በአሰብ የነበራቸውን ቆይታ ደጋግመው ቢያነሱት አይጠግቡትም። ከልጅነት እስከ እውቀት ኖረውበታል። ብዙ ነገሮች ተምረዋል፣ ከትንሽ እስከ ትልቁም ሰርተዋል ። ለስደት የበቁትም ከእዛው ስለሆነ ዛሬም አካባቢውን እንደሚናፍቁት ይናገራሉ።
የስደትን አስከፊነት ሲያነሱ ደግሞ “ማን እንደ ሀገር ”በሚል ቁጭት ጭምር ነው። የዛሬው የ“ህይወት እንዲህ ናት” አምዳችን እንግዳ አቶ ዮሀንስ ተፈራ። አቶ ዮሀንስ ዛሬ ኑሮአቸውን በኖርዌይ ኦስሎ ቢያደርጉም ትዝታና ፍቅራቸው ግን እትብታቸው በተቀበረባት እምዬ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው።“ሀገራችንን ልንሰራት ይገባል ”የሚል ጽኑ አቋምም አላቸው።
ትውልድ፣ እድገትና ትምህርት
አቶ ዮሀንስ የአቶ ተፈራ ለገሰ እና የወይዘሮ ዳርምየለሽ ሙሉነህ የአብራክ ክፋይ ሆነው ይህችን ምድር የተቀላቀሉት በ1952 ዓ.ም መስከረም 1 ቀን ነው። የተወለዱትም አዲስ አበባ ከተማ በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል መሆኑ ከወላጆቻቸው ተነግሯቸዋል።ይሁን እንጂ የአዲስ አበባ ቆይታቸው ከአንድ አመት በላይ አልዘለለም።
ብቸኛ የነበሩት አያታቸው እማሆይ ላቀች ደስታ ወደ ደሴ ወሰዷቸው። በደሴ በነበራቸው ቆይታ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በእቴጌ መነን ትምህርት ቤት፣ ሁለተኛ ደረጃን ደግሞ በጎጤ ሁለተኛ ደረጃ እና በወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት ተምረዋል ።
በትምህርት ላይ በነበሩበት ወቅት ግን ክረምቱን የሚያሳልፉት እንደማንኛውም ልጅ ውሀ ተራጭተውና በጭቃ ቦክተው አይደለም። እርሳቸው ከልጅነታቸው ጀምሮ የክረምቱን የተማሪ ዕረፍት የሚያሳልፉት አሰብ ገንዘብ በሚያስገኝ ስራ ላይ ተሰማርተው እንደነበር ያስታውሳሉ። ወደ አሰብ መጀመሪያ ያመሩት በንግድ ስራ ይተዳደሩ የነበሩ ቤተሰቦቻቸውን ተከትለው ነበር።
በክረምት አየሩ ሞቃታማ በመሆኑ ለእርሳቸው ምቹ ነበርና ሱቅ ውስጥ ተቀጥረው ይሰራሉ። መስከረም ሲጠባ ደግሞ ወደ ደሴ ይመለሳሉ።“ ትምህርት ቤት ሲከፈት የምንገባው በክረምት በሰራነው ገንዘብ ዘንጠን ነው። በናፖሊዮ ሸሚዝ፣ በሰዓትና በሀብል አጊጠን መስከረም ላይ ትምህርት ቤት እንገባለን። ስለዚህ አሰብ የምንሄድበትን የክረምት ወቅት እንናፍቃለን” ይላሉ። የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ ግን በቋሚነት አሰብ ወደብ ላይ መቀጠራቸውን ያስታውሳሉ።
