እማማ ጽዮን ሚካኤል አንዶም፤ የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ ባሕላዊ አልባሳት ፋሽን ዲዛይነር፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል፣ የሴቶች ማኅበር፣ ማየት የተሳናቸውና ቼሻየር ሆም ምግባረ ሰናይ ድርጅቶች መስራችና የቀድሞው የኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳዳር ደርግ ሊቀመንበር ጄኔራል አማን አንዶም ታላቅ እህት ናቸው። እኛም በዛሬው የባለውለታዎቻችን አምድ ላይ እኝህን የአገር ባለውለታ ልንዘክራቸው ወደናል።
የአገር ባህል አልባሳቶቻችን የእኛነታችን መገለጫ መሆናቸው እውነት ነው፤ እማማ ጽዮን አንዶምንም የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊ የባህል አልባሳት ዲዛይነር ያደረጋቸው ይኸው ነው። የአገር ባለውለታዋ እማማ ጽዮን የስራቸውን ያህል ብዙ የተነገረላቸው ባይሆኑም አገራቸውን በሚገባ አስተዋውቀው፣ ትውልድን በሙያቸው ጠቅመውና አስተምረው፣ ባህልን ማስተዋወቅ ብቻ ሳይሆን እራሳቸው ቱባ ባህል ሆነው ወደ’ማይቀርበት በመሄዳቸው ታሪካቸውን በደማቅ ቀለም ያጽፈዋል። እማማ ጽዮን አገርም ባህልም ነበሩ።
የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት የፋሺን ዲዛይነር … እማማ ጽዮን ሚካኤል አንዶም ካርቱም ከተማ ውስጥ የተወለዱ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ የባህላዊ አልባሳት በዘመናዊ መልኩ እንዲቀርቡ ያደረጉት ጥረትም ከፍ ያለ ዋጋን ያሰጣቸዋል። የአገር ባለውለታም ናቸው። በበጎ አድራጎት ተግባራቸውም ይታወቃሉ። ሁል ጊዜም የባህል ቀሚስ የሚለብሱት እማማ ጽዮን፣ እድሜያቸው ገፍቶ እንኳ መኪናቸውን የሚያሽከረክሩት፣ ልብሳቸውን የሚያጥቡትና ሌሎች ተግባሮቻቸውን የሚያከናውኑት … ራሳቸው እንደነበሩ የቅርብ ሰዎቻቸው ይናገራሉ። እማማ ጽዮን በ100 ዓመታቸው ነው ያረፉት። እማማ ጽዮን የጀግናውና የስመጥሩ የጦር አለቃ የጀኔራል አማን ሚካኤል አንዶም ታላቅ እህትም ነበሩ። ትግርኛ፣ አማርኛ፣ አረብኛ፣ ጣሊያንኛና እንግሊዝኛን አቀላጥፈው ይናገሩም ነበር። የአገራችን ሴቶች ከእማማ ጽዮን ሚካኤል አንዶም ጥንካሬና ስኬትን ሊማሩም ይገባል የሚል የግል አስተያየት ባክልም እወዳለሁ ።
የተለያዩ በጎ አድራጎት ድርጅቶች መስራች የሆኑት እማማ ጽዮን ሚካኤል አንዶም፤ ስለ ኢትዮጵያ ባሕላዊ ፋሽን ጅማሮ፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አመሰራረትና ስለ ታናሽ ወንድማቸው በአንድ ወቅት ከተናገሩት ውስጥም “… እኛ የተወለድነው ሱዳን ካርቱም ከተማ ነው፤ ለዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ አባታችን አስመራ ከተማ ላይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ከፍ ላለ የትምህርት ሁኔታ ወደ ሱዳን ካርቱም መሄድ ስለነበረባቸው ነው። በሱዳን ካርቱምም አባታችን የከፍተኛ ትምህርታቸውን አጠናቀው ከእንግሊዞች ጋር ጥሩ ስራ በማግኘታቸው እዛው በመቆየት እኛም ተወለድን” የሚለው ይታወሳል።
