ግጭት የትም አለ። ከአባባላችን ጀምሮ ”እንኳን ሰውና ሰው፣ እግርና እግርም ይጋጫል” ይባላል:: ችግሩ ያለው፣ የተፈጠረውን ግጭት ማስተናገዱ ላይ ነውና ወደ’ዛው እንሂድ።
”ኢትዮጵያ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎችን ከዘመናዊው ሕግ ጋር አብራ እንድታስኬድ የሰላም አባቶች መከሩ።” የሚል ዜና ከመገናኛ ብዙኃን (ለምሳሌ፣ ኢዜአ፤ ጥር 5/2012 ዓ.ም) መስማታችን ለብዙዎቻችን እንግዳ አይደለም። ጋሞ ጎፋ ዞን (ጋሞ ብሄረሰብ) ከቤተሰብ ጀምሮ ለሚፈጠር ጸብ የራሱ የሆነ ባህላዊ የግጭት አፈታት (በቤተሰብ ውስጥ የሚፈጠር ጸብ የሚፈታበት “ኡሩሻ” የተሰኘ የእርቅ) ስርአት አለው። ይህ ደግሞ በተግባርም የታየና አገርና ሀብትን ያዳነ ስለ ሆነ ብዙ መነጋገር ወይም ማብራሪያ የሚያስፈልገው ጉዳይ አይደለም።
በዞኑ ወይም በብሄረሰቡ ከቤተሰብ፣ ከፍ ሲልም ሰዎች ወደ ግጭት እየገቡ አይቶ ማለፍ በአካባቢው አጠራር “ጎሜ” ወይንም ሃጢያት በመሆኑ የተወገዘ ነው። ተጋጭተው ከተገኙም፣ በተጋጪዎች መካከል ገብቶ ለምለም ሳር፣ ኩታ ወይንም ጋቢ፣ የእንስሳት ቆዳና ሌሎች የጸብ ማብረጃ ተብለው የሚታወቁትን በመያዝ ፀቡ እንዲበርድ ይደረጋል።
በባህሉ መሰረት ጸብን ለማብረድ እድሜ የማይጠይቅ ሲሆን፤ ተጋጭዎች ወደ ግጭት ሊያመሩ የነበሩ ግለሰቦች ተረጋግተው “ዱቡሻ” ወደ ተሰኘ የግጭት አፈታት ስርአት በመሄድ ሰላምና እርቅ እንዲወርድ ይደረጋል። ግጭት ወደ ሁከት ከማምራቱ በፊት የመከላከል ተግባር በዱብሻ የተሰየሙ አባቶች ተግባር ሲሆን፤ በስርአቱ የሰውን ንብረት መዝረፍ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ሰውን መግድል፣ ጸብ ማጫር የተወገዘ ነው። ከላይ በጠቀስነው ቀን ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በአሁኑ ወቅትም የጋሞ የሰላም አባት በመሆን በዱቡሻ የእርቅ ስርአት ውስጥ እያገለገሉና ከአባቶች የወረሱትን ባህል ለአዲሱ ትውልድ እያስተማሩ የሚገኙት የእድሜ ባለጸጋው አቶ ዘለቀ አርጃሞ ከልጅነታቸው ጀምሮ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በዚህ ባህላዊ የእርቅ ስርአት መፍታት እንጂ ወደ ዘመናዊ ሕግ ተቋማት ሄደው እንደማያቁ ተናግረዋል።
‹‹የጋሞ ሽማግሌዎችም ሆኑ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን እንደየአካባቢው ባህልና ወግ መሰል የግጭት አፈታት ዘዴዎች ያላቸው በመሆኑ መንግስት ከዘመናዊ የህግ ስርአት ጋር በማዋሃድ ቢተገብረው የሚፈጠሩ ችግሮችን ከጅምሩ መፍታት ይቻላል የሚል እምነት አላቸው።” የሚል አስተያየትን የሚሰነዝሩት ከዚህ አይነቱ ቱባ እሴት በመነሳት መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል።
