መስከረም አጋማሽ ላይ የተጀመረው የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 13ኛ ሳምንቱ ላይ የደረሰ ቢሆንም ከዛሬ ጀምሮ ይቋረጣል። ምክንያቱ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለአፍሪካ ሃገራት ቻምፒዮንሺፕ (ቻን) ውድድር ዝግጅት የሚጀምርበት ወቅት በመሆኑ ነው። ቡድኑ ከነገ ጀምሮ የሚሰባሰብ ሲሆን፤ ጥሪ ከተደረገላቸው ተጫዋቾች መካከልም ከቡድኑ ጋር የሚቀጥሉት 28 ተጫዋቾች ተለይተው ታውቀዋል።
አልጄሪያ ዘንድሮ ለ7ኛ ጊዜ የምታዘጋጀው የአፍሪካ ሃገራት ቻምፒዮንሺፕ (ቻን) በመጪው ወር መጀመሪያ ሳምንት አንስቶ ይካሄዳል። በሃገር ውስጥ ሊጎች የሚጫወቱ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት የቻን ውድድር መቃረብን ተከትሎም ተሳታፊ ሃገራት ብሄራዊ ቡድኖቻቸውን ማዘጋጀት ጀምረዋል። ከእነዚህ ሃገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያም ከነገ ጀምሮ ወደ ዝግጅት የምትገባ ይሆናል። ለዝግጅቱም ሲባል በድሬዳዋ እየተካሄደ የሚገኘው የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከዛሬ ጀምሮ የሚቋረጥ መሆኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስቀድሞ ማሳወቁ ይታወሳል። ከነገ ጀምሮ ባለው ቀንም ለቡድኑ ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች ወደ ዝግጅት የሚገቡ ይሆናል።
ኢትዮጵያን የሚወክለው ብሄራዊ ቡድን የመጀመriያ ዙር ጥሪ የተደረገለት ባለፈው ህዳር ወር 2015ዓ.ም ሲሆን፤ የዋልያዎቹ ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የ42 ተጫዋቾችን ዝርዝር ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው። ይህም የሆነው ለውድድር ቅድመ ዝግጅት እንዲረዳ እና ተጫዋቾች በየክለባቸው በውድድር ላይ እያሉ ተገቢውን ክትትል እና ዝግጅት ለማከናወን እንዲያግዛቸው መሆኑንም በወቅቱ አሳውቀው ነበር። በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በተያዘው መርሃ ግብር መሰረትም ከነገ ጀምሮ ለቡድኑ ከታጩት ተጫዋቾች መካከል አብረው የሚቀጥሉት የ28ቱ ተጫዋቾች ዝርዝር ይፋ የተደረገ ሲሆን ከነገ ጀምሮ ሪፖርት በማድረግ ዝግጅቱ የሚጀመር ይሆናል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ገብረማርያም፤ አስቀድሞ ጥሪ የተደረገው ተጫዋቾች በሊግ ተሳትፏቸው አቋማቸውን ጠብቀው ብቃታቸውን እያሳደጉ እንዲቆዩ በሚል መሆኑን ገልፀዋል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የአሰልጣኞች ቡድን በድሬዳዋ ሲካሄድ በቆየው ፕሪምየር ሊግ ተገኝተው ተጫዋቾችን ሲመለከቱ መቆየታቸውንም አክለዋል። በግምገማቸው መሰረትም የቡድኑን ቁጥር በመቀነስ ከነገ ታህሳስ 18/2015ዓ.ም ጀምሮ በመሰባሰብ በቀጥታ የቻን ዝግጅታቸውን የሚጀምሩ ይሆናል። ፌዴሬሽኑም ለዝግጅቱ አስፈላጊ የሆነውን ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ዝግጅቱም ከኢትዮጵያ ባሻገር ከአልጄሪያ የአየር ሁኔታ ጋር ለመጣጣም እንዲያስችል ከሃገር ውጪ ለማድረግ መታሰቡን ዳይሬክተሩ አመልክተዋል። ለጊዜው ሞሮኮን ጨምሮ በሌሎች ሃገራት ዝግጅት ለማድረግ እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ ቢሆንም የተረጋገጠ ነገር የለም።
ፌዴሬሽኑ ከአስተዳደራዊ ድጋፍ ጎን ለጎን ለቡድኑ ቅድመ ዝግጅት እና ከውድድሩ ጋር ተያያዥ ለሆኑ ወጪዎች ከፍተኛ የፋይናንስ አቅም የሚያስፈልግ በመሆኑ የኢፌዴሪ መንግስት የ50 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርግለት ጠይቆ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል። ይኸውም ለሁለት ሳምንት ለሚደረገው ዝግጅት የሚውል ወጪ፣ ለጉዞ፣ በአልጄሪያ በሚኖረው ቆይታ ለሚኖሩ ወጪዎች እና ሌሎችም እንዲውል ገንዘቡ እንደተጠየቀ ዳይሬክተሩ አስረድተዋል። ቡድኑ በአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ባደረገበት ወቅት ከ35 ሚሊየን ብር በላይ ከመንግስት ድጋፍ መጠየቁን ያስታወሱት የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተሩ፤ መሰል የዓለም አቀፍ ውድድሮች ተሳትፎ ሲኖር ድጋፍ መጠየቅ የተለመደ መሆኑን ተናግረዋል። በመሆኑም መንግስትም እንደ ከዚህ ቀደሙ ድጋፍ ያደርጋል በሚል ፌዴሬሽኑ እየጠበቀ ይገኛል።
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ከሚመራቸው ውድድሮች መካከል አንዱ የሆነው ቻን፤ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳታፊዎችን ቁጥር አሳድጎ በ18 ብሄራዊ ቡድኖች መካከል ይከናወናል። ሃገራቱ በአምስት ምድብ የተከፈሉ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በምድብ አንድ ከአዘጋጇ አልጄሪያ፣ ሊቢያ እና ሞዛምቢክ ጋር ተደልድላለች። በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደው ይህ ውድድር በመጪው ጥር 5 -27/2015 ዓ.ም ድረስ የሚከናወን ይሆናል፡፡
ሰሜን አፍሪካዊቷ ሃገር አልጄሪያ ለውድድሩ የሚሆኑ አራት ስታዲየሞችን ያዘጋጀች ሲሆን፤ የመክፈቻው ስነስርዓትም በደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ በሚገኘውና ከ40ሺ ደጋፊዎች በላይ የመያዝ አቅም ባለው ባራኪ ስታዲየም እንደሚከናወን ታውቋል። ውድድሮቹ ከሚካሄዱባቸው ስታዲየሞች መካከል አንዱ ሚሉድ ሃደፊ ሲሆን፤ ከ40ሺ ሰው በላይ የመያዝ አቅም አለው። ቻዲድ ሃምላዊ ስታዲየም ከ22 ሺ በላይ ሰዎችን ሲቀበል፤ በሃገሪቷ በግዝፈቱ ሁለተኛ የሆነውና ‹‹ግንቦት 19/1956›› ተብሎ የሚጠራው ስታዲየም ደግሞ 56 ሰዎችን ያስተናግዳል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 17 /2015