በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካዊ ‹‹የንግድ ጄት›› አብራሪ የሆኑትን ኢትዮጵያዊው ካፒቴን አለማየሁ አበበን እናስታውሳለን። እኝህ ኢትዮጵያዊ ባለ ታሪክ በ93 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም የተለዩት ከአምስት ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ታኅሣሥ 26 ቀን 2010 ዓ.ም ነበር።
ካፒቴን አለማየሁ ገና ከአስር ዓመታቸው ጀምሮ አውሮፕላን በሰማይ ላይ ሲበር ሲያዩ አውሮፕላን አብራሪ የመሆን ሕልም እንደነበራቸው በተለያዩ ጸሐፊያን የተሰነደው ታሪካቸው ያሳያል። ህልማቸውን ለማሳካት ጠንካራ ትጋትና ስነ ምግባር የነበራቸው ካፒቴን አለማየሁ፣ በ1955 ዓ.ም የመጀመሪያውን ‹‹የንግድ (Commercial) ጄት›› በማብረር በዘርፉ ፈር ቀዳጅ ኢትዮጵያዊ እንዲሁም አፍሪካዊ ለመሆን በቅተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ1950ዎቹና በ1960ዎቹ ወደ ጄት ዘመን ሲሸጋገር ከፋና ወጊ አብራሪዎች ተጠቃሹ ካፒቴን አለማየሁ አበበ ነበሩ። የመጀመርያውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ‹‹ቦይንግ 720B›› አውሮፕላን በካፒቴንነት ያበረሩት ካፒቴን አለማየሁ፣ በዚሁ ተግባራቸው ‹‹የመጀመሪያው›› አፍሪካዊም ናቸው። በኅዳር 1955 ዓ.ም ቦይንግ ጄት ከሲያትል (አሜሪካ) ከቦይንግ ፋብሪካ አውሮፕላኑን እንዲያመጡ የተደረጉት ካፒቴን አለማየሁ አበበ እና ካፒቴን አዳሙ መድኃኔ ነበሩ።
ካፒቴን አለማየሁ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ለመቀላቀል የቻሉት በኢትዮጵያ አየር ኃይል በኩል በማለፍ ነው። በወቅቱ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በከፍተኛ ውጤት ያጠናቀቁ ተማሪዎች ወደ አቪዬሽን ትምህርት እንዲገቡ ሲደረግ ከዕድሉ ተጠቃሚዎች መካከል አንዱ ካፒቴን አለማየሁ ነበሩ። በ1943 ዓ.ም ምርጥ የሆኑ አብራሪዎች ከአየር ኃይል ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲዛወሩ በተወሰነው መሠረት፣ ካፒቴን አለማየሁ ከተመራጮቹ አንዱ መሆን ችለው የኢትዮጵያ አየር መንገድን ተቀላቀሉ።
በሦስት አስርታት ዓመታት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአገልግሎት ዘመናቸውም ከመጀመርያ የበረራ መኰንንነት እስከ ካፒቴንነት (ከየመጀመርያው የቦይንግ 720B ጄት ካፒቴንነት) እስከ አየር መንገዱ የበረራ ዘርፍ ምክትልና ዋና ኃላፊነት (ከ1948 እስከ 1960 ዓ.ም) ድረስ ሠርተዋል። ከ1961 እስከ 1972 ዓ.ም. ደግሞ የዓለም አቀፍ በረራዎች ዳይሬክተር፣ የበረራ ኦፕሬሽን ረዳት ጄኔራል ማኔጀር ሆነው አገልግለዋል። በ1968 ዓ.ም. የመጀመርያው አፍሪካዊ የቦይንግ 707 ጄት ካፒቴን ሆነው ሲሾሙ፣ በ1972 ዓ.ም የጄት ካፒቴኖች ፈታኝ በመሆን አገልግለዋል።
ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ አገልግሎታቸውን በ1974 ዓ.ም ፈጽመው ከተሰናበቱ በኋላ፣ በኡጋንዳና በየመን አየር መንገዶች ውስጥ በአሠልጣኝነትና በአማካሪነት ለአምስት ዓመታት ያህል ሰርተው የበረራ ምዕራፋቸውን ቋጭተዋል።
ካፒቴን አለማየሁ አበበ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ስራ አስፈፃሚ የነበሩትን ኮሎኔል ስምረት መድኃኔን እንዳስተማሯቸው ታሪካቸው ያስረዳል።
በሦስቱ መንግሥታት ዘመን በከፍተኛ የአገርና የሙያ ፍቅር አገራቸውን ያገለገሉት ካፒቴን አለማየሁ፣ ባለትዳርና የአራት ሴቶችና የአራት ወንዶች ልጆች አባት፣ እንዲሁም የአራት የልጅ ልጆች አያት ነበሩ። ዕውቅታቸውንና ልምዳቸውን ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ በማሰብም በ1997 ዓ.ም ‹‹ሕይወቴ በምድርና በአየር›› የሚል መጽሐፍ አሳትመዋል።
