የኢትዮጵያ መንግስት የቱሪዝም ዘርፉን የሀገሪቱ የምጣኔ ሃብት ምሰሶ በሚል ከያዛቸው አምስት ዘርፎች መካከል አንዱ አርጎታል። ዘርፉ በኢኮኖሚው ውስጥ የተሰጠውን ሚና እንዲጫወትም ስትራቴጂዎችን ነድፎና አደረጃጀት ፈጥሮ እየሰራ ይገኛል።
አገሪቱ በርካታ ባህላዊ፣ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና የአርኪዎሎጂ መስህብ ሃብቶችን እንዲሁም ሃይማኖትን እንዲሁም ባህልን መሰረት ያደረጉ የማይዳሰሱ እያሌ ሃብቶች ባለቤት እንደመሆኗ መንግስት ለቱሪዝም ዘርፉ ትኩረት መስጠቱ ይህን እምቅ ሀብት ተጠቅሞ ኢኮኖሚውን ወደፊት ለማራመድ የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።
የቱሪዝም ዘርፉ አመቱን በሙሉ እንቅስቃሴዎች የሚደረጉበት ቢሆንም በመስከረም፣ ታህሳስና ጥር ወራት ግን በርካታ የተለዩ እንቅስቃሴዎች ይደረጋሉ። በመስከረም ወር ሀገሪቱ የዘመን መለወጫዋን የምታከበርበት ከመሆኑ በተጨማሪ በኦሮሚያ የእሬቻ በአል፣ በደቡብ ክልል ደግሞ በርካታ ብሄሮችና ብሄሰቦች አዲስ አመታቸውን ያከብራሉ። ከእነዚህ ጋር በተያያዘ በርካታ ባህላዊ ስርአቶች የሚካሄዱ መሆናቸውን ተከትሎ በዚህ ወር የቱሪስቶች ፍሰት ከፍተኛ ይሆናል።
በታህሳስና ጥር ወራት ደግሞ ታላላቅ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ክብረ በዓላት ይካሄዳሉ። ይህን ተከትሎም ከአንድ ስፍራ ወደ ሌላ ስፍራ የሚደረገው ጉዞና ከዚያም የሚገኘው ምጣኔሃብታዊ ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። በእነዚህ ወራት በተለይ ከውጪ አገራት ከሚመጡ ቱሪስቶች፣ ትውልደ ኢትዮጵያን በተለየ መንገድ የአገር ውስጥ ጎብኚዎች መጠን በእጅጉ ከፍተኛ ይሆናል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በታህሳስና ጥር ወራት ወደ ሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለው የጎብኚዎች ፍሰት ይጨምራል። ምክንያቱ ደግሞ “ገናን በላሊበላ ወቅር አብያተ ክርስቲያናት” እና የጥምቀት “ከተራ” በዓልን ደግሞ በጎንደር ከተማ በልዩ ሁኔታ ለማክበር ከፍተኛ ፍላጎትና ፍሰት ስላለ ነው። ያለፉት ሶስት ዓመታት አሃዛዊ መረጃ ስንመለከት ቁጥሩ እያሻቀበ መምጣቱንም እንረዳለን።
በጎንደር ከተማ ያለውን መረጃ እንደምሳሌ ብንወስድ በእነዚህ የጎብኚዎች ፍሰት በሚበዛባቸው ወራት ጭምር በ2013 በጀት ዓመት የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ቁጥር 57 ሺህ ነበር። በ2014 በጀት ዓመት ይህ አሀዝ ወደ 325 ሺህ አሻቅቧል። በ2014 ዓም ብቻ ከአገር ውስጥ ጎብኚ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል። ይህ መረጃ የሚያሳየን ከውጪ አገራት የሚገቡትን ዲያስፖራዎች፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የውጪ አገራትን ጎብኚዎች ጨምሮ በእነዚህ ወራት ከፍተኛ የአገር ውስጥ ጎብኚዎች ፍሰት ወደ አካባቢው እንዳለ ነው።
