ሰውዬው በጠና ህመሙ ሳቢያ ካልጋ ከዋለ ቆይቷል። ችግሩ ስር ሰዷልና በሀኪም ቤት በዕምነትና ሀይማኖት ስፍራዎች ሲንከራተት ከራርሟል። ቆይቶ በሽታው ከአቅም በላይ ሆነ። ውሎ አድሮም ከእጅ ያለ ገንዘብ፣ ከቤት የቆየ ጥሪት ሁሉ ተሟጠጠ፡፡
ወዲህ የታማሚው ስቃይ ፋታ አልሰጠም። ወዲያም የቤት፣ የቤተሰቡ ችግር ቀላል አልሆነም። ይህኔ አንዳንዶች ይበጃል ያሉትን መላ ዘየዱ። ሰውዬው ከቤት ውሎ ህመሙን ከሚያዳምጥ፣ እጆቹን ለእርዳታ እንዲዘረጋ፣ በሚገኘው ገንዘብም የህክምናው ወጪ እንዲሸፈን ተወሰነ።
ውሳኔው መሬት ጠብ አላለም። ሁሉም የሚገኘውን ገንዘብ እያሰበ የታማሚውን ታክሞ መዳን ተመኘ። ሀሳቡን ለመተግበር ጊዜ አልፈጀም። የሰውዬውን የቀድሞ ገጽታና አሁን ያለበትን እውነታ የሚያሳዩ ፎቶግራፎች ተዘጋጁና፣ በሰፋፊ ባነሮች ታተሙ። ጉዳዩ በዚህ ብቻ አልበቃም። ምስሎቹን ለጥፎ የሚያሳይና ታማሚውን አስተኝቶ እርዳታ የሚያሰባስብ ሚኒባስ ታክሲ ጭምር ለመከራየት ታቀደ። የታሰበው አልቀረም። ዝግጅቱ ሲጠናቀቅ በቀን ኮንትራት የሚከፈለው መኪና ቀርቦ ህመምተኛውን ተረከበ፡፡
ሰውዬው በጀርባው ተንጋሎ በስቃይ እየተንገላታ ነው። ከመኪናው አናት ከፍ ብሎ የሚሰማው ሙዚቃ ‹‹እኔነኝ ደራሽ ለወገኔ›› ይሉትን ዜማ ይደጋግማል። በየመሀሉ ሙዚቃው እየቆመ በድምጽ ማጉያ መልዕክት ይተላለፋል። መልዕክቱን ለሚሰማው ሁሉ ሀዘን ያጭራል፣ ውስጥን ይነካል። አብዛኞች ቆም ብለው ፎቶዎችን ያስተውላሉ፣ በሚያዩት እያዘኑም ያላቸውን ይሰጣሉ፣ ይረዳሉ፡፡
ቀኑን ሙሉ በስቃይ የሚውለው በሽተኛ በእርዳታ ከሚያገኘው ገንዘብ የመኪናውን ኪራይ ሰጥቶ፣ ምሽቱን ከቤት ይገባል። ማግስቱን ሲመለስም የትናንቱ ውሎ እንደነበረው ይቀጥላል። በሙዚቃው መሀልም የተለመደው ቃል ይደጋገማል፡፡
‹‹እዚህ መኪና ውስጥ የምታዩት ወንድማችን አቶ እከሌ እከሌ ይባላል። ሁለቱም ኩላሊቶቹ ከጥቅም ውጭ በመሆናቸውና ለውጭ አገር ህክምናው ይህን ያህል ገንዘብ በማስፈለጉ የእናንተን እጅ ለማየት ተገዷል፣ በመሆኑም ….