የዞኑ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ሃላፊ አቶ ዘነበ በየነም ”የጋሞ ባህላዊ የእርቅ ስርአት በአካባቢው ጸብን የማብረድ ሚናው የጎላ ነው” በማለት ነው የአቶ ተስፋዬን አስተያየት የሚያፀኑት። ባህሉን ለሌሎች አካባቢዎችና ለአዲሱ ትውልድ ለማስተዋወቅ የህትመትና የተለያዩ መገናኛ ዘዴዎችን እየተጠቀሙ መሆኑንና ሌሎችም ይህንኑ ልምድ እንዲጠቀሙ መክረዋል።
ኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ከራሷ አልፋ ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች ሰላምን ለማውረድ የሚጠቅሙ በርካታ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች አሏት:: በመሆኑም ይህ የሚመለከታቸው አካላት ህግ አውጪዎችን ጨምሮ ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርአት እንዲዳብር እንዲሁም ከዘመናዊ የህግ ስርአት ጋር እንዲቀናጅ ማድረግ ላይ መስራት አለባቸው::
ኢትዮጵያ የተለያዩ የግጭት አፈታት ብልሀቶች ያሏትና ህብረትን፣ አንድነትን፣ ወንድማማችነትን፣ መቀራረብን የሚሰብኩ እሴቶች ባለቤት ሆና ግጭት ሊበረታባት እንደማይገባ በቁጭት የተናገሩት አቶ ተስፋዬ (በ2011 ዓ.ም በአርባ ምንጭ ሊከሰት የነበረውን ግጭት እንዲረግብ ካደረጉ የጋሞ የሰላም አባቶች መካከል አንዱ) ፤ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች በማህበረሰቡ ዘንድ ካላቸው ተቀባይነት አንጻር እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን የመቀነስ አቅም አላቸው። በመሆኑም፣ በእነዚህ ባህላዊ የግጭት አፈታትና ባህላዊ እሴቶች ውስጥ ያደገ ወጣት የአባቶችን ምክር እንዲሰማ ጠይቀው መንግስትም እሴቱን እንዲጠቀምበት ይመክራሉ።
ወደ ጉራጌ እንሂድ። የሪፖርተሩ ሲሳይ ዓለሙ ”የጉራጌዎች ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥነ ሥርዓት” በሚል ርእስ ለንባብ አብቅተውት በነበረ ጽሑፍ ላይ አንድን አዛውንት ”ድሮ እናንተ እንደኛ ወጣት በነበራችሁ ጊዜ አሁን በአገራችን እንደተከሰተው ዓይነት ምክንያቱ እንኳን ይህ ነው በማይባል ፀብ፣ ክርክር፣ ዘረኝነት፣ ግድያ ነበረ እንዴ? ብዬ ጠየቅኳቸው::” ይላሉ:: ቀጥለውም ‹‹ሰው ለሰው ይቅርና እግርና እግር ይጋጭ የለም፣ ፀብማ ነበረ’ አሉኝ:: ’ግን እውነት እልሃለሁ ልጄ እንደ አሁኑ ዓይነት የዘር፣ የብሔርና የጎሳ ግጭት ግን ዓይቼም፤ ሰምቼም አላውቅም። […] ልጄ አንዴ ሆኗል፤ እናንተ ወጣቶች በየአካባቢያችሁ ያለውን የግጭት አፈታትና የዕርቅ ሥነስርዓት ላይ አተኩራችሁ ልትሠሩ ይገባል:: አገራችሁን ኢትዮጵያ ጠብቋት’ ብለውኝ በነበርኩበት ጥለውኝ ሄዱ::” በማለት አስነብበው ነበር።
