ገና ኢትዮጵያዊ ትውፊት ካላቸው በዓላት አንዱ ነው። በተለይም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ክፍል በድምቀት ከሚከበሩትና ዘመናትን የተሻገረ ልዩ የአከባበር ዘዬ ካላቸው በዓላት አንዱ ነው። ከዜማው እንጀምር፤-
አሲና በል አሲና ገናዬ … እዮሀ
አሲናበል … እዮሀ …
አሲና ገናዬ
አሲና በል በገና ጨዋታ …እዮሀ
አሲና በል …እዮሀ
አሲና ገናዬ
አሲና በል …አይቆጡም ጌታ… እዮሀ
አሲና በል- እዮሀ
አሲና ገናዬ ፤
ለመሆኑ ይህ ከምን አንጻር ሆነ ካላችሁ መልሱ ብዙ ነው። አንዱ ከስያሜውና ከክብረ በዓሉ ጋር የሚያያዘው ጉዳይ እንደሆነ ብዙዎች በአስረጅነት የሚያነሱት ነገር አለ። ለአብነት ከእኛው ሊቅ መምህር ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ማብራሪያ እንነሳ።
ትርጉሙን በመዝገበ ቃላት ሐዲስ ላይ ሲያስቀምጡት ‹‹ጌና›› ሲሉ ይጠሩታል። ጌና ከጽር የተገኘ ሲሆን፤ የልደት ዋዜማ መጠሪያ ወይም ድራር ማለት ነው። ይኸውም ገሃድ ወይም በዓለ ልደት እንደማለትም ነው ይሉታል። የቀድሞ ስንክሳር የታህሳስ 28 ወይም 29 መግቢያ “እንተ በኵሉ ክብርት ጌና ዘይእቲ ልደቱ በሥጋ” ሲል የልደት በዓልን -ገና ብሎ እንደሚጠራውም ቀጥለው ጠቅሰውታል። ብዙ የኢትዮጵያን ሃይማኖታዊ፣ታሪካዊና ባህላዊ መስህብ ቦታዎች የሚያስጎበኙበት ነውም ባይ ናቸው።
ቃሉ ከግሪክ ገናና ከሚል ቃል የተገኘ እንደሆነ የጻፉም አሉ። ትርጉሙም የጊዜው መድረስ፣ ሊፈጸም ያለው እንደማለት ሲሆን፤ የጌታ መምጣትና የሰው ልጅን ከኃጢአት መንጻት ለመግለጽ የተቀመጠ እንደሆነ ያስረዳሉ። ለዚህም ነው ገና በብዙዎች ዘንድ የተለየ ትርጉም ተሰጥቶት የሚከበረው። በእምነት በባህልና በበዓሉ አከባበር የተለያየ ሁነቶችንም ያስተናግዳል።
በዓሉ በየዓመቱ ሁልጊዜ ታህሳስ 29 የሚከበር ሲሆን፤ የዘመነ ሉቃስ መጨረሻዋ ወር ጳጉሜን ስድስት ስለምትሆን ዘመነ ዮሐንስ ላይ በ28 እንዲከበር ተደርጓል። ይህም የተጀመረው በአፄ ዐምደ ጽዮን ዘመነ መንግሥት እንደሆነ ይገለጻል። ይህ በዓል ምንም እንኳን ኢትዮጵያውያን የዘመን አቆጣጠራቸው የተለየና ብቸኛ የሚያደርጋቸው ቢሆንም ኢትዮጵያውያን ግን ብቻቸውን አያከብሩትም። ሌሎች አገራትን ያስከትላሉ። ለአብነት ግብጽ፣ ሶርያ ሕንድና አርመን እንዲሁም የእስክንድርያ ቤተክርስቲያናት አብረዋት የልደት በዓልን በአንድ ቀን ከሚያከብሩት መካከል ናቸው። ወደ ሩቅ ምሥራቅ ስንሄድ ደግሞ ግሪክና ሩስያን እናገኛለን።
