ሁልጊዜም አዲስ የሚሆኑት፤ ሀዲስ አለማየሁ

ሀዲስ አለማየሁ በዚህ ዓመት፤ ታሪክ ብቻ ሳይሆኑ ዜና ጭምር ሆነዋል። ፍቅር እስከ መቃብር በፊልም ተሠርቶ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን መታየት ከጀመረበት ዕለት ወዲህ እንደ አዲስ አጀንዳ ሆኗል። ከ115 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥቅምት 7 ቀን 1902 ዓ.ም የተወለዱትና የዚህ ድንቅ መጽሐፍ ጸሐፊ የሆኑት ሀዲስ አለማየሁ የዚህ ሳምንት ባለታሪካችን ናቸው።

ሀዲስ አለማየሁ በሥነ ጽሑፉ ዘርፍ ብዙ ተብሎላቸዋል። ሀዲስ ግን ከሥነ ጽሑፍ ሥራዎቻቸው የበለጠ የኖሩት በፖለቲካ ሥራ ላይ ነው። መጽሐፎቻቸውም የፖለቲካ ተሳትፏቸው ውጤቶች ናቸው። የድርሰት ሥራዎቻቸውን ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ሕይወታቸውንም እንመለከታለን።

ሀዲስ ከአለቃ አለማየሁ ሰለሞን እና ከወይዘሮ ደስታ ዓለሙ በ1902 ዓ.ም ጎጃም ውስጥ ተወለደ። አያቱ (የእናቱ አባት) አለቃ ዓለሙ ስዩም በእንዶዳም ኪዳነ ምህረት ገዳም የዜማ መምህር ስለነበሩ ስድስት ዓመት ሲሞላው የግዕዝ ፊደሎችን ማጥናት ጀመረ። ከእንዶዳም ኪዳነ ምህረት በተጨማሪ በደብረ ኤልያስ፣ በደብረ ወርቅና በዲማ ጊዮርጊስ ገዳማት ተዘዋውሮ የድጓ፣ የቅኔና የመጻሕፍት ቤት (ትርጓሜ) ትምህርቶችን ተማረ። በትምህርቱም ከጓደኞቹ ሁሉ የላቀ ነበር። በ1918 ዓ.ም ሐዲስና ሌሎች ጓደኞቹ ከመምህራቸው መሪጌታ በላይ ጋር በመሆን ወደ አዲስ አበባ አቀኑ።

አዲስ አበባ ደርሰው ጥቂት ጊዜያትን ካሳለፉ በኋላ አቶ አያሌው ንጉሤ ከተባሉና በስዊድን ሚሲዮን ትምህርት ቤት ያስተምሩ ከነበሩ ግለሰብ ጋር ተዋወቁ። አቶ አያሌውም ሀዲስና ጓደኞቹ ወደ ስዊድን ሚሲዮን ትምህርት ቤት ገብተው ዘመናዊ ትምህርት እንዲማሩ መከሯቸው። ሀዲስ ትምህርት ቤቱ ሃይማኖቴን ሊያስለውጠኝ ይችላል ብሎ በመፍራቱ ጥቂት አመነታ። በመጨረሻ ግን ወደ ስዊድን ሚሲዮን ትምህርት ቤት ገብቶ ትምህርቱን ጀመረ። በሂደትም የዘመናዊ ትምህርትን ጥቅም በማወቁ የመንግሥት ትምህርት ቤት መግባት እንዳለበት ወስኖ ተፈሪ መኮንን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤትን ተቀላቀለ። ከራስ ኃይሉ ተክለሃይማኖት ግምጃ ቤት ባገኘው ወርሃዊ የገንዘብ ድጋፍም ከሦስተኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ድረስ ያለውን ትምህርቱን በተፈሪ መኮንን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታተለ።

