የምንጊዜም ድንቅ የረጅም ርቀት አትሌት የሆነችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ከአራት አመታት በኋላ ወደ ውድድር ትመለሳለች። ሶስት የኦሊምፒክ ወርቅ ሜዳሊያዎችና የበርካታ የአለም ቻምፒዮናዎች አሸናፊዋ ጥሩነሽ ከረጅም ጊዜ በኋላ ወደ ውድድር ስትመለስ የመጀመሪያ ውድድሯን በሂውስተን ግማሽ ማራቶን ለማድረግ ከአስር ቀን በኋላ ቀጠሮ መያዟ ታውቋል።
እኤአ በ2018 የመጨረሻ ውድድሯን ያደረገችው ጥሩነሽ በወሊድና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ከውድድሮች ርቃ የቆየች ሲሆን ዘንድሮ ግን ወደ ጎዳና ላይ ውድድሮች ፊቷን መልሳ በአትሌቲክስ ህይወቷ ተጨማሪ ስኬት ለማስመዝገብ እንደምትሮጥ የሂውስተን ግማሽ ማራቶን አዘጋጆች ያወጡት መግለጫ ይጠቁማል።
“ ሂውስተን የምወደው ውድድር ነው፣ ዝግጅቴም በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው፣ ያለኝን አቅም ለመፈተሽና የቀጣይ የአትሌቲክስ ህይወቴን ምእራፍ ለመወሰን ይህ መልካም አጋጣሚ ነው” በማለትም የ2017 ቺካጎ ማራቶን አሸናፊዋ ጥሩነሽ አስተያየት ሰጥታለች።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ የጎዳና ላይ ውድድሮች እየታየች የምትገኘው የጥሩነሽ ዲባባ ታናሽ እህት አና ዲባባም በዘንድሮው ሂውስተን ግማሽ ማራቶን ከእህቷ ጋር እንደምትወዳደር ታውቋል። ከሁለቱ እህትማማቾች ጎን ለጎን በ2021 የበርሊን ማራቶን ሁለተኛ ሆና ያጠናቀቀችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ህይወት ገብረኪዳን ተወዳዳሪ እንደምትሆን ይጠበቃል። የ2022 የአለም ቻምፒዮና ላይ አራተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችው ኤርትራዊቷ አትሌት ናዝሬት ወልዱም የዘንድሮው ሂውስተን ግማሽ ማራቶን ፉክክር አካል ሆናለች።
ፈጣን ሰአት ይመዘገብበታል ተብሎ በሚጠበቀው የዘንድሮው የሂውስተን ግማሽ ማራቶን ውድድር በሁለቱም ጾታ አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶች ከአስር ሺ ዶላር ጀምሮ ሽልማት እንደሚያገኙ የውድድሩ አዘጋጅ ኮሚቴ አሳውቋል።
የ37 ዓመቷ ድንቅ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የዓለማችን የምንግዜም ምርጥ የረጅም ርቀት ሴት ለመባል በመም ውድድሮች በርካታ ታሪኮችን መስራት የቻለች ሲሆን ወደ ጎዳና ላይ ውድድሮች በተለይም ወደ ማራቶን ፊቷን ካዞረች ወዲህም ስኬቷ ቢቀጥልም በተለያየ ምክንያት ከውድድር ርቃ ቆይታለች። ያምሆኖ በኦሊምፒክ፤ በዓለም ቻምፒዮና ፤ በዓለም አገር አቋራጭ ውድድሮች የሰበሰበቻቸው ሜዳልያዎችና አጠቃላይ ውጤቶቿ በረጅም ርቀት ታሪክ ከሚጠቀሱ የዓለም ምርጦች ተርታ ያሰልፉታል። ይህ ክብረወሰኗ ከዚህ በኋላ በማራቶን ምርጥ ውጤቶች እየታጀበ የሚቀጥል ከሆነም የምንግዜም ምርጥ የረጅም ርቀት ሴት አትሌት ለሚለው የክብር ማዕረግ የሚቀናቀናት ላይኖር ይችላል። ጥሩነሽ በኦሊምፒክ እና የዓለም ቻምፒዮና በተጎናፀፈቻቸው ሜዳልያዎች ቁጥር የኢትዮጵያ ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበች ሴት አትሌት እንድትሆን አስችሏታል።
ጥሩነሽ እኤአ በ2017 በ37ኛው የለንደን ማራቶን በሩጫ ዘመኗ ሁለተኛውን የማራቶን ውድድር አድርጋ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ስታጠናቅቅ ያስመዘገበችው 2፡17፡56 አዲስ የኢትዮጵያ ማራቶን ክብረወሰን እንደነበር ይታወሳል። ይህም እኤአ በ2012 በለንደን ኦሊምፒክ ቲኪ ገላና ካሸነፈችበት 2፡18፡58 ሰዓት በ62 ሰከንዶች የተሻለ ነበር።
ጥሩነሽ ዲባባ በለንደን ማራቶን ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈችው እኤአ በ2014 ሲሆን በወቅቱ 2:20:35 በሆነ ሰአት 3ኛ ደረጃን ይዛ ነበር ያጠናቀቀችው። ጥሩነሽ በ2017 የቺካጎ ማራቶን በወቅቱ የአለም ሶስተኛውን ፈጣን ሰአት አስመዝግባ ካሸነፈች በኋላ በ2018 የበርሊን ማራቶን ተሳትፋ ነበር። በዚህ ውድድር ፈጣን ሰአት ታስመዘግባለች ተብሎ ቢጠበቅም 2:18:55 ሰአት አስመዝግባ ሶስተኛ ሆና ነበር ያጠናቀቀችው። ያም ውድድር የመጨረሻ የማራቶን ውድድሯ ነበር።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 27 /2015