በልጅነት ዘመናቸው ከዘመናዊ ትምህርቱ ጎነ ለጎንም የመንፈሳው ትምህርት ተምረዋል። ዲያቆን ሆነውም በድቁና አገልግለዋል። ያኔ የተማሩት የግዕዝ ቋንቋ አሁን ድረስ ስንቅ ሆኗቸዋል፣ ይናገሩበታል፣ይጽፉታል፣ ያደምጡታል። እናም አሉ ከሚባሉ የግዕዝ አዋቂዎች ጋር ቢሰለፉ እንደማይሸነፉም በኩራት ይናገራሉ። የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ላይ ግዕዝ ተፈትነውም በጥሩ ውጤት ማለፋቸውን ይናገራሉ።
አቶ ዮሀንስ ህይወታቸው ተስተካክሎ እንዲቀጥል አድርገው የቀረጿቸው በጣም ጎበዝ ሰው የነበሩት ሴት አያታቸው መሆናቸውን ይናገራሉ። “አሁን ሳስበው ሳይማሩ እንደዚያ የነበሩ ቢማሩ ኖሮስ እላለሁ፤ልዩ ኢትዮጵያዊ ፍቅር እንዲያድርብኝ አድርገው ሰርተውኛል” በማለት ያመሰግኗቸዋል።
የትምህርት ፍላጎታቸውም በአጭሩ በሚባል ሁኔታ አልቀረም። አሁን በሚኖሩበት ኦስሎ “ሀይማኖት፣ ማህበረሰብና አለምአቀፍ ጉዳዮች” በሚል ዘርፍ የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሰርተዋል። የመመረቂያ ጽሁፋቸውን የሰሩት ደግሞ “በሳይበር ቸርችስ” ላይ ነው። በአሁን ሰዓት ሰዎች በአውሮፓና በአሜሪካ ወደ ቤተክርስቲያን የሚመጡበት ሁኔታ እየቀነሰ ነው፤ብዙ መንፈሳዊ ነገሮች የሚከወኑት በኢንተርኔት እየሆነ ነው። የኢንተርኔትን ታሪካዊ ዳራ እንዴት ለሀይማኖት እና ለማህበራዊ ጉዳይ እንደሚጠቅም ለማሳየት ነው በዚህ ላይ መመረቂያዬን የሰራሁት ይላሉ።
የአሰብ ትዝታ
አሰብ የተቀጠሩት በ1971 ዓ.ም ነው። ያኔ ወደቡ በጣም ኋላቀር ከመሆኑም በላይ ክሬን እንኳን እንዳልነበረው ያስታውሳሉ።“ ከወደቡ ጋር አብሬ ስላደግኩ ህይወቴ በሙሉ እዛው የሚያልፍ ይመስለኝ ነበር። በደርግ ጊዜ ሰዎች ወደ ውጪ አገር ለትምህርት ሄደው ሲቀሩ እኔ ግን በጭራሽ ከሀገሬ መውጣት አልመኝም ነበር። እንኳን በኬንያ በሱዳን ጠፍቶ መሄድ ቀርቶ ምቹ በሆነው መንገድ እንኳን አገሬን ጥዬ መሄድ ለእኔ የሞት ያህል ነበር” ሲሉ ለሀገራቸው የነበራቸውን ፍቅር፣ ለተሰማሩበት ሙያ ያላቸውን አክብሮትና ለአለቃቸው ያላቸውን ታማኝነት የሚገልጹት የአሁኑን ዘመን ወጣት በማስታወስ ነው ።
“በ20ዎቹ ዕድሜዬ ላይ እያለሁ ወደ ምዕራብ አገሮች ለትምህርት ለስልጠና ሄጃለሁ፤ ግን አልቀረሁም። ያኔ አላማዬ ሀገርን መርዳት፤ ወደቡን ማሻሻል ነበር”። የሚሉት አቶ ዮሀንስ ህንድና ራሽያ ተምረዋል። ሆላንድ አቅንተዋል። አገራቸውን ወክለውም በምስራቅና በመካከለኛው አፍሪካ የወደብ አገልግሎቶች በመሳተፍ ታንዛኒያ ሄደዋል፣ በኬንያ ቱሪስት ሆነው አልፈዋል። ያኔ በተዛወሩባቸው አገራት ኢትዮዽያውያን
ስደተኞችን አይተው መታዘባቸውን ይናገራሉ።
