በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመንግስት ተቋማት የቢሮ ኪራይ የሚወጣው ወጪ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣት በከተማ አስተዳደሩ ላይ ጫና ማሳደር ከጀመረ ቆይቷል። አብዛኞቹ የከተማ አስተዳደሩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች እና ወረዳዎች የራሳቸው ቢሮ የሌላቸው መሆኑ በከተማ አስተዳደሩ ላይ እያሳደረ ካለው ጫና ባሻገር የሚከራዩ ህንጻዎች ተቋማቱ መደበኛ ሥራዎቻቸውን እንዲያከናወኑ የማይመቹ፣ ለሥራ ተነሳሽነት የማያበረታቱና የማይማርኩ፣ ለተገልጋይ ደንበኛም ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት የማይጋብዙ ናቸው። በሌላ በኩል ከተማ አስተዳደሩ ለሌሎች መሰረተ-ልማቶች ማዋል የነበረበትን ከፍተኛ መዋዕለ-ነዋይ ለኪራይ ወጭ በመዳረጉ ለከተማው እድገት እንቅፋት እንደሚሆን አጠያያቂ አይደለም።
ከአዲስ አበባ ከተማ የመንግስት ንብረት አስተዳደር ባለስልጣን የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው፤ በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ ካሉት አጠቃላይ የመንግስት መስሪያ ቤቶች 65 በመቶ የሚሆኑት የመንግስት ተቋማት የራሳቸው ህንጻ የላቸውም። እነዚህ መስሪያ ቤቶች ቢሮ ተከራይተው ነው አገልግሎት የሚሰጡት። ህንጻ አላቸው የሚባሉትም ብዙ ችግር የሚስተዋልባቸውና እጅግ የተጣበቡ ናቸው።
የአዲስ አበባ ከተማ የመንግስት ንብረት አስተዳደር ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ አቶ የሱፍ ኢብራሂም እንደሚሉት፤ በከተማዋ የክፍለ ከተሞችን የቢሮ ችግር በአመዛኙ መቅረፍ የተቻለ ቢሆንም፣ ለከተማ አስተዳደሩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች እና ለወረዳዎች የሚፈጸመው የቢሮ ኪራይ በጣም አሳሳቢ ሆኗል። የቢሮ ኪራዩ የከተማ አስተዳደሩን የገንዘብ አቅም እየተፈታተነው ይገኛል። ለቢሮ ኪራይ ብቻ በአንድ ዓመት ከአንድ ቢሊየን ብር በላይ ወጪ እየተደረገ ነው። ለቢሮ ኪራይ እየወጣ ያለው ወጪ የከተማውን ሌሎች አንገብጋቢ ችግሮችን ለመፍታት ሊውል የሚገባ ነበር።
የቢሮ ኪራይ እያስከተለ ያለው ችግር በገንዘብ ብቻ የሚተመን አይደለም የሚሉት አቶ የሱፍ፤ የከተማ አስተዳደሩ ለቢሮ ኪራይ የሚያወጣው ወጪ የከተማዋን የህንጻ ኪራይ ስርዓት አጠቃላይ ገበያውንም እየረበሸ ነው ብለዋል። ከመንግስት በጀት የሚከፈል ገንዘብ ነው በሚል የመንግስት መስሪያ ቤቶች በካሬ ሜትር እስከ አንድ ሺህ ብር የሚከራዩበት ሁኔታም እንዳለ ጠቅሰው፣ ይህ የኪራይ ዋጋ እንዲንር እያደረገ ነው ይላሉ። ነጋዴዎች ህንጻ ተከራይተው እንዳይሰሩ እንቅፋት እየሆነ መምጣቱንም ጠቁመዋል።
ለመንግስት ተቋማት የሚፈጸመው ህንጻ ኪራይ ለሙስናና ብልሹ አሰራርም የተጋለጠ መሆኑንም በመጠቆም፣ ሁሉም አመራር በሚመቸው መንገድ በተበታተነ መልኩ የሚመራው መሆኑን ያመለከቱት። ስታንዳርድ የሌለው፣ የገበያ ጥናት የማይደረግበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም በርካታ መዘዞችን ሲያስከትል እንደነበር አቶ የሱፍ ጠቁመዋል።
