ሌላኛው የዚህ ሳምንት ክስተት ደግሞ በተለምዶ ‹‹የ60ዎቹ ትውልድ›› እየተባለ በሚጠራው የ1960ዎቹ የግራ ዘመም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ አንዱ ተሳታፊ የነበረው ጥላሁን ግዛው የተገደለበት ቀን ነው፡፡
ጥላሁን ግዛው የተገደለው ከ53 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ታኅሣሥ 19 ቀን 1962 ዓ.ም ነበር፡፡ የጥላሁን መገደል ሲሰማ ‹‹ጥላሁን ለምን ተገደለ?›› በሚል በተማሪዎች ከፍተኛ ተቃውሞ ተቀስቅሶ ነበር፡፡
በኢትዮጵያ የተማሪዎች እንቅስቃሴ የግራ ዘመም ፖለቲከኞች ስብስብ ተጠናክሮ አዞዎች(ክሮኮዳይልስ) የተሰኘ ቡድንን በመፍጠር 1957 ዓ.ም የኢትዮጵያ ተማሪዎች የትግል መርህ ‹‹መሬት ላራሹ›› መሆኑ ይፋ ተደረገ፡፡ መጋቢት 4 ቀን 1957 ዓ.ም ‹‹መሬት ላራሹን የምትሹ ፤ ተዋጉለት አትሽሹ›› እያሉ ተማሪዎች በአደባባይ ሰልፍ በወጡበት ወቅት የ11ኛ ክፍል ተማሪ የነበረው ጥላሁን በሰልፉ ተሳትፏል።
ጥላሁን ግዛው የ«አዞዎቹ» ዓላማ አራማጅና በኋላም ለመሪነት ለመታጨት የበቃ ወጣት ነበር። በ1961 ዓ.ም በተደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በመኮንን ቢሻው ቢሸነፍም በቀጣዩ ዓመት ኅዳር 1962 ዓ.ም በተደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በከፍተኛ ድምጽ ብልጫ አሸንፏል። ጥላሁን የፕሬዚዳንትነት ዘመኑ ቀዳሚ ሥራው የተማሪውን የመናገር ፣ የመጻፍና የመደራጀት ነጻነት ይበልጥ ማጠናከር ነበር። ለሁለት ወር ብቻ በፕሬዝዳንትነት የቆየው ጥላሁን የተለያዩ ሀሳቦች እንዲንሸራሸሩ በማበረታታት የሚታወቅ ታጋይ ነበር።
ታኅሣሥ 19 ቀን 1962 ዓ.ም ምሽት አንድ ሰዓት አካባቢ ከታናሽ ወንድሙ መኮንን ሲሳይ ጋር በመሆን ከስድስት ኪሎ በስተጀርባ አፍንጮ በር በሚባለው አካባቢ ፍቅረኛውን ዮዲት ታዬን ለመሸኘት ወጥተው ታርጋ በሌለው መኪና በተተኮሰ ጥይት ተገደለ።
ሱልጣን አባዋሪ የተባሉ ሰው ‹‹የተማሪው ትግልና የአብዮቱ ደመና›› በሚል ርዕስ አንታዛ መጽሄት ላይ ባቀረቡት ጽሑፍ የጠቀሷቸው ሌተናል ኮሎኔል ፍስሐ ደስታ ስለአሟሟቱ ሲገልጹ፤ ‹‹ስለ ጥላሁን ግድያ የተለያዩ ነገሮች ቢወሩም … ሐቁ ግን ግድያው የተፈፀመው በንጉሠ ነገሥቱ የክብር ዘበኛ፣ የንጉሱ የቅርብ አጃቢ ወይም አንጋች ክፍል ምክትል አዛዥ በነበሩት በኮሎኔል ጣሰው ሞጃ ትዕዛዝና ከብሔራዊ ጦር ተዛውረው እኔው ራሴ ደብረ ብርሃን ካሰለጠንኳቸው በኋላ የአንጋች ክፍል ባልደረባ በሆኑት ሁለት ወታደሮች ነበር። ለዚሁ ድርጊታቸውም ሁለቱም የምክትል መቶ እልቅና ማዕረግ የተሰጣቸው መሆኑን የድርጊቱ ፈፃሚዎች ነግረውኛል›› ብለዋል።
በግድያው የተቆጡ ተማሪዎች የጥላሁንን አስከሬን ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ (ስድስት ኪሎ) ቅጥር ግቢ በመውሰድ ከአዲስ አበባ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከመጡ ተማሪዎች ጋር የሀዘኑ ተካፋይ ሆኑ። የጥላሁን ታሪክና የትግል ዓላማ በግጥምና በስድ ንባብ እየተሰማ የሀዘን መግለጫው ዝግጅት ተካሄደ።
ቀጥሎም በተማሪዎች ሰልፍ ታጅቦ በክብርና በጀግንነት በሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የቀብሩ ሥነ ስርዓት ይፈጸም ዘንድ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ያደረጉት ጥረት በንጉሡ ጸጥታ ኃይሎች እርምጃ የተጨማሪ ተማሪዎችን ሕይወት ቀጥፎ አስከሬኑ ከተማሪዎቹ ተወሰደ።
የጥላሁን ግዛው አስከሬን ከተማሪዎቹ በኃይል እርምጃ ከተወሰደ በኋላ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ታኅሣሥ 22 ቀን 1962 ዓ.ም መላው ዘመድ አዝማድ በተገኙበት በአካባቢው ተማሪዎች ሰልፍ አጃቢነት በወቅቱ ትግራይ ጠቅላይ ግዛት በማይጨው ሕዝባ ማርያም ቤተክርስቲያን ተፈጸመ።
የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄም የጥላሁንን መገደል አስመልክቶ ባለ ሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ አወጥቶ ነበር፡፡ የመግለጫው ጥቅል መልዕክት፤ በጥላሁን መገደልና ከመገደሉ ተከትሎም በተከሰተው ተጨማሪ ጥፋት ሁሉ የወቅቱን ገዥ መንግሥት (የንጉሡን ሥርዓት) ተጠያቂ የሚያደርግ ነበር፡፡
አዲስ ዘመን እሁድ ታኅሣሥ 23 ቀን 2015 ዓ.ም