‹‹ይህ የጥንቷ ኢትዮጵያ ታሪክ ከሱዳን አጥበሀራ በነበርኩ ጊዜ የኢትዮጵያ ታሪክ ከመጽሀፈ ሲራክ እያነበብኩ ስለድንጋይ ጥበብና ስለሌላም ስከታተል እንደቆየሁ ጀቢል ኩራርና ጀቢል ኑባ ወደሚገኘው አገር ሄጄ የጥንት ቤተክርስቲያን ፍርስራሽና የክርስቲያን መቃብር አገኘሁ። ከዚያም ጀበል አባ ለአንድ ሰባት ወር እንደተቀመጥሁ አንድ ሽማግሌ ሰው ‹እንዲህ ካለ ዋሻ ውስጥ የክርስቲያን መጽሀፍት አለ› ብለውኝ አብረን ሄድን። ብዙ በብራና የተጻፉና የተቀዳደዱ መጽሐፎችንም አገኘን።
እንደገና ከሌላ ዋሻ ሄደን፣ ስንቆፍር ብዙ ጽላትና ቁርጥራጭ ካባዎችን፣ ቁመቱ ከ164 ብራና የአክሱማይ ሲራክን መጽሐፍ፣ የሱባን ታሪክ የያዘ መጽሐፈ ሱባኤ፣ እንደዚሁም በጣም የረዳኝ ሁለት መቶ ብራና፣ አራት መቶ ገጽ ያለው የኢትዮጵያ ነገሥታት ታሪክ ዘግዱር ዘእንዳ ቤት በተፈለፈለ የድንጋይ ጉድጓድ ከተልባና ከአመድ ጋር ተቀብሮ ተገኘ።
መጽሀፈ ሱባኤ፣ ከአዳም አስከቀዳማዊ ምኒልክ መጽሀፈ አክሱማይ ሲራክ ከቀዳማዊ ምኒልክ እስከ ዮዲት ፣ መጽሀፈ ታሪከ ነገስት ዘኢትዮጵያ በዘግዱር ዘአንደበት የተጻፈ፤ ከዮዲት እስከ ባካፋ ልጅ ዳግማዊ እያሱ ፣ ከዳግማዊ እያሱ ወዲህ እስከኃይለሥላሴ ፣ ማሕጸመ ነገስት ፣ ከመሪጌታ ጉባኤ ጎጃም ሊበን ውስጥ ከተገኘ መጽሐፍ በብዙ ችግርና ድካም ለማሳተም ወደ ኢትዮጵያ በ1966 ይዤው ገባሁ››
መሪ ራስ አማን በላይ
ነገደ ኢትዮጵያ ከተሰኘው መጽሐፋቸው የፊት ሽፋን ላይ የተቀነጨበ።
መሪ ራስ አማን በላይ ለሀገራቸው በርካታ ታሪካዊ መጽሐፍትን ያበረከቱ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ደራሲ ናቸው። መሪ ራስ አማን በተለይ ‹‹የጥንቷ ኢትዮጵያ ትንሳኤ ታሪክ›› በተሰኘው የብራና መጽሐፋቸው ይታወቃሉ። ከዚህ ባሻገር ከአዳም እስከ ቀዳማዊ ምኒልክ ያለው፣ ከመጽሐፈ ሱባኤ። ከቀዳማዊ ምኒልክ እስከ ዮዲት ፣ ከመጽሐፈ አክሱማዊ ሲራክ ። ከዮዲት እስከ ባካፋ ልጅ ዳግማዊ እያሱ ያለውን ከመጽሐፈ ነገስት። ከዳግማዊ እያሱ ጀምሮ እስከ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ያለውን ደግሞ ከመሪጌታ ጉባኤ ፤ ጎጃም ‹‹ሊበን›› ውስጥ ከተገኘ መጽሐፍ ተርጉመው ስለማቅረባቸው ታሪካቸው ያስረዳናል።
መሪ ራስ አማን የታሪክ ተመራማሪ፣ የነገረ መለኮት አዋቂና የጥንቷ ኢትዮጵያ ትንሳኤ ታሪክን ጨምሮ 24 መጽሐፍትን ለንባብ ያበቁ ታላቅ ደራሲ ናቸው። መሪ ራስ አማን በ1942 ዓ.ም በሰሜን ጎንደር ልዩ ስሙ ‹‹በለሳ›› በሚባል ስፍራ ነው የተወለዱት። የልጅነት ዕድገታቸው በቤተክህነት አካባቢ ነበርና የዘመኑን ዕውቀት ለመቅሰም አልዘገዩም።