እሳቸው ከአገራቸው መወጣት የማይ ፈልጉበትን ሶስት ምክንያቶችን ያነሳሉ። የመጀመሪያው አያታቸው ኢትዮጵያዊነትን በልባቸው እንዲገባ፣ ከደማቸው እንዲዋሃድ አድርገው ስለአስተማሩዋቸው ነው። ይሄ ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ አገራቸውን እንዲወዱ አድርጓቸዋል
ሁለተኛው ፈርሀ እግዚአብሄር ስላላቸው መሆኑን ይጠቅሳሉ። ሰውንና ቃልን በማክበር ስነምግባር ተሞልተዋል።አለቃዬ አምነው ልከውኝ እዛ ብቀር የአለቃዬን ስም ማስጠፋትና መበደል መስሎ ይሰማኛል ።
ሶስተኛ ደግሞ ከእኛ ቀጥለው ውጪ ሄደው ለመማር ተራ የሚጠብቁ ጓደኞች አሉን፤እኛ በተላክንበት አገር ብንቀር እነሱን ሁለተኛ የሚልካቸው አይኖርም። ስለዚህ የእነሱንም እድል ላለመዝጋት በማሰብ ወደ አገራችን በታማኝነት እንመለሳለን።
“ያኔ ወደ ውጪ የምንሄደው የደሀ ልጆች ነበርን። አሁን ተምረን ከምናገኘውም በላይ ሰርተን ትልቅ ገንዘብ ማግኘት እንችልም ነበር ፣ ኢኮኖሚውም ጥሩ ነበር ፤ነገር ግን የገንዘቡ ነገር ከሌላው ምክንያት አይበልጥብንም። ስለዚህ መቅረትን ግብ አድርገን አንንቀሳቀስም።” ይላሉ።
አንድ ወቅት ላይ እናታቸው አማላጅ ልከውባቸው እንደነበር አቶ ዮሀንስ ያስታውሳሉ። “ አገሪቱ ጦርነት ላይ ናት፤አሁን እንኳን አይምጣ እኔ ብነግረው ስለማይሰማኝ እናንተ ንገሩልኝ ብላ አማላጅ ላከች። ያኔ ቦሩ ደርሰዋል፤ ደሴ ደርሰዋል እየተባለ ባለበት ወቅት ነው። እኔ ግን በጭራሽ ብዬ ከሄድኩበት ሁሉ እመጣለሁ። በመጨረሻው ሰዓት አሰብን ለቀው ከወጡት የመጨረሻው ሰው እኔ ነኝ። ከአሰብ ስንወጣ የመጨረሻውን የወደቡን በር የማዘው እኔ ነበርኩ፤የጥይት ናዳ በነበረበት ወቅት ፖሊሶቹን አሰልፌ መርከብ ላይ አስወጥቼ፤እኔም ወደ የመን ወጣሁ”ሲሉ ከሚወዷት አገራቸው እንዴት እንደተለዩ ይናገራሉ። የአገር ፍቅር ስሜቴ በልጅነቴ የሰረጸብኝ ስለሆነ ላወጣው አልችልም። ስለዚህም ሰዎች ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው ሲሉ ትክክል ናቸው እላለሁ ።
ዛሬስ?
ዛሬ ኢትዮጵያና ኤርትራ ሁለት አገር ቢሆኑም እንኳን ሁለት አገር ናቸው የሚለው ነገር አይዋጥላቸውም። አንድ ሀይማኖት፣ አንድ ደም፣ ቋንቋ፣ ባህል ታሪክ… ያለው ህዝብ ነው። ስለዚህ ፖለቲካ የወለደው፣ ጊዜያዊ ስሜት የፈጠረው ይሆናል እንጂ ይሄ ህዝብ አንድ ይሆናል የሚል እምነት እንደነበራቸው ይናገራሉ። “ሁለቱም አገሮች ወደ ልባቸው ይመጣሉ ብዬም አስብ ነበር። አሁን የተፈጠረውን እርቅና ሰላም ሳይ ያኔም ይሄንን ማሰቤ ልክ ነበር እላለሁ። ገና ደግሞ የበለጠ አንድነት እንደሚኖር አምናለሁ። አንዳንድ ሰዎች ይህንን ስል ሞኝነት አድርገው የሚቆጥሩ አሉ፤ይሄ ግን የእኔ ሀሳብ ነው የእኔ እምነት።