በወቅቱ በትምህርት ቤቱ ውስጥ አመፅ ተቀስቅሶ ነበር፡ ‹‹ … የአመፁ ጠንሳሾች በእድሜያቸው በሰል ያሉት ተማሪዎች ናቸው … ›› ተብሎ በመታመኑ እድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ ተማሪዎች ማደሪያቸው ከትምህርት ቤቱ ውጭ ሆኖ እንዲማሩ ተወሰነ። ይህ ውሳኔ አዲስ አበባ ውስጥ ቤተሰብና የቅርብ ዘመድ ለሌላቸው የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች አስደንጋጭ ነበር። ሀዲስ አዲስ አበባ ውስጥ ቤተሰብም ሆነ የቅርብ ዘመድ ስላልነበረው ትምህርቱን ለማቋረጥ ተገደደ።

በወቅቱ በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ይሰጥ የነበረውን የመምህርነት ሥልጠና ወስዶ በስዊድን ሚሲዮን ትምህርት ቤት ማስተማር ጀመረ። ከዘጠኝ ወራት የመምህርነት ሥራ በኋላ ዳንግላ አካባቢ በነበረው የብሪታኒያ ቆንስላ ውስጥ እንዲሠራ ተመደበ። ዳንግላ አካባቢ የነበረው የብሪታኒያ ቆንስላ ከተዘጋ በኋላ ሀዲስ በአካባቢው የነበረው ጉምሩክ ተቆጣጣሪ ሆኖ መሥራት ጀመረ። በዚህ ሥራው ላይ ብዙም አልቆየም። በወቅቱ በአካባቢው የባሪያ ንግድ ይካሄድ ስለነበር የባሪያ ንግድ እንዲቆም የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ያወጣቸውን ድንጋጌዎችን የማስፈጸምና የመከታተል ኃላፊነት ተሰጥቶት ኃላፊነቱን አከናወነ። ከዚያም በዳንግላም ሆነ በመላው አገው ምድር የመጀመሪያ የሆነውን የዳንግላ ትምህርት ቤትን እንዲያቋቁም የተሰጠውን ኃላፊነት ተወጣ። ሀዲስ የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተርና መምህር ሆኖ አገልግሏል።

በ1928 ዓ.ም ወደ ደብረ ማርቆስ ተዛውሮ በንጉሥ ተክለሃይማኖት ትምህርት ቤት የእንግሊዝኛና የሂሳብ መምህር ሆነ። የወቅቱ የጎጃም ገዢ የነበሩትን የልዑል ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ ልጆችንም ያስተምር ነበር። እስከ ፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ጊዜ ድረስም በዚያው በደብረ ማርቆስ ቆየ።

ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ሀዲስ ከመንግሥት ሳይጠብቅ ራሱ ጠመንጃ ገዝቶ፣ የራስ እምሩን ጦር ተቀላቅሎ በአርበኝነት መዋጋት ጀመረ። የሕዝቡንና የአርበኛውን ስሜት የሚቀሰቅሱ የኪነ ጥበብ ሥራዎችንም እየሠራ አቅርቧል። በ1929 ዓ.ም ጎጀብ ወንዝ አካባቢ በተደረገ ውጊያ ላይ ተማርኮ ፖንዞ እና ሊፓሪ ወደሚባሉና በሳርዲና አካባቢ (ደቡባዊ ኢጣሊያ) ወደሚገኙ የሜዲትራኒያን ደሴቶች ተወስዶ ታሰረ። ከሰባት ዓመታት የእስራት ጊዜ በኋላ አርበኛው ሀዲስ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ።

ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሰም በማስታወቂያ ሚኒስቴር የፕሬስና ኢንፎርሜሽን ምክትል ዳይሬክተር ሆኖ ተሾመ። ሀዲስ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ በቆየባቸው ጊዜያት ሚኒስቴሩ በሰው ኃይልና በቁሳቁስ የተደራጀ እንዲሆንና ሥራውን በአግባቡ እንዲያከናውን ስለማድረጉ ቢትወደድ ዘውዴ ገብረሕይወት (የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ አምባሳደርና ቋሚ ተወካይ ሆነው ያገለገሉ) ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። ከዚያም ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተዛውሮ የአሜሪካ ጉዳዮች ክፍል ዳይሬክተር ሆነ።

