲያ ያመረቱትን የሴቶች የባሕል ልብስ ጽዮን ጥበብ ከተሰኘው ከሀገር ውስጥ ሱቆቻቸው አልፎ በአውሮፖ ሀገራት ውስጥም በራሳቸው መደብር ለባሕል ልብስ ተከታዮች ያቀርባሉ።
እንደ ሚለብሱት ልብስ ሥነ ምግባራቸውና አነጋገራቸውም የተዋበ እና በበጎ አድራጎት ሥራቸውም የተመሰገኑ እንደነበሩ የሚነገርላቸው እማማ ጽዮን አማርኛ፣ ትግሪኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ዓረቢኛና ጣሊያንኛ አቀላጥፈው ይናገራሉ። ብዙዎች ስማቸውን እንኳን ለማስታወስ በሚከብዳቸውና ምርኩዝ ተደግፈው በሚቆሙበት በዚያ እድሜ እሳቸው ግን ዓላማቸውን ሳይዘነጉ ለኖሩለት ዓላማ በወኔ ቆመው ሀገራዊ መውደዳቸውን አሳይተዋል። እድሜያቸው 90 ከሞላ በኋላ እንኳን መኪና ያሽከረክራሉ። ምግብ ማብሰልና ጽዳትም ሌላው የሚያስደስታቸው የየዕለት ተግባራቸው ነበር።
የሕይወት ዘመን ሩጫቸውን በድል ያጠናቀቁት እኚህ ሴት የሀገር ባህል ልብሳቸውን ለብሰው እንደተዋቡ አይቀሬውን ሞትን ሲጠባበቁት ቆይተው፣ በስተመጨረሻም በአንድ መቶ ዓመታቸው ኅዳር 29 ቀን 2015 ዓ.ም ዳግም ላይመለሱ ከነግርማ ሞገሳቸው አሸለቡ። በሕይወት ዘመናቸው በኢትዮጵያ ባሕላዊ የፋሽን እድገት ውስጥ የሠሩት ሥራም ለኢትዮጵያ ሴቶች ብቻ ሳይሆን ለሙሉ ትውልድ ማሳያና ዓርአያ ነው። ለሠሩት ሠራ የሚገባቸውን እውቅና ባያገኙም ሕያው ሥራዎቻቸው ለትውልድ ተርፏልና ክብር ለባሕል አምባሳደራችን!
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ጥር 1/2015