አሳዛኙና ልብ የሚነካው ንግግር በዝግታ ይቀጥላል። ፎቶውን ተመልካች፣ መልዕክቱን አድማጭ መንገደኛ ሁሉ ከታላቅ ሀዘን ጋር ከእጅ፣ ከኪሱ፣ከመሀረብ፣ ከቦርሳው የቻለውን ይሰጣል። አንዳንዶች ቀረብ ብለው በዓይናቸው የሚያዩትን ህመምተኛ ‹‹እግዜር ይማርህ፣ ያሰብከው ይሳካልህ ይሉታል። ቀኑ በተለመደው ሙዚቃና በጆሮ ገብ መልዕክት ታጅቦ እስከምሽቱ ይቀጥላል። ማግስቱም፣ እንደትናንቱ ሆኖ ያልፋል፡፡
የሰውዬው ሥቃይ አልቆመም። ህመሙ ጸንቷል፣ በሽታው ከፍቷል። በየዕለቱ ውስጡ እየደከመ፣ አካሉ እየዛለ ነው። የሚሰበሰበው ገንዘብ ለታሰበው ዓላማ የዋለ አይመስልም። ያለውን ከመጠቀም ይልቅ በየቀኑ ቦታ እየለወጡ መለመን ጣፋጭ አማራጭ ሆኗል።
ከዕለታት በአንዱ ቀን ታማሚው ስቃዩን መቋቋም ተሳነው፣ ከአልጋ ወርዶ ከመኪና መግባት ቢያቅተው ከቤት ተኝቶ ሊውል ግድ አለ። ሰዎቹ ይህን ሲያውቁ በርትቶ እንዲነሳ ወተወቱት። ፈጽሞ አልቻለም። እንዳሰቡት ሳይሆን ቀርቶ ህመሙ ቀናትን ቆጠረ ። ሰውዬው ከተኛበት አልተነሳም። አንድ ማለዳ ደግሞ ከነወዲያኛው አሸለበ፡፡
የታማሚውን የመዳን ፍላጎት ያወቁ፣ ጥረት ሩጫውን ያዩ በሞቱ አዘኑ፣ አለቀሱ ። ስቃይ ህመሙን የተረዱ ሌሎችም ሞቱን ‹‹እፎይታው ነው›› ሲሉ አሰቡ ። የሀዘን ቀናት አንድ ሁለት ተብለው ተቆጠሩ። ውሎ አድሮ ለቅስተኛው ተሸኘ ። ሀዘንተኞች ተጽናኑ ። ሟች በነበር እየተወሳ ፣በትዝታ ታወሰ፡፡
ከዕለታት በአንዱ ቀን የሟችን ፎቶና የ‹‹አድኑኝ›› መልዕክትን የያዘ ሚኒባስ በአንድ አካባቢ መታየቱ ተሰማ። ቀኑን ሙሉ ህመም ስቃዩን እየተረኩ፣ ስለህክምናው ወጪ የሚለፍፉ ሰዎች አሁንም ስራቸውን ቀጥለዋል። እሱ ሞቶ ቢቀበርም የእነሱ የገንዘብ ፍላጎት ፈጽሞ አላንቀላፋም። በየቀኑ የሚያገኙትን ጥቅም እየለቀሙ እፍታውን መካፈላቸውን ይዘዋል። ቦታ እየለወጡ፣ መረጃ እያዛቡ በሟች ስም ሲነግዱ የቆዩት ስግብግቦች ፖሊስ ደርሶባቸው በቁጥጥር ሥር እስኪውሉ በርካቶችን አታለዋል። ዕምነትና ሞራል የለሽ ሥራቸውም በእውነተኞቹ እርዳታ ፈላጊዎች ላይ ከባድ ተፅዕኖ አጥልቷል።
ይህን ጉዳይ እንደመነሻ ላውጋው እንጂ በከተማችን የሚስተዋለው መሰል ድርጊት ሀቀኛውን ከአጭበርባሪው ለመለየት የሚያዳግት ሆኗል። እርግጥ ነው ኩላሊትና ካንሰር ይሉት በሽታ ጊዜ አይሰጥም። ከስቃዩ ባለፈ ህክምናውን ለመሸፈን አቅም ሲያንስ፣ እጅ ሲያጥር ደግሞ የሰው ፊትን ማየት፣ እርዳታን መሻት ሊያስገድድ ይችላል፡፡
ጉዳዩ እንዲህ መሆኑ ላይ አይደለም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚስተዋለው በመኪና የመለመን ልማድ ለዓይን እስኪያዳግት፣ ለማመን እስኪቸግር እንደባህል ተለምዷል፣ እንደግዴታ ተቆጥሯል። አሁንም ይህን ጉዳይ ሳነሳ የተቸገሩ፤ እርዳታን የሚሹ፣ የሉም እያልኩ አይደለም። ከሚባለው በላይ በችግር ውስጥ ያሉ፣ በህመም የሚሰቃዩ ወገኖች መኖራቸው አይካድም። እንዲህ መሰሎች ባሉበት ግን ሀሰተኞቹ ተከልለው ብዙሀንን እንዳያታልሉ፣ ለእውነተኞቹም ዕንቅፋት እንዳይሆኑ ያሰጋል።
አሁን አሁን በሰፊ የፎቶግራፍ ባነሮች የሚሸፈኑ፣ በአሳዛኝ የ‹‹አድኑን ›› መልዕክቶች የሚታወቁ መኪኖች በእጅጉ በርክተዋል። የመኪኖቹን ሆድ ጠጋ ብሎ ላየውም ታማሚ ነው የሚሉትን ሰው ከነስቃዩ አስተኝተው የሚያስጎበኙ ጥቂቶች አይደሉም፡፡
