በተለምዶ ‹‹የታኅሳስ ግርግር›› እየተባለ ይጠራል። ይህ የታኅሳስ ግርግር ከ62 ዓመታት በፊት በወንድማማቾቹ ብርጋዴር ጀኔራል መንግሥቱ ንዋይ እና ገርማሜ ንዋይ በቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ መንግሥት ላይ የተደረገ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ነው።
በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን በዚህ ሳምንት ከታኅሳስ 4 ቀን ጀምሮ በተከታታይ እስከ ታኅሳስ 8 ቀን 1953 ዓ.ም የተደረጉትን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች እናስታውሳለን። በመጀመሪያ ክስተቶችን እናስቀምጥ።
ታኅሳስ 4 ቀን በወንድማማቾቹ መንግሥቱ ንዋይ እና ገርማሜ ንዋይ የተጠነሰሰው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተጀመረ። በነጋታው ታኅሳስ 5 የተሞከረው መፈንቅለ መንግሥት ዓላማውን ይፋ አደረገ። አሁንም በነጋታው ታኅሳስ 6 መፈንቅለ መንግሥቱን የሚቃረነው ወገን ውጊያ ጀመረ። ታኅሳስ 7 የመፈንቅለ መንግሥት ሞካሪዎቹ ኃይል እየተዳከመ በአንጻሩ ደግሞ የአክሻፊዎቹ ኃይል እያየለ ሄደ። ታኅሳስ 8 የመፈንቅለ መንግሥት ሞካሪዎቹ ኃይል ተደምስሶ፤ ንጉሠ ነገሥቱም ከብራዚል ተመልሰው በአስመራ በኩል አዲስ አበባ ገቡ።
የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847-1983›› በሚለው መጽሐፋቸው እንዳሰፈሩት፤ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ባይሳካም በፖለቲካው ተቃውሞ ግን ወሳኝ ሚና ተጫውቷል። የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራውን አድራጊ ወንድማማቾችም ወታደራዊውን እና ሲቪሉን የሚወክሉ ናቸው።
በወንድማማቾቹ ብርጋዴር ጀኔራል መንግሥቱ ንዋይና ገርማሜ ንዋይ የተመራው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ለኢትዮጵያ የተሻለ የአስተዳደር ስርዓት ለማምጣት ታልሞ የተደረገ ነበር።
በታኅሳስ ወር መጀመሪያ 1953 ዓ.ም ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ለጉብኝት ወደ ብራዚል መሄዳቸውን ተከትሎ፣ የክብር ዘበኛ ጦር አዛዡ ብርጋዲዬር ጀኔራል መንግሥቱ ንዋይ የመፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ የመጀመሪያና የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በዊስኮንሲን ዩኒቨርሲቲ እና በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ከተማሩት ታናሽ ወንድማቸው ገርማሜ ነዋይ ጋር መከሩ።
ብርጋዴር ጀኔራል መንግሥቱ ንዋይ የመፈንቅለ መንግሥት ሴራውን ሀሳብ የጠነሰሱት ከወቅቱ የፀጥታና ደህንነት ክፍል ኃላፊው ኮሎኔል ወርቅነህ ገበየሁ እና ከፖሊስ ኃይል አዛዡ ከብርጋዲዬር ጀኔራል ጽጌ ዲቡ ጋር ሆነው ነበር። ታኅሳሥ 5 ቀን 1953 ዓ.ም የወንድማማቾቹ ቡድን ዓላውን ለሕዝብ ይፋ አደረገ።
የተሻለ ማኅበረ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ስሪት ያላትን አገር እውን ለማድረግ ፍላጎትና ዓላማ እንዳለው ገለፀ። ‹‹ለውጥ ፈላጊ ናቸው›› የሚባሉት ልዑል ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ በጠቅላይ ሚኒስትርነት መሾማቸውንና አልጋ ወራሹን አስፋ ወሰን ኃይለሥላሴንም በማስማማት (አስገድደው ነው የሚሉም አሉ) መንግሥት በቆረጠላቸው ደመወዝ እየተዳደሩ ለሕገ መንግሥት የሚገዙ ንጉሥ ሆነው እንደሚያገለግሉ እራሳቸው ለሕዝቡ በራዲዮ እንዲያስተላልፉ አደረገ።