የባለስልጣኑ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ይድነቃቸው በበኩላቸው፤ አቶ የሱፍ ያነሷቸውን ችግሮች ይጋሩና ተጨማሪ ችግሮችንም ይዘረዝራሉ። አብዛኞቹ በኪራይ የሚያዙ ቢሮዎች መደበኛ ሥራዎችን ለማከናወን የማይመቹ፣ ለስራ ተነሳሽነት የማያበረታቱና የማይማርኩ መሆናቸውን ያመለክታሉ። እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ችግሩ አገልግሎት አሰጣጡ የተበታተነ እንዲሆን ምክንያት ሆኗል። ተገልጋዩ በአንድ ቦታ ላይ የተለያዩ አገልግሎቶችን ማግኘት አይችልም። የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማግኘት በአስሩም ክፍለ ከተሞች የተበታተኑ ቢሮዎች መሄድ ይጠበቅበታል። እነዚህ ቢሮዎች በአንድ ቦታ ተገንብተው አገልግሎት መስጠት ቢጀምሩ በመጀመሪያ የአገልግሎት አሰጣጡን በጣም ያቀላጥፋል። ይህም የመልካም አስተዳደር እና የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግር እያስከተለ ነው።
ምቹ የሆኑ ህንጻዎችን መከራየት ብዙ ወጪ ስለሚያስወጣ አብዛኞቹ ተቋማት ወጪ ለመቀነስ በሚል ምቹ ያልሆኑ ህንጻዎች ተከራይተው ለመስራት እንደሚገደዱም አመልክተዋል። አብዛኞቹ ህንጻዎች ለተገልጋዩም ለአገልጋዩም አስቸጋሪና ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት የማይጋብዙ ናቸው።
እንደ አቶ ይድነቃቸው ማብራሪያ፤ አብዛኞቹ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ተከራይተው የሚሰሩ በመሆናቸው አገልግሎት መስጫ ህንጻዎች ማሟላት አለባቸው ተብለው በመንግስት የተቀመጡ አገልግሎቶችን ለማሟላት ጭምር ችግር እየሆነ ነው። ለምሳሌ የህጻናት ማቆያዎች አንድ የመንግስት ህንጻ የግድ ማሟላት አለበት። በአዋጁ መሰረት ሴቶች ህጻናትን ይዘው መስሪያ ቤት ድረስ በመሄድ መንከባከብ አለባቸው። ለዚህ ደግሞ እያንዳንዱ የመንግስት መስሪያ ቤት የህጻናት ማቆያ መገንባት እንዳለበት በአዋጅ ተደንግጓል።
የመንግስት ተቋማት ተከራይተው በሚኖሩባቸው ህንጻዎች ላይ በቂ ቦታ ባለመኖሩ የህጻናት ማቆያ ለማዘጋጀት ከለለ። የካፌ አገልግሎት፣ የመኪና ማቆሚያ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና መስጫ አገልግሎቶችን መስጫዎችም መኖር እንዳለባቸው የተቀመጠ ቢሆንም፣ በኪራይ ቢሮዎች አገልግሎት የሚሰጡ መስሪያ ቤቶች እነዚህን አገልግሎቶችን ለመስጠት አዳጋች ሆኖባቸዋል።
በቋሚነት አስፈላጊ የሆኑ መሰረታዊ ነገሮችን ለመስራትም ችግር እየፈጠረ ነው። ብዙ ተቋማት በቴክኖሎጂ ስራቸውን ማዘመን ቢፈልጉም፣ በተከራዩባቸው ቦታዎች የሚዘረጉ መሰረተ ልማቶች ቋሚ ስላልሆኑ እንቅፋት እየሆነ ነው። እነዚህ መሰረተ ልማቶች እጅግ ውድ በመሆናቸው ቢሮዎች በተቀየሩ ቁጥር ለመቀየርም አዳጋች ናቸው። መንግስትን ለከባድ ወጪ ይዳርጋሉ። ኪራዩ የሚፈጥራቸው ችግሮች ዘርፈ ብዙ መሆናቸውን አቶ ይድነቃቸው ያብራራሉ።
ከቢሮ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ እንደነበር የሚያነሱት አቶ ይድነቃቸው፣ በተደረገው ጥረት በተለይም በክፍለ ከተሞች ደረጃ የነበረው የቢሮ ችግር በአመዛኙ መቀረፉን አንስተዋል። በክፍለ ከተማ ደረጃ ግን ሁለት ክፍለ ከተሞች ብቻ ናቸው። በኪራይ ቢሮ ውስጥ አገልግሎት እየሰጡ ያሉት። 9ኙ የራሳቸውን ህንጻ አስገንብተው ባስገነቡት ህንጻ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ጠቁመዋል።