ይህንን እዚህ መጥቀሳችን ብዙ ነገርን የተሸከመ ሀሳብ ስለቀረበበት ነው:: ዘመንም አንዱ በዚሁ እቅፍ ውስጥ የሚገኝ ፅንሰ ሀሳብ ነው። ጸሐፊው ”ጉራጌዎች እያንዳንዱ ተግባራቸው፣ ወግና ልማዳቸው፣ ሐዘንም ደስታቸው፣ የግጭት አፈታታቸው፣ የአረማመድና የአበላል ሥነ ሥርዓታቸው የጉራጌ ሽማግሌዎች ተሰባስበው አርቅቀው፣ ቃለ መሃላ በፈጸሙባቸው የጆካ ቂጫ፣ ሴራና የጎርደነ ባህላዊ መተዳደሪያቸው ላይ ባስቀመጡት ሕግና ደንብ መሠረት ነው የሚመሩት:: መላው ቤተ ጉራጌ የእነዚህ ደንብና ሕጎች ያለማቅማማት ተገዥ ነው::” በማለት ያሰፈሩትም ለጥቅስ የሚበቃ ብቻ ሳይሆን አስተማሪም ነውና እዚህ ሊጠቀስ የግድ ይሆናል።
ጸሐፊ ”ጥሉን የፈጠሩ ቡድኖች ወይም ግለሰቦች ጉዳያቸውን በቀነ ቀጠሮው መሠረት ሽማግሌዎቹ በዝርዝር ተመልክተው እስኪፈቱት ድረስ በመሃል ምንም ዓይነት የጥላቻ ንግግር እንዳያካሄዱ፣ ጥልም ሆነ ግጭት እንዳያስነሱ ሽማግሌዎቹ ከበድ ካለ ማስጠንቀቂያ ጋር ‹‹ኸተራት›› ይሰጣሉ::” ካሉን በኋላም ”ኸተራት ማለት ጉዳዩን በሽማግሌዎች እስኪታይ ድረስ በመሀል ምንም ዓይነት ጥልም ሆነ ዘለፋ እንዳይካሄድ የሚደነግግ ባህላዊ ሕግ ነው:: ይህን ኸተራት የጣሰ አካል ከፍተኛ የሆነ ቅጣት ይወሰንበታል:: ቅጣቱ ከማንኛውም ዓይነት የማኅበራዊ ጉዳዮች እስከ ማገድና ማግለል ሊደርስ ይችላል:: ለዚህም ነው ጉራጌዎች ለኸተራት ልዩ ሥፍራ የሚሰጡት::” በማለት የጉራጌን ባህላዊ ግጭት አፈታት ዘመናዊነት ይነግሩናል።
ውሳኔ አሰጣጥን በተመለከተም ”ሽማግሌዎቹ የጥፋት ብይኑን ለማስተላለፍ እውነት እንደ ፀሐይ ትብራ፤ እንደ ጨረቃም ትድመቅ በማለት የመክፈቻ ንግግራቸውን ካካሄዱ በኋላ ጥፋቱን ማን ጋር እንደሆነ በአንድ ድምፅ ይወስናሉ:: ለደቂቃዎች ከቦታው ገለል እንዲሉ የተደረጉ ባለጉዳዮች እንዲቀርቡ ከተደረገ በኋላ ከታላቅ ተግሳጽና ምክር ጋር ለአጥፊው ወገን የጥፋቱን ሁኔታ በዝርዝር በተመደቡ ሽማግሌዎች አማካይነት ይነገረዋል::
በውሳኔው አጥፊው ወገን ቅሬታም ሆነ አስተያየት እንዲያቀርብ ዕድል ይመቻችለታል:: ያቀረበው ቅሬታ አሳማኝ ከሆነ ጉዳዩን በድጋሚ እንዲታይለት ይደረጋል:: ካልሆነም ደግሞ አጥፊው ወገን ዳግም እንደዚህ ዓይነት ጥል ያላግባብ በሠፈሩና ከማንኛውም ዓይነት ግለሰብ ጋር እንዳይፈጠር ከማስጠንቀቂያ ጋር ቅጣቱን እንዲከፍል ይደረጋል:: እንደየ ሁኔታው ሽማግሌዎቹ የቅጣት ማቅለያ ካለ ያደርጋሉ:: በቅጣት የሚገኝ ገንዘብም ሆነ ማንኛውንም ዓይነት ንብረት ሽማግሌዎቹ በሚወስኑት ውሳኔ መሠረት ዕድራቸው ወይም የጋራ በሆኑ የማኅበራዊ ጉዳዮቻቸው ላይ እንዲውል ይደረጋል::” ሲሉ በጉራጌ ባህላዊ-ዘመናዊነት ላይ እንድንደመም ያደርጉናልና እናመሰግናቸዋለን።