አሁን አሰብን ብትመለከቺ ኢትዮጵያ ካልተጠቀመችበት ምንም ነው፤ ለኤርትራ መሀከለኛ ምድር የኑሮ ጠቀሜታ የራቀ ስለሆነ አሰብን አሰብ ለማድረግ የኢትዮጵያና ኤርትራ የተጋጠሙ መሆን ጠቀሜታው በርካታ ይሆናል።
አሰብን መጠቀም ሲቻል በርካታ የአፋር ህዝብ ተጠቃሚ ይሆናል። ኢትዮጵያም የወደብ ወጪዋን ትቀንሳለች። አሰብ የኢኮኖሚ መገልገያ ነው እንጂ አሰብ እንደ ጋሻ ጦር በፎቶ የምናሳየውና በባህልነቱ የምንኮራበት አይደለም። ለምሳሌ አውሮፓ ቤልጂየሞች ባህር አላቸው ፤እዛ ባህር አጠገብ ያለው አንድ ፋብሪካ ዕቃዬን የማስገባው በዚህ ባህር ብቻ ነው ብሎ ዘራፍ አይልም ፤እሱ በዚህ ባስገባ ምን ያህል እርካሽ ነው ይላል። ስለዚህ የእሱ ጉዳይ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው የቱ ነው የሚል ይሆናል እንጂ ዝም ብሎ እንደታሪክ የሚቀመጥ የፎቶ ምስል መሆኑ ቀርቷል። ግሎባላይዜሽን አገሩን ሁሉ መንደር አድርጎታል። ስለዚህ ይሄንን በመገንዘብ ሁሉንም ነገር ከወደብ ጋር በማቀናጀት የበለጠ ሁለቱ አገሮች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የሚያገኙበትን መንገድ ነው መፈለግ ያለባቸው።
የአፋር ህዝብ ፍቅር
አቶ ዮሀንስ በየጨዋታቸው መካከል ደጋግመው ከሚያነሱት መካከል አንዱ ነገር የአፋር ህዝብን መልካምነት ነው። የአፋር ህዝብ ብለው ጠርተው አይጠግቡም“ የአፋር ህዝብ ከወደደሽ ምን አለፋሽ ይሞትልሻል”ይላሉ። ከአፋር ህዝብ ጋር ሰምና ወርቅ ያደረጋቸው የአያታቸው በእዛ አካባቢ ተሹመው መሄድ ሲሆን እሳቸውም በቆይታቸው ከአፋሮች ጋር መግባባታቸው የአፋሮችን ምንነት ጠንቅቀው እንዲረዱ አድርጓቸዋል።
“አያቴ አውሳ አውራጃ አስተዳዳሪ ሆነው ተሹመው በሄዱ ጊዜ አፋሮቹ በጣም ብልህ ናቸው፣ አንድ ችግር በሚያጋጥምበት ወቅት እንኳን እስኪ ይጠሩ ተብሎ ሽማግሌዎች ይጠሩና የሚሰጡት ምክር መሬት ጠብ አይልም ይባል ነበር። ይሄንን አያቴ ሲነግሩኝ ስላደግኩ በአእምሮዬ የተሳለው የአፋሮች ብልህነት፣ ደግነትና ጥሩነት ነው። ደግሞም በስራ ቆይታም ከአፋሮች ጋር ስኖር የተባሉትን ሆነው አግኝቻቸዋለሁ።
የአፋር ህዝብ ኢትዮጵያዊነቱን የሚወድ ነው። በእያንዳንዱ ልብ ውስጥ ኢትዮጵያዊነት አለ። ለምሳሌ የመን ለአፋር ቅርብ ነው፤ ሳውዲዓረቢያ ቅርብ ነው፤ በሀይማኖት፣ በቋንቋም ተመሳሳይነት አላቸው፤ ነገር ግን ወደ እነሱ መሄድን አይፈልጉም። ውሃ ሳይኖራቸው፤ ምድረ በዳ ሆኖ፣ አቧራ እየቦነነባቸው እንኳን ኑሯቸውን እዚሁ ያደረጉት ኢትዮጵያውያን ስለሚወዱና በኢትዮጵያዊነታቸውም ስለሚኮሩ ነው።
አፋሮች አንዴ ልባቸውን ከከፈቱ ፍቅራቸው የዘላላም ነው። ለወዳጆቻቸው ይሞታሉ። አንድ ሰው ላይ ክፉ ነገር ቢመጣ ቤታቸውን፣ ልጆቻቸውን ትተው ያንን ሰው አጅበውና ሸኝተው ከአገር እንዲወጣ ያደርጋሉ፤ ያድናሉ። እስከዛ ድረስ ጥሩ ህዝቦች ናቸው። መካከላቸው ገባ ሲባል ደግሞ እንደሌላው ህዝብ ደሀ ሀብታም ብሎ ልዩነት የለም።
