«ወደ ስፍራው ጥቂት ሆነን ተንቀሳቀስን። ከእኛ በፊት ከተወሰኑ አዳኞችና ገብተው ቀርተዋል ከሚባሉት የመከላከያ አባላት ውጪ ወደ ውስጥ የገባ አልነበረም። ከ«ፈላታ»ዎች ጋር በአስተርጓሚ ተነጋግረናል፤ ከብቶቻቸውን ሳር ለማስጋጥ እንደሚመጡና ከብቶቻቸውን አንበሳ እንዳይበላባቸው ለማሸሽ ሳሩን እንደሚያቃጥሉት ገለጹልን። … በዛው የሱዳን ዲንደር የሚባል ፓርክ በቅርበት አለ፤ ከብቶቻቻውን እዛ ያሰማሩ እንደሆነ ስንጠይቃቸው ‹እዛማ አናስገብም፤ በጥይት ይመቱናል› አሉ።»
ይህን ያሉት አቶ ተሾመ ሙሉ ናቸው። አቶ ተሾመ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ማዕከላዊ ጎንደር ግብርና መምሪያ የደን አግሮፎረስትሪ ከፍተኛ ባለሙያ ሲሆኑ፤ አስቀድሞ «አላጥሽ» ይባል የነበረውንና አሁን አልጣሽ የሚባለው ብሔራዊ ፓርክ እንዲከለልና ትኩረት እንዲያገኝ የመጀመሪያውን ጥናት ለማድረግ ወደ ስፍራው በድፍረት የገቡ ሰው ናቸው። መግባት ብቻ አይደለም፤ ስፍራው እንደ ብሔራዊ ፓርክ እውቅና ይሰጠው ዘንድ እስከመጨረሻው የተሟገቱና የተከራከሩ፤ ደግሞም የተሳካላቸው እንጂ።
አልጣሽ የተባለው ብሔራዊ ፓርክ እውቅናን ያገኘው እንግዲህ ከዛ ጀምሮ ማለትም በ1998ዓ.ም መጋቢት ወር ላይ ነው። ታድያ ያን ጊዜ ወደ ስፍራው አቅንተው ሲመለከቱና «ፈላታ» ከተባሉት የናይጄሪያ ዘላኖች ጋር ሲነጋገሩ ያዩት ሁሉ፤ «ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል» እንዲሉ አስገድዷቸው ነበር። ለሱዳን ግብር የሚከፍሉ የናይጄሪያ ዘላኖች፤ የአልጣሽን ፓርክ ለከብቶቻቸው ማረፊያ አድርገውት፤ ለራሳቸውም ቢሆን ከብቶቻቸውን ከማረድ ተቆጥበው ለምግብነት የዱር እንስሳትን ለአደን እንደልብ ያገኙበት ሆኖ ኖሯል።
በቅድሚያ ግን ስለአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ ምን ያህል ሰው ያውቅ ይሆን? በመጀመሪያ ስያሜውን ስናነሳ፤ «አላጥሽ» የሚለው ቃል አረብኛ መሆኑን አቶ ተሾመ ነግረውናል። ይሁንና ቃሉን ወደ አማርኛ ለማቅረብ ታስቦ በኋላ ላይ «አልጣሽ» ተብሏል ይላሉ። አንዳንድ የጽሑፍ መረጃዎች እዚህ ላይ አክለው ስያሜው «አላጥሽ» የሚባል ወንዝ በፓርኩ ውስጥ እንደሚገኝና ስያሜው ከዛ የተወሰደ እንደሆነ ያስረዳሉ።
አልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ ከአዲስ አበባ 1ሺ25 ኪሎ ሜትር ከጎንደር ደግሞ 310 ኪ.ሜትር ርቀት፤ ምዕራብ ጎንደር ዞን፤ ቋራ የሚገኝ ፓርክ ነው። በምዕራብ በኩል በሱዳን ከሚዋሰነው የዲንደር ፓርክ ጋር፤ ከሰሃራ የሚነሳውን በረሃማነት በመግታትም ተስፋ የተጣለበትም ሰፊ የደን ሽፋን ነው፤ አልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ። ፓርኩ በተጨማሪ በምስራቅና በሰሜን በኩል የቋራ7 ቀበሌዎች እንዲሁም በደቡብ በኩል በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ያዋስኑታል።
