40ኛው የጃንሜዳ ኢንተናሽናል ሃገር አቋራጭ ቻምፒዮና በሱሉለታ ከተማ ተካሂዶ በደማቅ ሁኔታ ተጠናቋል። ውድድሩ ከትናንት በስቲያ ሲካሄድ በቡድን አማራ ክልልንና ኢትዮ ኤሌትሪክ ባለድል ሆነው የዋንጫ ተሸላሚ ሆነዋል።
ውድድሩ በ5 የተለያዩ ካታጎሪዎች ተከፍሎ በርካታ አትሌቶችን ያሳተፈ ሲሆን በድብልቅ ሪሌይ፣ በ6 ኪሎ ሜትር ወጣት ሴቶች፣ በ8 ኪሎ ሜትር ወጣት ወንዶች፣ በ10 ኪሎ ሜትር አዋቂ ወንዶችና ሴቶች ከ50 ዓመት በላይና በታች ባሉ ምድቦች ፉክክሮች ተከናውነዋል።
በ8 ኪሎ ሜትር የወጣት ወንዶችና በ6ኪሎ ሜትር የወጣት ሴቶች ውድድር በተከታታይ 14እና 35 ነጥቦችን በመሰብሰብ አማራ ክልል የዋንጫ ተሸላሚ ሲሆን፣ በአዋቂ ወንዶችና ሴቶች የ10 ኪሎ ሜትር ደግሞ ኢትዮ ኤሌትሪክ የዋንጫ ተሸላሚ መሆን ችሏል። በድብልቅ ሪሌይ ኦሮሚያ ክልል የወርቅ ሜዳልያ፣ ሱሉልታ የብርና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የነሐስ ሜዳለያ በማግኘት ከ1ኛ-3ኛ ያለውን ደረጃ ሲይዙ ኦሮሚያ ደንና ዱር፣ ኢትዮ ኤሌትሪክና ሲዳማ ቡና ቀሪዎቹን ደረጃ ይዘ ውድድሩን ማጠናቀቅ ችለዋል።
የዘንድሮ የአገር ኣቋራጭ ቻምፒዮና ለ40ኛ ጊዜ የተደረገና በተለያዩ ርቀቶች ጠንከር ያለ ፉክክሮችን ያስተናገደ ሲሆን፤ ከነዚህም መካከል በተጠባቂው የሴቶች 10ኪሎ ሜትር ውድድር የዓለም የ10ሺ ሜትር አሸናፊዋ ለተሰንበት ግደይ ውድድሩን በማፍጠን ተፎካካሪዎቿን በሰፊ ርቀት በመቅደም ባለድል መሆን ችላለች። ለተሰንበት ግደይ 35፡21.55 በሆነ ሰዓት አንደኛ ሆና ስታጠናቅቅ፣ ጌጤ አለማየሁ 35፡40፡ 87 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ፣ መቅደስ አበበ 35፡46.06 በሆነ ሰዓት የሶስተኝነቱን ደረጃ በመያዝ ማጠናቀቅ ችለዋል።
በወጣት ሴቶች የ6ኪሎ ሜትር ውድድር ለምለም ንብረት ከአማራ ክልል 20፡33.40 በሆነ ሰዓት 1ኛ፣ መልክናት ውዱ ከኢትየጵያ ንግድ ባንክ 20፡35.15 በሆነ ሰዓት 2ኛና ሰናይት ጌታቸው ከአማራ ክልል 20፡ 35.50 በሆነ ሰዓት ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቅ ችለዋል።በወጣት ወንዶች የ8ኬሎ ሜትር ውድድር በረከት ዘለቀ ከአማራ ክልል 24፡48.81 በሆነ ሰዓት 1ኛ፣ ቦኪ ዲሪባ ከኦሮሚያ ክልል 24፡49.13 በሆነ ሰዓት 2ኛና አቤል በቀለ ከአማራ ክልል 24፡51.43 በሆነ ሰዓት 3ኛ ደረጃን በመያዝ ውድድራቸውን ፈፅመዋል።
በ10ኪሎ ሜትር የአዋቂ ወንዶች ጠንካራ ፍክክር የተስተናገደ ሲሆን ያለፈው ውድድር አሸናፊ አትሌት በሪሁ አረጋዊ ከኢትዮ ኤሌትሪክ በ30፡44.20 በሆነ ሰዓት አሸናፊ መሆን ችሏል። ከተመሳሳይ ክለብ ታደሰ ወርቁ በ30፡5309 ሁለተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ጌታነህ ሞላ ከመቻል 30፡54.43 በሆነ ሰዓት በማጠናቀቅ ሶስተኛ ሆኗል።