ሌላው ይህ በዓል ለኢትዮጵያን የተለየ የሚሆንበት ምክንያት አከባበሩ የአገሪቱን ባህልና ባህሪ የያዘ መሆኑ ነው። አገራት በበዓላት ወቅት የራሳቸው የሆነውን ሁሉ አውጥተው ያሳያሉ፤ ማንነታቸውንና የእርስ በእርስ ትስስራቸውን ያጸናሉ። ባህላቸውን ትውልዱ ብቻ ሳይሆን ዓለም ጭምር እንዲያውቀው ያደርጋሉ። ኢትዮጵያ ቀደም ሲል በነበራት የበዓላት አከባበር ይህንኑ ተግባር ነው ስትከውነው የቆየችው።
የገና ጨዋታ ብቻውን በራሱ በርካታ ሀገርኛ ባህሪያትን የምናይበት በዓል ነው። እንደውም አፈታሪኮች እንደሚያስረዱት ጨዋታው የተጀመረው እረኞች የክርስቶስን መወለድ በሰሙ ጊዜ እንደተደሰቱና በደስታቸውም ወቅት በሚያግዱበት በትር (ዱላ) በደስታ ሲጫወቱ ውለዋል። እናም ይህን ተከትሎ ጨዋታው በአብዛኛው በወጣት ወንዶች ደምቆ ይውላል። በሚዳኙት ሽማግሌዎችና ጨዋታውን በሚከታተለው ነዋሪም ይታጀባል። በዚህ ውስጥ ደግሞ ብዙ መልዕክቶች ይተላለፋሉ።
አንደኛው በጾታ ተከፋፍሎ መከበሩ ሲሆን፤ ከዋዜማው የሚጀምረው ነው። ማለትም ታኅሣሥ 29ኝን የሚይዘው ዓመት በሙሉ ዋዜማው ላይ የወንዶች ገና ተብሎ ተሰይሞ በጨዋታ ሲደምቅ ይሰነብታል። ገና በ28 ሲውል ደግሞ የሴቶች ገና ስለሚባል ሴቶችም በጨዋታው ውስጥ ባይገቡም ተመልካች ሆነው እንዲሰየሙ ተደርጎ የገና በዓል ድምቀቶች ሲሆኑ ይስተዋላል።
በተመሳሳይ ገና የልጆችም ልዩ በዓል ተደርጎ ይከበራል። ምክንያቱም በጊዜው ልጆች ከብት ማገድ፣ ሥራ መታዘዝና ሌሎች ተግባራትን እንዲከውኑ አይገደዱም። ነጻነት ይቸራቸውና የፈለጉትን ጨዋታ ይጫወታሉ። ሳይሸማቀቁና ማንም ተቆጪ ሳይኖርባቸው ይጨፍራሉ፤ የተሰማቸውን እንዲናገሩም ይደረጋሉ። ማለትም ፊት ለፊት ሳይሆን በግጥሞቻቸው ውስጥ አድርገው የፈለጉትን መሸንቆጥ ይችላሉ።
እናም በነገው ዕለት የሚከበረውን የገና በዓል የወንዶች አለያም የልጆች ገና ብለን ልንወስደው እንችላለን። በዚህ ቀን ምን ምን ተግባር ይከወናል ከተባለ መግቢያችን ላይ ያወረድናቸው የዘፈን ግጥሞች የመጀመሪያውን ቦታ የሚይዙ ናቸው። ምክንያቱም አሲና ገናዬ ለማለት ዕለቱ ዛሬ ነው። እናም በተሰጣቸው ቀን ዳኛ ሰይመው በተለያዩ አካባቢዎች ላይ ግጥሚያ ያደርጋሉ። መመታታት ይኖራል፤ የአካል ጉዳት ጭምር ሊከሰት ይችላል። ነገር ግን ማንም የሚቆጣ፣ የሚጣላ አልያም አቁሙ ሊል የሚችል አይኖርም። መቃቃርም አይፈቀድም። ምክንያቱም ጥንጓ (ኳሷ) ኃይለኛ ለጊ ካገኘች የምታርፍበት ቦታ አይታወቅም። ስለዚህም ዓይን እንኳን ቢጠፋ ማንም አይቆጣም። ከዚህ ይልቅ ጨዋታውን በሚመለከቱ አባቶችም በድብድብ መሳቅ ይዘወተራል። ምክንያቱም ሽምግልናቸው ለገና ጨዋታ አይሠራም። ስለዚህም በገና ጨዋታ “እግር ይብሳል፣ያንከላውሳል።” እያለ ማስፈራራት፣ ራስን መቀወር ወይም እንቆራቆስ ብሎ እጅና እግርን በዱላው መምታት የተለመደ ነው። ለዚህም ነው በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ የምንለው።