ደራሲ ባልሆንም እፅፋለሁ
አቶ ዮሀንስ ደራሲ እንዳልሆኑ ይናገራሉ። ነገር ግን ማንኛውንም ነገር አስታውሰው፣ሳቢና ተነባቢ አድርገው የመጻፍ ችሎታ እንዳላቸው ደግሞ ያምናሉ። “እኔ ደራሲ አይደለሁም፤ ነገር ግን ጊዜ ወስጄ ብፅፍ ጥሩ ነገር መጻፍ እችላለሁ። በተለያየ አጋጣሚ የጻፍኩትን ያዩና ያነበቡ ሰዎች ሁሉ በፃፍኩት ነገር ይደነቃሉ፣ አሰብ ሲያዝ ግማሹ ሰው ወደ ኢትዮጵያ ግማሹ ወደ ጅቡቲ ሲሄድ እኔ ግን ወደ የመን ነው የተሰደድኩት። እዛ እያለን 11 የጦር መርከብ ባህር ሀይሉ ይዞ ሄዶ ነበር። ይሄ የኢትዮጵያ ህዝብ ንብረት ስለሆነ የት ላይ እንዳደረስነው ለህዝቡ ማሳወቅ አለብን ተብሎ ኮሜቴ ተቋቁሞ ነበር። ሶስት የታወቁ ሰዎች ደብዳቤ እንዲያረቁ ተደርጎ ቀናት ወስደው አርቅቀው መጡ፤ የፃፉትን አነበቡልን ብዙም ስሜት የሚሰጥ አልሆነልኝም። ከዛም ተቀብዬ እግሬ ላይ አስደግፌ ጻፍኩና ወዲያው አነበብኩላቸው፤ በጣም አደነቁት። ምንም ነገር ሳይጨመርበት ለአሜሪካ ሬዲዮ ድምጽ በድምጽ እንዲነበብ ወደ ከተማ ይዘው ሄዱ ።
አሁንም “ አሰብ ቀይባህርና ወደባችን በዚያን ጊዜ”የሚለውን መጻፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝ የደራሲነት ጉዳይ አይደለም። እኛ ከአሰብ ከወጣን በኋላ በኤርትራ ግዛት ተይዛ ባዶ ሆናለች። ከእኛ በፊት የነበሩ የአሰብን ታሪኩን የሚያውቁ ሰዎች አልቀዋል። በእኔ እድሜ ያሉት ደግሞ ድንገት ስለተፈናቀሉ የሉም። ስለዚህ አሰብ በወቅቱ የነበረችበትን ሁኔታ ታሪኩን የመፃፍ ሀላፊነትም ግዴታም አለብኝ ብዬ ስለማሰብ ነው ለመጻፍ የወሰንኩት።
አሰብ በአሁኑ የወጣቶች አባባል“ ፈታ“ የሚባልባት ከተማ ነበረች። አዲስ አበባ ላይ ለወር የሚባለው ገንዘብ አሰብ ላይ የዕለት ወጪ ነው። ሰዎች ገንዘብ አላቸው፤ ስራ አለ ፤ንግዱ የጦፈ ነው። ስለዚህ ገንዘብ ይገኛልም፤ ይወጣልም። ሁሉም ሰው የበረሀ አበል ይከፈለዋል። ስለዚህ የገንዘብ ቁጠባም ሆነ ስስት አይታሰብም። ይሄንን የአሰብን ጉዳይ አሁን ለመጻፍ ከሁሉም ሰው በተሻለ ሁኔታ ላይ ያለሁት እኔ ነኝ። ለዚህ ነው መጽሀፍ ለመጻፍ ታሪካዊ ሀላፊነት አለብኝ ብዬ የተነሳሁት። እኔ ባልጽፈው ታሪኩ ተቀብሮ ይቀር ነበር እኔም ስጽፍ ፈጣሪን እለምን የነበረው“ ጽፌ ሳልጨርስ አትግደለኝ ብዬ ነበር” አሁን ግን ጽፌ ስጨርስ ሸክም የቀለለኝ ያህል ነው የተሰማኝ ይላሉ። ከዚህ ቀጥሎም “ሁለት መጽሀፍ እጽፋለሁ” ሲሉም ቃል የሚገቡት አቶ ዮሃንስ ከሚጽፉትም አንዱ ኢትዮጵያና የመንን የሚመለከት ሲሆን ሌላው ደግሞ በህጻንነታቸው የሚያውቋትን ኢትዮጵያን የተመለከተ ነው።
