የሲሚንቶ እጥረትና የዋጋ መናር የኮንስትራክሽን ዘርፉን መፈታተን ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል። የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች እንዲጓተቱ ከማድረጉም ባሻገር የአገሪቱን ኢኮኖሚ ክፉኛ እየጎዳው ይገኛል።
ከከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የተገኘ መረጃም ይህንኑ ያመለክታል፤ መረጃው እንደሚያስገንዝበው፤ የሲሚንቶ እጥረትና የዋጋ መናር አንዱና ዋነኛው ምክንያት የአገሪቱ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በአቅማቸው ልክ እያመረቱ አለመሆኑ ነው።
በኢትዮጵያ ውስጥ 20 የሚሆኑ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ቢኖሩም፣ የእነዚህ ፋብሪካዎች የማምረት አቅም 17 ነጥብ አንድ ሚሊየን ቶን ቢሆንም፣ ማምረት ያለባቸውን ያህል እያመረቱ አይደለም። ወደ ስምንት ነጥብ አራት ሚሊዮን ቶን አካባቢ ብቻ ነው የሚያመርቱት። ይህ ከአቅርቦት አንጻር በመቶኛ ሲሰላ 45 ነጥብ 9 በመቶ ብቻ ነው።
መንግሥትም ይህን ችግር መቅረፍ ያስችላሉ፤ ገበያውንም ያረጋጋሉ ብሎ ያመነባቸውን እርምጃዎች ሲወስድ ቆይቷል። ለአብነትም የሲሚንቶ ዋጋ በመንግሥት ተወስኖ እንዲሸጥና የአንድ ኩንታል የሲሚንቶ ዋጋ መሸጫን ጨምሮ አንድ ግለሰብ ምን ያህል መግዛት ይችላል በሚለው ላይ ጭምር ገደብ አበጅቶ እንደነበርም ይታወሳል።
ይሁን እንጂ በዚህ እርምጃ የዘርፉን ችግር ማቃለል አልተቻለም። እንዲያውም የሲሚንቶ ዋጋ በመንግሥት ተወስኖ በተወሰኑ አካላት በኩል እንዲሸጥ መደረጉ ችግሩን አወሳስቦት በሲሚንቶ አቅርቦት፣ ዋጋ፣ ማጓጓዝ፣ ወዘተ በኩል ቅሬታዎች እንዲነሱ ሲያደርግ ቆይቷል፤ ህገወጥ የሲሚንቶ ግብይት ደርቷል። ከዚህ በተጨማሪም ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች ሲሚንቶ በቀላሉ ማግኘት እንዳይችሉ አድርጓቸው መቆየቱም እንደ አንድ ችግር እየተጠቀሰ ቆይቷል።
ባለፈው ሳምንትም መንግስት በሲሚንቶ ላይ የሚታየውን ችግር ይፈታል ያለውን አዲስ መመሪያ አውጥቷል። የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተሻለ በልሁ በወቅታዊ የሲሚንቶ ስርጭትና ግብይት ዙሪያ መግለጫ በሰጡበት ወቅት እንዳሉት፤ የሲሚንቶ ምርት ስርጭትን በተመለከተ የወጣው መመሪያ ቁጥር 908/2014 በአዲስ መመሪያ ተተክቷል።
በአዲሱ መመሪያ መሰረት፤ መንግስት ከሲሚንቶ ግብይት የወጣ ሲሆን፣ ግብይቱ በነጻ ገበያ እንዲካሄድ ተወስኗል። ከዚህ በኋላ የሲሚንቶ ግብይት በየትኛውም ቦታ ቁጥጥር እና ክትትል ሳይደረግበት በነጻ ገበያ መካሄድ ይካሄዳል።
አከፋፋዮችን እና ቸርቻሪዎችን መምረጥም የፋብሪካዎቹ ስራ ይሆናል። የፋብሪካዎቹ የመሸጫ ዋጋ ለጊዜው ምርታማነት እስከሚጨምር ድረስ በመንግስት የሚወሰን ሲሆን፣ የፋብሪካ ዋጋም በስድስት ወር አንድ ጊዜ በሚኒስቴሩ ይወሰናል።
መንግሥት ሽያጩ ያለ ደረሰኝ እንዳይካሄድ ቁጥጥር እንደሚያደርግ ሚኒስትር ዴኤታው አስታውቀው፣ በግብይቱ ውስጥም ህጋዊ ንግድ ፍቃድ እና ደረሰኝ ግዴታ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
