ኢትዮጵያ ውስጥ መብት በገንዘብ የሚገዛበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ ሕዝብ በአገልግሎት አሰጣጥ፣ ከመሬት ጋር በተያያዙ አሠራሮች፣ በፋይናንስ ዘርፍ፣ በሽያጭና ግዥ ሂደቶችና በፍትሕ አደባባዮች ቅሬታ እያሰማ ነው ። ችግሩ ከዕለት እለት እየተባባሰ እንጂ ሲሻሻል አይታይም።
ለዚህም ከሙስና ወንጀል ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጠንከር ያሉ ሕጎች ቢኖሩም አተገባበራቸው በመላላቱ፣ በሙስና የተሳተፉ አካላትን የማጋለጥና በሕግ የመጠየቅ ሁኔታ እምብዛም መሆኑ እንደምክንያት ይነሳል፡፡ ለዚህም መንግስትን ጨምሮ መላው ሕዝብ ተጠያቂ ስለመሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ።
በርግጥ ስለ ሙስናና ሊያስከትል ስለሚችለው አገራዊ አደጋ ብዙ ቢወራም፤ ችግሩን መዋጋት የሚችል ተቋም ተቋቁሞ ወደ ስራ ቢገባም፤ ለችግሩ በመንግስት ደረጃ የተሰጠው ትኩረት የችግሩን ያህል ባለመሆኑ ዛሬም ሙስና አገራዊ አጀንዳ ሆኗል።
አሁን ላይ ችግሩ የደረሰበት ደረጃም የከፋ ስለመሆኑም ዜጎች በእለት ተእለት ሕይወታቸው እየታዘቡት ያለ ተጨባጭ እውነታ ከሆነ ውሎ አድሯል። ይህን ጉዳይ ለመገንዘብ ወደ አንድ መንግስታዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ጎራ ማለት በራሱ በቂ ነው፡፡
የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት ማግስት ጀምሮ ሙስናን አምርሮ መታገል እንደሚገባ በተደጋጋሚ በአደባባይ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
‹‹ሙስና ዛሬ የአገራችን የደኅንነት ሥጋት ሆኗል፡፡ ወደ ብልጽግና የምናደርገውን ጉዞ እጅ ተወርች አሥሮ ለመያዝ ከጠላቶቻችን እኩል ሙሰኛው እየታገለን ነው፡፡ ሕዝባችን በአገልግሎት አሰጣጥ፣ ከመሬት ጋር በተያያዙ አሠራሮች፣ በፋይናንስ ዘርፍ፣ በሽያጭና ግዥ ሂደቶች፣ በፍትሕ አደባባዮች፣ በተለያዩ የመንግስት ተቋማት፣ የልማት ድርጅቶች፣ የህዝብ ተቋማት ወዘተ. በሚያጋጥመው ሙስና እየተማረረ ነው፡፡ …ከጸጥታ ሥጋቶች እኩል ሙስና የብልጽግና ጉዟችን ዋናው ዕንቅፋት ሆኗል›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ችግሩን አምርሮ መታገል እንደሚገባ ሲያሳስቡ የቆየት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሰሞኑን ደግሞ ችግሩን በዘመቻ መዋጋት የሚያስችል ስትራቴጂ ነድፈው ሰባት አባላትን ያቀፈ ብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ መቋቋሙንም ይፋ አድርገው ስራ አ ስጀምረዋል፡፡
መንግሥት የችግሩን አሳሳቢነት ተረድቶ ኮሚቴ ማቋቋሙ፣ በየደረጃው ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በተመሳሳይ ኮሚቴ ማቋቋማቸው ይበል ያሰኛል፡፡ በውሳኔው ማግስት የተጀመሩ ርምጃዎችም ይበረታታሉ። ነገር ግን ሥር የሰደደውን የሙስና ችግር በዚህ ብቻ ሊፈታ እንደማይችል ይታመናል፡፡
መንግሥት ባለፉት ዓመታት በጦርነት፣ በኮቪድ ወረርሽኝና መሰል የቤት ስራዎች በመጠመዱ ትኩረቱን ወቅታዊ በሆኑ ጉዳዩች ላይ ማተኮሩን ተከትሎ/ምክንያት በማድረግ ችግሩ ተስፋፍቶ፣ ሕጋዊ የሚመስል ስሪት ተበጅቶለት ታይቷል፡፡ ሌቦችም አገራዊ ችግሮችን እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅመውበታል። ይህን ችግሩን ለማስወገድ ለሚደረገው ትግል ”በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ” ሆኖበታል።
በርግጥ በነዚህም አገራዊ አስቻጋሪ ወቅቶች ሙስናን መታገል የሚያስችሉ ጥረቶች የሉም ማለት አልነበረም፤ ጥረቶች ተደርገዋል። ውጤታቸው ግን እንዲህ ነው ተብሎ አፍ ሞልቶ መናገር የሚያስችል አይደለም።
ለምሳሌ የአደጋ ስጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ከሙስና ጋር በተያያዘ ተጠያቂ ሆነው ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት እየተከታተሉ ናቸው፡፡ ችግሩ ግን አንድን አመራር ፍርድ ቤት በማቅረብ እና ተጠያቂ በማድረግ የሚፈታ አይደለም።
