የአዲስ አበባ ሾላ ገበያ አመት በአል አመት በአል ማለት ጀምሯል፤ ወይዘሮ አረጋሽ አሽኔም በዚህ ገበያ ለሸመታ ተገኝተዋል። ወይዘሮ አረጋሽ ገበያውን ዞር ዞር ብለው ማየታቸውን ይገልጻሉ፤ ከኑሮ ውድነት ጋር ተደማምሮ የበዓል ገበያው ዋጋ ውድ መሆኑን ይናገራሉ። እሳቸው አንዳሉት፤ ለበዓል አስፈላጊ የሆኑት ምርቶች ዋጋ በቅርቡ ከነበረው ዋጋ ሲተያይ ጭማሪ አሳይቷል። ባለፈው ሳምንት 15 ብር የነበረው የአንድ ኩሎ ቀይ ሽንኩርት ዋጋ አሁን 28 ብር ገብቷል ሲሉ ገልጸው፣ ከዚህ መረዳት የሚቻለው ዋጋው እጥፍ በሚባል ሁኔታ መጨመሩን ነው ይላሉ።
ሌሎች ለበዓል በሚያስፈልጉ ምርቶች ላይም ጭማሪ መታየቱን የተናገሩት ወይዘሮ አረጋሽ፣ ቅቤ በ800 ብር፤ የአበሻ ዶሮ በ850 ብር ገዝተዋል። በዓል ሲደርስ በምርቶች ዋጋ ላይ ጭማሪ ማድረግ ወይም የአቅርቦት መቀነስ እየተለመደ መምጣቱንም ነው ወይዘሮ አረጋሽ የጠቆሙት። በዓሉ ሳምንት ያህል ጊዜ እየቀረው የዋጋ ንረቱ እንዲህ ከሆነ በዓሉ ሲቃረብ ይበልጥ ሊጨምር እንደሚችል ወይዘሮ አረጋሽ ስጋት አድሮባቸዋል። በዚህ ጊዜ በዓልን ምክንያት አድርገው የሚደረጉ ጭማሪዎች አግባብነት የላቸውም ባይም ናቸው።
‹‹ገበያውን ተዘዋወሬ እንዳየሁት ለበዓል አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች በሙሉ በገበያ ውስጥ አሉ›› ያሉት ወይዘሮ አረጋሽ፣ በዓልን በዓል በአል የሚያሰኘው እንደ ባህላችን ለበዓል የተለመዱት ዶሮው በጉና የመሳሰሉት በየቤቱ ማግኘት ሲቻል ነው ይላሉ። ወይዘሮ አረጋሽ በአሁኑ የገበያ ሁኔታ ግን እነዚህን ለማሟላት እንደሚቸግር ይጠቁማሉ። ገበያው የደሃውን ህብረተሰብ አቅም የሚፈትን መሆኑን አመላክተዋል። ዋጋቸው ተመጣጠኝና አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል ያማከለ ቢሆን ሁሉም በአቅሙ የሚችለውን በማድረግ በዓሉን ተደስቶ ማሳለፍ እንደሚችል ያብራራሉ።
የበዓል ገበያው ከኑሮ ውድነት ጋር ተደማምሮ ሸማቹን ህብረተሰብ ከባድ ጫና ውስጥ መክተቱን ይናገራሉ። አውደዓመት በዓመት አንድ ጊዜ እንደሚመጣ ጠቅሰው፣ ገበያውም ሁሉም እንደየአቅሙ በዓሉን ለማክበር የሚያስችለውን ሸመታ የሚፈጸመበት መሆኑን ነው ያመላከቱት።
በየጊዜው እየጨመረ ያለው ማቆሚያ የለሹ የዋጋ ንረት ሸማቹን ተገቢ ላልሆነ ወጪ እየዳረገው ነው፤ በተለይ የሀገር ውስጥ ምርቶች ዋጋ ጭምሬ እንጂ ቅናሽ አለው ተብሎ አይታሰብም የሚሉት ወይዘሮ አረጋሽ፤ መንግሥት እንዳለፉት የበአል ወቅቶች ሁሉ አሁንም የዋጋ ንረቱን የማረጋገት ሥራዎቹን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
ወይዘሮ አረጋሽ በልጆቻቸው እንደሚደገፉ ይናገራሉ። አቅማቸው በፈቀደው መጠን ለበዓል የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ለመሸመት ጥረት አድርገዋል፤ ይህንን ማድረግ የማይችሉ ብዙዎች ሰዎች በአካበቢያቸው እንዳሉ አመላክተው፣ ጊዜው ቢከፋብንም እኛ በቻልነው አቅም መረዳዳት አለብን ሲሉም ያስገነዝባሉ፤ ‹‹ከልተረዳዳን አይሆንምና የተገኘውን ተካፈለን እንበላለን›› ይላሉ።