በ1938 ዓ.ም አቶ ሀዲስ አለማየሁ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ቆንስላ ተጠሪ ሆነው ተሾሙ። በዚህ ወቅት ነው የትዳር አጋራቸውን ወይዘሪት ክበበፀሐይ በላይን ያገኙት። የዋግሹም ተፈሪ ወሰን የልጅ ልጅ የሆነችው ወይዘሪት ክበበፀሐይ በወቅቱ በወይዘሮ አማረች ወለሉ አሳዳጊነት በኢየሩሳሌም ትኖር ነበር። በ1939 ዓ.ም በአትላንታ የቴሌኮሙኒኬሽን ጉባዔ ላይ ኢትዮጵያን በመወከል ወደ አሜሪካ ተጉዘው ለአምስት ወራት ያህል በአሜሪካ ቆይተዋል። በዚህ ወቅት ኢትዮጵያን በመወከል በሌሎች ጉባዔዎች ላይም ተሳትፈዋል። በመቀጠልም በዋሺንግተን ዲ.ሲ የሚገኘውና በራስ እምሩ ኃይለሥላሴ የሚመራው የኢትዮጵያ ለጋሲዮን ዋና ጸሐፊ ሆኑ። ከዚህ ኃላፊነታቸው ጎን ለጎን መደበኛ ባልሆኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባዔዎች ላይ ኢትዮጵያን በመወከል አገልግለዋል። በ1941 ዓ.ም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ የሽግግር ኮሚቴ የኢትዮጵያ ተወካይ ሆኑ። አቶ ሀዲስ በወቅቱ በአሜሪካ በነበራቸው ቆይታ በዋሺንግተን ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ሕግ ትምህርት ጀምረው የነበረ ቢሆንም ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ በመታዘዛቸው የጀመሩትን ትምህርታቸውን ሳያጠናቅቁት ቀርተዋል።

በ1942 ዓ.ም ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተመልሰው የሚኒስቴሩ የፕሬስና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀኔራል ሆነው መሥራት ጀመሩ። ከሁለት ዓመታት ቆይታ በኋላ ደግሞ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ። በዚህ ኃላፊነታቸው ላይ በነበሩበት ወቅት አሜሪካ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ የነበራትን ጣልቃ ገብነትና ጫና አምርረው ይቃወሙ ነበር። ጆን ስፔንሰር ከተባለው አሜሪካዊ አማካሪ ጋርም ሰፊ የሃሳብ ልዩነት ነበራቸው። ስፔንሰር ‹‹Ethipia at Bay – A Personal Account of The Haile-Selassie Years›› የሚል ርዕስ በሰጠው መጽሐፉ፣ ‹‹ … ራስ እምሩ፣ ሀዲስ ዓለማየሁ፣ ሲራክ ኅሩይ … ኮሙኒስታዊ እሳቤ አላቸው …›› በማለት ጽፏል። ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ከማይደግፉና ከሶቭየት ኅብረት ጋር ግንኙነት እንድትመሰርት ካደረጉ ሰዎች መካከል አንዱ ሀዲስ እንደነበሩ ስፔንሰር ገልጿል።

በሀዲስ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ላይ ጥናት ያደረጉት ጸጋዬ ኃይሉ ግን፤ ሀዲስ ከምስራቁ ይልቅ የምዕራቡ ዓለም ርዕዮተ ዓለማዊ እሳቤን ይመርጡ እንደነበር ጽፈዋል። ቢትወደድ ዘውዴ ገብረሕይወት እና ብላታ መሐሪ ካሣ በበኩላቸው፤ ሀዲስ ዓለማየሁ ለምስራቁም ሆነ ለምዕራቡ ርዕዮተ ዓለም የተለየ ፍላጎት አልነበራቸውም። የእርሳቸው ዋነኛ ጉዳይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና ሉዓላዊነት ነበር›› በማለት መስክረዋል። በእርግጥ ሀዲስ አለማየሁ ‹‹ኢትዮጵያ ምን ዓይነት አስተዳደር ያስፈልጋታል?›› በሚለው ሥራቸው ላይ ‹‹ …. ኢትዮጵያ ካፒታሊዝምንም ሆነ ሶሻሊዝምን ከመምረጥ ይልቅ ከሁለቱም ወገኖች ጥሩ የሚባሉትን ሃሳቦች በመውሰድ ከራሷ ታሪክ፣ ባሕልና ማኅበረሰብ ጋር የሚጣጣም አድርጋ መቅረፅ ያስፈልጋታል …›› ብለዋል።

