ኢትዮጵያ የታሪክ፣ ተፈጥሮ፣ ቅርስና የብዝሃ ባህል ባለቤት ነች። ከእነዚህ የቱሪዝም መስህብ ሀብቶቿ የምታገኘው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ግን አነስተኛ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። ከጎረቤት አገር ኬኒያ ጋር ሲነጻጸርም ኢትዮጵያ ከዘርፉ የምታገኘው ገቢ ዝቅተኛ ነው:: ለአብነትም በኢትዮጵያ ከፍተኛ ነው ተብሎ በቀዳሚነት ከተመዘገበው ከ920 ሺህ በላይ ቱሪስት ፍሰትና የ3ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ጋር ሲነፃፀር የኢትዮጵያ አፈጻጸም የኬኒያን የሩብ ዓመት አፈፃፀም እንደሚያህል መረጃዎች ያመለክታሉ። የቱሪስት ፍሰቱ በእጅጉ አነስተኛ ከመሆኑ በተጨማሪ ለጉብኝት የሚመጣውን ቱሪስት ቆይታ ለማራዘም የሚደረገው ጥረት ደካማ መሆኑ ይገለጻል።
ቱሪስቶች በኢትዮጵያ ያላቸውን ቆይታ እንዳያራዝሙ፤ ይዘው የመጡትን ገንዘብ መልሰው ወደ አገራቸው እንዲሄዱ ከሚያስገድዱ ምክንያቶች አንዱ በዘርፉ የተሰማሩት ባለሙያዎችና የአገልግሎት ጥራት ጉድለት መሆናቸው ይጠቀሳል። የሆቴል ሙያተኞች፣ የአስጎብኚዎችና ሌሎች ተያያዥ ሙያዎች ላይ የተሰማሩ አገልግሎት ሰጪዎች ብቃት(ፕሮፌሽናል) እና የአገልጋይነት ስሜት(ሆስፒታሊቲ) በሚፈለገው ደረጃ አለመሆን በችግርነት ይጠቀሳሉ።
የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎችንና መስህቦችን ጠንቅቆ አለማወቅና በመረጃ በተደገፈና ቱሪስቱን በሚስብ መልኩ ማስጎብኘት አለመቻል ቱሪስቱ የቆይታ ጊዜውን እንዳያራዝም ከሚያደርጉት ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳል:: የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ጥናትም ይህንኑ ነው ያረጋገጠው:: የቱሪዝም ኢንዱስትሪው በሚፈልገው ልክ ባለመሰራቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የቱሪስቶች ቆይታ አጭር እንደሆነና ገንዘባቸውንም ይዘው እንደሚመለሱ ጥናቱ አመላክቷል::
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በዘርፉ ላይ ለውጦች መታየት ጀምረዋል:: ዘርፉን በማነቃቃት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማሳደግ መንግስት ሰፋፊ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ እየሰራ ይገኛል።እየተከናወኑ ካሉ ተግባራትም አንዱ የሙያ ማሰልጠኛ ተቋማትን ማጠናከር እና የጥራት ደረጃቸውን ከፍ ማድረግ ነው። መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ማሰልጠኛ ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ ባለሙያዎች በንድፈ ሃሳብ የሚያገኙት እውቀትም ሆነ በተግባር የሚላበሱት ክህሎት የተሟሉ እንዲሆኑ የሚያስችል ነው።
የቱሪዝም ዘርፍ ባለሙያዎችን ለበርካታ አስርት ዓመታት በማፍራት የሚታወቀው የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ከላይ ካነሳናቸው ሀሳቦች ጋር የሚሄድ የምክክር መድረክ በቅርቡ አዘጋጅቶ ነበር። የምክክር መድረኩ በዋናነት ቱሪዝም እንዲነቃቃ፣ ጎብኚዎች ወደ አገሪቱ እንዲመጡና ከዚያም ባለፈ ቆይታቸውን ማራዘም እንዲችሉ ባለሙያውን በብቃትና በጥራት ማፍራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይም የመፍትሄ አቅጣጫ አመላክቷል። ኢንስቲትዩቱም የማሰልጠኛ ኢንስቲትዩቱን የስልጠና ጥራት ለማስጠበቅ አዲስ በተዘጋጁ የሥነምግባርና የአሰራር ሥርዓት ማኑዋሎች ላይ ትኩረቱን አድርጎ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ግብአት የሚሆኑ መረጃዎችን መሰብሰብ ችሏል::
በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ እንዳሉት፤ መንግሥት ለቱሪዝም ዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቷል፤ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን ከማስፋፋት ጎን ለጎን ዜጎች በዘርፉ በተመረጡ ሙያዎች ብቃት ያለውና የተሟላ የክህሎት ስልጠና አግኝተው፣ የኢኮኖሚው እንቅስቃሴ የሚፈጥረውን የስራ ዕድል በመጠቀም የሥራ ገበያውን እንዲቀላቀሉ ለማስቻል ከፍተኛ ጥረት በማደረግ ላይም ይገኛል:: የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ኢንዱስትሪው እንዲዘምን እና አገልግሎቱም እንዲሻሻል፣የዜጎች ዋንኛው የገቢ ምንጭ እንዲሆን፣ለወጣቶች ሰፊ የስራ እድል እንዲፈጥርላቸው፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ እንዱስትሪው የሰለጠነ፣ በቂና ብቁ የሰው ሀይል እንዲያገኝ በማድረግ ረገድ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎና የስራ ትብብር ይጠይቃል::
“አንስቲትዩቱ፣ በመንግስት የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት፣ የሚያስችለውን ተቋማዊ የአደረጃጀትና የአሰራር ማሻሻያዎች በማድረግ በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ላለፉት በርካታ ዓመታት በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ በርካታ ባለሙያዎችን ማፍራቱን ይጠቅሳሉ:: በምርምርና ማማከር መስኩም እንደዚሁ የበኩሉን አስተዋጽኦ በማበርከት አንጋፋና ስመጥር ተቋም መሆኑን ገልጸዋል::
እሳቸው እንዳሉት፤ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉ፣ ሙያን ማዕከል ያደረጉ የክህሎት ስልጠናዎችን የሚሰጡ የስልጠና ተቋማት ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ ቢሆንም፣ ከሀገሪቱ የሆቴል ኢንዱስትሪ መስፋፋት ጋር ተያይዞ አሁንም በገበያ ላይ ሰፊ የሆነ የሰለጠነ የሰው ሀይል እጥረት ጎልቶ ይስተዋላል::የስልጠና ተቋማት በርካታ ባለሙያዎችን በማሰልጠን በየጊዜው ሙያተኞችን ቢያፈሩም ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን የሰው ኃይል ማሟላት አልተቻለም::
“አሁን በዘርፉ የሚታየው የሰው ኃይል አቅርቦትና ፍላጎት ያለመጣጣም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ሲባል የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በሀገራችን የዘርፉ የልህቀት ማዕከል ሆኖ ለማገልገል በስፋት አቅዶ እየሰራ ይገኛል” ያሉት አቶ ጌታቸው፣ ኢንስቲትዩቱ የልህቀት ማዕከል ይሆናል ሲባል የላቀ ስልጠና፣ የላቀ የምርምር ሥራ እና የላቀ የማማከር አገልግሎት ይሰጣል ማለታቸው እንደሆነም ይገልፃሉ::
