በአልጄሪያ አዘጋጅነት በሚካሄደው የአፍሪካ አገራት ቻምፒዮንሺፕ(ቻን) ውድድር የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በውድድሩ ከሚካፈለው የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ያደርጋል።
በቻን ውድድር ለሶስተኛ ጊዜ ለመሳተፍ ትናንት በአገር ውስጥ የመጨረሻ ምዕራፍ ዝግጅታቸውን ያደረጉት ዋልያዎቹ፣ በሰሜን አፍሪካዊቷ አገር እስከ ውድድሩ መዳረሻ ዝግጅታቸውን የሚቀጥሉ ይሆናል። በዚህም ቆይታቸው በቻን ከሚሳተፈው ከሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን ጋር በሁለት ቀናት ልዩነት ሁለት የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን እንደሚያደርጉ ታውቋል።
በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከዚህ ቀደም ቡድኑ በሞሮኮ በሚኖረው ቆይታ ሁለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን እንደሚያደርግ መግለፁ የሚታወስ ሲሆን አንደኛው ጨዋታ ብቻ ከሞሮኮ ጋር እንደሚሆን ተነግሮ ነበር። የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን በቲውተር ገፃቸው ይፋ እንዳደረጉት ከሆነ ግን ዋልያዎቹ ሁለተኛውንም የወዳጅነት ጨዋታው ከሞሮኮ ጋር ያደርጋሉ።
የመጀመሪያው የቡድኑ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ከሶስት ቀን በኋላ ታኅሣሥ 29 ሲደረግ ሁለተኛው ደግሞ ከሁለት ቀናት በኋላ ጥር 1/2015 እንደሚከናወን ዋና ጸሐፊው አመላክተዋል። ዋልያዎቹ ወደ ሞሮኮ ትናንት ሌሊት ከማቅናታቸው በፊት ረፋድ ላይ የሀገር ቤት የመጨረሻ ልምምዳቸውን አከናውነዋል። ቡድኑ ለሁለት ሰዓት የዘለቀ ልምምዱን በሚሰራበት ጊዜም የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት እንዲሁም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ተገኝተዋል። ቡድኑ ልምምዱን ከጨረሰ በኋላም አምባሳደር መስፍን መንግስት ለብሔራዊ ቡድኑ ከፋይናንስ ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ እንደሆነ አስረድተው በውድድሩ የተሻለ ውጤት እንዲገጥማቸው ምኞታቸውን ገልፀዋል።
የቻን ውድድር ከመጀመሩ አስቀድሞ የተለያዩ ተሳታፊ አገራት የአቋም መፈተሻ ጨዋታ እያደረጉ የሚገኙ ሲሆን የውድድሩ አዘጋጅና በምድብ አንድ ከኢትዮጵያ ጋር የተደለደለችው አልጄሪያ ትናንት ቡድኗን ይፋ አድርጋለች።
አልጄሪያ ለውድድሩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ከሜዳ ውጪ በመስተንግዶ ሜዳ ላይ ደግሞ ቡድኗ ላይ የተለያዩ ሥራዎችን እየከወነች ትገኛለች። ከሁለት ወራት በፊት ጀምሮ የተለያዩ ተጫዋቾችን በመምረጥ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ላይ ዝግጅቷን ስታደርግ የቆየችው አልጄሪያ የመጨረሻ ስብስቧን ይፋ ስታደርግ የቀድሞ የብሔራዊ ቡድኑ አምበል የነበሩት እና አሁን የቻን ቡድኑን እያሰለጠኑ የሚገኙት ማጂድ ቡግሄራ ሦስት ግብ ጠባቂዎች፣ አስር ተከላካዮች፣ ሰባት አማካዮች እና ስምንት አጥቂዎችን በአጠቃላይ 28 ተጫዋቾችን በውድድሩ ለመጠቀም መርጠዋል።
ለዚህ ውድድር ዝግጅት በተለያዩ ቀናት እስካሁን አምስት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን ያደረገው የአልጄሪያ ብሔራዊ ቡድን የፊታችን ቅዳሜ ታኅሣሥ 29 ከጋና አቻው ጋር የመጨረሻ እንደሆነ የተገለፀውን የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ ቀጠሮ መያዙ ይታወቃል።
ሌላኛዋ በኢትዮጵያ ምድብ የምትገኘው ሊቢያ እግርኳስ ፌዴሬሽኗ አጋጥሞት የነበረው ችግር መፍትሔ አግኝቶ ትናንት ከኮትዲቯር ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ማድረጉ ታውቋል። የሊቢያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በገጠመው ችግር ምክንያት ከውድድሩ ራሱን ሊያገል እንደሚችል ከሁለት ቀናት በፊት የተነገረ ቢሆንም ትናንት ለችግሩ መፍትሔ በማግኘቱ ብሔራዊ ቡድኑ በውድድሩ እንደሚሳተፍ ተረጋግጧል። ብሔራዊ እግርኳስ ፌዴሬሽኑ የሂሳብ አካውንቱ በፍርድ ቤት በመታገዱ ምክንያት ወጪዎችን ለመሸፈን እቸገራለው ብሎ በይፋ መግለጫ አውጥቶ የነበረ ሲሆን የሀገሪቱ የስፖርት ሚኒስቴር ግን አስፈላጊ የወጪ ድጋፍ ለማድረግ በመወሰኑ ቡድኑ ቱኒዚያ ላይ እያደረገ ያለውን ዝግጅት አጠናክሮ ቀጥሏል ፤ በውድድሩም እንደሚሳተፍ ማረጋገጫ ተሰጥቷል።
በተያያዘ መረጃ በምድብ የመጀመሪያ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን የምትገጥመው ሞዛምቢክ ውድድሩ ወደ ሚካሄድበት አልጄሪያ ቀድማ የተገኘች የመጀመሪያዋ ሀገር መሆኗን ሶከር ኢትዮጵያ ዘግቧል። በቻን ውድድር ለሁለተኛ ጊዜ የምትሳተፈው ሞዛምቢክ ከሁሉም ሀገራት ቀድማ ከቀናት በፊት አልጄሪያ ደርሳለች። ዋልያዎቹም የመጨረሻ ምዕራፍ ዝግጅታቸውን ሞሮኮ ካደረጉ በኋላ ጥር 3 ወይም 4 ወደ አልጄሪያ የሚያመሩ ይሆናል። በአሠልጣኝ ቼኪኒዮ ኮንዴ የሚመራው የሞዛምቢክ ብሔራዊ ቡድን ወደ ሥፍራ አቅንቶ በቀጣዮቹ 15 ቀናት ዝግጅቱን ካደረገ በኋላ ጥር 6 የመጀመሪያ ጨዋታውን ከኢትዮጵያ ጋር በባራኪ ስታዲየም ያደርጋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 26 /2015