‹‹የኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ሻኪሶ ወረዳ ምድሩ ሁሉ ወርቅ ነው። በሌሎች የከበሩ ማዕድናትም ቢሆን ኣካባቢው በተፈጥሮ ታድሏል። በአለም በእጅጉ ተፈላጊ የሆነው የኤመራልድ ማእድን መገኛም ነው፤ የዚን ማእድን አንዱ ግራም ከ85ሺ እስከ አንድ መቶ ሺ ብር ዋጋ ያወጣል፤ በኤመራልድ ሀብት ኢትዮጵያ ከኮንጎ ቀጥላ ሁለተኛ እንደሆነች ይነገራል። ይላሉ በጉጂ ዞን በወርቅ ልማት የተሰማሩት አቶ መኩሪያ ባሳዬ። በእኔ እምነት በዚህ ሀብት ላይ ጥናት ቢደረግ ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ሀገር ትሆናለች። ለካሜራ መሥሪያ ግብአት የሚውለው የታንታለም ማዕድንም ኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት ይገኛል።›› ሲሉ ይጠቁማሉ።
ባለሀብቱ በጉጂ ዞን ኦዶ ሻኪሶ ወረዳ ያለው የወርቅ ማዕድን ክምችት ብቻውን ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ የማዕድን ሀብቱ በአግባቡ ቢለማ ከዘርፉ የሚገኘው ሀብት ከኢትዮጵያም አልፎ ለጎረቤት ሀገሮች እንደሚተርፍ ነው የጠቆሙት። ባለሀብቱ ቁጭት በተቀላቀለበት ስሜት የወርቅና የከበሩ ማዕድናት ባለቤት ስለሆነው ጉጂ ዞን ሻኪሶ ወረዳ ሲያብራሩም ‹‹በዚህ ማእድን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማሳደግ የሚቻለው ግን የማእድን ሀብቱን የግል ጥቅማቸውን ከሚያስቀድሙ ህገወጦች መከላከልና ለሀገር ተቆርቋሪ የሆኑ አልሚዎችን በልማቱ ማሳተፍ ሲቻል ነው›› ብለዋል።
አቶ መኩሪያ የታይም ጀነራል ቢዝነስ ግሩፕ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው። የወርቅ ማዕድን ልማትን ‹ሀ› ብለው የጀመሩበት የወርቅ ምድር በሆነው ጉጂ ዞን ሻኪሶ ወረዳ ነው። በአካባቢው የሚካሄደው የማዕድን ሀብት በሚገባው ደረጃ ለምቶ በሀገራዊ ምጣኔ ሀብት ላይ ድርሻ አለማበርከቱ ሀገራዊ ቁጭት አሳድሮባቸዋል።
ህገወጥነቱ ተስፋፍቶ የውጭ ዜጎች ሳይቀሩ በአካባቢው ላይ ሆነው ያለከልካይ ሀብቱን ለግል ጥቅማቸው ሲያወሉ ማየታቸው አንገብግቧቸዋል። ‹‹ኢትዮጵያ ባለፉት ጊዜያቶች በውስጥና በውጭ በተፈጠረባት ጫና ምክንያት የውጭ ምንዛሪ እጥረት በገጠማት ጊዜ ወደ ገንዘብ ልትቀይረው የምትችለው ሀብት እያላት ተቸግራ ሀብቱ የግለሰቦች መጠቀሚያ ሆኖ ከማየት በላይ ምን የሚያም ነገር ይኖራል? ሲሉም ይጠይቃሉ።