ሁለቱ ክፍለ ከተሞች የራሳቸው ህንጻ ባለቤት ለመሆን ሂደት ላይ መሆናቸውን ያነሱት አቶ ይድነቃቸው፤ የራሱ ህንጻ ግንባታ ያላጠናቀቀው የልደታ ክፍለ ከተማ የግንባታ ስራው መቋረጡን ይጠቅሳሉ። ግንባታው እንዲቋረጥ ምክንያት የሆኑ ችግሮችን ፈጥኖ በማስወገድ ግንባታውን ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
እንደ አቶ ይድነቃቸው ገለጻ፤ አዲስ የተቋቋመው ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ደግሞ የራሱን ለመገንባት ቦታ አዘጋጅቶ ዝግጅት እያደረገ ነው። በክፍለ ከተማ ደረጃ ያለው የመንግስት መስሪያ ቤቶች የህንጻ ችግር በአጭር ጊዜ ውስጥ ይፈታል ተብሎ ይታሰባል።
በከተማዋ የከፋ የቢሮ ችግር ያለው በወረዳ ደረጃ ነው የሚሉት አቶ ይድነቃቸው፤ ወደ 120 የሚሆኑ የወረዳ የመንግስት ተቋማት ህንጻ ተከራይተው አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል። የራሳቸው ህንጻ ያላቸው ጥቂት ወረዳዎች ቢኖሩም፣ አገልግሎት የሚሰጡባቸው ህንጻዎች እጅግ ጠባብ መሆናቸውን ይገልጻሉ። ቀደም ሲል 70 የሰው ሀይል ይይዛሉ ተብለው የተሰሩ እንደሆኑም ተናግረው፣ የወደፊት ሁኔታን ታሳቢ ሳያደርጉ የተገነቡ እንደሆኑም ነው ያመለከቱት። በአሁኑ ወቅት ወረዳዎች ከ400 እስከ 500 የሰው ሀይል አላቸው ይላሉ።
የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ የሱፍ እንደሚሉት፤ የመንግስት ቢሮዎች ከኪራይ ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ አማራጭ በመፍትሄነት እየተወሰዱ ነው። ችግሩን በዘላቂነት መፍታት የሚቻለው ሁሉም ተቋማት የራሳቸው ህንጻ እንዲኖራቸው በማድረግ ሲሆን ፣ የራሳቸው ህንጻ እስኪኖራቸው ድረስ ደግሞ ከቢሮ ኪራይ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመቅረፍ የእርምት እርምጃዎች ተወስደዋል።
ከዚህ በፊት ከቢሮ ኪራይ ጋር ተያይዞ ይፈጸሙ የነበሩ ህገ ወጥ ተግባራትን ለመከላከል የቢሮ የኪራይ ጣራ ተቀምጧል፤ ስታንዳርድም ተዘጅጋጅቷል። የትኛውም መስሪያ ቤት ከዚያ ጣራ እና ስታንዳርድ ውጭ መከራየት አይችልም። በገበያ ውስጥ የዋጋ ለውጥ ካለ ደግሞ የገበያ ጥናት በየስድስት ወሩ እየተካሄደ ነው። ማሻሻያ መደረግ ካለበትም በዚያ የገበያ ዋጋ ላይ በመመርኮዝ ይታያል። በተጋነነ ዋጋ ተከራይተው የነበሩትን ባለስልጣኑ ከነበሩበት ህንጻ ማስወጣቱን ነው የጠቆሙት።
ለአብነት ያህል በየካ ክፍለ ከተማ በካሬ እስከ አንድ ሺህ ሲከፈል የነበረ ሲሆን፣ የኪራዩ ዋጋ የተጋነነ በመሆኑ ባለስልጣኑ አስወጥቷል። በዚህም በክፍለ ከተማው የነበረው የተጋነነ የህንጻ ኪራይ ቀንሷል። በየካ በካሬ እስከ ከ200 እስከ 350 ብር ወርዷል። እነዚህ የመንግስት ተቋማት በብዙ ሺህ ካሬዎች የሚለካ ህንጻ በሚከራዩበት ወቅት በመንግስት በጀት ላይ ያለው ጫና ከፍ ያለ ነው ይላሉ።
በተለይም ለሴክተር መስሪያ ቤቶች የሚሆን ህንጻ ተገንብቶ እስኪጠናቀቅ ድረስ የግብር ከፋዩን ገንዘብ ከብክነት በጸዳ መንገድ በአግባቡ መጠቀም እንዲቻል እንዲሁም ህገ ወጥ ተግባራትን በሚፈጽሙት ላይ ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያስችል ስርዓት እየተገነባ ነው።