ባለድሉ አትሌት በሪሁ አረጋዊ ለውድድሩ በደንብ ዝግጅት ማድረጉን ተናግሮ፣ ውድድሩ በጣም ፍክክር የነበረበትና አየሩም ትንሽ እንደከበደው ገልፃል። በሪሁ በማሸነፉ ደስተኛ እንደሆነና ለቀጣይ የአውስትራልያው የዓለም አገር አቀራጭ ቻምፒዮናም ጠንካራ ዝግጅት ለማድረግ ልምዱን ተጠቅሞ የወርቅ ሜዳለያ እንደሚያስመዘግብ በልበሙሉነት ተናግሯል። ‹‹ሀገርን መወከል ስሜቱ ከፍታ ነው፤ለሀገር ትልቅ ኃለፊነት ነው ይዘክ የምትሄዳው፣ ምክንያቱም ለሃገርና ለራስ ብለህ የምትሰራው ይለያያል›› ሲልም አስተያየቱን ሰጥተል። በዚሁ ምድብ ከተመሳሳይ ክለብ ውድድሩን በሁለተኝነት የጨረሰው ታደሰ ወርቁ በበኩሉ፣ የውድድሩ ስፍራ ጥሩ እንደነበረና መጨረሻ ላይ ንፋስ እንዳስቸገረው ገልፆ በቡድን ለማሸነፋቸው ምክንያት ጠንካራ ዝግጅት ማድረጋቸው ምክንያት እንደሆነ ተናግሯል። ‹‹ለዓለም አገር አቀራጭ ቻምፒዮናው የበለጠ ጠንከር ያለ ዝግጅት ማድረግ አለብን፣ ምክንያቱም እዛ የምንፎካከራቸው ኬንያዊያንና ዩጋንዳዊያንን ነው›› ሲልም ታደሰ አስተያየቱን ሰንዝራል።
ከ50 ዓመት በላይ የአንጋፋ አትሌቶች ውድድር አብደላ ሱሌማን በአንደኝነት ሲያጠናቅቅ፤ አያሌው እንዳለና ገፊ አባይ ሁለተኛና ሶስተኛ በመሆን ማጠናቀቅ ችለዋል። ከ50 ዓመት በታች የአንጋፋ አትሌቶች ውድድር ዳግሞ አስፋ ጥለሁን አንደኛ፣ ተስፋዬ ያያ ሁለተኛና እሱባለው አስናቀ ሶስተኛ በመሆን ጨርሰዋል።
በውድድሩ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት ረዳት ኮሚሽነር ጄነራል ደራርቱ ቱሉን ጨምሮ፣የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በባህልና ስፖርት ሚኒስትር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ድዔታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የኬንያና የምስራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ሪጅን ፕሬዘዳንት ጀነራል ጃክሰን ትዊና የአትሌቲክስ ሪጅኑ ዋና ፀሀፊ ዶክተር ኢንጂነር ሲዲቅ ኢብራሂም መታደም ችለዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀደሚ ፕሬዘዳንት አትሌት ገዛኸኝ አበራ የውድድሩን መጠናቀቅ አስመልክቶ፣ ውድድሩ በጣም ጥሩ እንደነበረና አመርቂ የሚባል ውጤትም እንደተገኘበት ገልፃል። ገዛኸኝ አያይዞም በውድድሩ ለዓለም ቻምፒዮና ጥሩ የሆኑ ተወዳዳሪዎችንም ለመምረጥም እንዳስቻላቸው ተናግሯል።
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 25 /2015