አቶ መኩሪያ ብሄራዊ ባንክ መግባት ያለበት ወርቅ ላለመግባቱ አንዱ ምክንያት ህገወጥነትን መከላከል አለመቻል እንደሆነ ይገልጻሉ። ህገወጥነቱ ተስፋፍቶ ሀብት እየባከነ መሆኑን የበለጠ መገንዘብ የቻሉት በወርቅ ማዕድን ልማት ላይ በስፋት ለመሥራት ወስነው ከማዕድን ሚኒስቴር የልማትና የጥናት ፈቃድ ወስደው ሥራ ለመጀመር እንቅስቃሴ በጀመሩበት ወቅት ነው።
አቶ መኩሪያ የማዕድን ሀብት የሚያስገኘውን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ለመገንዘብ በማይችሉበት እድሜ ላይ ሆነው ነበር ጉጂ ዞን ሻኪሶ ወረዳ የወርቅ ማዕድን ልማት የጀመሩት። ከቁፋሮ ጀምሮ ከአልሚዎች ዱቄት፣ ወርቅ ገዝተው ለገበያ በማቅረብ ሲሰሩ በቆዩባቸው ጊዜያት የማዕድን ልማት ሥራው ምን ያህል ከባድ እንደሆነ፣የጥቅም ግጭትም የሚያስነሳ እንደነበር ያስታውሳሉ፤ የጥቅም ግጭቱ እስከ ህይወት መስዋእትነት የሚያደርስ መሆኑን ይገልጻሉ።
በሥራው ውስጥ ለመቆየትም እልህ ያስያዛቸው ዘርፍ ሆኖ ነው ያገኙት። የተለያዩ ፈተናዎችን አልፈውም ሌላው ዓለም ለወርቅ ማዕድን ልማት የሚጠቀምበትን ቴክኖሎጂ በሀገራቸው ውስጥ እውን ለማድረግና የማዕድን ልማቱን ትልቅ ደረጃ በማድረስ የራሳቸውን አበርክቶ ለመወጣት በመትጋት ላይ ናቸው።
እንዲህ ለትጋት ያበቃቸው በጉጂ ዞን ቦሬ ወረዳ ጎምቢሶ ኡሙሪ መረቱ ቀበሌ ውስጥ ዶማና ዲጅኖ ተጠቅመው ከአምስት ቀናት ሙከራ በኃላ መጠኑን በውል ባያውቁትም ወደ 22ሺ ብር ያስገኘላቸውን ወርቅ ማግኘታቸው ነው። ወቅቱ በ1980ዎቹ አካባቢ ነበር። በኃላም ከአካባቢው ዱቄት ወርቅ ከአልሚዎች እየተረከቡ አዲስ አበባ ወስደው ይሸጡም ነበር። ይህ የመጀመሪያው የወርቅ ማዕድን ልማታቸው በውስጣቸው የፈጠረችባቸው ጥሩ ስሜት ልዩ ነበር።
አቶ መኩሪያ ለተለያዩ ጫናዎችም ተዳርገዋል፤ ይህን ተከትሎም በ1980ዎቹ መጨረሻ ከዘርፉ ወጥተዋል። በጥቅሜ መጣህ ከሚል ግለሰብና በቡድን ተደራጅተው በማዕድን ሥራው ላይ ከሚገኙ ጀምሮ በቀደመው የመንግሥት ሥርአት ይደርስባቸው በነበረው ጫና በልማቱ እንዳይቀጥሉ የሚያደርግ ብዙ ፈተና ገጠማቸው። በወቅቱ የነበረው መንግስትም ወንጀለኛ ብሎ አስሯቸዋል፤ ተንገላትተዋል፤ ለኪሳራም ተዳርገዋል።
መሰናክሎችን አልፈው ተስፋ ሳይቆርጡ በማዕድን ልማቱ ላይ የቆዩት አቶ መኩሪያ ሀገራዊ ለውጥ ከተደረገ በኃላ ደግሞ ወደ ወርቅ ማዕድን ልማቱ ተመለሱ። ካለፈው ትምህርት አግኝተውና በዘርፉ ላይም የነበራቸውን ቆይታ በመጠቀም በዘርፉ ከፍተኛ ለውጥ ለማስመዝገብ ሰፊ እቅድ ይዘው ነው የተመለሱት።