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ኢንስቲትዩቱ ከባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ትብብር ውጭ፣ የቱንም ያህል ቢሮጥ በዕቅድ ይዞ የተነሳውን ትልቅ ሀገራዊ ግብና ዓላማ ብቻውን ማሳካት አይችልም። ስለሆነም የሆቴልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪው፣ በሙያ ደረጃ ዝግጅት፣ በስርዓተ ስልጠና ቀረጻ፣ በትብብር ስልጠና፣ በብቃት ምዘና ሂደት፤ በጥናትና ምርምር፣ በባለሙያ ልውውጥ እና በመሳሰሉት ጉዳዩች ዙሪያ የላቀ ተሳትፎ እንዲኖረው ይፈለጋል::
የምክክር መድረኩ ያስፈለገበትን ዋናው አላማን አስመልክተው አቶ ጌታቸው እንደገለጹት፤ ተቋሙ ቀደም ሲል የጀመረውን ከኢንዱስትሪው ጋር ተቀራርቦ የመስራት ባህሉን የበለጠ በማጎልበት ወደፊት ጠንካራና ዘላቂ የስራ ቅንጅት ተፈጥሮ ውጤትን ታሳቢ ያደረጉ ስራዎችን ለመስራት፣ ብቁና በተግባር የተፈተነ የቱሪዝም ባለሙያ ለማፍራት የሚያስችል ምቹ ሁኔታን መፍጠር ነው። በመሆኑም በዘርፉ የሰው ሀይል ልማት ዙሪያ በትብብርና በመደጋገፍ ስሜት የሚከናወኑ ተግባራትን በመለየት በቀጣይ ዕቅድን መሠረት ያደረጉ ስራዎችን መስራት ይጠበቃል።
አቶ አሸናፊ ሙሉጌታ በቦሌ የአምባሳደር ሆቴል ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሆኖ እየሰራ ይገኛል:: ትምህርቱን በሆቴልና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ነው የተከታተለው። በዚሁ ሰልጥኖ በተመረቀበት ኢንስቲትዩት በተዘጋጀው መድረክ ላይ ተካፍሏል:: እኛም በስልጠና ጥራትና የትብብር ስልጠና ዙሪያ ሀሳቡን እንዲያካፍለን ጠይቀነው፤ ኢኒስቲትዩቱ በዘርፉ ልምድ ካላቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ማድረጉና ግብአት መሰብሰቡ ለስልጠና ጥራትና ብቁ ባለሙያዎች ለማፍራት ያግዛል ብሏል::
“በቱሪዝም ዘርፍ ሥርአተ ትምህርት የሚቀርፁ ባለሙያዎች እያንዳንዱን የዘርፉን ኦፕሬሽን የሚያውቁና በውስጡ ያለፉ መሆን ይኖርባቸዋል ብዬ አምናለሁ” የሚለው አቶ አሸናፊ፤ ስርዓተ ትምህርቱ በዘርፉ ልክ ከተቀረጸና ተማሪዎች የተግባርም ሆነ የፅንሰ ሃሳብ ስልጠና ከወሰዱ ገበያው ላይ ተፈላጊነታቸው እንዲጨምር ይረዳል ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል። የንድፈ ሀሳብና የተግባር ትምህርትን ያጣጣመ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑ በመጥቀስም ከኢንዱስትሪው አንቀሳቃሾች ሆቴሎች፣ ቱር ኦፕሬተሮችና መሰል ተቋማት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግም ጠቁሟል።
ኢንስቲትዩቱ የስልጠናና የቅበላ አቅሙን ለማሳደግ ሪፎርም እያካሄደ መሆኑ የሚያበረታታ ነው የሚለው አቶ አሸናፊ፣ ስኬታማ ሪፎርም ለማካሄድም የኢንስቲትዩቱን ምሩቃን ቀጣሪ ከሆኑ የሆቴል ፣ የቱር ኦፕሬተርና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ጋር ምክክር ማካሄዱን አድንቋል። ከኢንስቲትዩቱ ተመርቀው ወደ ስራ የሚሰማሩ ሰልጣኞች ያሉባቸው ክፍተቶች፣ መጨመር ያለባቸውና ተገቢ አይደሉም ያሏቸውን ኮርሶች እንዲሁም ለተግባራዊ ትምህርት እና በቋንቋ ብቃት ዙሪያ ሰፋ ያሉ ሃሳቦችን አንስቷል።
ከመድረኩ የተነሱ ሀሳቦችንም በመውሰድ ወደ ተግባር እንደሚለውጡ ተስፋ እንደሚያደርግ የተናገረው ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፣ አዲስ በሃላፊነት የተሾሙትን የኢንስቲትዩቱ የስራ ኃላፊዎች የትምህርት ተቋሙን ለመለወጥ እያከናወኑ ያሉት ተግባራት የሚያበረታታ መሆኑንም ጠቁሟል።