ይህ ባህላዊ ጨዋታ ብዙ ለየት የሚያደርጉት ነገሮች ያሉት ነው፤ በሕግ የሚመራም ነው። ለአብነት ያክል ብንመለከት አስቀድሞ ሁለት ሰዎች የሚመረጡበት መሆኑ አንዱ ነው። ከምርጫው በኋላ ተጫዋቾቹ ወደ አባቶች መቅረብና መመረጥ ግዴታ አለባቸው። በጨዋታው ሕግ በሚጋጠመው ቡድን መካከል የተለያየ ቁጥር ያለው ተጫዋች ይዞ መግባት ይቻላል። ለምሳሌ ጨዋታው በመንደሮች መካከል ከሆነ የታች አምባው 50 ተጫዋች ቢኖሩት የላይ አምባው 100 መያዝ ይችላል። ማንም አይከለክለውም።
ሌላው የገና ጨዋታን ለየት የሚያደርገው ነገር በንጉሣውያን ዘመን የመኳንንቱ አሽከሮች፣ የንጉሡና የንግሥቲቷ አሽከሮች የጌቶቻቸውን ስም ለማስጠራት የሚሳተፉበት የነጻነት በዓል መሆኑ ነው። ይህ ጨዋታ ሌላም አስደናቂ ነገር አለው። አሸናፊ ለሆኑት ቡድኖች ፍሪዳ ይጣልላቸዋል፤ የተጣለው ጠጅ ይቀርብላቸዋል። ከዚያ ያንን እየበሉና እየጠጡ፣ እየዘፈኑ ሲሸልሉና ሲያቅራሩ ይውላሉ ፤ያድራሉ። በዚህ ውስጥ ደግሞ የተሰማቸውን ሁሉ ይናገራሉ፤ ሀሳባቸውን በነጻነት ይገልጻሉ። መንግሥትን ጭምር የሚሸነቁጡበት ዕድል የሚያገኙበትም እንደሆነ ይታመናል።
እስኪ ከሚዘፍኑትና ከሚሸልሉበት ግጥሞች መካከል ጥቂቶቹን እናንሳ።
“ማታ ነው ድሌ፣
ይሄ ነው አመሌ።
አሲና በል አሲና ገናዬ።
ኦ! ጉ! አሲና በል አሲና ገናዬ።
ግፋው ግፋው አለኝ እኔ እንደምን ልግፋው፣
የአንድ በሬ ጨጓራ እንደ ቅል የነፋው።
የብብቱ ሽታ፣ የመንፈቅ በሽታ።
የጀርባው መረሬ፣ ያውላል ጥንድ በሬ።
ካስር ጋን አተላ፣
አይተርፈው በአንኮላ።
እግርህ የሸረሪት ሆድህ የእንቁራሪት፣
ቀን እንደጠላሁ ና እንዳትመጣ ሌሊት።”
ይህ ሽንቆጣ ለተራው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለመኳንንቱና ለነገሥታቱም ይሆናል። ምክንያቱም እነርሱን የወከሉ ሰዎች በመካከል አሉ። እናም የሕዝብ ስሜትና ሀሳብ የሚንጸባረቅበት መድረክ ተደርጎም ይወሰዳልና ልዩ ትኩረት የሚቸረው ነበር። የነጻነትና የመናገሪያ መድረክ በመሆኑም መሪዎች እህ ብለው ያደምጣሉ፤ የሕዝብን ስሜት ይለዩበታል። የተሳሳቱትንም ያርሙበታል። ሕዝብ እንደ ሕዝብ ቅሬታውን ያሰማበታል። ለዚህም ነው የዚህ ቀን
“በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ
በገና ጨዋታ የለም ሎሌ ጌታ።” እየተባለ የሚዘፈነው።
የገና ጨዋታ ሌላም ለአገር አበርክቶ አለው። ይህም ከበዓሉ ጋር ተያይዞ የሚደረጉ መልካምና አስተማሪ ተግባራት ናቸው። መረዳዳትን፣ መተጋገዝን፣ አብሮ መብላትና መጠጣትን የሚያላምድ ባህሪን የምናይበት ነው። ወራትና ይዘው የሚመጡትን መልካም ገጽታ የምናስተውልበት ነው። እንዴት ከተባለ ይህንን የስነቃል ግጥም እንመልከተው።