ሀዲስ በዲፕሎማትነት ዘመናቸው ኢትዮጵያን ወክለው ከተሳተፉባቸው አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉባዔዎች መካከል የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት ጉባዔ (እ.አ.አ 1948፣ሮም)፣ አራተኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ (እ.አ.አ 1949፣ኒው ዮርክ)፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔዎች (እ.አ.አ 1952፣ኒው ዮርክ እና 1956፣ፓሪስ) እና የአፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉባዔ (እ.አ.አ 1964፣ሌጎስ) ይጠቀሳሉ።

እ.አ.አ በ1956 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ አምባሳደርና ቋሚ ተወካይ ሆነው በተሾሙበት ጊዜ ዋነኛ ተግባራቸው፤ የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ሶማሊላንድ የድንበር ጉዳይ ነበር። ስፔንሰር ሀዲስ በድንበር ላይ የነበራቸውን አቋም ሲገልፅ ‹‹ … የኢትዮጵያ ንብረት የሆነችን ቅንጣት ታክል ቁራሽ መሬት የመስጠት ፍላጎትና ዝግጁነት አልነበረውም …›› ብሏል። በዚህም ነው ሀዲስ ስለድንበሩ ጉዳይ የሚደራደረው የኢትዮጵያ ቡድን መሪ ተደርገው የተሾሙት። ምንም እንኳን የድንበር ማካለል ድርድሩ ያለስምምነት ቢጠናቀቅም፤ ሀዲስ የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር ብርቱ ጥረት አድርገዋል።

በመንግሥታቱ ድርጅት የነበራቸውን የአራት ዓመታት ከአምስት ወራት ቆይታ ሲያጠናቅቁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ሆነው ተሾሙ። በዚህ ወቅት ነበር ሀዲስ ‹‹ልዩ ማስታወሻ›› የሚል መልዕክት ለንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ያቀረቡት። በዚህ መልዕክታቸው በ1953 ዓ.ም የተሞከረው መፈንቅለ መንግሥት መንስኤና ወደፊትም የመንግሥት አሠራር ካልተሻሻለ የከፋ ችግር ሊያጋጥም እንደሚችል በመጥቀስ ኋላ ቀር የሆነው የኢትዮጵያ ማኅበረ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መዋቅር ሊሻሻል እንደሚገባ ገልጸዋል። ይህ መረር ያለ የሀዲስ ምክረ ሃሳብ ሥልጣናቸውንና ክብራቸውን እንደዓይናቸው ብሌን ለሚጠብቁት ለንጉሠ ነገሥቱ ምቾትን አልሰጠም።

ንጉሠ ነገሥቱ ሀዲስን ቢሯቸው አስጠርተው ‹‹ድፍረት ስለተሞላበት›› ደብደቤያቸው ገሰጿቸው። ሀዲስ ግን በንጉሠ ነገሥቱ ሃሳብ ባለመስማማት በመልዕክታቸው ካሰፈሩት ሃሳብ በተጨማሪ ሌሎችንም ምክረ ሃሳቦችን ለንጉሠ ነገሥቱ ተናገሩ። መልዕክቱ ለንጉሠ ነገሥቱ በደረሳቸው በስምንተኛው ቀን ሀዲስ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ እንዲሆኑ ተደረገ። ንጉሠ ነገሥቱ ራሳቸው የትምህርት ሚኒስትር ስለነበሩ ሹመቱ ከፍተኛ ትችት የሰነዘሩባቸውን ደፋሩን፣ በግልፅ ተናጋሪውንና ትሁቱን ሀዲስን ከጎናቸው አድርገው ለመቆጣጠር እንደሆነ ግልፅ ነበር።