እንደ አቶ መኩሪያ ገለጻ፤ የማዕድን ልማቱን በጀመሩበት ጉጂ ዞን ሻኪሶ ወረዳ ሰፋ ያለ ልማት ለማከናወን ፍቃድ ወስደው ሲንቀሳቀሱ ያልጠበቁት ነገር ገጠማቸው። አካባቢው ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የተለያዩ ሀገሮች ዜጎች የውጭ ዜጎች ተሰማርተዋል። እርሳቸው ወደ ልማቱ ከመግባታቸው በፊት የውጭ ዜጎቹ በአካባቢው ላይ በምን ሁኔታ ልማቱን እያከናወኑ እንደሆነ ለማጣራት ቅድሚያ ሰጥተው መሥራት ጀመሩ። ባደረጉት ማጣራትም በአነስተኛ የማዕድን ልማት ላይ ተሰማርተው ነው የሚሰሩት። ለአካባቢው አርሶ አደሮች የተወሰነ ገንዘብ በመስጠት መሬቱን በመቆፈር የማዕድን ፍለጋ እያደረጉ እንደሆነም ተከታትለው ደረሱበት።
ግለሰቦቹ የሚያለሙት ማዕድን የት እንደሚገባም የሚከታተልና የሚቆጣጠር አካል እንደሌለም ባደረጉት ክትትል መረዳት ቻሉ፤ በዚህም ህገወጥነቱ ሥር የሰደደ መሆኑንም ተገነዘቡ፤ በሀገር ደረጃ እርምጃ የሚያስፈልግ ሆኖ አገኙት። ችግሩ መፍትሄ እንዲያገኝ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ድረስ በር አንኳኩተዋል። የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚደንት አቶ ሽመልስ አብዲሳንም አግኝተው ጉዳዩን አሳውቀዋቸዋል።
ህገወጥነትን መከላከል የመንግሥት ድርሻ ብቻ አይደለም በማለት የዜግነት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ያደረጉት ጥረት በመንግሥት ምላሽ በማግኘቱም በህገወጥ ተግባሩ ይንቀሳቀሱ የነበሩ የውጭ ዜጎች ከአካባቢው ርቀዋል። ይህን ውጤት ለማምጣትም ሶስት ወራት ያህል ጊዜ ወስዷል። አቶ መኩሪያ አሁን ጉጂ ዞን ላይ ወርቅ በአግባቡ እየተመረተ እንደሆነ ማረጋገጥ ችለዋል።
ሁለተኛው ተግባራቸው መሠረተ ልማት ማሟላት ነበር። መንግሥት ባያሟላም የኔም ድርሻ ነው ብለው ልማቱን በሚያከናውኑበት አካባቢ 41 ኪሎሜትር ተራራ አስቆርጠው መግቢያ መንገድ አሰርተዋል። ልማቱን ለማከናወን የተረከቡት ቦታ በዞኑ በሚገኙ አምስት ወረዳዎች 381(ሶስት መቶ ሰማኒያ አንድ )ኪሎሜትር የሚሸፍን ሲሆን፣የደለል ወርቅ ልማትና የጥናት ሥራ ለመሥራት ያቀዱትን ለማሳካት በዚህ መልኩ ምቹ አደረጉ።
የመንገድ መሠረተ ልማቱን ካሟሉ በኃላ ደግሞ ተደራጅተው አብረዋቸው የሚሰሩ የአካባቢውን ወጣቶች ማዘጋጀት ነበረባቸው። በልማቱ ሀብቱ በሚገኝበት አካባቢ የሚኖረውን ማህበረሰብ አሳታፊ ማድረግ ካልተቻለ በአንድ ድርጅት ወይንም ኩባንያ ብቻ ልማቱ ውጤታማ አይሆንም የሚሉት አቶ መኩሪያ፣ የአካባቢው ወጣቶችና ማህበረሰቡ ተጠቃሚ ሲሆኑ የእኔነት ስሜት ይፈጠራል ይላሉ። ማህበረሰቡ ተጠቃሚ ሲሆን ሀብቱን እንደሚጠብቅና ህገወጦችንም እንደሚከላከል ይገልጻሉ።