”በማንኛውም ዓይነት፣ በጥልም ሆነ ባለመግባባት ወቅት የሰው ነፍስ ከጠፋ ጉራጌዎች እስከ ሰባት ዓመት የሚውስድ ባህላዊ የዕርቅ ሥነሥርዓት አላቸው::” ሲሉም ፅሁፋቸውን ይደመድማሉ። (ሌሎችንም በተመለከተ አብዱልፈታህ አብደላ ያዘጋጁትን፣ ”የኢትዮጵያ የሀገር በቀል የአስተዳደር፣ የህግና የፍትህ ሥርአቶች ማውጫ፤ ቅፅ 1”ን መመልከት ይቻላል። በተለይም በ”ክፍል አራት” ስር የሚገኘውን ”በደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚገኙ …” በሚል ርእስ ስር የተካተተውን ማየቱ ጠቃሚ ይሆናል።) ሌላውና ባህላዊ እሴቱ ወደ ሆነው “አፊኒ” እናምራ።
ባለሙያዎቹ ”ሀገር በቀል ዕውቀቶች ለዘመነው ማኅበረሰብ ምሰሶዎች ናቸው።” እንደሚሉት ሁሉ፣ የአማርኛ ትርጉሙ “ሰማችሁ ወይ” ማለት የሆነው “አፊኒ” የሲዳማ ህዝብ እንደማኅበረሰብና እንደ ትውልድ ለዘመናት ጠብቆና ተንከባክቦ ያቆየው የራሱ የሆነ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴ ነው:: የፎክሎር (የባህል ጥናት) ባለሙያው ሙሉነህ ካሳ የአካባቢው ተወላጅ አዛውንት የሆኑትን አቶ መብራቱ ማቲዎስ አፊኒን ጠቅሶ እንደሚነግረን ከሆነ በሲዳማ ባህል ሰዎች ሲናገሩ “አፊኒ” ሳይባል ጣልቃ አይገባም። በሌላ መልኩ አንድ የተበደለ ሰው ማንኛውም አይነት እርምጃ ከመወሰዱ በፊት በአጠገቡ ላሉት ወይም ለታላላቆቹ “አፊኒ” በማለት ማሳወቅ ባህላዊ ግዴታው ነው። ይህንን ሳያደርግ በግብታዊነት እርምጃ የወሰደ እንደሆነ ቅጣት ይጣልበታል። አጥፊው ቅጣቱ በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት እንዲያጣ ስለሚያደርገው ከባድ ይሆንበታል:: ከቅጣቶቹ ውስጥ እድር፣ እቁብ ወይም ሌሎች ማኅበራዊ ተሳትፎዎች ላይ ያለውን ሥልጣንና መብት እንዲያጣ፣ እንዳይሸጥ እና እንዳይገበይ፣ ልጆቹን እንዳይድር የሚከለክሉ ሊሆኑ ይችላሉ::
አፊኒ እውነትን ከማፈላለግና ከፍትሕ አሰጣጥ ጋር በእጅጉ ይተሳሰራል። እውነትን በማጣራትና በማረጋገጥ ወደ’ሚቀጥለው እርምጃ ለመራመድ አፊኒ ወሳኝ መንገድ ነው። ይህም የሚሆነው አፊኒ በጉዳዩ ላይ እውቀት ያለው ማንኛውም ሰው መረጃ እንዲሰጥ ሰፊ እድል ስለሚሰጥ ነው። በመሬት፣ በድንበር፣ በትዳር፣ ነፍስ በማጥፋት፣ በጠለፋ፣ የሰው ሀቅ በመብላት፣… ስሞታ የቀረበባቸው ጉዳዮች ወደ ሕግ ከማምራታቸው በፊት በሲዳማ ባህል በአፊኒ ስርዓት ይዳኛሉ።
