ከሳምንት በፊት የተጠናቀቀው የኳታር ዓለም ዋንጫ በርካታ አስደናቂ ጉዳዮች የታዩበት ነው። የሞሮኮ ብሄራዊ ቡድንም የአለም ዋንጫው አስደናቂ ክስተት እንደነበር አለም በሙሉ ድምጽ የሚመሰክረው ነው። በአለም ዋንጫው የእግር ኳስ ኃያል ሃገራትን ጭምር ሳይጠበቅ በማሸነፍ አራተኛ በመሆን ያጠናቀቁት የአትላስ አንበሶች፣ በአፍሪካ እግር ኳስ የመጀመሪያው የግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚ አገር በመሆን አዲስ ታሪክ ማስመዝገብ ችለዋል::
በኳታሩ አለም ዋንጫ አፍሪካዊ መሰረት ያላቸው ተጫዋቾችና አሰልጣኞች ትኩረት ስበውም ነበር:: አህጉራቸውን የወከሉት የአፍሪካ ቡድኖችን ጨምሮ ጥቁር ተጫዋቾች በአውሮፓ ቡድኖች ውስጥ በብዛት በታዩበት በዚህ አለም ዋንጫ፣ አፍሪካዊያኑ አምስት ቡድኖች ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካውያን አሰልጣኞች መመራታቸው ይታወቃል።
ከእነዚህ አሰልጣኞች መካከል ባስመዘገበው ስኬት መሰረት በቀዳሚነት የሚቀመጠው የአትላስ አንበሶቹ አለቃ ዋሊድ ሬግራጉዊ ነው:: የቀድሞው እግር ኳስ ተጫዋች የአሰልጣኝነት ህይወቱን አሃዱ ካለ 10 ዓመታትን ብቻ ያስቆጠረ ቢሆንም በዚህ ዓለም ዋንጫ ቡድኑን የማሰልጠን ዕድሉን ማግኘቱ ሃገሩን በክብር ስፍራ ከማስቀመጥ አልፎ በአህጉር አቀፍ ደረጃም የደማቅ ታሪክ ባለቤት ለመሆን ችሏል:: ውልደቱን በፈረንሳይ ያደረገው ጎልማሳው አሰልጣኝ ‹‹ሃገር ማለት ልብህ ያለባት ስፍራ ናት›› በሚለው ታዋቂ አባባል መሰረት አውሮፓዊቱን ሃገር ሳይሆን የዘር ሃረጉ የሚሳብባትን ሞሮኮን መምረጡ ለስኬት አብቅቶታል::
የአትላስ አንበሶቹ አንበሳ ተብሎ የተወደሰው የዋሊድ ሬግራጉዊ ውልደት እአአ በ1975 በፓሪስ ደቡብዊ ክፍል ኮርቢል-ኢሶኔስ ከተባለ ስፍራ ነው:: እግር ኳስን በተወለደበት አካባቢ በሚገኝ ቡድን ውስጥ መጫወት የጀመረ ሲሆን፤ የ23 ዓመት ወጣት ሳለም መቀመጫውን በፓሪስ ያደረገውን ሬሲንግ ፓሪስ የተባለ ቡድን ተቀላቀለ:: እአአ እስከ 2009 ባሉት ዓመታትም በስድስት የፈረንሳይ ክለቦች ውስጥ በተጫዋችነት አሳልፏል:: ከ2009-2012 ባሉት ዓመታት ግን ከአውሮፓ ወደ ሞሮኮ በመምጣት መግሪብ አትሌቲኮ ቴቱዋን የተባለውን ክለብ ተቀላቅሎ በተጫዋችነት አሳልፏል:: የእግር ኳስ ተጫዋችነት ዘመኑ እስኪጠናቀቅ ድረስም የሞሮኮ ብሄራዊ ቡድንን ሲያገለግል የቆየ ሲሆን፤ እአአ በ2004ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ሃገሩ የዋንጫ ተፋላሚ በነበረችበት ወቅትም ከቡድኑ ጋር ነበር::
አሰልጣኙ በተጫዋችነት ወደ ሞሮኮ መምጣቱን ተከትሎ የአሰልጣኝነት ህይወቱም በዚያው የቀጠለ ሲሆን፤ እአአ በ2012 የብሄራዊ ቡድኑ ምክትል አሰልጣኝ ሆኖ አገልግሏል:: ከሁለት ዓመት በኋላም ፋዝ ዩኒየን ስፖርት የተባለውን ክለብ ለአንድ ዓመት የማሰልጠን ዕድል በማግኘት እአአ እስከ 2019 ድረስ ቆይታ አድርጓል:: ቀጣዩን አንድ ዓመት በኳታሩ ክለብ አል ዱሃይል ካሳለፈ በኋላ፤ ወደ ሃገሩ በመመለስ የካዛብላንካውን ታዋቂ ክለብ አልዋይዳድን በማሰልጠን የሊግዋንጫን እንዲሁም የካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ተቀናቃኙን ክለብ አል ሃሊን በመርታት ለሶስተኛ ጊዜ እንዲያነሳ አድርጓል:: ይኸውም በሞሮኮ እግር ኳስ ታሪክ ዋንጫውን ያሳካ ሁለተኛው አፍሪካዊ አሰልጣኝ አድርጎታል::
