ባለፈው ሳምንት በ82 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ፔሌ ባለፈው ረቡዕ ስርዓተ ቀብሩ ተፈፅሟል። በፈረንጆቹ 1940 በደቡብ ምሥራቅ ብራዚል ከድሃ ቤተሰብ የተወለደው ፔሌ፣ ድህነትን ለማሸነፍ ጫማ ከመጥረግ በዘለለ ብዙ ችግሮችን ተጋፍጣል። ችግሮቹን አሸንፎም በእግር ኳሱ የማይረሳ ታሪክ ጽፏል። በዚህም መላው ዓለም በእግር ኳስ ንጉሥነቱን እንዲቀበል አድርጋል። ኤዲሰን አራንቴስ ዶ ናሲሜንቶስ ወይም ፔሌ፣ ሦስት የዓለም ዋንጫዎች በማንሳት በታሪክ ብቸኛው ከመሆኑ በተጨማሪ በርካታ ግቦችንም በማስቆጠር የክብረወሰን ባለቤት ነው። ፔሌ የእግር ኳስ ነገር ሲነሳ ስሙ በቀዳሚነት የሚጠቀስ እና ታሪኩ ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታት በመላው ዓለም የናኘ ሰው ቢሆንም ብዙ ያልተነገረ ታሪክና ገጠመኝ አለው። ከነዚህ መካከል ጥቂቶቹን በዛሬው የስፖርት ማህደር አምዳችን እንመልከት።
ጊዜው እኤአ 1968 ነው፣ የብራዚል ቡድን ለኦሊምፒክ ዝግጅት ይረዳው ዘንድ ከኮሎምቢያ አቻው ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ ቦጎታ ነበር። በወቅቱ ቀይ ካርድ የሚባል ነገር የለም፣ የጨዋታው ዳኛ ጉሌርሞ ቬላስጌዝ ፔሌ በኮሎምቢያ ተጫዋች ላይ ጥፋት በመፈጸሙ ከሜዳ እንዲወጣ አዘዙ፣ በዚህ ጊዜ በስታዲየሙ ውስጥ ቀውጢ ተፈጠረ። ብራዚላውያኑ ተጫዋቾች የቡድናቸው ወሳኝ ተጫዋች ከሜዳ እንዲወጣ መታዘዙ አስቆጣቸው፣ የእግር ኳሱን ኮከብ ለመመልከት ስታዲየም የታደሙት ኮሎምቢያውያንም የፔሌን ከሜዳ መባረር በመቃወማቸው ግርግር ተፈጠረ። ዳኛውም በተፈጠረው ውዝግብ መሃል ጉሸማ ደርሶባቸው ፊሽካቸውን ለአንደኛው የመስመር ዳኛ አስረክበው ከሜዳ ሲወጡ፣ ፔሌ ወደ ጨዋታው እንዲመለስ ተደርጎ ግጥሚያው የቀጠለበት አጋጣሚ ፔሌ ምን ያህል ተፅዕኖ እንደነበረውና በሁሉም ዘንድ እንደሚወደድ ያሳየ ነው።
ሌላው ፔሌ ሲነሳ ጨዋታ ለማየት ተኩስ አቁም የተደረገበት አስደናቂ አጋጣሚ ነው። እኤአ በ1960ዎቹ ፔሌ የሚጫወትበት የሳንቶስ ቡድን በዓለም ላይ ካሉ ዝነኛ ክለቦች መካከል አንዱ በመሆኑ፣ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያስገኙ የወዳጅነት ጨዋታዎችን በዓለም ዙሪያ እየተጓዘ ያደርግ ነበር። ከእነዚህ ጨዋታዎች መካከል ሳንቶስ በ1969 በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ወደ ነበረችው አፍሪካዊት አገር ናይጄሪያ በመሄድ በቤኒን ከተማ ካለ ቡድን ጋር ተጋጥመው 2 ለ 1 አሸንፏል።
በወቅቱ ቢያፍራ የተባለችውን ግዛት ከናይጄሪያ ለመገንጠል የተጀመረ ጦርነት ይካሄድ ነበር። ፔሌ የሚገኝበት የሳንቶስ ቡድን የደኅንነት ስጋት ስለነበረው ለጨዋታ ከማምራቱ በፊት ተዋጊዎቹ ወገኖች ተኩስ ለማቆም ተስማምተው ነበር።
በእርስ በርስ ጦርነቱ የሚሳተፉት ወገኖች ጨዋታው በሚካሄድበት ወቅት ጦርነቱን እንደሚያቆሙ እና አንዳቸው በአንዳቸው ላይ ጥቃት እንደማይሰነዝሩ አረጋግጠዋል።ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ዝነኛው ፔሌ በቡድኑ ውስጥ መካተቱ ነበር።
