ትምህርት በአንድ አገር የሚፈለገውን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማስመዝገብ ወሳኝ ምዕራፍና መሠረት የሚጣልበት ዘርፍ ነው። በዚህም በዘርፉ የሚታዩ መልካም ስኬቶችም ሆኑ እንቅፋቶች በሌሎች ሰብአዊም ሆነ አገራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደራቸው አይቀሬ ይሆናል። በመሆኑም የመማር ማስተማር ሂደቱ ሠላማዊ እንዲሆን ማረጋገጥ የግድ ይሆናል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሠላምና ደህንነት ትምህርት ክፍል በማህበራዊ ሳይኮሎጂ ተመራማሪ እንዲሁም መምህር ፕሮፌሰር ሀብታሙ ወንድሙ እና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ታቦር ገብረ መድህን ጋር የነበረንን ቆይታ እንዲህ ይዘንላችሁ ቀርበናል።
ያለበት ሁኔታ
በአገሪቱ የብሔር ብሔረሰቦች፣ የኃይማኖት . . . ብቻ ሳይሆን ሌሎች በርካታ ልዩነቶችን የሚያሳዩ ነገሮች አሉ። ሆኖም ልዩነቶቹ ብቻቸውን ወደ ግጭት ባያመሩም ለግጭትና አለመረጋጋት ግን ቆስቋሽ ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉ አያጠራጥርም ሲሉ የሚናገሩት ፕሮፌሰር ሀብታሙ፤ ሌሎች ጥቅም ፈላጊ ኃይሎችም ይህን ተጠቅመው ያልተገቡ ድርጊቶችን ሊፈፅሙ ስለሚችሉ በዚያ ረገድ ጥንቃቄ ያሻዋል ይላሉ። አንድ ኃይማኖት ወይንም ብሔረሰብ ብቻ ካለባቸው አገራት ወይንም በአገሪቱ ከሚገኙ ክልሎች ውስጥ ካሉ ትምህርት ተቋማት ጋር ሲነፃፀር በአዲስ አበባ ያለው ሁኔታ ይለያል።
እስካሁን ባለው ሁኔታ በአዲስ አበባ የመማር ማስተማሩ ሂደት ሠላማዊ ነው የሚሉት ደግሞ ዶክተር ታቦር ናቸው። ይህን ይበሉ እንጂ የመማር ማስተማሩን ሠላማዊነት ሊያውኩ የሚችሉ፣ ገፊ ውጫዊ ምክንያቶች መኖራቸውንና ከሌላውም ጎልተው መታየታቸውን ሳያነሱ አላለፉም። ዶክተር ታቦር እንዳብራሩልን አንደኛው ምክንያት ትምህርት ቤቶችን የፖለቲካ እንቅስቃሴና አስተሳሰብ ማራመጃ መድረክ ለማድረግ ያለ ፍላጎት መሆኑን በማንሳት፤ ይህን በሚመለከት የዘንድሮ ዓመት የትምህርት ዘመን የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት ትምህርት ‹‹ሀ›› ተብሎ ሊጀመር ዝግጅት ሲደረግ ከመነሻው የተከናወኑ ተግባራት እንዳሉ ይጠቁማሉ። በዚህም እስከ ታች ላለው መንግሥታዊ መዋቅር፣ ለገዢው ፓርቲ የድርጅት መዋቅር፣ ለትምህርት ቤቱ ማህበረሰብና ለርዕሰ መምህራን ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ሲሠራም ቆይቷል።
በዚህ መሠረት የትኛውም ፓርቲ ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ በትምህርት ቤት ውስጥ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሌለበት በተደረገው ውይይት ከስምምነት በመድረስ ማስቆም እንደተቻለ ዶክተር ታቦር ይናገራሉ። በዚህም የትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ፤ ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ በትምህርት ቤት ውስጥ ማንኛውንም ዓይነት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ማድረግ አይችልም። ይህም ሲባል አባል አይመለምልም፣ አይሰበስብም እንዲሁም ማስታወቂያ አይለጥፍም ማለት ነው።
