40ኛው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል ሀገር አቋራጭ ሻምፒዮና ነገ በኦሮሚያ በሱሉልታ ከተማ ይካሄዳል። በውድድሩ የሚያሸንፉ አትሌቶች እ.ኤ.አ የካቲት 23/2023 በአውስትራሊያ ባትሪስ ከተማ ለሚካሄደው 44ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉ ይሆናል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በየዓመቱ ከሚያካሄዳቸው ውድድሮች አንዱ የሆነው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል ሀገር አቋራጭ ውድድር ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ የሚካሄድ ሲሆን የበርካታ ሀገራት አትሌቶችም ተሳታፊ ናቸው። በነገው ውድድርም ከጎረቤት ሀገራት ኤርትራ፣ ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ዩጋንዳ፣ ጅቡቲና ሱዳን አትሌቶች እንዲሳተፉ የተጋበዙ ቢሆንም የሱዳን አትሌቶች ብቻ ለመሳተፍ ፍቃደኛ መሆናቸው ተገልጿል። በዚህ ውድድር ከሀገር ውስጥ 7 ክልሎች፣ 2 የከተማ አስተዳደሮች፣ 22 ክለቦች፣ 8 ቬትራን አትሌቶች፤ 231 የግል ተወዳዳሪዎች የሚሳተፉበት እንደሆነም ተነግሯል።
በውድድሩ ታዋቂና ኢትዮጵያን በተለያዩ የዓለም መድረኮች በመወከል ስኬትን የተቀደጁ አትሌቶች ተሳታፊ እንደሚሆኑ የተገለጸ ሲሆን ከነዚህም መካከል እንደ ሙክታር እንድሪስ፣ ሰለሞን ባረጋ፣ አቤ ጋሻው፣ ሰንበሬ ተፈሪ፣ አክሱማዊት አምባዬና ጎይቶቶም ገብረስላሴ ከዋንኞቹ ተሳታፊዎች መካከል ናቸው።
ተወዳዳሪ አትሌቶች በአዋቂ ወንድ 358፣ በአዋቂ ሴቶች 134 ከ20 ዓመት በታች ወንድ 217 ከ20 ዓመት በታች ሴት 176 በድብልቅ ሪሌ 64 አንጋፋ አትሌቶች 80 በአጠቃላይ 1029 አትሌቶች ይሳተፋሉ። የውድድር ካታጎሪ በወጣት ሴቶች 6 ኪሎ ሜትርና በአዋቂ ሴቶች 10 ወንዶች 10 ኪሎ ሜትር እንዲሁም በድብልቅ ሪሌ 8 ኪሎ ሜትር እንደሚሆኑም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሻምፒዮናውን ለማከናወን ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መድቧል። ለዉድድሩ ሽልማት የሚውል 865ሺ ብር እንደተዘጋጀ ፌዴሬሽኑ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል። በውድድሩ በሁሉም ከታጎሪ ከ1ኛ-3ኛ ለሚወጡ አትሌቶች የወርቅ የብርና የነሐስ ሜዳሊያ የሚበረከት ሲሆን ከ1-6 ለሚወጡ እንደየደረጃው የገንዘብ ሽልማት የሚሰጥ ይሆናል። የቡድን አሸናፊ ለሚሆኑ ለ5ቱም ካታጎሪዎች ደግሞ ለእያንዳንዳቸው የዋንጫ ሽልማት ተዘጋጅቷል። ውድድሩን ለመምራትና ለመደገፍ በዳኝነት፣ በቴክኒክ፣ በኮሙኒኬሽን፣ በሕክምናና በሌሎች አገልግሎት ከ160 በላይ የሰው ሃይል እንደሚሠማራም ተነግሯል፡፡
ኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት ገዛኸኝ አበራ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ውድድሩ ቀድሞ ከሚካሄድበት ከጃንሜዳ ወደ ሱሉልታ የተወሰደበትን ምክንያት ሲያስረዳ ‹‹ጃንሜዳ እኛ በነበርንበት ወቅት እኛንና ሌሎች እኛን መሰል አትሌቶችን ያፈራ ነው፤ ጃንሜዳ ከዚህ በፊት በኮቪድ ምክንያት የገብበ ቦታ ስለነበር ሜዳው የተስተካከለ ስላልሆነ የውድድር ሥፍራውን ከከተማ ውጪ ልናደርግ ግድ ሆኗል›› ሲል ተናግራል፡፡ ገዛኸኝ አያይዞም አምና በጃንሜዳ በተደረገው ውድድር በዚሁ ምክንያት ብዙ አትሌቶች ስለተጎዱ ይሄንኑ ለማስቀረትና አትሌቶችን ለኢንተርናሽናል ውድድር በጉዳት ላለማጣት በማሰብ ተፈጥራዊ በሆነ ቦታ ውድድሩ እንዲከወን መወሰኑን አስረድተል፡፡
የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና እ.ኤ.አ 1973 ጀምሮ ለ43 ጊዜ የተካሄደ ሲሆን ኢትዮጵያ በ1981 ስፔን ማድሪድ ከተማ ከተካሄደው ሻምፒዮና ጀምሮ በተከታታይ ለ35 ጊዜያት መሳተፏ ይታወቃል፡፡ በዚህ የውድድር መድረክ ባለፉት የውድድር ዓመታት ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገቡት ሴት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ፣ ጌጤ ዋሚ፣ ብርሃኔ አደሬ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ መሰለች መልካሙና ለተሰንበት ግደይ በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ሲሆን በወንዶች ደግሞ ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገ/ገብረስላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ገ/እግዚአብሔር ገ/ማርያምና ሐጎስ ገ/ሕይወት ለአብነት የሚጠቀሱ አትሌቶች ናቸው። የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ዘንድሮ ለ40ኛ ጊዜ የሚካሄድና ባለፉት በርካታ ዓመታት ለአትሌቶች የውድድር እድልን የፈጠረ እንዲሁም ሀገርን ወክለው የሚሳተፉ አትሌቶችን በመምረጥ ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበበት ውድድር መሆኑንም ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡
የሀገር አቋራጭ ውድድር ተፈጥራዊ በሆኑ መሰናክሎች ሜዳማ፣ ዳገታማ፣ ቁልቁልታማ፣ ጭቃማና ሌሎች ጉልበት የሚፈታተኑ መልካ-ምድሮች አትሌቶች የሚፈተኑበት ተወዳጅ የአትሌቲክስ ውድድር ሲሆን፣ በአውሮፓ በተለይም በእንግሊዝ አገር ተጀምሮ በዓለም አትሌቲክስ ተቀባይነት በማግኘት በአሁኑ ጊዜ በሁለት ዓመት አንድ ጊዜ በዓለም ሻምፒዮና ደረጃ ይካሄዳል።
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 22 /2015