የአማራ ክልል በታህሳስና የጥር ወራት በርካታ ጎብኚዎችን ያስተናግዳል። የአማራ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ አባይ መንግስቴ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጡት መረጃ እንዳስታወቁት፤ ክልሉ ዘንድሮም የገናንና የጥምቀትን በዓላት በታሪካዊዎቹ ጎንደርና ላሊበላ ከተማ ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን ለማስተናገድ ሰፊ ዝግጅት አድርጓል። በዚህ ሰሞንም እስከ 750 ሺህ የሚጠጉ ጎብኚዎችን በመቀበልና በማስተናገድ 2 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት አቅዶ እየሰራ ነው። የዘንድሮውን የገናን በአልም ትናንት በመላው ኢትዮጵያና በተለይ ደግሞ በታሪካዊቷ የላሊበላ ከተማ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ምእመናን በታደሙበት በደማቅ ስነስርአት ተከብሯል።
የልደት በዓልን በላል ይበላ
የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ከሚያነቃቁ ክበረ በዓላት አንዱ የሆነው በተለይ በኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በደማቅ ስነስርአት የሚከበረው የእየሱስ ክርስቶስ የልደት/ ገና/ በዓል ትናንት በታሪካዊቷና አስደናቂ ውቅር ዓብያተ ክርስቲያናትን በያዘችው ላል ይበላ ከተማ ተከብሯል። በአሉ በዋናነት ግን ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ወደ ስፍራው በመትመም አስደማሚ ወቅት ማሳለፍ የሚቻልበት በብዙሃኑ ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ ነው። በዚህ ሃይማኖታዊ ይዘት ባለው በዓል ላይ ከመላው ዓለም የሚመጡ ጎብኚዎች በስፋት የሚገኙ አንደመሆናቸው ዘንድሮም በርካታ የእምነቱ ተከታዮች፣ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች በበአሉ ላይ ተገኝተዋል።
ጎብኚዎች በእለተ ገና በላሊበላ ተገኝተው ክብረ በዓሉ ላይ ይታደሙ እንጂ አብዛኞቹ ግን በዚያው ቆይታቸውን ለሁለትና ሶስት ቀናት ያራዝማሉ። ዋንኛ ምክንያታቸው ደግሞ በአካባቢው በከተማዋ የሚገኙትን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሳይንስ የባህልና ትምህርት ድርጅት ዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡትን ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ከጫፍ እስከጫፍ መጎብኘት ነው። ከዚያ በተጨማሪ በከተማዋ የሚገኙ (የይምርሃነ ክርስቶስን ታሪካዊ ቤተክርስቲያን ጨምሮ) ልዩ ልዩ ስፍራዎችን ይጎበኛሉ ።በዚህም ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ፍሰት ይደረጋል፤ ከዚህም የቱሪዝም ምርት አገልግሎት አቅራቢዎች፣ አስጎብኚዎች፣ ሆቴሎችና ማህበረሰቡ በእጅጉ ተጠቃሚ ይሆናሉ።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የጸርሐ ቅዱስ ላሊበላ ዓለምአቀፍ ቅርስ ዋና አሥተዳዳሪ አባ ፅጌ ሥላሴ በመገናኛ ብዙሃን የዘንድሮውን ክብረ በዓል የእምነቱ ተከታዮች ወደ ስፍራው እንዲመጡ ጥሪ ባስተላለፉበት መልእክታቸው ላይ አንደተናገሩት፤ በዚህ ዓመትም በዓሉ የቅዱስ ያሬድ ዝማሬና የቤዛ ኩሉ ሥርዓት ዝግጅትን ካሕናት ሲከውኑ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል። በተጨማሪም ምእመናን በቤተክርስቲያን ግቢ የሚገኙ የእንግዶች ማረፊያዎችን ማስተካከል እና የውኃና መብራት አገልግሎት እንዲኖር በማድረግ አስፈላጊውን ስራ መስራታቸውን ገልፀዋል። ምእመናን ቤታቸውንና ግቢያቸውን ጨምሮ ለእንግዶች ማረፊያ እንዲሆን ማዘጋጀታቸውንም ጠቁመዋል። የደከሙትን እንግዶች እግር የማጠብ፣ ስንቅ የመስጠት ስነስርዓት እንደሚኖርም ገልፀው ነበር።