ከዚህ ቀደም የህዋስ ውይይት፣ የድርጅት ልሣን ማሰራጨትና መሠል ተግባራት ይካሄዱ እንደነበርም ዶክተሩ አስታውሰዋል። ይህም ትምህርት ቤቶች ከፖለቲካ ነፃ ከመሆናቸው አኳያ ሲከናወን የነበረው ተግባር ትክክል እንዳልነበር ገዢው ፓርቲም ለይቶ ገምግሞታል። በመሆኑም ችግር ለመፍታት በወሰደው ቁርጠኛ እርምጃ ምንም ዓይነት ስብሰባ በአዳራሽም ሆነ በመማሪያ ክፍል ውስጥ እንዳይደረግ ተከልክሏል። ይህን የማያደርግ አካል ካለም ትምህርት ቤቱ ኃላፊነት የሚወስድ ሲሆን፤ የትምህርት ቤቱን አመራርም ተጠያቂ ይደረጋል።
የትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማር ሥራቸው ሠላማዊ እንዲሆን የሚያግዝ የሠላም ኮንፍረንስ እየተዘጋጀ መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር ታቦር፤ በመድረኮቹ ላይ መምህራን፣ ወላጆች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ ምሁራን፣ የምክር ቤት አባላትና ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ አካላት በተገኙበት ተከታታይ መድረኮች እየተዘጋጁ ውይይት በመደረግ ላይ መሆኑን፤ ወደፊትም የሚፈጠሩ መድረኮች የሚኖሩ ሲሆን፤ በትምህርት ቤቶች አካባቢ ያሉ አዋኪ ጉዳዮች ምንድን ናቸው? በሚል በሚገባ ተጠንተው መለየታቸውንም አስረድተዋል።
የችግሮቹ ምንጭ
ተቋማቱ ከመላ አገሪቱ በተውጣጡ ብሔርና ኃይማኖት፤ እንዲሁም በእነዚህ ላይ መሠረት ባደረጉ አስተሳሰቦች የተቀረፀ ማንነት ያላቸው የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መገኛ ስፍራ በመሆናቸው በቀላሉ ለግጭትና ለሠላም ማጣት መነሻ ሊሆኑ ይችላሉ። ሠላም ከግል ስሜት ጀምሮ በሚከሰቱ አለመግባባቶች ሊደፈርስም ይችላል። በትምህርት ተቋማት ደግሞ እነዚህ የተለያየ አመለካከት ያላቸው ተማሪዎችና መምህራን በመኖራቸው ሠላማዊውን የመማር ማስተማር ተግባር በማይረባ ምክንያት በቀላሉ ሊያደፈርሱት ይችላሉ። በዚህም ከግል እስከ ትልቅ ግጭት የሚደርሱ ከሥነምግባር ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ፣ ከሥራና ካለመግባባት ጋር የሚመጡ፣ አንዳንዴም ካለመደማመጥ እንዲሁም የሌሎች መሣሪያ በመሆን የሚከሰቱ ግጭቶችና የሠላም መደፍረሶች እንደሚከሰቱ ፕሮፌሰር ሀብታሙ ያስረዳሉ።
በትምህርት ቤቶች ውስጥ ፖለቲካዊ እንቅስ ቃሴ ማድረግ ለሠላም መደፍረስ እንደ አንድ መንስኤ ስለሚሆን የማስቆም ሥራ መሠራቱን የሚጠቁሙት ዶክተር ታቦር፤ ሠላማዊውን የመማር ማስተማር ሥራ የሚያውኩ ውጫዊ ምክንያቶች እንዳሉም ይገልፃሉ። በአጠቃላይ በአገሪቱ ያለው ነባራዊ ሁኔታ፣ በብሔር በጎሳ ላይ ያተኮረና በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ችግሮች፣ የፖለቲካ አቀንቃኞች መብዛት፣ በድረገፆችና በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚተላለፉ መልዕክቶችና ትንኮሳዎች ሁሉ ገፊ ምክንያቶች ሆነው ይታያሉ። በተጨማሪም ትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚደረጉ የተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎችን እንደ አንድ የችግር ምንጭ ተጠቃሽ ያደርጋሉ። በእነዚህ ተማሪዎችን ገበያ አድርገው ተከትለው የሚሄዱ በርካታ እንቅስቃሴዎች ዙሪያም ፆታን መሠረት ያደረጉ ትንኮሳዎች ይከሰታሉ።