እሳቸው እንደሚሉት፤ ‹‹መሪ ራስ›› የሚለው ስያሜ በእነ አጼ ይኩኑአምላክ ዘመን ከነበሩ የማዕረግ ስሞች አንዱን ያስታውሳል። ‹‹መሪ ራስ›› ንጉሱ ዘንድ የሚቀርቡ አቤቱታዎችን በወጉ ተቀብሎ መልዕክቱን በጽሁፍ ለሚያደርስ ባለሟል የሚሰጥ የማዕረግ ስም ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞም አማን ያለፈውን ዘመን እውነታ ከማንነታቸው ግብር ጋር አያይዘውታል። ከስማቸው ፊትም ‹‹መሪ ራስ›› የሚለውን ስያሜ ለራሳቸው ሰጥተው ስሙን ተዋርሰዋል ፤ ያለፈውን ዘመን አስታውሰዋል። ይህ ብቻ አይደለም። እሳቸው በቆሙበት ዘመንም በርካታ ታሪክን ጽፎ ለትውልድ በማሳለፍ ፣ ለአንባብያን በማድረስ ያበረከቱት ሚና በእጅጉ የላቀ ነው። ለዚህም ውለታቸው የጥንቱን ዘመን ማዕረግ ወርሰው የግል መጠሪያቸው አድርገውታል። መሪ ራስ አማን በላይ ። በ1957 ዓ.ም መሪ ራስ አማን ከትውልድ አገራቸው በለሳ ርቀው ሊሄዱ ግድ ሆነ። ምክንያታቸው ደግሞ የቤተክህነት ትምህርት ነበር ። በወቅቱ ለቅኔው መወድስ፣ ለአቋቋም፣ ለድጓና ጾመ ድጓው፣ ለቅዳሴው ፣ ለብሉይ ሀዲስና ዜማው አብዝተው ተጉ። የዕጽዋዕት መድኃኒትን፣ የሀረግ ስዕልን፣ የኢትዮጵያ ታሪክ አቡሻህርን /ባህረሀሳብን/ ለማወቅ ጎጃም፣ ወሎና ሸዋን ዞሩ። በየአድባራቱ፣ በየገዳማቱ ከረሙ። መንዝ ምድር ዘልቀው በትምህርቱ ልቀው እስከሚፈለገው ደረጃ መጠቁ።
ይህ ብቻ አልበቃቸውም። በውስጣቸው የሰረጸውን ዕውቀት ለትውልድ በሚተርፍ ተግባር ዕውን ሊያደርጉት ተዘጋጁ። የአማን ህልም ረዥምና ጥልቅ ነበር። እንዲህ መሆኑ የትውልድ ቀያቸውንና ቤተሰቦቻቸውን አስረሳቸው። ከ30 ዓመታት በላይም ከማንም ሳይገናኙ ድምጻቸው ጠፋ። ይህኔ በህይወት መኖራቸውን ያላመኑ ዘመዶች አልቅሰው፣ ሙሾ አውርደው እርም አወጡ።
የመሪ አማን የመጀመሪያ ትልም የያዙትን ጥልቅ ዕውቀት ወደጥበብ ሥራዎች መተርጎም ላይ አተኮረ ። የዜማ ልክን መሰረት አድርገው የጽሁፍ ሥራቸውን ‹‹አሀዱ›› ብለው ጀመሩ። በወቅቱ መሪ አማን ውስጣቸው ወደብህትናው ዓለም ያደላ ነበር። አጋጣሚ ሆኖ በቅርብ ያገኙዋቸው ሁለት መነኮሳት ወደ አገረ ግብጽ የመሄድ ፍላጎት እንዳላቸው አወቁ ። አማን እነሱን ተከትለው በመተከል ቻግኒ መንገድ አብረዋቸው ሊሄዱ ተሰናዱ። ውሎ አድሮ ጉዞው ተጀመረ።
