እውነት አፋችን ላይ ሰላም የሚለው ቃል እንደሚቀለን፤ በወሬ ሰላምን እንደምንናፍቅ ለሰላም ተግባራዊነት እንነሳለን ወይ ? ብዬ ልጠይቅ ወደድኩ። እስኪ አንድ እንበል በታሪክ እንጣላለን በጣም የሚገርመው ታሪክ ሲሰራ ለአገር ድልና የበላይነት ከፍ ለማድረግ ሆኖ ሳለ ለአገር ታሪክ የሰሩ ድንቅ አባቶቻችንን በብሄር ደሴት ውስጥ ከበን ለማሰር እንሞክራለን።
የአገርን ሉአላዊነት ያስጠበቁትን አጥንታቸውን ከስክሰው፤ ደማቸውን አፍስሰው ከሰው በላይ ቀና እንድንል ዋጋ የከፈሉልንን ታሪክ ሰሪዎቻችንን የኔ፤ የኔ በሚል ውሃ በማይቋጥር ሀሳብ፤ የተከበረ ክብራቸውን ስናቀል፣ ባልተወለድንበት ዘመን በተሰራ ታሪክ ስንደነቋቆል እውነት እኛ ሰላምን እንፈልጋለን አያሰኝም ትላለችሁ።
ሁሉም በዘመኑ የዘመኑ ጀግና መሆን ሲገባው፤ ዘመን የሚጠይቀውን ገድል እንደማስቀመጥ ይልቁኑ በጠባብነት ገመድ ተተብቶብ ሲደነቃቀፍ ከመመልከት የበለጠ ምን ፀያፍ ድርጊት ይኖር ይሆን ?
ልቀጥል፤ በዘር እንጣላለን። ወደን መርጠን ባልተወለድንበት፤ እገሌ ከዚህኛ እገሊት ደግሞ ከዛኛው እየተባለ ጎጣጎጥ ስናበጅ ምንም አይነት የራስ አስተዋፅኦ በሌለበት በፈጣሪ ፍቃድ በሆነ ማንነት ለሞት ለመጠላላት እራሳችንን አሳልፈን ሰጥተናል።
ሰው ሰውነቱ ቀርቶ አማራ፥ ኦሮሞ፥ ትግሬነቱ ሲጎላ ከዚህ የባሰ ሰላምን የሚየሳጣ፣ ሰላምን የሚያደፈርስ ይኖር ይሆን ? እናስ ዘር ቆጠራችንን ሳናቆም ስለምን ሰላምን ናፈቅናት? ሰላም በናፍቆት ሰላም በማውራት የሚገኝ ቢሆንማ ጉንጫችንን ስናለፋ በዋልን ነበር።
በኃይማኖት እንጣላለን፤ እዚህ ጋ ደግሞ ሌላ ትኩሳት አለ ዘፋኙ። መቼስ ሰላም ናፋቂዎቹ መካከል ፈጣሪን ከሚያምኑት የላቀ ማንም አይገኝም። ማንም ሰው ማንነቱ ተከብሮ ይኖርለት ዘንድ የሌሎችን ኃይማኖት ማክበር ግድ ሊለው ሲገባ ባልተገራ አንደበት አንዱን ሀይማኖት የበላይ ሌላውን የበታች እያደረጉ ማንኳሰስ ማጣጣል፤ ባልተገባ ቋንቋ የሌላውን ሐይማኖት በስርአት አልበኝነት መዘርጠጥ እውን ከሰላም ፈላጊዎች የሚገኝ ነው ብላችሁ ታምናላችሁ ?
በቋንቋ እንጣላለን ፤ አንድ ቋንቋ የአንድ ህዝብ ወይም የብሔር ቋንቋ ወይም ከተለያዩ ህዝቦች እና ብሄሮች የሚግባቡበት ነው። የቋንቋ የግንኙነት ስርዓት ሲሆን ይህም በአፍም በፅሁፍም ሊሆን የሚችል ነው። ዋና አላማው በሰዎች መካከል መግባባት እንዲኖር በሚያረጋግጡ የድምጽ፣ የምልክት፣ የሰዋሰዋዊ ህጎች ድምር ነው። ታዲያ ይህ ለመግባቢያነት የተፈጠረ መሳሪያ ጭራሽ መጣያና መነጣጠያ ሲሆን ምን ይሉያል!።
በቋንቋ ተግባብቶ ዓለም ከምድር አልፎ ሰማይ ላይ በሚወጣበት ዘመን፤ ጨረቃና ፕላኔቶችን በሚያጠናበት በዚህ በዘመነ ዘመናዊነት የእገሌ የእገሊት ዘር እንዲህ አለ እንዲህ አለች በሚል ጥብብ ያለ እንደ ጋሪ ፈረስ ብቻ ፊት ፊቱን እያየን የዓለምን ስፋት ሳንመለከት አንድ አይነት ቋንቋ እየተነጋገርን ቋንቋችን ተደበላልቆ ያን ማረቅ የተሳነን እኛ እውን ሰላምን አፋችን ላይ እንዳለው ከልብ እንፈልገዋለን?