የፓርኩ የቆዳ ስፋት 266ሺ570 ሄክታር ነው፤ እንግዲህ ከዋና ከተማይቱ አዲስ አበባ አምስት እጥፍ አካባቢ ይበልጣል ማለት ነው። የሙቀት መጠኑን በተመለከተ ከ13 እስከ 46 ዲግሪ ይደርሳል። አልፎ አልፎ ከሚታዩ ተራሮች በቀርም የመሬት አቀማመጡ ሜዳማ ነው። እንዳልነው ምንም እንኳ ፓርኩ እንደ ብሔራዊ ፓርክ እውቅና የተሰጠው በቅርብ ጊዜ ቢሆንም፤ የተለያዩ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ከ1970ዎቹ ጀምሮ ህብረተሰቡ የሚጠብቀው ጥብቅ ደን ነበር።
ይህን ያህል ስለፓርኩ አልን፤ ዛሬስ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል? ፓርኩ አሁንም ከፈተናዎች የተላቀቀ አይደለም። ይህም በአንድ ወገን «ከሞኝ ደጃፍ…» እንዳሉት፤ ከናይጄሪያ ይመጣሉ በሚባሉት ፈላታዎች እየተበዘበዘ ይገኛል። እነዚህ ፈላታ የተባሉ ሰዎች ሳይሳሱና ሳይሰስቱ ይጠቀሙበታል፤ ክረምት እያሳረፉ በጋውን ይሰፍሩበታል።
የሚያሳዝነው ደግሞ ከውጪ አደጋ ልንጠብቀው ባንችል እንኳ በዙሪያው ያለውና
የሰፈረው ማኅበረሰብን የየእለት ኑሮውን ለመግፋት ሲል ደኑን እየገፋው መገኘቱ ነው። የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶክተር ደሳለኝ መንገሻ በበኩላቸው፤ ፓርኩ በመገናኛ ብዙሃን ብዙ ያልተነገረለት እንደሆነና ከሌሎች ፓርኮች አንጻር ትኩረትም እንዳልተሰጠው አንስተዋል።
ዶክተር ደሳለኝ እንዳሉት ፓርኩ ባለው ሀብት ብቻ ሳይሆን ቅርሶች የሚገኙበት ታሪክ የተመዘገበበት ስፍራም ነው። መገኛው የሆነው ቋራ የንጉሥ አጼ ቴዎድሮስ የትውልድ ስፍራ ከመሆኑ በተጓዳኝ፤ አጼ ኃይለሥላሴ በጣልያን ወረራ ወቅት፤ ከእንግሊዝ ስደት መልስ በሱዳን ወደ አገራቸው ሲገቡ በዚህ ፓርክ አልፈው ነበር። ማለፍም ብቻ አይደለም፤ በቤኒሻንጉል ክልል አዋሳኝ በሚገኝ ኦሜድላ በሚባል መንደር አካባቢ በሚገኘው የፓርኩ ክፍል ከሚገኝ አንድ ግዙፍ ዛፍ ውስጥ ተጠልለው ለስምንት ቀናት አካባቢ ቆይተውበታል።
በፓርኩ ውስጥ ምን ይገኛል የተባለ እንደሆነ ደግሞ እንዲህ ነው። ባለጥቁር ጋማ አንበሶች በዚህ
ፓርክ ይገኛሉ የተባለ ሲሆን ከዛ በተጨማሪ 32 ትላልቅ አጥቢ የዱር እንስሳት፤ 180 የአዕዋፍት ዝርያዎች፤ 8 ተሳቢ እንስሳት፤ 57 ትላልቅ የዛፍ ዝርያዎች ይገኛሉ። በቁጥር 14 የሚደርሱ የተለያዩ የቁጥቋጦ ዝርያዎች፣ 10 ዓይነት የሳር ዝርያዎች እንዲሁም 16 ዓይነት የዓሳ ዝርያዎች በአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ አሉ።
ከሁለት ወር ገደማ በፊት ጎንደር ዩኒቨርሲቲ አልጣሽ ብሔራዊ ፓርክን እንታደገው ብሎ የአማራ ክልል ዩኒቨርሲቲዎችን ለአጋርነት ጠርቶ ነበር። ይህም ጥሪ ለሚመለከታቸው ሁሉ ጭምር የቀረበና ብዙዎችም የተሳተፉበት ነው። ዶክተር ደሳለኝ ይህን ጥሪ ባቀረቡበት ወቅት፤ ፓርኩን በግራና በቀኝ ካጀበው አደጋ ለመታደግና በውስጡ ያለውን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም ነቅቶ መንቀሳቀስ እንደሚገባ ገልጸውም ነበር።
በዛም ላይ በፓርኩ ላይ ጉዳት ሳይደርስ ነገር ግን ለማኅበረሰቡ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በመፍጠር እንዲንከባከበው ማድረግ ይቻላል ብለዋል። ከዛም ጎን ለጎን መሰረተ ልማቱ እጅግ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያለና መንገድ እንኳ የሌለው