በማኅበረሰቡ ዘንድ ግጭቶች በአፊኒ የመፈታት እድላቸው ከፍ ያለ ነው:: … አፊኒ በአንድ እና በሁለት ሰዎች መካከል ውሳኔ አይሰጥም። አራት እና አምስት ከዚያም በላይ በሆኑ ሰዎች አማካኝነት ይከወናል። አፊኒ በጉዱማሌ (ጉዱማሌ ቀጥተኛ የአማርኛ ትርጉሙ “አደባባይ” ማለት ሲሆን፤ የፍቼ ጫምባላላንና የዳኝነት ስነ-ስርአትን ጨምሮ ሌሎችም ማኅበራዊ ጉዳዮች ይከናወኑበታል::) እና መሰል ትልቅ የዋርካ ጥላ የሚገኝባቸው የሸንጎ አውዶች ላይ ይከወን እንጂ በዕለት-ተእለት መስተጋብር ውስጥ ሰዎች ሲጋጩ እዚያው በተጋጩበት ቦታ ላይ አስታራቂዎች ደርሰው ቦታ ሳይመርጡ በአፊኒ ስርዓት መሰረት ግጭቱን ሊፈቱ ይችላሉ” ሲልም ያብራራልናል።
”በአፊኒ ስርዓት መሠረት ሽማግሌዎች ቁጭ ብለው “halaale” (“ሀላሌ” ሀገር በቀል እውቀትን በመመርኮዝ በሸንጎ አውዶች ላይ ጭምር እውነትን ይዞ በመቅረብ ሃቅን ለባለሀቁ የመፍረድ ሂደት ሲሆን፤ በሲዳማ ብሄር ዘንድ ፈጣሪ ነው ተብሎም ይታመናል። “hola halaale” የሚባል የሚታመን መርህም አላቸው። ይህም (እግዚኦ ለእውነት) እንደማለት ነው።”) ስራ ይሰራሉ።” ሲልም ያክላል።
የጌዴኦን ”ኦዳ ያዓ ሶንጎ” ባህላዊ ሸንጎንም ከዚሁ ጋር አያይዞ ማየት ይቻላል። በግለሰቦች ወይም በቡድኖች መካከል ግጭት ቢፈጠር፤ ተጎጂው አካል አጠገቡ ላሉ ሰዎች አፊኒ (ሰማችሁ ወይ) መበደሌን ብሎ ስሞታውን ያሰማል። አፊኒ ከተባለ በኋላ ግጭት ይረግባል። ወቃሽ እና ተወቃሽን የመለየት እንዲሁም ችግሮችን የመፍታት ስራ ነው የሚሰራው። በየፍርድ ቤቱ ያሉ መጉላላቶችን፣ ጊዜ እና ወጪን ይቆጥባል፣ ማኅበራዊ ትስስርን ያጎለብታል። ትልልቅ ግጭቶች በሚኖሩበት ጊዜ በአፊኒ ውስጥ “ቆሬ” (ነገርን ለነገ ማሳደር ወይም ጉዳዩ ጀርባው ይጠና እንደማለት) የሚባል ስርአት አለ። ተበዳይን ”ሄደህ ከልጆችህ ከቤተዘመዶችህ መረጃ አሰባስበህ ቅረብ” የሚባልበት መሆኑን የእሴቱ ባለ ቤቶች ይናገራሉ።
“ለምሳሌ አንድ የሰውን ንብረት የሰረቀ ግለሰብ መስረቁን ሽማግሌዎች ተሰብስበው በሀላሌ መርህ መሰረት እንዲያምን ይጠየቃል። አላምን ካለ “hola halaale” (እግዚኦ ለእውነት) ብለው እውነቱን ለፈጣሪ ትተው ይለያያሉ። ይህም ሽማግሌዎቹ እውነታውን ለፈጣሪ በመተዋቸው የተበላው የሰው ሀቅ መቅሰፍትን ይዞ ይመጣል ተብሎ ይታመናል። ለዚህም ነው የሲዳማ ማኅበረሰብ መቅሰፍት ከመምጣቱ በፊት የሀላሌ መርህ ባህላዊ እሴትን የእለተ እለት የህይወት መስተጋብሩ ያደረገው” ሲልም የክልሉን ባህል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ጠቅሶ ያብራራል።