እርሳቸው እንዳሉት፤ በዚህ አስተሳሰብ 6ሺ700 (ስድስት ሺ ሰባት መቶ) ሰዎችን ወደ ልማቱ ለማስገባት ለአንድ ወር የተለያዩ ወጪዎችን ችለው በወርቅ ማጣራት ስልጠና እንዲያገኙ አድርገዋል።
በስልጠናውም ወጣቶቹ ታማኝ አልሚ አንዲሆኑም እርሳቸው ከታዳጊነት እድሜያቸው ጀምሮ ያሳለፉትን ውጣ ውረድና የስኬት ተሞክሮአቸውን አካፍለዋል። 60 ሣንቲም ይዘው የሸንኮራ አገዳ ንግድ እንደጀመሩና በዚያ አድገው በተለያየ የንግድ ሥራ ውስጥ እንዳለፉ፣በኃላም ወደ ወርቅ ልማት መምጣታቸውን በመጥቀስ ልምዳቸውን ማካፈላቸውን ያብራራሉ። ውጣ ውረዶችን አልፈው ስኬት ላይ የደረሱት ታማኝና ታታሪ በመሆናቸው መሆኑን በመግለጽ እንደመከሯቸውም ነው የሚናገሩት።
አቶ መኩሪያ እሳቸው አለመማራቸውንም ለወጣቶቹ አልሸሸጓቸውም። ያልተማሩትም ወላጆቻቸው የትምህርትን ጥቅም ባለማወቃቸው እንደሆነና ጥሩ ገበሬ እንዲሆኑላቸው ካላቸው ፍላጎት እንደሆነም ይነግሯቸው እንደነበር ይገልጻሉ። ሰው ራሱን ለመጥቀምና ሀገሩንም ለማገልገል ፍላጎት ካለው ስኬታማ መሆን እንደሚችል በመጥቀስ፣ ወጣቶቹ የተሰማሩበት ልማት የሀገር ኢኪኖሚን የሚያሳድግ መሆኑን በመጥቀስም፣ በጥቂት ጥቅም ተታልለው ጉዳት እንዳያደርሱ ሁሌም እንደሚመክሯቸው አቶ መኩሪያ ይናገራሉ።
ለሥራ ዝግጁ ካደረጓቸው ወጣቶች መካከል የዩኒቨርሲቲ ምሩቆች መኖራቸውንም የተናገሩት አቶ መኩሪያ፣ ወጣቶቹ በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥራ እንዲሰሩም ከሁለት ሚሊየን ብር በላይ ወጭ አድርገው የወርቅ ማጠቢያ መሽን ገዝተው ልማቱ በሚከናወንበት ቦታ በመትከል በቅርቡ ማስመረቃቸውን ገልጸዋል።
በወቅቱም የታይም ጄኔራል ቢዝነስ ግሩፕ የሆነው ታይም ድርጅት በዞኑ የገናሌ ወንዝ ተፋሰስን ይዞ አና ሶራ፣ቦሬ፣ኦርዳ ጂላ ወረዳዎች ውስጥ የወርቅ ማዕድን ማውጣት ሥራ አስጀምሯል። በድርጅቱ በቀረበው የወርቅ ማጠቢያ ማሽን ልማቱን ለማከናወን ሰልጥነው ወደ ሥራ የገቡት ወጣቶች ካለሙት 30 በመቶ ድርሻ እንደሚኖራቸውም ነው የተናገሩት። ለአብነትም ከልማቱ ሽያጭ 10 ሚሊየን ብር ቢገኝ ሶስት ሚሊየኑ የወጣቶቹ ድርሻ ነው።ከገቢው 30 በመቶ የነዳጅ፣30 በመቶ የማሽን ኪራይ፣10 በመቶ ደግሞ ሥራውን ለሚያስተባብረው እንዲውል ተደርጎ ነው የተሰላው።
‹‹ሁሉም ፊቱን ወደ ልማቱ በማዞር በርብርብ በትክክል ቢሰራ እንዲሁም ሀብቱን ለመቀራመት የሚሯሯጠውን ማስቀረት ቢቻል በማዕድን ልማት ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ለማምጣት አምስት አመት በቂ ነው››የሚሉት አቶ መኩሪያ፣ እርሳቸው በግላቸው ጥረት ከማድረግ ወደኃላ እንደማይሉ ነው ተናገሩት።