ሌላ ልጨምር፤ በፖለቲካ አመለካከት እንጣላለን፣ ምንም ሰው የሌላውን አመለካከት ለመጨፍለቅ እስካልሞከረ ድረስ የራሱ የሆነ ፖለቲካዊ አመለካከት ሊኖረው መብቱ ነው። ግን እኔን ሰሙኝ፤ እኔን ተከተሉኝ በሚሉ አዋቂ ነን ባዮች የተነሳ የራስ አመለካከት የወል ይሆንና የፀብ መነሻ ይሆናል። በግድ እምነትና አመለካከትን ለመጫን በሚፈጠር ሽኩቻ ውስጥ ነው ፖለቲካ ራሱ ዱላ መማዘዣ፤ ነፍስ መጣፊያ የሚሆነው።
ጥንታዊት፤ ለዓለም የአንድነት ተምሳሌት የሆነችው አገራችን፤ የቀደሙት አባቶቻችን በብዙ የተጋድሎ መስዋእትነት ያቆዩልን አገራችን ባንዲራ /አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ/ መጣያችን መሆኑስ ምን ይሉታል? አንድ ሰላም ረሃቤ ነው ከሚል ማህበረሰብ የአገር መለያ የሆነው ቀለም ሲታይ ፍቅርን እና አንድነትን መስበክ ሲኖርበት መለያያ የሚሆንበት ምክንያትስ ምድነው? ።
ይህ ፀብ ያለሽ በዳቦ የሆነው አመላችንን በጉያችን ሸሸገን አገራችንን ሰላም ያድርግልን ቅብርጥሶ ስንል አያምርብንም ሰላም በአፍ ሳይሆን በተግባር የሚገለጥ ነው። ሰላም ሰው የመግደልን ያህል አሰቃቂ ባይሆንም፤ በይቅርታ ራስን መስበርን ዝቅ ማለትን፤ ለእያንዳንዱ ነገር ልብን ክፍት ማድረግ በቅንነት ማሰብን፤ ራስን በትህትና መግደልን ይጠይቃል።
ሰላም በእውነት የሚፈልግ የሚበረበርና የሚለመድ ነው። ሰላም ሰላም ብቻ ማለት ሰላምን አያመጣም ካለን ክፉ አመል ቀንስ አድርገን ለደግ ደጉ ጊዜ ስንሰጥ ነው እውን የሚሆነው። እስኪ አስቡት በስንቱ እንጣላለን፣ እንሰዳደባለን፣ ሰውን እናንቋሽሻለን፣ እንገዳደላለን። ይበቃል…. በቃ። ቆም ብለን ማሰቢያ ጊዜያችን አሁን ነው። እኔ የወደድኩትን ውደዱ፣ እኔ ያመንኩትን እመኑ፣ እኔ የጠላሁትን ጥሉ፣ እኔ ያልኩትን በሉ በቃ! እኔ፤ እኔ፤ እኔ ይብቃ እና የጠፋብንን፤ አንድ የሚያደርገንን፤ የሚያቀራርበንን እኛን እንፈልግ።
እውነተኛ እኛነታችን ሰላምን ስለመሻቱ፤ ባህሪያችን ሰላምን ስለመፈለጉ እናረጋግጥ፤ ራሳችንን እንመርምር። ውስጣችንን አሳምነን በእውነት መሻት ሰላምን እንፈልገው። ለይምሰል ለታይታ አፋችን ላይ ብቻ ሰላም ሰላም አንበል። ውስጣችን ሰላም ከሌለ ሰላም ከየት ነው የሚመጣው? በሰላም መኖር ከልብ ከፈለግን ከልባችን እንጣር። ልብ ያለው ልብ ይበል !
ብስለት
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24/2015