”ለሲዳማ ከሀላሌ በላይ መሀላ የለም። ሀላሌ ከ“ማጋኖ” (ፈጣሪ) ጋር የሚያገናኝ ድልድይ” ነው። ”የሀላሌን መርህ የሚጥስ ማንኛውም የብሄረሰቡ ተወላጅ በራሱ ላይም ሆነ ከእርሱ በሚፈጠረው ተከታይ ትውልድ ላይ መልካም ነገር አይገጥመውም የሚል ፅኑ እምነት በማኅበረሰቡ ዘንድ አለ” ሲልም ሀሳቡን ያስረግጣል።
በባሌ ዞን የተደራጁ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ለህብረተሰቡ አማራጭ የፍትህ ተቋም ሆነው እያገለገሉ እንደሚገኙ፤ የዞኑ የባህላዊ ፍርድ ቤቶች የሶስት ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ በሮቤ ከተማ በህዳር 8 ቀን 2015 ውይይት መካሄዱ፤ በዞኑ ከ200 በሚበልጡ ቀበሌዎች የተደራጁት ባህላዊ ፍርድ ቤቶች በህብረተሰቡ መካከል የሚያጋጥሙ አለመግባባቶችን በቅርበት በመፍታት አማራጭ የፍትህ ተቋም ሆነው እያገለገሉ እንደሚገኙ ኢዜአ፣ ህዳር 9 ቀን 2015 ይዞት በወጣው ዜና አመላክቷል::
በዚሁ ሥራ ላይ ባህላዊ ፍርድቤቶቹ ተቋማቱ ህብረተሰቡ በማህበራዊ መስተጋብር የሚያገጥሙትን አለመግባባቶች ወደ መደበኛ ፍርድ ቤቶች በመውሰድ ያወጣ የነበረውን ገንዘብ፣ ጊዜና ጉልበት ለልማት ስራው እንዲያውል እያስቻሉት መሆናቸው ፤ በመደበኛ ፍርድ ቤቶች ላይ ይደርስ የነበረውን የሥራ ጫና በማቃለል ለፍትህ ስርዓቱ መሻሻልም የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙም ጠቅሷል::
ባህላዊ ፍርድ ቤቶቹ ባለፉት ሶስት ወራት ወደ መደበኛው ፍርድ ቤት ይመጡ የነበሩ ከ7ሺህ በላይ የክስ መዝገቦችን በሽምግልና መፍትሄ እንዲያኙ ማድረጋቸው፤ በህብረተሰቡ መካከልም መቀራረብን እያጎለበቱ እንደሆነ፤ እየተቀዛቀዘ የነበረውን አገር በቀል የግጭት አፈታት ስርዓት ተቋማዊ በሆነ መልኩ እንዲተገበር እድል መፍጠራቸውንም አውስቷል:: (በኦሮሚያ ክልል ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች በተጨማሪ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች እንዲቋቋሙ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 240/2013 ጨፌ ኦሮሚያ በማጽደቅ ሥራ ማሥጀመሩ ይታወሳል::) ከዚህ ሁሉ የምንረዳው አቢይ ጉዳይ ቢኖር ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርአቶቻችን ተጠናክረው መቀጠል፤ ተቋማዊ በሆነ መልኩም እንደገና መመስረት ያለባቸው መሆናቸውን ሲሆን፤ ይህንን ልምድ ሁሉም ክልሎች ሊወስዱት፤ ከገባንበትም አዘቅት እንወጣ ዘንድ ስራ ላይ ሊያውሉት ይገባል እንላለን።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 14/2015