ሁሉም መንገደኞች ወደዛሬዋ ደቡብ ሱዳን ‹‹አጥበሀራ›› ሲደርሱ ግን ከመሀላቸው አንዷ መነኩሲት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉ። በዚህ መሀል አማን ለሌላ ሰው ተላልፈው ‹‹ጀበል ኑባ›› ወደሚባል ስፍራ እንዲሄዱ ተወሰነ ። ከቀናት በኋላ ጾመ ፍልሰታ ሆነ። ይህን ተከትሎም ለሱባኤ ወደ አንድ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ አመሩ። ቦታው ድንጋያማና ቋጥኝ ነው ። አማን ብቻቸውን አይደሉም ። ከእሳቸው ጋር ሌሎች ሰዎች ነበሩ ።
ለጾም ጸሎት በቆሙበት ስፍራ አማን ዓይንና እጃቸው አላረፈም። ዙሪያ ገባውን በጥልቀት ቃኙ፣ ቦታው ፍጹም አስደነቃቸው። ይህ ብቻ አልበቃቸውም። ቋጥኙን እየዳሰሱ፣ እየነካኩ፣ መቆርቆር፣ መቦርቦርን ያዙ። ግዙፉ ቋጥኝ አልከፋባቸውም ። ቀስ እያለ እጃቸው ላይ መናድ ፣ መፈረካከስ ያዘ። ይህን ያዩ ሌሎች እሳቸውን ሊመስሉ በቋጥኙ ላይ ዘመቱ። ተጋግዘው ፣ ተረባርበው ግዙፉን ግዑዝ ፈረካከሱት።
ከቆይታ በኋላ ከቋጥኙ ሆድ በተቀበረ ሳጥን በርከት ያሉ የቤተክርስቲያን ዕቃዎች፣ መጽሐፍትና ውድ ጌጣጌጦች ተገኙ ። አማን በሚያዩት ጉዳይ ላይ አተኮሩ። የተገኙት መጽሐፍትና ጥቅሎች በሀገራቸው የሌሉ ነገር ግን ስለኢትዮጵያ ታሪክ የሚያውሱ የብራና ላይ ታሪኮችን የሰነቁ ነበሩ። የሰዎቹ ዓይኖች ከሳጥኑ ጌጣጌጦች ላይ አረፈ። ከተገኙት ዕቃዎችም ሁሉም እንደየፍላጎታቸው አነሱ። የአማን ምርጫ ግን የብራና መጽሐፍቱና ጥቅሎቹ ታሪኮች ላይ ብቻ ሆነ። ውሎ አድሮ አማን ቅርሶቹን እንደያዙ ከሀገረ ሱዳን ወጡ። አብሯቸው የነበረው ሰው በእጁ ካሉት ሀብቶች የሚሸጠውን ሸጦ የመንገዳቸው መሪ ሆነ።
በባቡር ተጉዘው በሀያት ገደሀሪፍ፣ ባንቦዲያ፤ በመደኔ ሪሰርስ አቆራርጠው በማንኩሽ ጉባ ቻግኒ ኢትዮጵያ ምድር ደረሱ። አማን ተመልሰው ወደ አገር ቤት ሲገቡ በአገረ- ሱዳን ያገኟቸው ድንቅ መጽሐፍት በእጃቸው ላይ ነበሩ። ጥቂት ቆይቶ ሸዋ ምድር ‹‹ሽንኩርት ሚካኤል›› ከሚባል ስፍራ ተቀመጡ። ይህ ጊዜ በግዕዝ፣ በሱባ ቋንቋና በጥንት አማርኛ የተጻፉትን ግኝት መጽሐፍት በማስተርጎም የተጉበትና በተለይ የሚታወቁበትን ‹‹የጥንቷ ኢትዮጵያ ትንሳኤ ታሪክ››ን የጻፉበት ዘመን ነበር ።
ከ1962 ዓ.ም ጀምሮ መጽሐፉን ለማሳተም ጥረት ሲያደርጉ ቆዩ ። እንዳሰቡት ሆኖ ዕቅዳቸው አልሰመረም። መጽሐፉን የገመገሙና በጥልቀት ያዩ ሁሉ ታሪክን የሚቀይር ነው ሲሉ በስጋት መለሱላቸው። አማን አስተያየቱን ተቀበሉና እሱን ትተው ወደሌሎቹ ጽሁፎች አተኮሩ። ‹‹ዘግድሮ›› የተባለው ጸሀፊ እስከ አጼእያሱ ድረስ ያለውን የኢትዮጵያ ታሪክ በሰፊው አስቀምጦታል። አስቀድሞም በዮዲት ዘመን ወደሱዳን የተሰደደው አክሱማዊት ሲራክ ይህን ታሪክ ጽፎታል። አማን በሱባ ቋንቋ የተፃፈውን በጎ እያስተረጎሙ የመጽሐፍቱን ምስጢራት መረመሩ።