ማንኛውም ቢሮ ያለ መዋቅር በራሱ ቢሮ መከራየት አይችልም ያሉት ዋና ስራ አስኪያጁ፣ የውል መነሻ እና የባለስልጣኑን ጥናት መሰረት አድርገው እንዲከራዩ መደረጉን ይገልጻሉ። ያም ቢሆን በጨረታ ህጉ መሰረት ነው ውድድር የሚደረገው ይላሉ።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ቀደም ባሉት ጊዜያት ግን የጨረታ ህጉን ወደ ጎን በመተው ኪራይ ሲፈጸም ነበር። ያ ደግሞ ከጀርባ ችግር ሲፈጥር ቆይቷል። ተገልጋዩን እና አገልጋዩን ለችግር ሲያጋልጥ ነበር። መንገድ በሌለበት፣ ለትራንስፖርት ምቹ ባልሆነበት እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ባልተሟሉበት አመራሩ ሰራተኛውን በመጫን ምቹ ያልሆነ ቦታ ላይ ሲያስገባ ቆይቷል።
አቶ የሱፍ ከቢሮ ኪራይ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ችግሮችን በመሰረታዊነት መቅረፍ የሚቻለው ለከተማው ሴክተር መስሪያ ቤቶች የሚሆን ግዙፍ ህንጻ በመገንባት እንዲሁም እያንዳንዱ ወረዳ የራሱ የቢሮ ህንጻ ባለቤት እንዲሆኑ በማድረግ ነው ሲሉ ያብራራሉ።
እሳቸው አንዳሉት፤ በዚህም መሰረት ለሴክተር መስሪያ ቤቶች የሚሆን ግዙፍ ህንጻ ለመገንባት ዝግጅት እየተደረገ ነው። ለአብነትም ግዙፍ ህንጻ መገናኛ አካባቢ ለመገንባት ዝግጅት ተደርጎም ነበር። ለህንጻው የሚሆን 6 ነጥብ 2 ሄክታር መሬት ከተዘጋጀ በኋላ የአዋጭነት ጥናት ሲካሄድ ቦታው በጣም የተጨናነቅ ስለሆነ፤ ተጨማሪ ግዙፍ ህንጻ በአካባቢው ሲገነባ በቀጣይ የበለጠ መጨናነቅ ስለሚፈጠር ቦታውን መቀየር አስፈልጓል።
በአሁኑ ወቅት ጥቁር አምበሳ አካባቢ ከተክለ ሃይማኖት ቤተክርስቲያን እስከ ጎማ ቁጠባ ወደ 11 ነጥብ 6 ሄክታር ቦታ ተዘጋጅቷል። ይህንን ቦታ የመጥረግ እና የማዘጋጀት ስራ እየተሰራ ነው። የሚገነባው ህንጻ 20 የሚሆኑ ሴክተር መስሪያ ቤቶችን በአንድ ላይ ለማሰባሰብ ያስችላል። ካርታው በመንግስት ንብረት አስተዳደር ባለስልጣን ስም ተሰርቷል። የጨረታ እና ቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተጠናቀዋል።
በቦታው ላይ ያሉ ባለመብቶችን ህግን በተከተለ መንገድ የማስነሳት ስራ እየተሰራ መሆኑን የሚያነሱት አቶ የሱፍ፣ ፕሮጀክቱ ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቅ ትልቅ ፕሮጀክት መሆኑን ያመለከቱት። ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የሴክተር መስሪያ ቤቶችን የቢሮ ችግር በዘላቂነት እንደሚፈታና ለከተማ አስተዳደሩ እፎይታ እንደሚሰጥና በየዓመቱ የሚወጣውንም ወጪ እንደሚያስቀር መሆኑን ጠቁመዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ የፕሮጀክቱ ግንባታ በቀጣይ አንድ ዓመት ውስጥ ለመጀመር ታስቧል። ባለስልጣኑ ለፕሮጀክቱ ግንባታ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጓል። የሚቀረው የበጀት ጉዳይ ነው። ፕሮጀክቱ የሚጠይቀው ገንዘብ ከፍተኛ ስለሆነ ሀገሪቱ አሁን ካለችበት የኢኮኖሚ ሁኔታ አንጻር ሌሎች አንገብጋቢ ፕሮጀክቶችን የማስቀደም ፍላጎቶች በመንግስት በኩል ስለታየ የጊዜ ማስተካከያ ሊኖር ይችላል።
በወረዳዎች የሚስተዋለውን የቢሮ ችግር ለመቅረፍ ደግሞ ለወረዳ ስማርት ቢሮዎችን ለማዘጋጀት ባለስልጣኑ ከሜጋ ፕሮጀክቶች ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር በጣም ውጤታማ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል። ስማርት ቢሮዎች ተገንብተው ሲጠናቀቁ በወረዳዎች የሚታዩ ከቢሮ እጥረት ጋር የተያያዙ ችግሮች ይቀርፋሉ ተብሎ ይታሰባል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 29 ቀን 2015 ዓ.ም