ጉዳዩን አስመልክተን ያነጋገርናቸው የዘርፉ ተዋናዮችም መንግሥት የወሰደው እርምጃ ተገቢነት እንዳለው አረጋግጠዋል። የኮንስትራክሽን ድርጅት ባለቤትና በሪልስቴት ዘርፍ የማማከር ሥራ የተሰማሩት ኢንጂነር ደሳለኝ ከበደ፤ ከዚህ ቀደም የሲሚንቶ ምርት ከገበያ ጠፍቶ እንደነበርና ለማግኘትም እጅግ አስቸጋሪ እንደነበር ያስታውሳሉ። መንግሥት ሲሚንቶ ላይ የሚታየውን ይህን ውስብስብ ችግር ማቃለል ያስችላል በማለት ስራ ላይ ያዋለው መመሪያ ችግሩን ይበልጥ እንዳባባሰው ነው የጠቆሙት።
የሲሚንቶ ምርት በጥቂት ግለሰቦች እጅ ውስጥ ገብቶ በህገወጥ መንገድ ሲሸጥ እንደነበረ ጠቅሰው፣ አንድ ኩንታል ሲሚንቶ እስከ 2500 ብር ያለ ደረሰኝ በህገወጥ መንገድ እየተሸጠ የጥቂቶች መጠቀሚያ ሆኖ መቆየቱን አመልክተዋል። አሁን መንግሥት በገበያው ውስጥ ያለውን ችግር በመረዳት መመሪያውን በማሻሻሉ ደስተኛ መሆናቸውን የሚናገሩት ኢንጂነር ደሳለኝ፣ ገበያው ይረጋጋል የሚል እምነት እንዳላቸውም ይገልጻሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ በተሻሻለው መመሪያ መሰረት በአሁኑ ወቅት የሲሚንቶ ምርት ገበያው ላይ መታየት ጀምሯል። ይህም ይበል የሚያሰኝና የተሻለ ነገር እንደሚመጣም ያመላከተ ነው።
በዚሁ የመንግሥት ውሳኔ ብቻ የሲሚንቶ ምርት በገበያው ከመታየት ባለፈ ዋጋውም በአንድ ሶስተኛ መቀነስ መቻሉን ጠቁመዋል። አሁን አንድ ኩንታል ሲሚንቶ አንድ ሺ 700 ብር እየተሸጠ እንደሆነ የተናገሩት ኢንጂነር ደሳለኝ፤ ይህም መንግሥትን የሚያስመሰግን ተግባር ነው፤ በዚሁ ይቀጥል ብለዋል።
በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩት የዘርፉ ባለሙያ ኢንጂነር መጽሐፈ መክብብም ሀሳብ የኢንጂነር ደሳለኝን ሀሳብ ያጠናክራል። ኢንጂነር መጽሐፈ እንዳሉት፤ በቀድሞው መመሪያ መሰረት ቀደም ሲል ሲሚንቶ በቀላሉ ማግኘት አይቻልም። ፍላጎቱን ማሟላትም አልተቻለም። ሲሚንቶ ለማግኘት የሚደረጉ ምዝገባዎችም ውጤት አላሳዩም። ሲሚንቶው በህገወጥ መንገድ በድብቅና በሌሊት ሳይቀር ሲሸጥ ቆይቷል። ይህም አላስፈላጊ ለሆኑና ለማይመዘገቡ ወጪዎች ሲዳርጋቸው ቆይቷል።
በዚህም እርሳቸውን ጨምሮ አብዛኛው ተጠቃሚ ሲማረር እንደቆየና የተጀማመሩ ፕሮጀክቶች እንዳይቋረጡ በሚል ብቻ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለመስራት ሲሞክሩ መቆየታቸውን ይናገራሉ። ይህ አይነቱ ሁኔታና ተያያዥ ችግሮች የገበያ አለመረጋጋት እንዲፈጠር ሲያደርጉ መቆየታቸውን ነው የተናገሩት። እያሻቀበ በቆየው የሲሚንቶ ዋጋ ምክንያት የመኖሪያ ቤት ዋጋ እየናረ መሆኑን ይገልጻሉ።
የኮንስትራክሽን ዘርፍ ሰፊ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ጠቅሰው፣ በተፈጠረው የሲሚንቶ እጥረት ከሲሚንቶ ጋር ተያያዥ የነበሩ ሥራዎች ሲቋረጡ አብዛኛው ሠራተኛም ከሥራ ውጭ ለመሆን እንደተገደደ የተናገሩት ኢንጂነር መጽሐፈ፤ በርካታ ሠራተኞች ሥራ ፈት ሆነው ቤተሰቦቻቸውን መደገፍ መቸገራቸውን ይገልጻሉ። ይህም የሲሚንቶ እጥረትና የዋጋ ውድነት ተጽዕኖው ሰፊ መሆኑን ያመለክታል ይላሉ።