ሴት ተማሪዎች ሲወጡ ሲገቡ በመተንኮስ የሚጀመሩት እኩይ ድርጊቶች በግለሰብ ደረጃ የሚያስነሱት ግጭት መልካቸውን ቀይረው ወደ ቡድን ፀብነት ይለወጣሉ። ይህም አደጎ ብሔርን መሠረት ያደረገ ፀብነት ያመራል። ሁለት ተማሪዎች ወይ ደግሞ አንድ ከሌላ ትምህርት ቤት ከመጣ ተማሪ ጋር ይጋጫል። ከዚያ ወደ ቡድን ከፍ ብሎ ቀጥሎ ብሔርን መሠረት ያደረገ ግጭት ይሄዳል። ይህንንም በቅርብ በመከታተል ከወላጆችና ከመምህራን እንዲሁም ከአካባቢው ኅብረተሰብ ጋር በመሆን የመፍታት ሥራ እየተሠራ ነው። ከዚህ ጋር በተገናኘ ቦሌ አካባቢ ያጋጠሙ ምልክቶች ነበሩ። ይህም ሆኖ ግን ከምልክቶች በዘለለ የጎላ ችግር እንዳላጋጠመም ኃላፊው ይናገራሉ።
ቀጣይ
በከተማዋ ያለው የተማሪዎችም ሆነ የመም ህራን ስብጥር ሲታይ ከበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች የተውጣጣ በመሆኑም ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ለዚህም መፍትሔ የሚሆነው የተወሰኑ መሠረታዊ የሚመስሉ ልዩነቶች ቢኖሩም እንኳ ግልጽ አድርጎ መነጋገርና መወያየየት፣ ሕግና ደንብ ማክበሩ ካለ እንዲሁም መምህራኑም ተማሪዎችም ይህን ማድረግ ከቻሉ ወደ ሠላም ለመሄድ አያዳግትም። ሠላማዊ ባህልን ማዳበር በትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማሩ የሚጠበቅበትን ግብ እንዲመታም የሚያበረክተው አስተዋፅዖ ቀላል እንዳልሆነ ፕሮፌሰር ሀብታሙ ያስረዳሉ።
የሠላም ባህል እንዴት ይዳብር? የሚለውም በጣም ሰፊ ጽንሰ ሃሳብ አምቆ የያዘ በመሆኑ ሠላም ምንድን ነው? ሠላማዊ ባህልስ? በዚህ ውስጥስ የተማሪዎች፣ የመምህራንና የትምህርት ተቋማት ድርሻ ምን ሊሆን ይገባል? በሚል መወያየት ይገባል። ተማሪዎችና መምህራን ሊሠሩ የሚችሉትንና የሚገባቸው ጉዳዮች አንስቶ መምከሩ ተገቢ ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ ታዲያ ተማሪዎች፣ መምህራንና ወላጆች ያላቸው ሚና የማይተካ እንደሆነም የማህበራዊ ሳይኮሎጂ ተመራማሪና መምህሩ ያብራራሉ።
ከተሰጠው የኃላፊው መረጃ መረዳት እንደሚቻለው እነዚህ ሦስት ቁልፍ አካላት በቅንጅት በመሥራት ስለ መማር-ማስተማር ሂደትም ሆነ አጠቃላይ የተማሪዎች እንቅስቃሴን በተመለከተ ክትትል ማድረግ ይገባቸዋል፤ ይጠበቅባቸዋልም። በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተማሪዎች የፖለቲካዊ አጀንዳዎች ሰለባ ሲሆኑ ይታያልና ይህ ችግር እንዳይዛመት፣ ጉዞውን ለመግታትና በተከሰተባቸው አካባቢዎችም ምን ጩን ለማድረቅ አዲስ አበባ የሚገኙ ትምህርት ተቋማት፣ መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም ወላጆች በተቻለ መጠን ኢትዮጵያን የሚያንፀባርቁ ናቸው። በመሆናቸውም በዚህ ላይ በትኩረት መሥራት ትልቅ መፍትሔ በመሆኑ ችላ መባል የሌለበት መሆኑን ነው ፕሮፌሰር ሀብታሙ ምክረ- ሃሳባቸውን የሚሰነዝሩት።