ሌላኛዋ የበዓል ገበያ ሸማች ወይዘሮ መቅደስ አበበ በበኩላቸው የገና በዓል ገበያ ድምቀት ከሌሎች በዓላት ገበያ እንደሚለይ ነው የሚናገሩት። ልዩ የሚያደርጉትን ለበዓሉ ድምቀት የሚያስፈልጉ የስጦታ እቃዎች እና ጌጣጌጦች ጭምር የሚገዙበት፣ይህን ሁሉ ተከትሎም ግርግርና ትርምስ የሚበዛበት መሆኑን ያብራራሉ።
ይሁንና የዘንድሮው በዓል እንደሌላ ጊዜ የገና በዓል ግርግርና ትርምስ ያልበዛበትና ቀዝቀዝ ያለ መሆኑን መታዘባቸውን ጠቅሰው፣ ለገበያው መቀዛቀዝ ምክንያቱ የኑሮ ውድነት መሆኑን ነው የተናገሩት። የኑሮ ውድነቱ የሰውን የመግዛት አቅም መፈተኑን ለእዚህ በማሳያነት ይጠቅሳሉ።
ወይዘሮ መቅደስም እንደ ወይዘሮ እንደ ወይዘሮ አረጋሽ ገበያውን ተዘዋውረው ተመልክተዋል። በዚህም የሽንኩርት፣የቅቤ እና የዶሮ ምርቶች በገበያው እንደልብ መኖራቸውን አረጋግጠዋል፤ የምርቶቹ ዋጋ እንደ በዓል ሰሞን ገበያ የተጋነነ እንዳልሆነም ጠቅሰው፤ ሰሞኑን ከነበረው ዋጋ ጋር ሲነጻጸር ግን ጭማሪ ማሳየቱን ነው የጠቆሙት።
ለበዓል አስፈላጊ የሆኑ ምርቶች ገበያው ላይ መገኘታቸው ብቻውን በቂ እንዳልሆነም ነው ወይዘሮ መቅደስ የሚናገሩት፤ የዋጋ ጭማሪው ከኑሮ ውድነቱ ጋር ተዳምሮ የሸማቹን ኪስ እንደሚያራቁትና ለተጨማሪ ወጪ እንደሚዳርግ ይገልጻሉ።
‹‹እኔ መግዛት የፈለግኩትና የገዛሁት አይመጣጠንም፤ ከቤት ሲወጣ ይህንን ያህል ብር ሊፈጅብኝ ይችላል ብዬ የመደብኩት ብር የምፈልገውን ሳልገዛበት ነው የጨረስኩት››ያሉት ወይዘሮ መቅደስ፤ የኑሮ ውድነት በየጊዜው እየጨመረ የብር መግዛት አቅም እየቀነሰ መምጣት በዓልን እንደሌላው ጊዜ ሁሉንም አሟልቶ ማክበር እንዳይቻል እያረገው መሆኑን አመላክተዋል። የኑሮ ውድነትና በዓል ሲገጣጠሙ ኑሮን የበለጠ ከባድ እንደሚያደርጉት ነው የገለጹት።
እሳቸው አንደሚሉት፤ የአንድ ዶሮ ዋጋ ከ550 ብር እስከ 805 ብር ድረስ ይጠራል። ዶሮ ለመስራት የሚያስፈልጉት የሽንኩርት፣ የቅመማቅመም ፣ቅቤ እና የእንቁላል ዋጋ በዚህ ላይ ሲደማመር ወጪው ምን ያህል ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም።
የኑሮ ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለ ለበዓል የሚያስፈልጉ ግብዓቶች መሸመት ይቅርና ለመኖርም አዳጋች ሁኔታ ይገጥመናል ሲሉም ስጋታቸውን ይጠቁማሉ። ኑሮ እንዲዚህ እሳት እየሆነ በሄደ ቁጥር የሚጎዳው ህብረተሰቡ መሆኑንም አመልክተው፣ መንግሥት እና የሚመለከታቸው አካላት በእዚህ ላይ ይበልጥ ሊያስቡበት እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት።
ሌላዋ አስተያየት የሰጡን ወይዘሮ አምሳለ ተሾመ፤ ለበዓሉ የሚያስፈልጋቸውን ሽንኩርት፣ እንቁላልእና ዶሮ ከገበያ በተሻለ ዋጋ መሸመታቸውን ይናገራሉ፤ የሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት ምርቶችን የሚያቀርቡት ዋጋ ከገበያው የተሻለ መሆኑንም ይጠቁማሉ።