“በከተማዋ ለረጅም ጊዜ ተቋርጦ የነበረው የመብራትና የውኃ አገልግሎት ወደ ነበረበት በመመለሱ በዚህ ዙሪያ ችግር የለም” ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፤ ተዘግተው የቆዩ ሆቴሎች ለእንግዶች አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መኾናቸውንም ተናግረዋል። የከተማዋን ጸጥታና ደኅንነት ለመጠበቅም ከመንግሥት አካላት ጋር በቅንጅት እየሠሩ እንደኾነ ጠቁመው በዚህ ዙሪያ ምንም አይነት ስጋት አንደሌለ ነው መልእክታቸውን ያስተላለፉት።
አባ ፅጌ ሥላሴ መዝገቡ እንዳሉት፤ የቀደምት አባቶችን ታሪክ ለማስታወስና በረከታቸውን ለማግኘት በርካታ ምእመናን ከተለያዩ አካባቢዎች በእግራቸው ወደ ከተማዋ ገብተዋል። እነሱን ለማስተናገድም አስፈላጊውን ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል። በላሊበላ ዙሪያ በርካታ የሚጎበኙ መንፈሳዊ መዳረሻዎች ስለሚገኙ ምእመናን የቆይታ ጊዜያቸውን አራዝመው ጉብኝት እንዲያደርጉም በወቅቱ ጥሪም አስተላልፈዋል።
የክልሉ መንግስት ስለ በዓሉ ምን ይላል
በዚህ ወቅት ከመቼው ገዜ በተለየ የአገር ወስጥ ቱሪዝም ፍሰቱ ወደ ሰሜኑ ክፍል ይጨምራል። ይህም ለቱሪዝም ምርት አቅራቢዎች፣ ሆቴሎች፣ የሆስፒታሊቲና የማስጎብኘት ተግባር ላይ ለተሰማሩ አካላት ትልቅ ትንሳኤ ነው። በተለይ ከዚህ ቀደም በጦርነትና በወረርሽኝ ምክንያት ተዳክሞ የነበረው እንቅስቃሴ መነቃቃትን እንደሚያሳይ ይጠበቃል። አሀዛዊ መረጃዎች እንደሚያመለክቱትም፤ በተለይ ወደ አማራ ክልል የሚያቀኑ ጎብኚዎች ብዛት ከፍተኛ ነው። በዚህ መሰረት የአማራ ክልል 750 ሺህ ተጓዦች በክልሉ ይገኛሉ ብሎ ዝግጅቱን አጠናቆ እየጠበቀ መሆኑን አስታውቋል።
የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ በክልሉ ከታኅሣሥ ጀምሮ የሚከናወኑ የተለያዩ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ ክብረ በዓላትን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ ላይ የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ ጣሂር ሙሀመድ እንዳሉት፤ በጦርነቱና በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ተጎድቶ የነበረውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማጠናከር የተሻለ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው።
በጎንደር ከተማ በተለየ መልኩ የሚከበረውን የጥምቀት በዓል፣ በሰሜን ሸዋ በኢራንቡቲ የሚከበረውን የጥምቀት በዓል፣ በእንጅባራ ከተማ የሚከበረውን የአገው ፈረሰኞች በዓል፣ በደብረ ታቦር ከተማ የሚከበረውን የመርቆርዮስ በዓልና ሌሎች በዓላትም በደመቀ መልኩ እንዲከበሩ ቢሮው ከአካባቢው አስተዳደሮችና ማኅበረሰቡ ጋር እየሠራ መሆኑን ሃላፊው አብራርተዋል።