“ታኅሣሥ ገሠገሠ ከተፍ አለ ገና፣
እጠብቅሀለሁ አንተ ልጅ ቶሎ ና።
ይወዘውዘኛል አልጠላኝም ገና፣
ፍቅር ሞገደኛው እየነሳኝ ጤና።
ምግብ አያስበላ አያስለብስ ልብስ፣
ሞገደኛው ፍቅሩ ይዞኝ በታኅሣሥ።
በማለዳ ጀንበር በገና ጨረቃ፣
እኔን እኔን ብላ መጣች ተደብቃ።
ይለናል። መጪው ወር ጥር እንደሆነ ይነግረናል፤ ጥር ሲታሰብ ደግሞ ሠርግ ግድ ነው። ሠርግ ሲታሰብ ደግሞ የእህሉ መድረስ ይታሰባል። ስለዚህም ታኅሣሥ እህሉ ታጭዶ ጎተራው የሚሞላበት ጊዜ እንደሆነ ይነግረንና ጥር የፍቅርና የጋብቻ ወቅት እንደሚሆን ያበስረናል። ስለዚህ ገና መልካም ነገርን ማብሰሪያ ጭምር ተደርጎ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ይከበራል።
ዛሬስ ካልን መልሱ ይታወቃል። በምዕራባውያኑ ባህል ተጠምደን እኛነታችንን ለሌላ አስረክበናል። የማናውቀውን የገና አባት (ሳንታ) ፣ የክሪስማስ ዛፍና ብልጭልጭ ነገሮችን እያበዛን ሁሉ ነገራችንን ትተነዋል። በተለይም በከተሞች አካባቢ በመጤ ባህል የመወረር ሁኔታ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ ነው። እንዲያውም እስከ ገጠር ተስፋፍቶ ቱባው ባህላችን እየተዋጠ ይገኛል።
የባዕድ ሀገራት ልማድና ሥርዓት ተቀላቅሎበን ጉራማይሌ አከባበር ላይ እንደደረስን እየተመለከትን ነው። ኢትዮጵያ በበዓል አከባበር ሁኔታ አልሰለጠነችም የሚል አስተሳሰብ ያለውም ሰው በርካታ ሆኗል። ነገር ግን እኛ የሰለጠነው ገና ጥንት ነው። ለሌሎች ተምሳሌት የሆንባቸው ብዙ ነገሮች ያሉንም ዛሬ በመጣው ‹ስልጣኔ› ወይም ‹ዘመናዊነት› ሳይሆን ትናንት በነበረን ነገር ነው።
ትናንት ባህላችንን አክባሪና በማንነታችን ኩሩ ስለነበርን ለእኔ ሳይሆን ለእኛ ስንል ኖረናል፤ ብቻ መብላትን የምንጸየፍም ነበርን። ትናንት ‹በሕግ አምላክ› ስንባል ጸባችንን የምናቆም ሕዝቦች ነበርን። ትናንት ባንዲራችን ሲሰቀል በያለንበት ቆመን የምናከብርና ለክብሩ ጎንበስ ቀና የምንል ነበርን። ትናንት አንድነታችን ያበረ፣ ማንም የማይበጥሰው ፤ ለማንም የማንበረከክ ነበርን። ዛሬ ላይ ግን ለሰው ባህል እጅ የምንሰጥና ውጪ አምላኪ እየተሸረሸረ መጥቷል ።
ከላይ እንዳነሳነው በመጤ ባህል እየተዋጥን ከመምጣታችንም በላይ እን በዳንኪራና ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ፣ በስካርና አልባሳት ሽሚያ የሚያከብረው እየተበራከተ መጥቷል። እንደውም የምሽት ክበቦች በራቸው በሰፊው የሚከፈተው፣ የሚታደሰውና የሚመረቀው የገና በዓልን አስታኮ እስኪመስል ድረስ ውክቢያው የበዛ ነው። በዚህ መሐል ግን ያጡ ወገኖቻችንን የሚያስታውሱና ባላቸው አቅም ሁሉ በዓላትን ከተቸገሩ ወገኖች ጋር የሚያሳልፉ ሰዎችን ሳያመሰግኑ ማለፍ አይቻልም።