‹‹ያሻር›› የተሰኘው ቃል ‹‹ሰራዊት›› ማለት ነው። ይህ እውነት በኦሪት፣ በመጽሐፈ ዘኁልቁና በመጽሐፈ መሳፍንት ላይ ተጠቅሷል። በዚህ ርዕስ የተጻፈው የእያሱ መጽሐፍ በጥልቀት ስለ ሥነፍጥረት አጀማመርና ሌሎች መሰል ታሪኮች ያወሳል።
‹‹ያሻር›› የሚለው መጽሐፍ ስለሰማያትና በሌላው ዓለም ስላለው ሌላ ህይወት የሚተርክ ነው። ‹‹መጽሐፈ ሰረገላ ታቦር›› የተባለው መጽሐፍም ፍጥረታቱ አንዳቸው በሌላቸው ዓለም ውስጥ ፈጽሞ መገናኘትና መኖር እንደማይችሉ ያስረዳል። ‹‹መጽሀፈ ሱባኤ›› የተባለው ደግሞ ‹‹በመጽሀፈ ኦሪት›› የሚመሰል ነው። በዘመነ ኦሪት በሙሴ እውቅና በኦሪ ልጅ ‹‹ባስልኤ›› አማካኝነት ከያሻር መጽሐፍ ተጣቅሶ የተጻፈ ነው።
በመሪ ራስ መጽሐፈ ሱባኤ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው ‹‹ኢትኤል›› በእግዚአብሔር መንፈስ እየተመራ ከሴም ተነስቶ ግዮን ወደተባለው ‹‹አንኤል›› ወንዝ የሚመጣበትን ተከትሎ ከምንጩ ራስ በአራት መቶ ቀናት ደርሷል። ያም ምድር ‹‹ያስፕድያና ዮጵ›› የሚባለው ቢጫ ወርቅ ይገኝበታል። በያስፕድ ዕንቁና በዮጵ ወርቅ ስለከበረ ‹‹ኢትኤል›› መባሉ ቀርቶ ስሙ ለዘላለም ‹‹ኢትዮጵ›› ተብሎ ተሰይሟል።
ኢትዮጵም ግዮን የሚያስገብራቸው ወንዞች የፈለቁበትንና ግዮን የሚፈስበትን በስሙ ‹‹ኢትዮጵያ›› ተብሎ እንዲጠራ ሰይሞታል። የምድሩም ዳርቻ እስከ ታላቁ ባህር ድረስ። ግዮን ማለት ‹‹ፈሳሽ ፈረሰኛ ውሀ›› ማለት ሲሆን ‹‹አንኤል›› ማለት ደግሞ ‹‹የእግዚአብሔር ወንዝ›› እንደ ማለት ነው።
ዘዳግም የተጻፈው ግን በራሱ በሙሴ እጅ ነበር። መጽሐፈ ሱባኤ በቀዳማዊ ምኒልክ ዘመን ተዘግቶ እንዲቀመጥና የሙሴ ኦሪት ብቻ እንዲነገር በመታወጁ መጽሐፉ በድብቅ እየወጣ እስከ ጎንደር ዘመነ መንግስት ድረስ ለፍልስፍና አገልግሎት ሲውል ቆይቷል።
የኢትዮጵያ ትንሳኤ ታሪክ መጽሐፍ ደራሲ መሪ ራስ አማን ከሱዳን ወደ አሜሪካ ገብተው ኑሮ በጀመሩ ማግስት ዳግም ሊያሳትሙት ሞከሩ ። ጊዜው የደርግ ዘመን ነበርና ‹‹የነገስታት ታሪክ አይታተምም›› በሚል ሰበብ ለንባብ ሳይበቃ ቀረ። ከዓመታት በኋላ ግን መንግስት ተቀየረ። አማንም ብዙ የደከሙበትን መጽሀፍ ለህትመት አበቁት። የዚህን መጽሐፍ ታሪክም በርካቶች አንብበው እጅግ ወደዱት፣ ተመራመሩበትም።