“በሰከላም ላይ ሚከበረውን የግዮን በዓል በድምቀት ለማክበር ተዘጋጅተናል” ያሉት አቶ ጣሂር ሙሀመድ ለሁሉም በዓላት ለሚታደሙት እንግዶች የቱሪዝም ትውውቅ በማድረግ ዘርፉን የማጠናከር ሥራ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል። ቢሯቸው ከዓመት ወደ ዓመት የጎብኚዎች ቁጥር እንዲጨምር እየሠራ መሆኑንም ተናግረዋል።
ከሰሞኑ እየወጡ በሚገኙት መረጃዎች መሰረት በልዩ ሁኔታ በሰሜኑ ክፍል የሚከበሩ በዓላትን አስመልክቶ የማረፊያ ስፍራ ስለመጥፋት፣ የዋጋ ጭማሪና ለእለት ፍጆታ የሚሆኑ እቃዎች እየተወደዱ ስለመሆናቸው ይነገራል። ይህንን ፍራቻ ወደ አካባቢው የሚያቀኑ ተጓዦች መጉላላት እንዳይደርስባቸው ስጋታቸውን በማህበራዊ ሚዲያና ሌሎች አማራጮች ሲገልፁ ተሰምቷል። ይህንን ውዥምብር የክሉ አመራሮች ለማጥራት እየሞከሩ ነው።
አቶ ጣሂር ጉዳዩን ለማጥራት በሰጡት መግለጫ ላይ በተለይ በዓላቱ በጎንደርና በላሊበላ ከተሞች ሲከበሩ አላስፈላጊ የዋጋ ንረት እንዳይኖር ከነጋዴው ማኅበረሰብ ጋር ውይይት እንደሚደረግ ተናግረዋል። የዋጋ ንረቱ ቱሪስቶችን ሊጎዳ ስለሚችል አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሬ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ እርምት የመውሰድ ተግባር እንደሚፈጸም አስገንዝበዋል። ነጋዴዎች የበዓላቱን ድባብ ማጠልሸት እንደሌለባቸው አሳስበዋል።
በጥር ወር ብቻ ሳይሆን ዓመቱን ሙሉ የሚመጡ እንግዶች በተለይ የአገልግሎት ዘርፉን ተጠቃሚ ስለሚያደርጉ አስተማማኝ ጸጥታ እንዲኖር፣ የዋጋ ማስተካከያ በማድረግ፣ የአካባቢን ፅዳት በመጠበቅ በኩል ተገቢው የቅድመ ዝግጅት ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።
የቱሪዝም ሚኒስቴር ተግባር የአገር ውስጥ ቱሪዝም እድገት
የቀድሞው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መንግስት ባደረገው ማሻሻያ መሰረት የአደረጃጀት ለውጥ ተደር ጎበታል። በዚህም መሰረት “ቱሪዝም ሚኒስቴር” ብቻውን እንዲደራጅ ተደርጓል። ቱሪዝም ሚኒስቴር በአዲሱ አደረጃጀት ዘርፉን እያንቀሳቀሰ ይገኛል። ይህ ተቋም ከአምስቱ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች ውስጥ አንዱ የሆነውን ዘርፍ እየመራ ስር ነቀል ለውጥ የማምጣት ሃላፊነት ተጥሎበታል።
ሚኒስቴሩ የመስህብ ሃብቶችን የማስተዋወቅ፣ ገበያ የማፈላለግ፣ የማልማትና የመጠበቅ ተግባር ከማከናወኑም ባሻገር የአገር ውስጥ ቱሪዝምን የማበረታታትና ንቅናቄ የመፍጠር ድርሻውንም መወጣት እንዳለበት ይታመናል። ይህንን ለማስፈፀም ደግሞ ከሰሞኑ “ልወቅሽ ኢትዮጵያ” የሚል ኢትዮጵያውያን ጎብኚዎችን የሚያበረታታ ንቅናቄ ጀምሮ በርካታ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል። አዳዲስ መዳረሻዎችን በማስተዋወቅና ጥቆማ በመስጠት ለጎብኚዎች አማራጮችን ከመፍጠር ባሻገር በታህሳስና ጥር ወራት በተከታታይ በሰሜኑ ክፍል በታላቅ ድምቀት የሚከበሩትን ክብረ በዓላት እንደ ምቹ አጋጣሚ ወስዶ ጎብኚዎች ወደ ስፍራው እንዲያቀኑ እያበረታታ ነው።