ኢንስቲትዩቱ እንዲህ ዓይነት መድረኮችን በማዘጋጀት ግብዐት መውሰዱ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ዕድገት ጉልህ ሚና እንዳለው አንዳንድ የመድረኩ ተሳታፊዎችም ገልፀዋል:: በምክክር መድረኩ የተሳተፉ አብዛኞቹ ተሳታፊዎች ከኢንስቲትዩቱ የተመረቁና በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ኃላፊ ሆነው እየሰሩ ያሉ መሆናቸውንም ሀሳባቸውን ከሰጡት ለመረዳት ችለናል:: ይህም ኢንስቲትዩቱ ባለሙያዎችን በማፍራት በዘርፉ ያለው ሚና የላቀ መሆኑን ያስገነዝባል::
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ይህንን የምክክር መድረክ ከማዘጋጀቱና ከኢንዱስትሪው አንቀሳቃሾች ጋር ምክክር ከማድረጉ አስቀድሞ የስልጠና ጥራትን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ የተዘጋጁ አዳዲስ የአሰልጣኞችና የሰልጣኞች የሥነምግባር ማኑዋል እና የሬጅስትራር አሰራር ስርዓት ላይ ከአሰልጣኞች ጋር ውይይት አካሂዷል::
የአሰራር ማንዋሎቹ ተቋሙ በዘርፉ የመሪነት ሚናውን በመወጣት ምሳሌ እንዲሆን የሚያስችሉ መሆናቸውን የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አባተ ይገልጻሉ:: በተለይም አሰልጣኞች ውጫዊና ውስጣዊ ሥነ ምግባርን በመላበስ በተቋሙ ውስጥ ለተማሪዎቻቸው ጥሩ ምሳሌ በመሆን፣ በሀገር ደረጃ ብቃት ያላቸው የቱሪዝም እና የሆቴል ባለሙያዎችን ለማፍራት እንደሚያግዝ አስረድተዋል:: አዲስ የሬጅስትራር አሰራር ሥርዓት መዘጋጀቱ ትክክለኛ የሰልጣኖች መረጃ እንዲኖር ለማድረግ፣ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ኢንዲሁም ለሚከሰቱ ችግሮች ተጠያቂነትን ለማስፈን ያስችላልም ሲሉ አብራርተዋል::
ቱሪዝም በግሉም ሆነ በመንግስት አካላት ውስጥ በሚገኙ በርካታ ባለድርሻ አካላት ካልተደገፈ ውጤታማ እንደማይሆን የተለያዩ ተሞክሮዎች ያሳያሉ:: በዋናነት ቅንጅት፣ ተግባቦትና ምክክርን የሚሻ ልዩ ልዩ ተቋማትን የሚያሳትፍም መሆን ይጠበቅበታል። በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ጀምሮ በመስኩ የተሰማሩ ልዩ ልዩ አካላትን በማካተት ሁሉን አቀፍ የቱሪዝም እድገት ለማምጣት ምሁራኑ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ልዩ ልዩ ሳይንሳዊ ምርምሮች ላይ የድርሻቸውን ማበርከት ይጠበቅባቸዋል።
የሆቴል፣ የቱርስት ኦፕሬተርና መሰል ኢንዱሰትሪውን የሚያንቀሳቅሱ ተቋማት የተማሩና ለቱሪዝሙ እድገት እርሾ የሆኑ ሙያዎች ላይ እውቀት ያላቸውን ከማሳተፍ ይልቅ በዘመድ አሊያም በሌሎች ጥቅማጥቅሞች ማሳተፍን ምርጫቸው ያደርጋሉ። በእርግጥ ይህ አሰራር በግሉም ሆነ በመንግስት የቱሪዝም መስሪያ ቤቶች ውስጥ የሚታይ መሆኑን የሚያሳዩ በርካታ መረጃዎችን መጥቀስ ይቻላል።
የቱሪዝምን ፅንሰ ሃሳብ የሚያስጨብጡ እንዲሁም የኢትዮጵያን ሃብቶች ለማልማትና ከዚያ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችል እውቀት የሚያደረጁ የትምህርት ተቋማት እየበዙና በየደረጃው እየተከፈቱ ሲመጡ ከፍተኛ በዘርፉ የተማረ የሰው ሃብት ፍሰት እንደሚመጣ ይጠበቃል። ይህን ተከትሎ ከባለድርሻ አካላት ውይይት በተካሄደ ቁጥር የሚነሳው “የሙያና ፕሮሚካፌሽናሊዝም” ችግር እየተቀረፈ እንደሚመጣ መገመት አያዳግትም።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 16/2015