በኢትዮጵያ ስፖርት ውስጥ አንድ የተለመደ ባህል አለ። ይህ ልምድ በብዙዎቹ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ዘወትር የሚስተዋል ጎጂ ባህል ነው። ፌዴሬሽኖች በተለያዩ ምክንያቶች በተለይም ከበጀት እጥረት ጋር በተያያዘ አመቱን ሙሉ ተቀምጠው ከርመው አለም አቀፍ ውድድሮች ሲቃረቡ ለዝግጅት ሲጣደፉ ማስተዋል የተለመደ ነው። ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ መድረኮች አበረታች ውጤት እያስመዘገበችባቸው ከሚገኙ ውድድሮች አንዱ ወርልድ ቴኳንዶ ነው። በዚህ ስፖርት የኦሊምፒክ ተሳትፎን ጨምሮ በአፍሪካ ደረጃ ከቅርብ አመታት ወዲህ ሜዳሊያዎች እየተመዘገቡ ሲሆን በቀጣይ አመታትም የተሻሉ ውጤቶች ይመዘገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። ይሁን እንጂ ቀጣይ ለሚጠብቁ ውድድሮች ከወዲሁ ስትራቴጂክ እቅዶችን ነድፎ ውጤታማ ዝግጅት ማድረግ ለነገ የማይባል የቤት ስራ ነው።
የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን በዚህ ረገድ ለአስራ ሶስተኛው መላ አፍሪካ ጨዋታዎችና ለ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ ውድድሮች ዝግጅቱን ከወዲሁ እንደሚጀምር ጠቁሟል። ፌዴሬሽኑ ለዝግጅት ይረዳው ዘንድ ከመጪው ጥር ወር ጀምሮ ውድድሮችን እንደሚያካሄድም በተለይ ለአዲስ ዘመን ገልጿል።
የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን በሃገር ውስጥ በዓመት አራትና ከዚያ በላይ ውድድሮች ያዘጋጃል። ከነዚህም ውድድሮች መካከል ከመጪ ጥር ወር ጀምሮ የሚካሄደው የኢትዮጵያ ቻምፒዮናና ሌሎችም ለሁሉም ክፍት የሆኑ ውድድሮች ተጠቃሽ ናቸው። ፌዴሬሽኑ በእነዚህ ውድድሮች አትሌቶች አቋማቸውን እንዲፈትሹ ከማድረግ ባሻገር በአህጉርና በአለም ዓቀፍ ደረጃ ለሚካሄዱ ውድድሮች ተመልምለው ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ያደርጋል።
ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ መድረክ በወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት ብዙም የተሳትፎ ታሪክ ቤይኖራትም ባለፈው ቶኪዮ 2020 ለመጀመሪያ ጊዜ መሳተፍ ችላለች። በመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ግን በዚህ ስፖርት በርካታ ጊዜ ተሳትፋ በሜዳሊያዎችን መሰብሰብ ችላለች። ኢትዮጵያ ባለፈው አስራ ሁለተኛው መላ አፍሪካ ጨዋተዎች ተሳትፎዋም አንድ ወርቅ፣ አንድ ነሃስና ዲፕሎማ በማስመዝገብ ከአትሌቲክስ ቀጥሎ ውጤታማ በመሆን የሚጠቀስ ስፖርት ነው። በቀጣዩ መላ አፍሪካ ጨዋታዎችም የተሻለ ውጤት ለማምጣት ብሄራዊ ቡድን በማቀፍና ተወዳዳሪዎችን በመመልመል ፌዴሬሽኑ ከወዲሁ ዝግጅት እንደሚያደርግ አሳውቋል። በቀጣይ ለፓሪስ ኦሊምፒክ ማጣሪያም ዝግጅቱ ቀደም ብሎ እንደሚጀመር ተጠቁሟል። ለዚህም ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ እቅድ አውጥቶ በአፍሪካ ደረጃ የሚደረጉትን ውድድሮች እንደ አቋም መፈተሻ ጨዋታ እንደሚጠቀምባቸው ገልጿል።