የህይወት ፈተና
ለእኔ ትልቁ ፈተና ከሀገሬ ተነጥዬ መኖሬ ነው ይላሉ አቶ ዮሀንስ። አንድም ጊዜ ከአገሬ ተለይቼ በውጪ እኖራለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም። ኢትዮጵያ ለእኔ አገር ብቻ ሳትሆን ቅድስትም ናት፤ በመላ አለም ብዙ ዞሪያለሁ። ከአርባ በላይ አገራትን ረግጫለሁ፤ ማንም ግን እንደ ኢትዮጵያ የሚሆን አገር፤ እንደ ኢትዮጵያዊ የተባረከ ህዝብ የለም። ለምሳሌ አገራችን ላይ አንድ ኢትዮጵያዊና ፈረንጅ ቢጣሉ ኢትዮጵያውያን የሚጮሁት ለፈረንጁ ነው። እንግዳ ስለሆነ መከበር አለበት ብለው ያስባሉ። በሌላ በኩል ደግሞ በውጪው ዓለም በተመሳሳይ ጠብ ቢፈፀም ሁሉም የሚጮኸውና የሚያግዘው ለዜጋው ነው። በዚህ ኢትዮጵያውያን በጣም እንለያለን፤ እንግዳ አክባሪዎች ነን።
ምግብ አቅርቦ እባካችሁ ብሉልኝ ብሎ የሚለምን፤አልጠገብክም ብሎ በጉርሻ የሚያስጨንቅ እንዲህ አይነት ህዝብ ያለው እዚህ ብቻ ነው። በሌላው ዓለም ምግብ ይቀርባል ከበላህ ብላ ካልበላህ ደግሞ ተወው ነው፤ ልመና የለም። ይሄን ህዝብ ግን በእጃችን ስለያዝነው ዋጋው አይሰማንም በማለት ነው ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ያላቸውን ክብርና አድናቆታቸውን የገለጹት። ከዚህ ህዝብ ርቆ መኖርም ምን ያህል ከባድ መሆኑን በውስጡ አልፈው አይተውታል።
ሌላው ያነሱት ጉዳይ ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ በጣም ክፉ ፣ጨካኝ እና ባለጌ የሚባለው ሰው በአንዳንድ አገሮች ላይ አንድ ቁጥር “ ጨዋ” የሚባል የጸባይ ዋንጫ ተሸላሚና ቅዱስ ሰው ይሆናል። ስለዚህ ብዙ ጥሩ ጥሩ ነገሮች አሉን እና እናክብራቸው ነው ምክራቸው።
አቶ ዮሀንስ እንደሚሉት ኢትዮጵያዊ ባህላችን ውስጣችን ገብቶ ያለ ነገር ነው፤ የሚለቀን አይደለም። ለምሳሌ እኔ በደርግ ዘመን መሆን ያቃተኝ “ኢሰፓ መሆን ነው። ምክንያቱም ሀላፊ ሆኜ ቢሮዬ ትልቅ ሰው ሲመጣ ተነስቼ ሰው አስቀምጣለሁ ። ሁሉንም ሰው ጋሼ ብዬ እጣራለሁ።
ወደ ሆላንድ 14 ሰዎች ለትምህርት ተላክን። ከአስራ አራታችን አንዱ ልጅ ያደገውና የተማረው ኩባ ነበር። አንድ ፈረንጅ ታዲያ ይሄ ልጅ የእናንተ ዜጋ አይደለም አለን። ከእኛ ባህል ወጣ ያለ ስለነበር ነው። በአጠቃላይ ኢትዮጵያዊነት ጥሩ ነገር ነው።
ምክር ለወጣቱ