እሳቸው አንዳሉት፤ ገበያ ላይ ሽንኩርት 28 ብር ሲሸጥ፣ የሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት ዘንድ ግን 20 ብር ነው እየተሸጠ ያለው፤ የስምንት ብር ልዩነት አለው። የእንቁላል ዋጋ ገበያ ላይ አሥር ብር ሲሆን፣ ሸማቶች ዘንድ ግን ስምንት ብር ከሃምሳ ሳንቲም ነው። ዶሮ ገበያ ላይ እስከ 850 ይጠራል፤ እሳቸው ግን ዶሮ በ350 ብር ገዝተዋል።
ወይዘሮ አምሳለ በሌሎች የበዓል ገበያ ምርቶች ላይ ግን የዋጋ ጭማሪ አጋጥሟቸዋል። እሳቸው አንደሚሉት፤ ለበዓሉ ይቅርና በሌላው ጊዜም የገበያው ሁኔታ በየጊዜው ጭማሪ እንጂ ቅናሽ አሳይቶ አያውቅም። አንድ እቃ ዛሬ በሚጠራው ዋጋ ነገ አይገኝም ፤ ይጨምራል። በየዕለቱ አዳዲስ ዋጋ መስማት ተለምዷል። ለአብነት ባለፈው ሳምንት እሳቸው በሚያዘወትሩት ገበያ የሽንኩርት ዋጋ 15 ብር ነበር፤ አሁን ደግሞ 20 ብር ሆኗል። በሳምንት ጊዜ የአምስት ብር ልዩነት ታይቷል። እንደዚህ አይነት ጭማሪዎች በበዓል ሊጋነኑ ይችላሉ እንጂ በሌላውም ጊዜ ምክንያታቸው ሳይታወቅ በየቀኑ የሚጨምሩበት ሁኔታ ተለምዷል።
ሰው እንደ ቤቱ እንጂ እንደ ጎረቤቱ አይኖርም ሲሉ ወይዘሮ አምሳል ገልጸው፣ እሳቸው አቅማቸው በፈቀደው መጠን ለበዓሉ የሚፈልጉትን ሸማምተዋል፤ በዓሉን እንደሌላው ጊዜ አርገው ማሳለፍ ባይችሉም፣ የሸማመቷቸውን አብቃቅተው ለመዋል አቅደዋል። ህብረተሰቡስ ከየት ያመጣዋል፤ ነጋዴውም ሸማቹን ሊያስበው ሊራራለት አንደሚገባም ያስገነዘቡት።
የኑሮ ውድነቱና የገበያው መዋዝቅ፣ የገቢና የወጪ አለመመጣጠን ኑሮውን እጅግ ፈታኝና ከባድ ማድረጋቸውን ወይዘሮ አምሳል አስታውቀው፣ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ለበዓል የሚያስፈልገውን ተጨማሪ ወጪ ይቅርና የዕለት ጉርሱን ለማግኘት እየተቸገረ መሆኑን ጠቁመዋል።
ገበያ ላይ የሚታየውን ችግር ለመፍታት የሸማች ህብረት ስራ ማህበራት በየቦታው እንዲስፋፉ ማድረግ እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት፤ ማህበራቱ የሚያቀርቧቸው ምርቶች ዋጋ የህብረተሰቡን የመግዛት አቅም ያገናዘቡ መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል። ማህበራቱ ምርቶችን ይበልጥ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያቀርቡበት ሁኔታ መመቻቸት እንዳለበትም ይገልጻሉ።
የቅቤ ነጋዴዋ ወይዘሮ መሠረት ንጉሴ ግን የቅቤ ዋጋ ብዙም እንዳልጨመረ ነው የሚናገሩት። እሳቸው እንደሚሉት፤ ለጋ ቅቤ 800 ፤ መካከለኛ 700 ብር እየተሸጠ ነው፤ አሁን ካለው የዋጋ ንረት አንጻር የቅቤ ዋጋ ጭማሪ ብዙም የተጋነነ እንዳልሆነ የሚናገሩት ወይዘሮ መሠረት ፤ የዘይት ዋጋ ከቅቤ ዋጋ በልጦ ባለበት በዚህ ጊዜ የቅቤ ዋጋ ብዙም ጭማሪ አላሳየም ባይ ናቸው።