በቀጣዩ ቀን በወንድማማቾቹ የተጠነሰሰውን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የሚቃረነው እና የንጉሡ ታማኝ የሆነው የእነ ጄኔራል መርዕድ መንገሻ ኃይል ሙከራውን ለማክሸፍ ዝግጅቱን ጨረሰ። በአየር እና በታንክ ጭምር የተፋፋመ ውጊያ ሲጀምር፤ ብርጋዴር ጀኔራል መንግሥቱ ንዋይ መምሪያ ክፍላቸውን ወደ ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት (የአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ) አዛወሩ።
በቀጣዮቹ ቀናት የምድር ጦሩንና የአየር ኃይሉን ያላሳተፈው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እየተዳከመ፤ በአንጻሩ ደግሞ የንጉሱ ታማኞች እያደር እየበረቱ መሄዳቸውን የተገነዘቡት እነ ብርጋዴር ጀኔራል መንግሥቱ ንዋይ በቁጥጥራቸው ስር የነበሩትን መሳፍንት፣ መኳንንት፣ ሚኒስትሮችንና መኮንኖችን ወደ ሌላ ቦታ አዛውረው፣ አልጋወራሹንና አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ደግሞ ለብቻቸው እንዲጠበቁ አደረጉ።
ጄኔራል ጽጌ ዲቡ ወዲያው ከተቃራኒ ወገን (ከንጉሡ ታማኞች ማለት ነው) በተተኮሰ ጥይት ሲገደሉ፣ እነ ብርጋዴር ጄነራል መንግሥቱ ደግሞ የያዟቸውን እስረኞት ረሽነው ለማምለጥ ወስነው፤ ራስ አበበ አረጋይ፣ ሜጄር ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ፣ ራስ ስዩም መንገሻ፣ አቶ መኮንን ሀብተወልድ፣ አባ ሐና ጅማና ሌሎች የንጉሰ ነገሥቱ ባለስልጣናት ተረሽነው ሞቱ።
በሁለቱ ወገኖች መካከል በተደረገ የተኩስ ልውውጥም የሞቱ ባለስልጣናት ነበሩ። ከእነዚህም መካከል የስመ ጥሩው አርበኛ የኃይለማርያም ማሞ ልጅ እና የንጉሠ ነገሥቱ የልጅ ልጅ የልዕልት ሶፊያ ደስታ ባል የሆኑት ሻምበል ደረጀ ኃይለ ማርያም ይጠቀሳሉ።
ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴም ጉብኝታቸውን አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ። በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ተሳትፈዋል የተባሉት ወገኖችም እየታደኑ ተገደሉ። የመንግሥት ግልበጣው መሪ የነበሩት ብርጋዴር ጀኔራል መንግሥቱ ንዋይም ተይዘው በስቅላት ተቀጡ። ወንድማቸው ገርማሜ ነዋይ ደግሞ በሽሽት ላይ ሳሉ ዝቋላ አካባቢ ከሚያድኗቸው ፖሊሶች ጋር በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ተገደሉ። የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራውም ሳይሳካ በአጭሩ ተቋጨ።
እንደ ፕሮፌሰር ባህሩ ገለጻ፤ የመፈንቅለ መንግሥት ሞካሪዎች ዋና ስህተት የጦሩ ዋና አካል የሆነውን የምድር ጦሩን እና የአየር ኃይሉን አለማሳተፋቸው ወይም ሳይቀድመን እንቅደመው በሚል ከጥቅም ውጭ አለማድረጋቸው ነው።
‹‹አማፅያኑ ቢወገዱም ያቀጣጠሉት የለውጥ ችቦ ከእነርሱ ጋር አልጠፋም›› ያሉት የታሪክ ጸሐፊው፤ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው እንዲያውም የተጀመረው ተቃውሞ የበለጠ እንዲጠናከር ነው ዕድል የፈጠረው። ይህንንም በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ማግስት በህቡዕ ይወጡ የነበሩ መልዕክቶች ያረጋግጣሉ።
‹‹አንድ ሺህ ቀኖች በግ ሆኖ ከመኖር አንድ ቀን አንበሳ ሆኖ መሞት ይሻላል፣ ካለ ደም ስርየት የለም፣ ለአመጸኞች መገዛት ኃጢአት ሲሆን በአመጸኞች ላይ ማመጽ የተቀደሰ ሥራ ነው፣ የታኅሳስ ሰማዕታት አልሞቱም አሉ በሕይወት….›› የሚሉ መሪ ቃሎች በታሪክ ምሁሩ መጽሐፍ ላይ ይገኛሉ። እንዲህ እንዲህ እያለ ለ13 ዓመታት ያህል የቆየው የንጉሡ ሥርዓት፤ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት ባለመቻሉ 1966 ላይ ዋናው አብዮት ተቀጣጥሎ ፍጻሜውን አገኘ።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን እሁድ ታህሣሥ 9 ቀን 2015 ዓ.ም