እንደ ግሪኮች አገላለጽ ‹‹ኢትዮጵያ የጥቁር ህዝቦች አገር›› ማለት ናት። ራስ አማንም ይህን አባባል አይቃወሙም። በጽሁፋቸው ላይ እንደሚሉት ደግሞ ‹‹ኢት›› ማለት ‹‹ስጦታ›› ማለት ሲሆን፤ ‹‹ዮጵ›› ሲታከልበት ደግሞ የወርቅ ስጦታ ይሆናል። ግሪኮች ከእኛ በፊት አልነበሩምና ስም ሊያወጡልን አይችሉም የሚሉት አማን ‹‹ጵ›› ይሏት ፊደል በኢትዮጵያ እንጂ በእነሱ የፊደል ዘር ውስጥ እንደሌሎች በማስረጃነት ይገልጻሉ።
መሪ ራስ ካሳተሟቸው 24 መጽሐፍት መካከል ፤- የጥንቷ ኢትዮጵያ ትንሳኤ ታሪክ፤ የሱባ ቋንቋ መዝገበ ቃላት፤ መጽሐፈ ብሩክ /ብሩክ ዣንሸዋ/፤ የልቤ ወዳጅ የሰው ዘር ልጅ፤ ምክር ከእኔ ስማ አንተ ወገኔ ፤ መፅሐፈ ሰረገላ ታቦር፤ መጽሐፈ ፈውስ ፤ ብርሀነ ህይወት ዘበአማን የሚሉትና ሌሎችም ይገኙበታል።
መሪር ራስ አማን በላይ እነዚህን መጽፍት ለንባብ ሲያበቁ በበርካታ ችግርና መከራዎች ተመላልሰው ነው። አማን ስለሀገራቸው ያላቸው ክብርና ፍቅር ከምርምር ይጀምራል። ተደብቆ የቆየውን የኢትዮጵያ ታሪክ ለመላው ዓለም ለማስተዋወቅ ያደረጉት ጥረትም ስለሀገር የከፈሉትን ታላቅ ውለታ የሚመሰክር ነው።
መሪ ራስ አማን ያላቸውን ዕውቀት ከራሳቸው ይዘው ከመኖር ይልቅ ለሌላው ወገን ለማካፈል ሲጥሩ ቆይተዋል። በሀገር ውስጥና በውጭ አገራት በነበራቸው ቆይታ ከጽሁፍ ዓለም ተለይተው አያውቁም። ህይወታቸውን በሙሉ ስለሀገርና ወገናቸው ታሪክ በመጻፍ አሳልፈዋል።
መሪ ራስ አማን መጸሐፍቶቻቸውን ለማሳተም ያሳለፉትን ውጣውረድ በነገደ ኢትዮጵያ መጸሐፋቸው የጀርባ ገጽ ላይ እንዲህ ሲሉ ገልጸውታል ‹‹ በጊዜው የነገሥታትን ታሪክ ማሳተምና ማወደስ አደገኛ ነበር። ሁኔታውም በጣም አሰጋኝ፤ እናም ብዙ ሺ ማይልስ ከኔ ጋር ለብዙ ዓመታት ተንከራተተ። አሁን ጊዜውና አጋጣሚው ፈቅዶ አቋርጦ ከሄደበት ከምድረ አሜሪካ በሀገሩ በኢትዮጵያ በወንድሞቼ ብርታት ለመታተም በቃ። በዚህ አጋጣሚ አፈር የተጫናቸው መጻሕፍትና ንዋየ ቅዱሳት ቀስ በቀስ እየወጡ እውነተኛ ታሪካችን እየታወቀ እንደሚሄድ የዘወትር ጸሎቴ ነው። ››
ታላቁ የጥበብ ሰው ተመራማሪ፣ ደራሲና ፈላስፋ መሪ ራስ አማን በላይ በሚኖሩበት አገረ አሜሪካ ሎስአንጀለስ ባደረባቸው ህመም በህክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ65 ዓመታቸው የካቲት 21 ቀን 2006 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ‹‹ስም ከመቃብር በላይ ይውላል›› እንዲሉ እሳቸው ቢያልፉም ታላቁ ሥራቸው ህያው ምስክር ሆኖ ታሪካቸውን ሲያስጠራ፤ አገር ወገናቸውን ሲያኮራ ይኖራል።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 26 /2015