‹‹ቅቤ የምናመጣው ከአርሶ አደሮች ነው፤ አርሶ አደሮች የቅቤ ዋጋ አሁን ስለደረሰበት ዋጋ ብዙ ምክንያቶችን ይጠቅሳሉ›› የሚሉት ወይዘሮ መሠረት፣ የኑሮ ውድነቱ የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በር ማንኳኳቱን ይናገራሉ። አርሶ አደሮች ለመሸጥና ለመግዛት የሚያወጡት ዋጋ እኩል እንዳልሆነና ከገቢው ወጪው እየበለጠባቸው ስለመምጣቱ እየተናገሩ ስለመሆናቸው አርሶ አደሮችን ጠቅሰው ያብራራሉ። ‹‹እኛም እንደ ነጋዴ በዋጋ ላይ የምንጨምረው ህብረተሰቡን በሚጎዳ መልኩ አይደለም›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ‹‹የተጋነነ ዋጋ ብንጠራ ማን ይገዛናል›› ይላሉ። በመተሳሰብ መስራት ጥሩ መሆኑንም ይገልጻሉ።
የዶሮ ነጋዴው አቶ አለሙ ፈይሳ፤ ዶሮ በአማካይ በ450 እና 850 መካከል እየተሸጠ መሆኑን ይገልጻሉ። ዶሮ በብዛት ወደ ገበያ መግባቱን ጠቅሰው፣ ዋጋቸውም ቢሆን ተመጣጣኝ መሆኑን ነው የተናገሩት። ለዶሮ መኖ የሚወጣው ወጪ ውድ እየሆነ ከመምጣቱ ጋር በተያያዘ የዶሮ ዋጋ ጭማሪ እያሳየ ነው ይላሉ።
በገበያው ላይ የሚታየው ዋጋ የኑሮ ውድነቱ ያስከተለው እንጂ ለበዓሉ ተብሎ በተደረገ የተለየ ጭማሪ ምክንያት የተከሰተ አይደለም ሲሉም ያብራራሉ። እስካሁን ባለው ሁኔታ ገበያው ከሌላው ጊዜ ትንሽ መቀዛቀዝ እንደሚታይበት አቶ አለሙም አረጋግጠዋል።
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ ለገና እና ጥምቀት በዓላት ገበያ አቅርቦት በቂ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል። ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ምርቶች በበቂ ሁኔታ ከክልሎች እንዲገቡ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉም አመላክተዋል።
የቢሮ ሃላፊው አንዳሉት፤ ቢሮው ለገናና ጥምቀት በዓላት 60 ሺ ዶሮዎች ፣ 90 ሺህ ኩንታል ጤፍ እና ከ15 ሺህ በላይ የእርድ እንስሳት ወደ ገበያ ይቀርባሉ። ከዚህ በተጨማሪም በሸማቾች በኩል 5 ነጥብ 4 ሚሊየን ሊትር ዘይትና 30 ሺህ ኩንታል ስኳር ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ይደረጋል።
የዋጋ ጭማሪና የምርት መደበቅን ለመከታተልም ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደሥራ መግባቱን ነው ኃላፊው የተናገሩት፤ ይህንን ለመከታተልና ግልፅ ለማድረግም በመረጃ ተደራሽነት ላይ እንዲሰራ ቁጥጥሩን ለማጠናከር በምክትል ከንቲባው የሚመራ የአቅርቦት ንዑስ ኮሚቴ መቋቋሙንም አመላክተዋል።
ምርት ከክልሎች ወደ ገበያ ማዕከላት በሙሉ አቅም እንዲገባ ዝግጅት መደረጉም ያመላከቱት ኃላፊው፤ በገበያ ላይ ጫና እንዳይፈጠር ጊዜያዊ የገበያ ማዕከላት መቋቋማቸውም ነው የገለጹት።