ዶክተር ታቦር በበኩላቸው፤ ትምህርት ቤቶች የፖለቲካ አጀንዳዎች ማስፈፀሚያና ተጋላጭ መሆን የለባቸውም ሲሉ የመምህሩን ሃሳብ ይጋራሉ። ምክንያቱም ይላሉ ዶክተሩ፣ ትምህርት ቤት ውስጥ በርካታ ሕፃናት ይገኛሉ። በቅድመ መደበኛ ከሚገኙት ከአራት ዓመት ሕፃናት ጀምሮ በወጣትነት ዕድሜ እስካሉት የነገ አገር ተረካቢ ዜጎች ሰብእና መቅረጫ ስፍራ እንደሆነም መገንዘብ የሚያስፈልግ፤ የእነዚህን የማኅበረብ ክፍሎች ጤናማ እድገትና ሁለንተናዊ ደህንነት በመጠበቅ አገሪቱ ከእነርሱ የምትጠብቀውን ጣፋጭ ፍሬ እንድትበላ፤ ሠላማዊ የመማር-ማስተማር ሂደት እንዲኖር ማድረግ፤ ሠላማዊ መሆኑንም ማረጋገጥ የሚያስፈልግ፤ ለዚህም ደግሞ ተቋማቱ ብቻ ሳይሆኑ መላው ኅብረተሰብም ከፍተኛ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ ነው።
የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ታቦር እንደሰጡት ማብራሪያ ከሆነ በአሁኑ ወቅት መንግሥት ችግሮቹን ከምንጫቸው ለማድረቅ እየሠራ ያለውን ሰፊ ሥራ አጠናክሮ በመቀጠል ላይ ያለ ሲሆን፤ በቀጣይም ከከተማ ከፍተኛ አመራሮች ጀምሮ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የውይይት መድረክ ይዘጋጃል። የቢሮው ኃላፊነት የመማር-ማስተማሩ ሥራ ሠላማዊ እንዲሆን ማረጋገጥ በመሆኑም በየትኛውም መንገድ ይህን የሚያስተጓጉሉ ተግባራትን ለማስወገድ በትኩረት እንደሚሠራም ኃላፊው ያረጋግጣሉ። በሌላ በኩል መምህራን በኅብረተሰቡ ውስጥ የሚገኙ፣ ተቀባይነት ያላቸውና በትምህርት ቤቶች ብቻ ሳይሆኑ በሚኖሩበት አካባቢም በአርአያነት የሚታዩ ስለሆነ ለሠላሙ መረጋገጥ የሚኖራቸው ሚና ከሁሉም የላቀ ይሆናል።
ይህ ብቻ አይደለም፤ እንደ ኃላፊው ማብራሪያ ሁሉም የበኩሉን መወጣት በሚያስችለው መል ኩም የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች በማዘጋጀት በኅብረተሰቡ ውስጥ ሚናቸውን እንዲወጡ፤ ትምህርት ቤት ያሉ ወጣቶችም ድርጊትን በምከ ንያት የሚፈጽሙ፣ አቋም የሚይዙና በምክንያት የሚወስኑ እንዲሆኑ አድርገው እንዲያስተምሩ ይደረጋል።
የመማር-ማስተማር ተግባር አቢይ ትኩረት ትውልድን በዕውቀት፣ በክሂሎት፣ በአስተሳሰብ፣ በሥነ-ልቦናና በሥነምግባር መገንባት ነው። ዋነኛው የትምህርት ዓላማም ምክንያታዊ የሆነ፣ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የሚያስብ ዜጋን መፍጠር ነው። የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚሠራው ሥራም እየተጠናከረ ሲሄድ ይህን መሠል ምክንያታዊ ትውልድ የመፍጠር ሥ ራውም አብሮ ለስኬት ይበቃል። በመሆኑም በአጠቃላይ ኅብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ሠላማዊ ሁኔታ በመጠቀም የመማር-ማስተማሩ ሂደት ከሚጠበቅበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ እና አስፈ ላጊውን አገራዊ ጥቅም እንዲያስገኝ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ታቦር ጥሪያቸውን ያስተላልፋሉ።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 7/2011
ፍዮሪ ተወልደ