ኢትዮጵያውያን በሃይማኖታዊ፣ በመንፈሳዊ፣ በትውፊታዊ፣ በባህላዊ እሴቶች የበለጸግንና መተኪያ የማይገኝልን ሕዝቦች ነን። የሚጣል ነገር የሌለብን። ገናን አድምቀን የምናሳልፍበት ላሊበላን የመሰለ ማንም ጋር ያልተሠራ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያን ያለን። ስለዚህም ወደልቦናችን መመለሱ ይጠቅመናል። ግዴለሽነቱና ምን የአገባኝ ስሜቱን ወደጎን መተው አለብን። ራሱን ከዘመነው ጋር ያዘመነ እየመሰለውና የራሱን ባህል በመናቅ ባህር ውስጥ መዘፈቁን እናቁመው።
በእርግጥ እዚህ ላይ አንድ ሀሳብ ማንሳት ግድ ይለናል። ሁሉንም በአንድ መጨፍለቅ ተገቢ አይደለም። ባህል አክባሪዎችን በየዘመኑ እናያለን። የነበርንበትን መልካም እሴት ያስቀጠሉ ወጣቶችም አባቶችም በየአካባቢው አሉ። ለአብነት የጎጆ ቤታችን ትዝታ እንዲመጣ ከፈረንጁ ዛፍ ወደ ግርግም እያመጡ ባህላችንን ጠብቀን ቤታችንን እንድናሳምር እያገዙ ያሉ ሰዎች ብቅ ብቅ እያሉ ነው። በተመሳሳይ አንዳንድ አባቶች በከተማ ሳይቀር የገና ጨዋታ የምንጫወትበትና ፍቅራችንን የምናጠነክርበትን ሁኔታ እየፈጠሩልን ይገኛሉ።
በቴሌቪዥን መስኮትና መሰል የሚዲያ አማራጮች ላይ በመቅረብም ባህልን የመመለስ ሥራ የሚሠሩም አልጠፉም። እናም እነዚህን እና መሰል እሴቶቻችንን እንዳይጠፉ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያበርከቱልንን ሳያመሰግኑ ማለፍ ንፉግነት ነውና በርቱልን ለማለት እፈልጋለሁ።
ትውልዱን በማንነቱ የሚኮራና የራሱን ባህል የሚወድ ማድረግ ላይ ከመንግሥት ጀምሮ መሥራት ያስፈልጋል። ልዩ ትኩረትም ሊሰጠው ይገባል። አሁን ጊዜው እንደሀገር የምንሠራበት ወቅት ነው። ባህላችንን ምርኩዝ አድርገን መረዳዳት አለብን፤ ማንነታችንን መገንባትም ውዴታችን ሳይሆን ግዴታችን ነው። መልካም እሴቶቻችንን በማጎልበትም በየአካባቢው የሚታየውን ግጭት ማስቆም ይጠበቅብናል።
ከዚያም አለፍ ብለን ባህላዊ ሀብታችንን ወደ ቱሪዝም መስህብነት ማሳደግ አለብን። ምክንያቱም ይህ ጊዜ ለሌሎች አገራት የበረዶ ወቅት ነው። ፀሐይ የሚናፈቅበት ጊዜ። ለእኛ ደግሞ ብሩህና የደስታ ጊዜያችን ነው። እናም እነርሱ እኛን ናፍቀው እንዲመጡ ማድረግ ይገባናል። ከእነርሱ በምናገኘው ገንዘብም አገራችንን ከፍ እናደርጋለን። ስለዚህ መዘመን በባህል ልኬት ይሁን፤በገና በዓልም ኢትዮጵያዊነታችን ጎልቶ ይውጣ እንላለን ። መልካም በዓል!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ታህሳስ 28 ቀን 2015 ዓ.ም