የቱሪዝም ሚኒስቴር የገበያ ልማትና ግብይት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ዳዊት የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ ኢንዱስትሪው መነቃቃት እያሳየ መሆኑን ይናገራሉ። በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ተከስቶ የነበረው ጦርነት ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተደምሮ የቱሪዝም ዘርፉ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሮ ቆይቷል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተፈጠረው ግጭት ተጽእኖ ካሳደረባቸው ዘርፎች መካከል አንዱ ቱሪዝም ነው ይላሉ።
ሰላም ለቱሪዝም እድገት ቁልፉ መሳሪያ ነው የሚሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ከዚህ አኳያ የሰላም ስምምነቱ ለዘርፉ ወሳኝ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን ይናገራሉ። ይህንን ተከትሎ በታህሳስና በጥር ወቅት የሚከበሩትን የገና እና ጥምቀት በዓል ታሳቢ ባደረገ መልኩ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን የማስተዋወቅ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።
በዓሉን ለመታደም ከውጪ አገራት ለሚመጡ እንግዶችና ከአገር ውስጥ ወደ ስፍራው ለሚያቀኑ እንግዶች ላልይበላና አካባቢውን እንዲጎበኙ ፓኬጆች መዘጋጀታቸውን ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸዋል። የሠላም ስምምነቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ያላትን የቱሪዝም መስህብ ለአገር ውስጥና ለውጭ ጎብኝዎች ለማስተዋወቅ እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረው፤ በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በተዘጋጀው መርሃ ግብር ላይ እንዲሳተፉ ሚኒስቴር መሪያቤቱ ጥሪ በማድረግ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ ነው የገለፁት።
እንደ መውጫ
የቱሪዝም ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የአገር ውስጥ ጎብኚዎችን የማነቃቃት ግብ በስትራቴጂ የተቀመጠ ነው። ለረጅም ዓመት የሚቆይና በስፋት ይሰራበታል። ይህ ስራ በአገራችን እንደ ባህል ተደርጎ እስኪወሰድ ድረስ የሚቀጥል እንደሆነ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በተደጋጋሚ ሲገልፅ ይሰማል። ኢንዱስትሪው በተለያዩ ወቅታዊ ምክንያቶች ከገባበት መቀዛቀዝ እንዲላቀቅ ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ ስፍራ አዳዲስ መስህቦችን ለመመልከት የሚደረጉ ጉዞዎች እንደ ባህል መውሰድ ይኖርባቸዋል። ለዚህ ደግሞ ገናን፣ ጥምቀትንና መሰል ክብረ በዓላትን እንደ ጥሩ አጋጣሚ መውሰድ ያስፈልጋል።
ከአንድ አካባቢ የሚነሳ ማህበረሰብ በሌላ ጥግ ያለውን የአገሩን ክፍል (በሃይማኖታዊ ጉዞም ሆነ የመስህብ ስፍራዎችን ለመመልከት በሚደረግ መነሻ) በሚጎበኝበት ግዜ ባህሉም ሆነ የአኗኗር ሁኔታው ምን ያህል አንድ አይነትና የተመሳሰለ እንደሆነ የማየት እድልም ይኖረዋል። ይሄ ደግሞ ከኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ ባሻገር አንድነትን ለማጠናከር በእጅጉ ጠቃሚ እንደሆነም ይታመናል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 30 /2015