ለነዚህ ዝግጅቶች ከፋይናንስ አኳያ ከመንግስት በጀት በተጨማሪ የተለያዩ ስፖንሰሮችን የማፈላለግ ስራዎች እየተሰሩ የሚገኙ ሲሆን፣ ፌዴሬሽኑ ከሚያገኛቸው ገቢዎች የውድድር ወጪዎቹን በራሱ ለመሸፈን ማቀዱን አስታውቋል። ለዚህም ስፖርቱ ላይ በደንብ ኢንቨስት ማድረግ ከተቻለ ከተሳትፎም ባሻገር አመርቂ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ተገልጿል።
ፌዴሬሽኑ ስፖርቱን ለማሳደግ ከሚሰራቸው ስራዎች መካከል ብቁ የሆኑ ሙያተኞችን ማፍራት አንዱ ነው። “ሙያተኛውን የሚለካበትና የቀበቶ ደረጃን የሚያሳድግበት ፈተና እንደለው ይተወቃል” የሚሉት የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፍቅሩ ተቋም፣ ሙያተኛው የሰራውንና የሰለጠነውን በማሳየት የቀበቶ ደረጃውን እንዲያገኝ እገዛ እንደሚደረግ ይናገራሉ። በዚህም እንደ ሃገር ብዙ ሙያተኞችን በመፈተን እንደ ዓለም አቀፍ ዕውቅና እንደሚሰጣቸውም ገልጸዋል። ሙያተኛ ሲባል ስፖርተኛው፣ አሰልጣኝና ዳኞች መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ፍቅሩ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭምር መስራት የሚችሉ ብቁ ዳኞችና አሰልጣኞች በዘረፉ እንደሉ ጠቁመዋል። ለአብነትም የአፍሪካ የውድ ቼርማን(ሊቀመንበር) ማስተር አዲስ ኡረጌሳ የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ እንደሆነም አስታውሰዋል። በዳኝነትም በኩል በአስራሁለተኛው መላ አፍሪካ ጨዋታዎች መዳኘት የቻሉ ኢትዮጵያዊን ዳኞችም እንደነበሩ ተጠቅሰዋል። ፌዴሬሽኑ እነዚህን ባለሙያዎች የሚያፈራው በሃገር ውሰጥ እንዲገደቡ ሳይሆን እንደ አትሌቲክሱና እግር ኳሱ በዓለም መድረክ እንዲሳተፉ መሆኑንም ተናግረዋል።
እንደ አቶ ፍቅሩ ገለጻ፣ የወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት ከተደራሽነትና ከተዘውታሪነት አንጻር በሰፊው እየተሰራበት ይገኛል። በሁሉም ክልልና ከተማ አስተዳደር ከዞን እስከ ወረዳ የተስፋፋና የሚዘወተር ስፖርትም ነው። ወርልድ ቴኳንዶ ተወዳዳሪና በአህጉርና በአለም አቀፍ ደረጃ ውጤት በማምጣት የተሻለ ቢሆንም ከዚያ በላይ ስኬት ማስመዝገብ ይቻላል። ነበር ግን በበጀትና ሌሎችም ችግሮች የተሻለ ውጤት ማምጣት አልተቻለም። ስፖርቱ በኢትዮጵያ አሁን ካለበት የተሻለ ውጤት እንዲያመጣ በፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ደረጃ ጭምር ስልጠናዎችንና ውድድሮችን እንዴት መደረግ እንዳለባቸው ውይይት ተደርጓል። የዓለም ዓቀፍ ስልጠናዎችን ወደ ሃገር ውስጥ አምጥቶ እንደሚሰጥ የገለጹት ኃላፊው ባለሙያዎችን ወደ ውጭ ልኮ ለማሰልጠን ብዙ ወጪ ስለሚጠይቅ በትንሽ ወጪ በሀገር ውስጥ ለብዙ ባለሙያዎች የስልጠና የአቅምግንባታ ድጋፍ እንደሚሰጥ ተናግረዋል። በዚህ በ2015ዓ.ም ከኦሊምፒክ ሶሊዳሪቲን ጨምሮ ሁለት ስልጠናዎች እንደተሰጡ ገልጸዋል።
እንደ አትሌቲክሱ ሁሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፖርቱ ተወዳዳሪ ሆነው ውጤት የሚያሰመዘግቡ አትሌቶችን ለማፍራትም ፌዴሬሽኑ ጠንካራ ስራ እንደሚሰራ የገለጹት አቶ ፍቅሩ፣ በቶኪዮ በአንድ ተወዳዳሪ ብቻ የነበረው ተሳትፎ በፓሪስ ኦሊምፒክ በሙሉ ቡድን እንዲሆን ጥረት ይደረጋል ብለዋል።
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 28 /2015