ይህ ብቻም አይደለም፣ ከመንገዱ ዳርቻ ከቆመው መኪና ዙሪያ የሚታዩ ወጣቶች ባዶ ካርቶኖችን ይዘው አላፊ አግዳሚውን በልመና ያታክታሉ። እነዚህ ወጣቶች እርዳታ መጠየቃቸው አንድ ጉዳይ ሆኖ መንገደኞች እንዳይራመዱ፣ አልፈው እንዳይሄዱ የሚጠቀሙበት ስልት የሚያሸማቅቅ ነው። አንዳንዴ ወጣቶቹ የሚጠይቁትን ሰው ፍላጎት የሚጠብቁ አይሆኑም። በርቀት ያዩትን መንገደኛ አጠገባቸው እስኪደርስ ጠብቀው በልመና መድረሻ ያሳጡታል። እግረኛው የመጀመሪያዎቹን አልፎ ወደፊት ለመራመድ መንገዱ የዋዛ አይሆንለትም። ሰጥቶ ማለፍ ግዴታና ግዴታ የሆነ ያህል ከፊት ከኋላው የሚከተሉት ባለካርቶኖች ከአእምሮ በላይ ይሆኑበታል።
እርዳታ መጠየቁ በአንድ መስመር ከሁለትና ሶስት በላይ ሊያጋጥም ይችላል። በተለይ በርካቶች በሚያዘወትሩት ቦታ የተለያዩ ሰዎች ተመሳሳዩን ድርጊት ሲፈጽሙት ይስተዋላል። ባለካርቶኖቹ እግረኞቹን አጥብቆ ከመለመን ባለፈ መብራት ይዟቸው የሚቆሙ መኪኖችንም ጭምር በልመና ያስጨንቃሉ፡፡
ከፊት ከኋላ ሆነው ካርቶኖቻቸውን እየነቀነቁ፣ የሚጠይቁት ተለምዷዊ ምፅዋትም በብዙዎች ዘንድ የሚሰለች ሆኗል። አብዛኛው ተመልካች የወጣቶቹን ድርጊት በበጎ የሚያውን ያህል ጥቂት የማይባለው ደግሞ በተከፈለ ልብ ያስተውለዋል። ስለ ህመምና ስቃይ ሲባል ነፍስን መታደጉ መልካም ጉዳይ ሆኖ ከዚህ ጀርባ ሊኖር የሚችልን ማጭበርበርም ከጥርጣሬ ያኖረዋል፡፡
አዎ! ምን አልባትም ወጣቶቹ ጊዜና ጉልበታቸውን የሚከፍሉበት ተግባር ብዘዎች እንደሚያምኑት ከቅንነት የመነጨ ይሆናል። ይህን በማድረጋቸው ታማሚዎችን ታድገው፣ ለህክምናም አብቅተው በምስጋና ተመርቀው ይሆናል፡፡
እንዲህ አይነቶቹ ልበ መልካሞች ሁሌም አእምሯቸውና እጃቸው ከክፉ ድርጊቶች የጸዳ ሆኖ ይቀጥላል። በፈጸሙት በጎ ተግባርም መልካምነታቸው ሲከፍላቸው፣ ሲዘክራቸው ይኖራል፡፡ሁሌም ቢሆን እንዲህ አይነቶቹ ደጋጎች ለደግ ስራ አይቦዝኑም፡፡ለመልካም ሥራ አይዘገዩም፡፡
ከዚህ በተቃራኒ ያሉቱ ግን ሁሌም በጥርጣሬ ዓይን የሚስተዋሉ ናቸው። በየጊዜው የሚሰነዝሯቸው የምፅዋት እጆች መልካም ፍሬን አይዙም። ስራቸው ከምርቃት ይልቅ በእርግማን የተዋዛ፣ በጥቅማጥቅም የታሰረ ነው። ዓላማቸው ትርፍን ማጋበስ ነውና ምንይሉኝን አያውቁም፣ ስለሰው መኖርና መሞት ግድ የላቸውም። ስራቸው ገንዘብ እስካስገኘ ድረስ ያለውን ሞቷል፣ የሞተውን ተነስቷል ለማላት አይቸገሩም፡፡
ወዳጆቼ! በየጊዜው የምናስተውለውና የሚያጋጥመን የማጭበርበር ድርጊት መልኩን እየለወጠ በእኛ ላይ መተግበሩ ብርቃችን አልሆነም፡፡ከዚህ አንጻር በየዕለቱ ለሚያጋጥሙን አዳዲስ ድርጊቶች በርካቶቻችን እውነታውን ብንጠራጠር የሚያስፈርድ አይሆንም፡፡
ከሁሉም ግን ከነገሮች ጀርባ የሚደጋገሙትን ተለምዷዊ ድርጊቶች በሁለት ልቦና ማየት፣ መቃኘቱ አይከፋም። እዚህ ላይ ‹‹ሁለት እግር አለኝ ተብሎ ከሁለት ዛፍ አይወጣም››ይሉት አባባል ላይሰራ ይችላል። አንዳንዴ በሁለቱም እግር ከሁለት ዛፍ ለመውጣት መሞከሩም ሊያዋጣ ይችላል። ‹‹ጠርጥር ከገንፎም ውስጥ አለ ስንጥር›› እንዲሉ ነውና ፡፡
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 17 /2015