መንግሥት ባለፈው ሳምንት መመሪያውን ካሻሻለ ማግስት ጀምሮ በዋጋ ላይ መጠነኛ ለውጥ መታየት መጀመሩን የጠቀሱት ኢንጅነር ደሳለኝ፤ ይህ ሆነ ማለት ችግሩ ሙሉ ለሙሉ ተቀረፈ ማለት እንዳልሆነም ነው የገለጹት። አሁንም የፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን ስለመኖሩ ጠቁመዋል።
እንደሳቸው ገለጻ፤ የኮንስትራክሽን ሥራ በአገሪቷ እጅጉን እየተስፋፋ በመሆኑ ከፍተኛ የሆነ የሲሚንቶ ፍላጎት አለ። ይህን ፍላጎት ማርካት የሚችሉ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በአገሪቱ የሉም።
በቀድሞው አሰራር ምርቱ በገበያ ውስጥ የማይታይና ሲገኝም የተጋነነ ዋጋ ይጠየቅበት እንደነበረ አስታውሰው፣ በዚህ የተነሳም ሰዎች እንደአቅማቸው መግዛት አይችሉም ነበር ይላሉ። በአዲሱ መመሪያ መሰረት የሲሚንቶ ገበያ ሊረጋጋ እንደሚችል ተናግረዋል። መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ ሲል ባወጣው የቀድሞው መመሪያ ያለአግባብ የተጠቀሙ ጥቂት የማይባሉ ግለሰቦች መኖራቸውን ገልጸው፣ የአሁኑ እርምጃ የሚደገፍ ቢሆንም አሁንም ክትትል ማድረግ የግድ መሆኑን ያስገነዝባሉ።
ችግሩን በዘላቂነት መፍታት የሚቻለው የምርት አቅርቦትን ካለው ፍላጎት ጋር በማጣጣም መሆኑን ያመለከቱት ኢንጂነር ደሳለኝ፤ በሰላምና ጸጥታ ችግር ማምረት ያቋረጡ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ወደ ሥራ ሲገቡ፣ አዳዲስ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ማምረት ሲጀምሩ፣ ሌሎች ፋብሪካዎችም በሚሰሩት የማስፋፊያ ሥራ በሙሉ አቅም ማምረት ሲጀምሩና አጠቃላይ የምርት አቅርቦቱ ሲሰፋ በሲሚንቶ ገበያ ላይ የሚስተዋለው ችግር በዘላቂነት እንደሚፈታ ተናግረዋል።
ሲሚንቶን ጨምሮ በአገሪቱ የሚስተዋሉ ለግንባታው ዘርፍ የሚያስፈልጉ ማንኛቸውም እጥረቶች በተለይም የጥሬ ዕቃ አቅርቦት በአገሪቱ የሚገኝላቸው ምርቶች በአገር ውስጥ በስፋት መመረት የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠርና ማበረታት እንደሚያስፈልግም ይጠቁማሉ።
መንግሥት መመሪያውን ማሻሻሉ እንደ አንድ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን የገለጹት ኢንጂነር መጽሐፈ፤ የሲሚንቶ ገበያ ሙሉ በሙሉ በነጻ ገበያ መመራት ባይችልም መንግሥት የዋጋ ቁጥጥር ማድረጉ ለጊዜው መፍትሔ መሆን እንደሚችል ነው የጠቀሱት። በአገሪቱ ካለው የምርት እጥረት ጋር በተያያዘ ከአምራችና ሸማቹ ውጭ ያሉ ዘርፉን የሚዘውሩት በርካታ አካላት መኖራቸው ችግሩን ለመፍታት አስቸጋሪ እንደሚሆኑ ስጋቱ እንዳላቸው ገልጸዋል።
የዘርፉ ዋናው ችግር የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም ነው ያሉት ኢንጂነር መጽሐፈ፣ መንግሥት ችግሩን በዘላቂነት መፍታት የሚቻልበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ዝግጁ መሆኑን መግለጹን ጠቅሰዋል፤ ኢንጂነሩ መንግስት ፋብሪካዎች መለዋወጫ የሚያገኙበትን የውጭ ምንዛሪ እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር፣ በሰላምና ጸጥታ ችግር ምክንያት ምርት ያቆሙትን የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ፣ ቁጥጥሩን ለማጠናከር በሚያደርገው ጥረት የሲሚንቶ ገበያውን ማረጋጋት ይቻላል የሚል ዕምነት አላቸው። መንግሥት ዋጋ መወሰኑ እንዳለ ሆኖ፤ ምርቱን በየቦታው ለማሰራጨት የነበረውን ኃላፊነት መተው በራሱ ትልቅ ለውጥ ይፈጥራል ይላሉ።
