
የኮተቤ የእንስሳት ገበያ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ደርቷል። እዚህም እዚያም ገዥዎች የመረጡትን በግና በሬ ለመግዛት ከሻጮች ጋር የዋጋ ክርክር ያደርጋሉ። የቅርጫ የሚሆን በሬ ለመግዛት ወደ ገበያው መጥተው ከሻጩ ጋር በሬውን ለመግዛት ሲነጋገሩ ከተመለከትናቸው ገዥዎች መካከል አንዱ አቶ መገርሳ ከኒሳ ናቸው።
አቶ መገርሳ ከኒሳ የቅርጫ በሬ ለመግዛት ወደ ገበያው የመጡ መሆናቸውን ገልጸው፤ በኮተቤ ብረታ ብረት በሬና በግ ተራ ያለው የዋጋ ሁኔታ ካለፉት ጊዜያት ጋር ሲነጻጸር የዘንድሮው መጠነኛ ጭማሪ አሳይቷል ይላሉ።
በዘንድሮው የገና የበዓል ገበያ አነስ ያለ በሬ እስከ 30 ሺህ ብር ዋጋ የሚጠየቅ ሲሆን፣ ትላልቅና የደለቡ በሬዎች ደግሞ ከ85 ሺህ ጀምሮ እየተሸጡ መሆኑን ይገልጻሉ። ይህም ዋጋ ካለፉት የበዓላት ጊዜያት ጋር ሲነጻጸር መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ መኖሩ ያሳያል ይላሉ።
ብዛት ያላቸው በሬዎች ለበዓል ገበያ ማቅረባቸውን የሚገልጹት አቶ አብዱረህማን ጋሻው፤ በበሬ ላይ መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ ሊከሰት የቻለው የእንስሳት መኖና የትራንስፖርት ዋጋ በመጨመሩ እንደሆነ ይናገራሉ።
ከባለፉት ጊዜያት ጋር ሲነጻጸር የበግ ገበያው ዋጋ ጭማሪ አሳይቷል ያሉት ከካዛንቺስ የመጡት አቶ ከበደ ካሳ ፤በግ 7 ሺህ 500 ብር መግዛታቸውን አስረድተዋል። በሌላ በኩል የበግ ገበያው ከ4 ሺህ ጀምሮ እስከ 18 ሺህ ድረስ በመሸጥ ላይ መሆኑንና መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን እኛም በምልከታችን ታዝበናል።
በሌላ በኩል በሾላ ገበያ ዶሮ በስምንት መቶ 50 ብር ሲገዙ ያገኘናቸው ወይዘሮ ጸሀይ እሸቱ፤ ዶሮ በገበያው ለምርጫ በሚመች መልኩ መቅረቡን ያነሳሉ። ካለፈው በዓል ጋር ሲነጻጸር ያለው የዋጋ ልዩነት እምብዛም ነው ባይ ናቸው።
ዶሮ ባለፉት ጊዜያት 7 መቶ ብር ይሸጥ የነበረ መሆኑን በማስታወስ በዘንድሮው በዓል የዋጋ ጭማሪ መኖሩን ያነሱልን በዶሮ ሽያጭ ላይ ተሰማርተው ያገኘናቸው አቶ ሙሉብርሀን ገብረ መስቀል ናቸው። በዚህም መካከለኛ ዶሮ ሰባት መቶ 50 ብር ሲሆን ጥሩ የተባለ ዶሮ ደግሞ እስከ ስምንት መቶ 50 ብር ድረስ እየተሸጠ ይገኛል።
በባለፈው ዓመት ለአንድ ትልቅ ዶሮ በአንድ ሺህ ብር መግዛታቸውን አስታውሰው ፤በዘንድሮው ሁለት ዶሮዎችን በአንድ ሺህ 800 ብር መግዛት መቻላቸውን የገለጹልን አቶ መንበሩ ክፍሌ የተባሉ ናቸው። ካለፈው ዓመት የዋጋና አቅርቦት መጠን ጋር ሲታይም የተጋነነ ልዩነት አለመኖሩን ጠቁመዋል።
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 28 /2015