ማንም ሰው እንዲኖር የምመክረው በሀገሩ ላይ ነው። ሰዎች በተለይ ወጣቶቹ ይሄንን ምክር አይሰሙም። የመን እንኳን አትሂዱ እየተባሉ ወደ ደሀ ሀገር ይሄዳሉ። የመን እኮ አንድ ሰው ስጋ ከበላ ስጋ መብላቱን ሰበብ ፈልጎ ይነግርሻል። እዛ ቦታ ግን ኢትዮጵያውያን አትሂዱ ቢባሉ አይቀሩም፤ ይሄዳሉ ፤ተባረውም በድጋሚ ይመለሳሉ። ይሄ ያሳዝናል። ድሮ ግን እንዲህ አልነበረም፤ አሜሪካ አውሮፓ ለትምህርት የሄደ ሰው ትምህርት ጨርሶ ምርቃቱ ከወር በኋላ ከሆነ ዲፕሎማውን በፖስታ ቤት ላኩልኝ ብሎ አንድ ወር ላላመቆየት ወደ ሀገሩ ይመጣል። በእርግጥ አሁን የኢኮኖሚ ችግሩ አለ። ሆኖም ግን እንደ አገር የሚሆን ነገር የለም። እኔም ውጪ ሀገር በመኖሬ ደስተኛ አይደለሁም፤ነገሮች ቢስተካከሉልኝ አንድ ቀንም ውጪ አልኖርም።
አውሮፓና አሜሪካን መኖር በራሱ ይለያያል፤ አሜሪካ ብዙ ኢትዮጵያዊያንን ማየት በራሱ ያስደስታል። አውሮፓ ደግሞ በጣም ትንሽ ሰው ነው የሚኖረው ፤ስለዚህ ኖርዌይ ስኖር የሚሰማሽ ባይተዋርነት ነው። ስለዚህ እኛ ሀገራችንን ብንሰራት ጥሩ ነው። እነሱም ደሀ ሀገር ነበሩ ሀገራቸውን ሰርተው ነው አሁን ለደረሱበት ደረጃ የደረሱት። የዛሬ 100 ዓመት ኖርዊጂያን በዓለም ሁለተኛው ስደተኛ ሀገር ነበሩ፤ ስደታቸው ደግሞ በረሀብ ምክንያት ነው። ሆኖም ግን ጠንክረው በመስራታቸው ዛሬ ለደረሱበት ደረጃ ደርሰዋል። ስለዚህ እኔ ማለት የምፈልገው ስደት በረከት አይደለም መርገም ነው። ምድራችን ላይ መኖር ነው መታደል። ስለዚህ ሀገራችንን ልንሰራት ሀላፊነትም ግዴታም ያለብን እኛ ነን።
ቋንቋና ስራ
አቶ ዮሀንስ ከአገር ውስጥ ግዕዝ፣ ትግርኛና አማርኛ፣ ከውጪው ደግሞ እንግሊዝኛ፣ ኖርዊጂያን፣ አረብኛና ራሽኛን ጠንቅቀው ይናገራሉ ፤ይጽፋሉ፤ ያነባሉ። በተለያዩ ቦታዎችም በተለያየ ስራ ሲያገለግሉ ቢቆዩም አሁን ግን የኦስሎ የኢትዮያዊ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መጋቢ ሆነው በሙሉ ጊዜያቸው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።
ቀጣይ ዕቅድ
ለአገር የሚጠቅም ነገር ለመስራት አስባለሁ። በባህር ዘርፍ ብዙ ልምዶች አሉኝ፣ ብዙ ወደቦችን ጎብኝቻለሁ። ስለዚህ ማሰልጠኛ ቢቋቋም ሀሳቦች በመስጠት፣ በመደገፍ በመሳሰሉት እውቀቴን በማካፈል ለማገልገል ዝግጁ ነኝ። እንዲሁም በምኖርበት አገርም ዲያስፖራውን በማስተባበር ለአገር ግንባታ ግብአት የሚሆን ነገር መስራት እፈልጋለሁ። ቀደም ሲል ዲያስፖራው መርዛማ አመለካከት ነበረው አሁን ግን ተለውጧል።
ሌላው ደግሞ በተለያየ ልማት ውስጥ ብሳተፍ የሚልም ሀሳብ አለኝ። ለምሳሌ አፋር አትክልት፣ ቲማቲምና ሽንኩርት አምርቶ ገበያ አጥቶ ሲበሰብሰ ከማየት እንዴት ነው ፋብሪካ አቋቁመን መርዳት የምንችለው የሚለውን በማሰብ የአቅማችንን ብንሰራ እላለሁ።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6/2011
በአልማዝ አያሌው