በአፍሪካ የትምህርት ዘርፍ ላይ ያተኮረ ጉባዔ ሲካሄድ፤ ሀዲስ በኢትዮጵያ ስለነበሩት ትምህርት ቤቶችና ተማሪዎች ቁጥር ያቀረቡት ሪፖርት ንጉሠ ነገሥቱን አናደዳቸው። ይህም የንጉሠ ነገሥቱንና የሀዲስን ቅራኔ እያሰፋው ሄደ። ከዚህ በተጨማሪም ሀዲስ ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር በመተባበር ባዘጋጁት የትምህርት ዘርፍ እቅድ ላይ፣ ለዘርፉ ከሚመደበው በጀት መካከል 25 በመቶ ያህሉ ብቻ ለአስተዳደራዊ ጉዳዮች እንዲሆንና ቀደም ሲል ለአስተዳደራዊ ጉዳዮች ሲመደብ የቆየው 75 በመቶ የዘርፉ በጀት ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ለትምህርት ግብዓቶች ማሟያ እንዲውልና እቅዶችን ከማዘጋጀትና አፈጻፀሞችን ከመከታተል በስተቀር ያሉት ሥራዎች በዘርፉ ባለሙያዎች ብቻ እንዲከወኑ ያቀረቡት ሃሳብ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀረ።

በዚህ ጊዜ ሀዲስ መንግሥት የትምህርት ዘርፉን ለመለወጥ ፍላጎት እንደሌለው በማመናቸው ከሥልጣን መልቀቂያ አቀረቡ። በመቀጠልም ለአምስት ዓመታት ያህል በእንግሊዝና እና በኔዘርላንድስ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው አገለገሉ። ሀዲስ እንግሊዝ በነበሩበት ወቅት ባለቤታቸው ወይዘሮ ክበበፀሐይ በላይ አረፉ። በልጅ ያልታጀበው ጋብቻ በዚሁ ተቋጨ፤ ሀዲስም በድጋሚ ወደ ትዳር አልተመለሱም። አዲስ አበባ ቀጨኔ አካባቢ የሚገኘውን ቤታቸውንም ለሕፃናት ማሳደጊያ እንዲሆን ለከተማው አስረከቡ።

ፀሐፌትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ሲሾሙ፤ ሀዲስ ከለንደን ተመልሰው የእቅድና ልማት ሚኒስትርነቱን ያዙ። ሀዲስ፤ የተማሩ ወጣት ኢትዮጵያውያንን በማሰባሰብ ሚኒስቴሩ በሰው ኃይል የተደራጀ እንዲሆን አደረጉት። ሦስተኛው የአምስት ዓመት የልማት እቅድ (Third Five Year Development Plan) የተዘጋጀውም በዚህ ወቅት ነበር። ይሁን እንጂ ለእቅዱ ማስፈጸሚያ የተመደበው በጀት ሲቀነስ ሀዲስ ባለመስማማታቸው በድጋሚ ከኃላፊነታቸው ለቀቁ። ከዚያም እስከ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል ሆነው እስከ አብዮቱ ፍንዳታ ድረስ ቆዩ።