በዚሁ እግረ መንገድ ስለኢትዮጵያ አየር መንገድ ታሪክ በጥቂቱ እንቃኝ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተመሠረተው ከጣልያን ወረራ በኋላ ነበር። የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ተዋናይ የነበረችው ጣልያን በ1933 ዓ.ም ከኢትዮጵያ የአምስት ዓመት ወረራ ተሸንፋ ከወጣች ከአምስት ዓመት በኋላ በዚሁ በታኅሳስ ወር 1938 ዓ.ም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተቋቋመ።
በአሜሪካ ሠራሽ አውሮፕላኖች የበረራ ሥራ የጀመረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጊዜው ከቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ጋር በተደረገ ስምምነት አየር መንገዱን ያቋቋመው ዛሬ ላይ ገበያ ላይ የሌለው የአሜሪካኑ ትራንስ ወርልድ አቪየሽን TWA (Trans World Aviation) ነበር።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስተዳዳሩም በአሜሪካዊያን እጅ ነበር። ዓለም አቀፍ ጉዞውንም አሀዱ ብሎ የጀመረውም ወደ ግብፅ ዋና ከተማ ካይሮ ሳምንታዊ በረራ በማድረግ ነው። ይህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተመሠረተ በሦስተኛው ወሩ መጋቢት 30 ቀን 1938 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ተነሥቶ ካይሮ ድረስ ያካሄደው ዓለም አቀፍ በረራ ነው፡
አየር መንገዱ ሲመሠረት ከአሜሪካ ወታደራዊ ኃይል የተገዙና በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ያገለገሉ አምስት ዲ.ሲ. 3 (DC 3-C47) አውሮፕላኖች ነበሩት። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራውን ሲጀመር ይገለገልበት የነበረው የአዲስ አበባ አውሮፕላን ማረፊያ በጦር ኃይሎች በሚባል በሚጠራው ቦታ ሥር የሚገኘውን ማኮብኮቢያ ሜዳ ነበር። ሜዳው ለአውሮፕላን ለመንደርደሪያ በቂ ስላልነበር ቀስ በቀስ ዋና ማረፊያ ጣቢያው ቦሌ ወደ ሚገኘው ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ አዘዋወረ። የጦር ኃይሎችን አንዳንድ ሰዎች አሮጌው አውሮፕላን ማረፊያ በሚል ይጠሩታል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተመሠረተበትን 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ 2013 ዓ.ም አክብሯል። አየር መንገዱ በዓለም ላይ እጅግ ተወዳዳሪ ከሆኑ ግዙፋ ገናና ስምና ዝና ካላቸው ተርታ የሚጠቀስ ነው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካ ምርጡና ቀዳሚ አየር
መንገድነት ሽልማትን በተደጋጋሚ ማሸነፉም ስምና ዝናው ገናና እንደሆነ ማሳያ ነው። ሽልማቱን ከሰጡት ውስጥ በብሪታኒያ አየር መንገዱ የራሱ የአውሮፕላን አብራሪዎች የበረራ አስተናጋጅ ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ያለው ሲሆን ዓለም አቀፍ ደረጃውን ያሟላና ለአፍሪካ አገሮችና ለሌሎችም ጭምር ሥልጠና በመስጠት በማስመረቅ የሚታወቅ ነው። ለግል አብራሪና ለንግድ አውሮፕላን አብራሪ ፈቃድ በመስጠት የአገርና የውጪ ዜጎችን በማሠልጠን ከአርባ ዓመታት በላይ የቆየ ልምድ አለው። ለብዙ የአፍሪካ አገሮች ብሔራዊ አየር መንገዶች እና ለግል አውሮፕላን ባለንብረቶች የአውሮፕላን ጥገና በማካሄድም የሚሠራ ተቋም ነው።