እሳቸው እንዳሉት፤ በአምስት አመት ጊዜ ውስጥ በማዕድን ዘርፍ ለ 55ሺ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር አቅደዋል። የኢትዮጵያን የወርቅ አቅርቦትም በ25 በመቶ ለማሳደግ ይሰራሉ።
ባለሀብቱ በኩባንያ ደረጃ ኢትዮጵያ ውስጥ በወርቅ ልማት ላይ ከሚገኘው ሜድሮክ ወርቅ ኩባንያ ጋር ብቻ ሳይሆን፣አፍሪካ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ ኩባንያዎች ጋር ተወዳዳሪ የሆነ ኩባንያ በመፍጠር ኢትዮጵያን በልማቱ የማሳደግ ራዕይም ሰንቀዋል። ‹‹ኢትዮጵያ በቂ ሀብት አላት። የተማረ የሰው ኃይልና ቴክኖሎጂ ነው የሚያስፈልጋት፤ ድርጅቴ ይህንን ለማሟላት ዝግጁ ነው።›› የሚሉት አቶ መኩሪያ፣ አሁን ለጊዜው ወጣቶቹ እንዲያለሙበት የተተከለው የወርቅ ማጠቢያ ማሽን በሀገር ውስጥ ተመርቶ የሚቀርብና እስከ 65 በመቶ ወርቅ ለማውጣት አቅም ያለው መሆኑን ይገልጻሉ።
አቶ መኩሪያ በማሽኑ የታጠበው ወርቅም እንደሚታይ ጠቅሰው፣ ይህ መሆኑ ለስርቆት የመጋለጥ እድሉን ሰፊ እንደሚያደርገው ይገልጻሉ። በማምረት አቅሙም ሆነ ታጥቦ የወጣው ወርቅ ከእይታ ውጭ እንዲጠራቀም የሚያደርግ የተሻለ ቴክኖሎጂ ከአሜሪካና ከቻይና ሀገሮች በግዥ ለማምጣት ድርጅቱ ጥረት እያደረገ መሆኑን አስታወቀው፣ አንድ ማሽንም ሀገር ውስጥ መግባቱን ይገልጻሉ።
በተለይ ከአሜሪካ በግዥ ለማስገባት የታቀደው ማሽን ከፍተኛ መጠን ያለው ድንጋይ በመፍጨት ወርቅ መለየት እንደሚያስችል አብራርተው፣ 220 ቶን በሰአት የመፍጨት አቅም እንዳለውም ነው ያመለከቱት። የማሽን ገጠማው የሚከናወነውም ግዥው ከተፈጸመበት ሀገር በሚመጡ ባለሙያዎች መሆኑን ይገልጻሉ። ባለሙያዎቹ ለሀገር ውስጥ ባለሙያዎችም ሥልጠና እንዲሰጡ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ እንዲህ ያለውን ማሽን የሚጠቀሙት እንደካናዳ ያሉ ሀገራት ናቸው። ደርጅታቸው ከነዚህ አቅም ካላቸው ማእድን አምራቾች ጋር ተወዳድሮ ለመሥራት ጥረት እያደረገ ነው።
አቶ መኩሪያ፤ በማዕድን ልማቱ ትልቁ ጥቅሜ ያሉት ወርቁ ለሀገር ጥቅም እንዲያስገኝ ማድረግ አንዱ ነው፤ ወርቅ ለብሄራዊ ባንክ ሲያስገቡና የባንኩ እንቅስቃሴ ሲጨምር የእሳቸው ሽያጭ መጨመሩንም ሌላው ጥቅም ይሉታል። ‹‹እኔ አንድ ያለችኝ ሀገር ኢትዮጵያ ናት፤ ለዚህች ሀገር መሥራት አለብኝ››ሲሉ ገልጸው፣ በሥራቸው ለሀገር ፍቅር ያላቸውን ስሜት በመግለጽ ሁሉም በዚህ መንፈስ እንዲሰራ ጠይቀዋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 28 ቀን 2015 ዓ.ም