ከአራት ወራት በፊትም የሞሮኮ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ በመሆን ተመረጠ፤ ስራውንም የጀመረው ከማዳጋስካር ጋር በነበራቸው የወዳጅነት ጨዋታ ነበር:: የ47 ዓመቱ አሰልጣኝ ቡድኑን በተረከበበት ወቅት በበርካታ የስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ተቃውሞን ያስተናገደ ሲሆን፤ ከዚያም አልፎ ‹‹አቮካዶ ራስ›› የሚል ቅጽል ስምም ተሰጥቶት ነበር:: ይሁንና አሰልጣኙ ዓላማውን ለማሳካት ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ራሱን አግልሎ የቆየውን አሽራፍ ሀኪሚን ቡድኑ በመመለስ፣ በተጫዋቾች መካከል ጠንካራ ቁርኝት በመፍጠር እንዲሁም በማነሳሳት ከስኬት መድረስ ችሏል::
አሰልጣኙ በዓለም ዋንጫው ቀላል የሚመስለውን ነገር ግን በርካታ ቡድኖች መተግበር ያልቻሉትን በጠንካራ መከላከልና በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ጠንካራ ቡድን ከመፍጠር አልፎ፤ ራሱን ከመጠላት ወደ ብሄራዊ ጀግናነት ቀይሯል:: ቡድኑንም በዓለም ዋንጫው ምድብ ስድስት ቀዳሚ በመሆን 16ቱን ሲቀላቀል በስፔን እና ፖርቹጋል ላይ ፍጹም የበላይነትን ወስዶ ነበር። በግማሽ ፍጻሜው ፍልሚያም የ2018 የአለም ቻምፒዮኗ ፈረንሳይን በማስጨነቅ ለደረጃ ተፎካካሪነት በማብቃት ደማቅ ታሪክ ማስመዝገብ ችሏል:: ከሃገሩ አልፎ ለአፍሪካዊያን አሰልጣኞችም አርዓያ መሆን የቻለው ይህ አሰልጣኝ በብዙዎች ዘንድ አድኖቆት እየጎረፈለትም ይገኛል::
‹ባልተጠበቀ ሁኔታ ቤልጂየም፣ ስፔን እና ፖርቹጋልን በማሸነፋችን፤ ብዙዎች ተዓምር ነው እንደሚሉ እርግጠኛ ነኝ:: ነገር ግን ይሄ ጠንክሮ የመስራት ውጤት ነው››:: የሚለው ዋሊድ ሬግራጉዊ ከዓለም ዋንጫው በፊት ቡድኑን በ3 ጨዋታዎች ላይ ብቻ ነበር መምራት የቻለው::የአፍሪካ ብሄራዊ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በርካታ የአውሮፓ አሰልጣኞችን ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ቀጥረው እንዲያሰለጥኑ አድርገዋል። ነገር ግን ዋሊድ ሬግራጉዊ የሰራውን ገድል ፈፅመው አፍሪካን እግር ኳስ አንድ እርምጃ ማራመድ አልቻሉም።
ይህ ስኬት የተመዘገበው በምዕራባዊ አሰልጣኝ ቢሆን ኖሮስ ብለን ብናስብ ደግሞ ስኬቱ የሃገሪቱ መሆኑ ይቀርና የአሰልጣኙ ማንነት ይበልጥ ትኩረት ያገኝ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። የሞሮኮ ስኬት የአፍሪካን እግር ኳስ ስነ ልቦና ከፍ ከማድረግ አኳያ ከፍተኛ ሚና ስለሚኖረው ውጤቱ ከዚህ በኋላ ለሚኖረው ተሳትፎ መጠቀም ከተቻለ ትልቅ ግብአት በመሆኑ አሰልጣኙ ለብዙዎች ምሳሌ ሆኗል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 16/2015