መንግሥት በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማቃለል እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ እንደሆነና አሁን የተወሰደው የመመሪያ ማሻሻያ ውጤት ሊያመጣ የሚችል ጊዜያዊ መፍትሔ እንደሆነ ተናግረው፣ ዘላቂ መፍትሔውንም ጠቁመዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ፍላጎቱንና አቅርቦቱን ማጣጣም ያስፈልጋል። ለዚህም አዳዲስ የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን መገንባትና ለነባሮቹን ድጋፍና ማበረታቻ ማድረግ ይስፈልጋል።
ኢንጅነር መጽሐፈ በቁጥጥር አስፈላጊነት ላይ ኢንጂነር ደሳለኝን ያነሱትን ሀሳብም የሚያጠናክር አስተያያት ሰጥተዋል። እንደ ኢንጂር መጽሐፈ ፈለጻ፤ በሂደት ከሚመጣው ዘላቂ መፍትሔ በተጨማሪ መንግሥት አሁን ያወጣውን ማሻሻያ ተግባራዊ በማድረግ ውጤታማ መሆን እንዲቻል ቁጥጥር ላይ አተኩሮ መስራት ያስፈልጋል። ያ ካልሆነ የቀደመው ችግር አዙሪት ሆኖ ይመጣል። በቁጥጥርና ክትትል የዘርፉ ስጋት የሆኑ ችግሮችን መቅረፍ ይቻላል።
‹‹በዋናነት መንግሥት ስትራቴጂክ የሆኑ ዕቅዶችን በማዘጋጀት የቅድመ ዝግጅት ሥራ መሥራት ይኖርበታል›› ያሉት ኢንጅነር መጽሐፈ፤ ለነገሮች የሚሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑ ችግሮች እንዲፈጠሩ ምክንያት መሆኑን ይጠቁማሉ። ችግሮች ከተከሰቱ በኋላ ደግሞ ለማስተካከል የሚደረገው ጥረት ብዙ ጊዜ ውጤታማ ካለመሆኑም በላይ ብዙ ዋጋ እንደሚያስከፍል ገልጸዋል። ለሲሚንቶ ብቻ ሳይሆን እንደ አገር ለማንኛውም ጉዳይ ትልቅ ትኩረት መስጠትና ቀድሞ መዘጋጀት ውጤታማ እንደሚያደርግ ነው ያመለከቱት።
‹‹አገሪቷ በማደግ ላይ ያለችና ከፍተኛ ፍላጎት ያላት በመሆኗ የሲሚንቶ ገበያን ለማረጋጋት በብዙ ማምረት መፍትሔ ነው‹‹ የሚሉት ኢንጂነር ደሳለኝ፤ ኢንዱስትሪው ግዙፍ በመሆኑ አገር ውስጥ ካለው አምራች በተጨማሪ የውጭ ባለሃብቶችን በመጋበዝ ፋብሪካ ተክለው ማምረት እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባ አመላክተዋል።
የአገር ውስጥ ባለሃብቶችም ህንጻ ብቻ ከሚሠሩና መኪና አስመጥተው ከሚሸጡ ወደ ኢንዱስትሪ የሚገቡበትን ሁኔታ ማመቻቸትና ማስለመድ አስፈላጊና የግድ እንደሆነም ነው ኢንጂነር ደሳለኝ ያስገነዘበቱት። ለሲሚንቶ ግብዓት የሚሆኑ ጥሬ ዕቃዎች በስፋት በአገር ውስጥ እንደሚገኙ ጠቅሰው፤ ዋናው ማሽኑን መትከልና መለዋወጫዎችን ማስገባት መሆኑን ይገልጻሉ። ለዚህም መንግሥት ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንደሚጠበቅበት አስረድተዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 19 /2015