ከቦይንግ አውሮፕላን አምራች ኩባንያ ጋር ከ60 ዓመታት በላይ የዘለቀ የንግድ ግንኙነት ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ ለመንገደኞች አገልግሎት ቦይንግ 787 (Boeing 787 Dreamliner) አውሮፕላኖች በማዘዝና በአፍሪካ አገልግሎት ላይ በማዋል የመጀመሪያው ነው። ይህንንም የተረከበው ድሪምላይነር አውሮፕላን በነሐሴ ወር 2012 ዓ.ም ነበር። አየር መንገዱ ቦይንግ 777 ቦይንግ 787 ቦይንግ 737 በአጠቃላይ 68 እጅግ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን ይጠቀም እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ።
በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1960ዎቹ D720 የመጀመሪያው ጄት ኤንጅን ያለው አውሮፕላን ወደ አፍሪካ ያመጣው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ ከዚያም ቦይንግ 707፣ 727፣737፣ 757፣ 767ን በማስመጣት ሲያገለገል ቆይቷል። ይህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቦይንግ አንድ ምርት ውጭ ሁሉንም የቦይንግ አውሮፕላኖች እንደተጠቀመ ነው ሰነዶች የሚያስረዱት። የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁንም ስም እና ዝናው እንደቀጠለ ነው።
ንጉሥ ላሊበላ እና የገና በዓል
ስመ መንግሥታቸው ገብረመሥቀል፤ አንዳንድ ሰነዶች ላይ ደግሞ ገብረክርስቶስ ይባል። ይህ የ12ኛው ክፍለ ዘመን (1120 ዓ.ም) ታሪክ ነው። አጼ ላሊበላ በላስታ ላሊበላ ታኅሳስ 29 ቀን 1120 ዓ.ም እንደተወለዱ ታሪካቸው ያሳያል። እነሆ በዚሁ ቅዱስ ቦታ ላይ የገና በዓል በየዓመቱ ታኅሳስ 29 ቀን በድምቀት ይከበራል። ይህንኑ ምክንያት በማድረግ የዚህ ሳምንት አካል ስለሆነ ስለንጉሥ ላሊበላ ታሪክ ጥቂት እንቃኝ።
የዛግዌ ሥርዎ መንግሥት ንጉሥ ነበሩ። ለ40 ዓመታት ያህል በንጉሥነት የቆዩ ሲሆን ታሪካቸው ከ12ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ እስከ 13ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ድረስ ይዘልቃል።
የንጉሥ ላሊበላ ታሪክ በዋናነት የሚታወቀው የዓለም ሀብት በሆነው የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት ነው። ከባለቤታቸው እቴጌ መስቀል ክብራ ጋር በመሆን 11 ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን አሰርተዋል። እነዚህም፤ ቤተ መዲሃኒያለም፣ ቤተ ማርያም፣ ጎለጎታ ሚካኤል፣ ኪዳነ ምህረት፣ ሥላሴ፣ ቤተ አማኑኤል፣ ቤተ ሊባኖስ፣ ቤተ ገብርኤል፣ ቤተ መርቆሬስ፣ ቤተ ጊዮርጊስ እና ቤተ መስቀል ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ ቤተ ጊዮርጊስ በመስቀል ቅርጽ የተሰራ ነው።
ስለ አጼ(ንጉሥ) ላሊበላ ይህ ታሪክ ይነገራል። ንጉሡ ላሊበላ የሚለውን ስም ያገኘው፣ ሲወለድ በንቦች ስለተከበበ ነው ይባላል። ላል ማለት በአገውኛ ማር ማለት ሲሆን፤ ላሊበላ ማለትም ላል ይበላል (ማር ይበላል) ማለት አንደሆነ ይነግራል። ውቅር ቤተ ክርስቲያናቱን ንጉሡ ጠርቦ የሰራቸው ከመላዕክት እገዛ ጋር እንደሆነ ደግሞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ይነግራል።
በ16ኛው ከፍለ ዘመን አውሮፓዊ ተጓዥ ላሊበላን ተመልክቶ «ያየሁትን ብናግር ማንም እንደኔ ካላየ በፍጹም አያምነኝም» ሲል ተናግሮ ነበር።
ቅዱስ ላሊበላ ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ ሕንጻዎችን ለመገንባት አሰበ፤ ከዚያም በጊዜው ከነበሩት አባቶች በተለይ ቀይት ከምትባል ባለአባት የጠየቀውን 40 ጊደር ለመግዛት በሚያስችለው ወርቅ ቦታውን ገዝቶ በከርሰ ምድር ውስጥ ያሉትን ሕንጻዎቸ ሊያወጣ ተዘጋጅ። ቅዱስ ላሊበላ የሚገነባባቸውን መሳሪያዎችለ 10 አመታት አዘጋጅቶ፤ በ1157 ዓ.ም ነግሶ በ1166 ዓ.ም ሕንጻውን ገንብቶ ጨረሰ። ቅዱስ ላሊበላ ከ40 ዓመታት የንግስና ዘመን በኋላ በተወለደ በ97 ዓመቱ ሰኔ12 ቀን 1217 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 30 /2015