ይህ በእንዲህ እንዳለ መጪውን የገና በዓል ምክንያት በማድረግ የምርት አቅርቦት እጥረት እንደማያጋጥም የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ማስታወቁን መረጃዎች አመልክተዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የገና በዓልን የምርት አቅርቦት በማስመልክት ከፌደራል ህብረት ስራ ኮሚሽን ፣ከስኳር ኮርፖሬሽን እና ከንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ጋር በመሆን ሰሞኑን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
በዓሉን ምክንያት በማድረግ ለፍጆታ የሚውሉ ምርቶች ፍላጎት ስለሚጨምር የአቅርቦት ክፍተት እንዳይፈጠርና ህብረተሰቡ ላልተገባ ዋጋ እንዳይጋለጥ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ሲሰራ መቆየቱን በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚነሲቴር የሀገር ውስጥ ንግድና ሸማቾች ጥበቃ መሪ ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ መስከረም ባህሩ ተናግረዋል።
በዓሉን ምክንያት በማድረግ የግብርና ምርቶች፣ የእንስሳት ውጤቶች እና የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች እቅርቦት እጥረት እንዳይኖርና ማህበረሰቡ ላልተገባ ዋጋ ጭማሪ እንዳይጋለጥ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተጠቁሟል።
የፌዴራል ህብረት ስራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አብዲ ሙመድ እንደገለፁት፤ በአዲስ አበባ 137 ሸማች ማህበራት በዓሉን ምክንያት በማድረግ የተለያዩ ምርቶችን በማቅረብ ኤግዚቢሽንና ባዛር ተዘጋጅተዋል።
በአሁኑ ወቅት ምንም አይነት የምርት እጥረት እንደሌለ የገለፁት ምክትል ኮሚሽነሩ ፣በቅዳሜና እሁድ ገበያ ማዕከላት ምርቶች እየቀረቡ በመሆኑ ህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚፈልገውን ምርት እንዲሸምት ምክትል ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል።
እሳቸው አንዳሉት፤ ሽንኩርት ከ15 እስከ 22 ብር፣ ቲማቲም ከ15 እስከ 23፣ ጤፍ 44 እስከ 49፣ ስንዴ ዱቄት በኪሎ 55 ብር፣ በቆሎ ዱቄት 33፣ ዶሮ ከ350 እስከ 500 ብር በህብረት ስራ ኮሚሽን በኩል እየቀረቡ ናቸው። ህብረተሰቡ ተረጋግቶ እንዲሸምት ጥሪ አቅርበዋል።
161 ሺህ 200 ኩንታል በላይ የግብርና ምርቶች ወደ ገበያ መቅረባቸውን የገለፁት አቶ አብዲ ከ225 በላይ የህብረት ስራ ማህበራት ልኳንዳ ቤቶች በዓሉን በማስመልከት በተመጣጣኝ ዋጋ ስጋ እንደሚያቀርቡ ገልፀዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 26 /2015