የሳንቶስ ቡድን ተጫዋቾች እኤአ በ1972 ለግጥሚያ ወደ ካሪቢያኗ አገር ትሪንዳድ ኤንድ ቶቤጎ ለግጥሚያ በሄዱበት ጊዜ በአገሪቱ ሰላም ስላልነበረ በቶሎ ግጥሚያቸውን አደርገው ወደ አገራቸው ለመመለስ ጓጉተው ነበር። ነገር ግን በጨዋታው ላይ በ43ኛው ደቂቃ ፔሌ ግብ ሲያስቆጥር ያልጠበቁት ነገር ተከሰተ። በስታዲየሙ የነበሩት ተመልካቾች በደስታ ሜዳውን ጥሰው ገቡ። ከዚያም ግብ ያስቆጠረውን ፔሌን በትከሻቸው ላይ ተሸክመው ከስታዲየም ውጪ ይዘውት በመውጣት በጎዳናዎች ላይ እየጨፈሩ ደስታቸውን ይገልጹ ነበር። በወቅቱ ከቡድኑ አባላት ተለይቶ በደጋፊዎቹ ወደ ጎዳና የተወሰደውን ፔሌን ከትከሻቸው ላይ አውርዶ ከቡድኑ ጋር ለመቀላቀል ከፍ ያለ ጥረት ተደርጋል።
ፔሌ ድንቅ አጥቂ ብቻ አልነበረም፣ በተቃራኒው ግብ ጠባቂ ሆኖ በተጫወተበት አጋጣሚ አንድም ጊዜ ግብ አለማስተናገዱ ብዙዎችን ያስገርማል። ፔሌ ቡድኑ ሳንቶስ በተጫወተባቸው ዓመታት አራት ጊዜ ግብጠባቂ ሆኖ የመሰለፍ እድል ገጥሞታል። አንደኛው ቡድኑ ለብራዚል ቻምፒዮና ለግምሽ ፍጻሜ በደረሰበት ወቅት ነበር። ፔሌ በግብ ጠባቂነት በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች ላይ አንድም ግብ ተቆጥሮበት አያውቅም።
ፔሌ በተነሳ ቁጥር የሚታወስ አንድ ታሪክ አለ። ይህ ታሪክ ከኢትዮጵያው የስፖርት አባት ይድነቃቸው ተሰማ ጋር የተያያዘ ነው። እኤአ በ1970 13ኛው የዓለም ዋንጫ በሜክሲኮ እየተካሄደ ነበር። ዓለም ዋንጫውን አስመልክቶ ለኢትዮጵያውያን ትንታኔ ያቀረቡት ይድነቃቸው ተሰማ ሲሆኑ ጥያቂያቸውን ለማቅረብ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በሚሰራጭ ፕሮግራም ላይ 10 የስፖርት ጋዜጠኞች ተገኝተዋል። ደምሴ ዳምጤ ከኢትዮጵያ ሬድዮ፤ ግርማ ሰይፉ ከአዲስ ዘመን፤ በሃይሉ አስፋው ከዛሬይቱ ኢትዮጵያ፤ ኢብራሂም ሃጂ ከበሪሳ ጋዜጣ፤ ሰለሞን ገብረእግዚአብሕር ከኢቲቪ፤ ይንበርብሩ ምትኬ ከኢትዮጵያ ሬድዮ፤ ሃድጉም መስፍን ከዓልአለም ጋዜጣ፤ ገዛህኝ ፂዮን መስቀል ከኢዜአ እና አዋያዩ ፀጋ ቁምላቸው ነበሩ።
90 ደቂቃዎችን በፈጀው መግለጫ ላይ ላይ ከቀረቡ ጥያቄዎች አንዱ ከፔሌና ከማራዶና የቱን ያደንቃሉ? የሚል ነበር። ይድነቃቸው ምላሽ ሲሰጡ ‘’አንድ ያልገባችሁ ነገር ፔሌን አናውቀውም ስትሉ እራሳችሁን ልጅ ማድረጋችሁ ነው? ወጣት ነኝ ለማለት ካልፈለጋችሁ በቀር ፔሌ ሲጫወት አይታችሁታል። ማራዶና በአሁኑ ትውልድም እንደምናየው ጥሩ ተጫዋች ነው ግን ግራኝ ነው” ብለው ማስረዳታቸውን ሲቀጥሉ ሁለቱን ተጨዋቾች ማነፃፀር በእጅጉ እንደሚከብድ ሊያመለክቱም ሞክረዋል። ፔሌ በሁለቱም እግሮቹ እንደሚጫወት፤ ሰውነቱም የተደላደለ እንደሆነና ኳስን የመቆጣጠር ብቃቱ በጣም የተሻለ መሆኑን ይድነቃቸው አስረድተዋል። ማራዶና ብዙ ጊዜ ኳስን በእራሱ እንደማይነካ ፔሌ በአንፃሩ ብዙ ጎሎችን ያስገባው በጭንቅላቱ ገጭቶ እንደሆነና ፍጥነቱም እንደሚያስደንቅ አብራርተዋል። ማራዶና ሰባት የእንግሊዝ ተጫዋቾችን አብዶ ሰርቶ ማግባቱ አለምን ማስደነቁን የጠቀሱት ይድነቃቸው፤ ፔሌ እስከ ዘጠኝ ተጫዋቾችን አብዶ ሰርቶ ማግባቱን ይህን ብቃቱንም ከ30 ጊዜ በላይ እንደደገመው አስቀምጠዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 30 /2015