መሆኑንም አንስተዋል። መንገድ መስተካከል እንዳለበት፤ የሰው ኃይል እጥረት እንዳለና የጠባቂዎች ቁጥር አነስተኛ መሆኑን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምርምርን የማህበረሰብ አገልግሎት ቡድን ማየት መቻሉን ጠቅሰዋል።
«እጅግ አደገኛ በሆነ ፍጥነት ዛፎች እየተጨፈጨፉና ደኑ በቃጠሎ እየጠፋ ነው።» ያሉት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቀድሞው ፕሬዚዳንት፤ በሱዳን አቋርጠው የሚመጡት «ፈላታ» የተባሉ ሰዎች በጣም የታጠቁ መሆናቸውንም አንስተዋል። ይህም እየገፋ ከሄደ የሰሃራን በረሃ ሊከላከል የሚችለውን ደን ማጣት፤ ስነ ምህዳሩ ላይም ተጽእኖ እንደሚኖረውም ጭምር ያሳስባሉ።
ኢትዮጵያ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ሆና ገና ያልተዳሰሱና ጥቅም ላይ ያልዋሉ እጅግ በርካታ የተፈጥሮ ጸጋና ስጦታዎች አሏት። ይህ መልካም ሆኖ፤ እንደ አገር ሀብቱን እንዴት መጠቀም እንደሚገባ ባለማወቅና ከዛሬ አሻግሮ ለማየት በመሳን ምክንያት፤ ከኢትዮጵያ ደጅ ሞፈር እየተቆረጠ ነው። ይህን የአልጣሽን ነገር አነሳን እንጂ፤ ምን ያህል አቅም እንደሌለ የሰሞኑ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የእሳት ቃጠሎ አሳይቶናል። ከዚህ ግን ክፍተትን እየሞሉ ለነገ የተሻለ መሆን ላይ ማተኮር ይገባል።
አልጣሽን ከፈላታዎችም ሆነ ከራሳችን ጥፋት ለማዳን የሁሉም ርብርብ ይጠየቃል። የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጥሪና ጩኸትም ሁሉም ተጋርቶ ሊያስተጋባና፤ የጋራ የሆኑ ሀብቶቻችን ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል። አገር በሰዎች እርስ በእርስ መገፋፋት ብቻ ሳይሆን የተፈጥሮ ሀብትን ካለአግባብ በማባከንና ሚዛኑን በማዛባትም ልትፈርስ፣ ልትጎዳና ልትጠፋ ትችላለችና፤ በጎረቤት አገራት እየደረሰ ያለውን የተፈጥሮ አደጋም አይተን፤ ይህን ችላ ማለት የለብንም።
በቸልታም ይሁን በመዘንጋት ትኩረት ያልተሰጠውና እኛም አክብረን ያላስከበርነው፤ ደግሞም እንደ ሞኝ ሌሎች ሞፈር የሚቆርጡበትን የእኛውን አልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ በስስት ልንጠብቅ ይገባል። ሁሉም በያለበት ሥራውን ቢሠራ መልካም ነው። እንግዲህ ነገራችንን ከማብቃታችን በፊት ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም አልጣሽ ፓርኩን ጎብኝቶ በነበረ ጊዜ «አልጣሽ አረንጓዴው ዘብ – የቋረኞቹ ምድር» በሚል ርዕስ ከጻፈውና በድሬ ትዩብ ከሰፈረው ጽሑፍ አንዱን አንቀጽ እንካችሁ፤
«ከተራራው አናት ሆኜ አልጣሽን አየሁት። የመለሰኝ አድማስ ነበር። ሰሚ ካገኘሁ ለሀገሬ መንግሥት መንገር እፈልጋለሁ። አፍንጫችን ላይ የሚገኘው የሱዳኑ ዳንዲር ደን አልጣሽ ያልተመቻቸውን ዱር እንስሳት ተቀብሎ ያስተናግዳል። እነሱም እንደ ሰው እንዳይሰደዱ አልጣሽን እንጠብቀው። እንዴት በገዛ መሬቴ ላይ ስለ ናይጄሪያ አርብቶ አደር እሳቀቃለሁ። የቀረንን ካልጠበቅን ምንም አይቀረንም።» ሰላም!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6/2011
ሊድያ ተስፋዬ