ደርግ ተመስርቶ ልጅ እንዳልካቸውና ካቢኔያቸው ሥልጣን እንዲለቁ ጥያቄ ሲያቀርብ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ በግንባር ቀደምትነት ያጫቸው ሰው ሀዲስ አለማየሁ ነበሩ። በሌተናንት ጀኔራል አማን ሚካኤል አንዶም በኩል ለጠቅላይ ሚኒስትርነት መታጨታቸው የተነገራቸው ሀዲስ ግን፤ የደርግን ዝርዝር ዓላማና ፕሮግራም የሚያስረዳቸው ሰው ሳያገኙ በመቅረታቸው በዕጩነታቸው ሳይስማሙ ቀሩ። ደርግ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴን ከዙፋን አውርዶ ራሱን ‹‹ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት›› ብሎ ሰይሞ መንግሥታዊ ሥልጣን ከጨበጠ ከዓመት በኋላ ባቋቋመውና ከየአካባቢው የተወከሉ እውቀትና ልምድ ያላቸው ግለሰቦች በተካተቱበት የመማክርት ሸንጎ ውስጥ ጡረታ እስከወጡበት ጊዜ ድረስ ለሁለት ዓመታት ያህል አገልግለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UN Economic Commission for Africa) አዲስ አበባ ላይ እንዲቋቋም የተደረገው በሀዲስ አለማየሁ ብርቱ ጥረት ነው። ሀዲስ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ አምባሳደርና ቋሚ ተወካይ በነበሩበት ወቅት ብዙ የአፍሪካ ሀገራት በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር ስለነበሩና ቅኝ ገዢዎች ቅኝ የሚገዟቸውን እንዲለቁ ሲጠየቁ ከሚያቀርቧቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ ሀገራት «አብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች ነጻ ቢወጡ በኢኮኖሚ ራሳቸውን አይችሉም» የሚል ነበር። ሀዲስም ምክንያት ነው ተብሎ የቀረበው ነገር ቅኝ ገዢዎቹ ጭቆናቸውን ለማራዘም የሚጠቀሙበት ዘዴ መሆኑ ስለገባቸውና አፍሪካን በዘላቂነት ከቅኝ ግዛት ማላቀቅ የሚቻለው የአፍሪካውያንን ትብብር በማጠናከርና የአሕጉሪቷን የኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍታት ሲቻል መሆኑን በማጤን አንድ አፍሪካዊ ተቋም እንደሚያስፈልግ አምነውበት ሃሳባቸውን ለንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ አቅርበው የአፍሪካ የኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዲስ አበባ ላይ ሊቋቋም ቻለ።

ሀዲስ አለማየሁ በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚታወቁት ዘመን ተሻጋሪና አስደናቂ በሆኑ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎቻቸው ነው። ሀዲስ ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር››፣ ‹‹ወንጀለኛው ዳኛ››፣ ‹‹የልምዣት››፣ ‹‹ትዝታ››፣ ‹‹ተረት ተረት የመሰረት፣ ‹‹ኢትዮጵያ ምን ዓይነት አስተዳደር ያስፈልጋታል?››፣ ‹‹ሐበሻና የወደኋላ ጋብቻ››፣ እና ‹‹የትምህርትና የተማሪ ቤት ትርጉም›› የተሰኙ ልብ ወለዳዊና ኢ-ልብ ወለዳዊ የድርሰትና የተውኔት ሥራዎችን አበርክተዋል። በተለይ ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር›› የተሰኘው ሥራቸው በኢትዮጵያ የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ከታዩ ሥራዎች መካከል ከግንባር ቀደምቶቹ ተርታ የሚሰለፍ ሆኖ ዘልቋል። ለሥነ ጽሑፍ ሥራዎቻቸውም የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የሥነ ጽሑፍ ሽልማትን አሸንፈዋል። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጥቷቸዋል። ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ያሰራላቸው ከነሀስ የተቀረፀ ሐውልት በ2009 ዓ.ም በደብረ ማርቆስ ከተማ ቆሞላቸዋል። የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበርም በ2002 ዓ.ም ለክብር ዶክተር ሀዲስ አለማየሁ ያዘጋጀው የፖስታ ቴምብር በኢትዮጵያ የፖስታ ድርጅት ታትሞ ተሠራጭቷል።

በኢትዮጵያ የፖለቲካና የሥነ-ጽሑፍ ዘርፎች ላይ ገናና ስም የነበራቸው ደራሲ፣ መምህር፣ ፖለቲከኛ፣ አርበኛ፣ ባለቅኔ፣ … የክብር ዶክተር ሀዲስ አለማየሁ ኅዳር 26 ቀን 1996 ዓ.ም በ94 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ሥርዓተ ቀብራቸውም በአዲስ አበባ፣ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል።

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 10/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You