በተቀናጀና ዘላቂነት ባለው መልኩ ከፍ ባለ ቁርጠኝነት ሊተገበር የሚገባ ነው፤ ለሙስና በር የሚከፍቱ አሰራሮችን ከመድፈን ጀምሮ፤ ሙሰኞችን ለፍርድ በማቅረብ እና ለጥፋታቸው ተመጣጣኝና አስተማሪ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል። ለሙስና የበለጠ ተጋላጭ ናቸው የሚባሉ ተቋማት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል።
ከሁሉም በላይ የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ የተሰጠውን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣትና ትርጉም ያለው ውጤት ለማምጣት እንዲችል የኅብረተሰቡ ሙሉ ትብብር ወሳኝና እጅግ አስፈላጊ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
ሌቦችን የሚያጋልጡ ሰዎችን በመሸለም እና ከለላ በመስጠት ማበረታታት አስፈላጊ ነው፡፡ ማኅበረሰቡ የሚጨበጥ ነገር ማየት ስለሚፈልግ መሬት ላይ የሚታይ ርምጃ እየወሰዱ ሕዝብ በመንግሥት ርምጃ መተማመን እንዲኖረው ማድረግ ይገባል።
በርግጥ የሙስና ወንጀል በሚስጥርና በጥንቃቄ የሚፈጸም ወንጀል እንደመሆኑ ስርቆት መፈጸሙን ለማወቅ የሚያስችል ምንም አይነት ምልክት ማግኘት አይቻልም፡ ፡ ድርጊቱ በድብቅ እና በሚስጥር ከመፈጸሙ ባሻገርም አጥፊው ለምርመራ መነሻ ሊሆን የሚችል አሻራ የማጥፋት አቅም ስላለውም ከነባር ወንጀሎች ለየት ያደርገዋል፡፡
የሙስና ወንጀል በቀጥታ በአንድ ግለሰብ ወይም ቡድን ላይ የሚያደርሰዉ ጉዳት ላይኖር ይችላል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ በአገርና በህዝብ ላይ የሚያሳርፈው ጉዳት ግን እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ግለሰብ ወይም ቡድን በቀጥታ ተጠቂ ስለማይሆንም ወንጀሉ ተፈጽሞ እንኳ ቢገኝ ያገባኛል ብሎ ጉዳዩን ለህግ የሚጠቁም፣ አስፈላጊዉን ማስረጃ በማቅረብ እንዲመረመርና አጥፊዎች እንዲቀጡ የሚያደርግ ሰው ላይገኝ ይችላል፡፡ በዚህም ምክንያት ወንጀሉ ሳይጣራ ተዳፍኖ የሚቀርበት አጋጣሚ እጅግ ብዙ ነው፡፡
ከዚህ አንጻር ዜጎች ስለሙስና በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በስፋት መስራት ያስፈልጋል። የሙስና ወንጀል አገርን አደጋ ውስጥ በመክተት ትውልድ ተሻጋሪ ችግር ምንጭ ሊሆን እንደሚችል ተረድቶ ሊዋጋው የሚችልበትን የአይምሮ ዝግጁነት መፍጠር ወሳኝ ነው።
በኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥታዊ ሌብነት/ሙስና ከጊዜ ወደ ጊዜ መልኩን እየቀያየረና በጣም ተቋማዊ በሚመስል ደረጃ ጎልብቶና የአገር ህልውና ስጋት ሆኖ ይታያል፡፡ ግለሰቦች ተጠያቂነትን ባለመፍራት ጭምር በአደባባይ የሚያደርጉት ነገር እየሆነ መጥቷል።
ለውጡ እንዲመጣ አንዱ ምክንያት ሕዝቡ በመንግሥታዊ ሌብነት እጅግ በመማረሩና ያንን ለማስወገድ በተደረገ ትግል እንደነበር ማንም የሚዘነጋው አይመስለኝም፡፡ በተለይም በሕዝባዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ማለትም እንደመሬት አስተዳደርና ገቢዎች አካባቢ የነበረው ችግር ማንሳት ይቻላል፡፡ ይህ ደግሞ የሕብረተሰቡን አቅም በመፈታተኑ መንግሥት ላይ ያለው እምነት ተሸርሽሮ ወደ ተቃውሞ ማምራቱን መንገር ለቀባሪው ማርዳት ይሆናል፡፡
ችግሩ አሁን ላይ በመንግሥታዊ መዋቅር ስር የሰደደ ሆኗል፡፡ የሌብነት ሰንሰለት ተዘርግቶለት በከፍተኛ አመራሮች ጭምር እየተሠራ መሆኑ ችግሩን ለመቅጨት አዳጋች ሊያደርገው እንደሚችል መገመት ይቻላል። በሙስና ላይ የሚደረገው ትግል በሚፈለገው ደረጃ ውጤት እንዳያመጣ ምክንያት የሆነው ሌብነት /ሙስና ባህል መሆኑና እንደመብት የተቆጠረበት ደረጃ መድረሱ ነው።
ወቅታዊው አገራዊ የፖለቲካ ችግር እንደሽፋን በመጠቀም ሰዎች ዘርፈው ሲጠየቁ ብሄርንና ሃይማኖትን እንደ ሽፋን በመጠቀም በሙስና ወንጀል ተጠይቀው የፖለቲካ ምህዳርን ለማስፋት በሚል የሚለቀቁ ሰዎች መኖራቸው ሌብነት እንዲበረታታ ስለሚያደርግ ሁሉም በኔነት ስሜት ሊታገለው ይገባል፡፡
በአጠቃላይ ሌብነትና ሌቦች ላይ የተጀመረው አገር አቀፍ ዘመቻ ኮሜቴ ከማቋቋምና መግለጫ ከመስጠት ባለፈ በተጨባጭ ወንጀለኞቹን የማጋለጥና ለህግ አሳልፎ መስጠትን ይጠይቃልና የተጀመረው እርምጃው ተጠናክሮ ይቀጥል እላለሁ፡፡
ሜሎዲ ከኳስ ሜዳ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 6/2015