የእማማ ጽዮን አባት ብዙ ቋንቋዎች መናገር የሚችሉም ስለነበሩ ለፈረንጆቹ በአስተርጓሚነትም መስራታቸውን ከህይወት ታሪካቸው እንረዳለን። የእማማ ጽዮን አንዶም አባትም ልጆቻቸውን ሱዳን ካርቱም ላይ ይውለዷቸው እንጂ ያደጉት አዲስ አበባ ከተማ ነው።
እማማ ጽዮን ስለ እናታቸውም ይህንን ብለው ነበር “… እናቴ በወቅቱ የተማረች ቢሆንም ትምህርቷ ግን ዘመናዊ ትምህርት ሳይሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት፤ እንዲሁም የቤት ሙያን ያካተተ ነበር። ነገር ግን እድገቷ ከስዊድኖች ጋር ስለነበር ዘርፈ ብዙ የምትባል ባለሙያ ነበረች፤ በዚህም የሁሉንም ልጆቿን ልብስ ቤት ነበር የምትሰፋው።”
የእናታቸው የልብስ ስፌት ሙያ ደግሞ እማማ ጽዮንንም ይስባቸው ስለነበር ስፌትን ገና በ12 ዓመት እድሜያቸው ይሞካክሩት ነበር፤ የአባታቸው በርካታ ቋንቋ ተናጋሪነትም ወደ’ሳቸውም ሄዶ አምስት ያህል ቋንቋዎችን አቀላጥፈው መናገርም አላቃታቸውም። በተለይም የልብስ ስፌት ሙያ ተሰጥጾአቸውን ያዩት አባታቸው ዝም ሊሏቸው አልፈለጉም፤ እናም ስጦታ ብለው የስፌት መኪና ገዝተው ሰጧቸው። በዚያም ለአሻንጉሊቶቻቸው ልብስ እየሰፉ ቀስ በቀስም የራሳቸውን ልብስ ሰፍተው እስከመልበስ የሚያደርስ ባለሙያ ሆኑ። እማማ ጽዮን በራሳቸው ይህንን ያህል ርቀት ይሂዱ እንጂ ኋላ ላይ አባታቸው አስተማሪ ቀጥረውላቸውም ልብስ ስፌት እንዲማሩ አድርገዋቸዋል።
በወቅቱ ፋሽን የሚባል ነገር ባይኖርም የአገራቸውን ጥበብ ሲያዩትም ሲለብሱትም እጅግ ያስውባቸው ስለነበር ለምን በተለያየ ፎርም አልሰራውም ብለው ተነሱ፤ በዚህም አንድ የአገር ባህል ልብስ ይሰሩና ደረቱና እጅጌው ላይ ጥበብ እያስገቡ ሌላ ገጽታን ይፈጥሩለት ያዙ፤ ይህ ሁኔታ ደግሞ ተወደደላቸው።
….. በ5 ሳንቲሜትር የተለመደውን የጥበብ አሰራር እሳቸው ወደ 50 ከዚያም ቀስ ብለው እስከ ሶስት ሜትር ርዝመት ያለው ጥበብ በመስራት ብቸኛዋና የመጀመሪያዋ ዲዛይነር ሆኑ። በወቅቱ ሴቶች በጣም ተማሩ ከተባለ 8ተኛ ክፍል ድረስ ብቻ ነበር፤ እሳቸው ግን አጋጣሚው ተመቻችቶላቸው በእንግሊዝ ትምህርት ቤት 12ኛ ክፍል የመድረስን እድል አግኝተዋል። ይህ ሁኔታ ታክሎበት በራሳቸው የሚተማመኑ፤ ለሚሰሩት ስራ ሙሉ ኃላፊነትን የሚወስዱ ልበ ሙሉ ሴትም አድርጓቸዋል። በወቅቱ ልብስ ሰፍቶ ለሌሎች ሰዎች መሸጥ በጣም ነውር የነበረ በመሆኑ እማማ ጽዮን የሰሯቸውን ልብሶች ራሳቸው ነበር የሚለብሷቸው። የጃንሆይ ልጆችና የልጅ ልጆች ደግሞ እርሳቸው የሚለብሱትን ባዩ ጊዜ “ስሪልን” እያሏቸው ይሰሩም ነበር።
በጣም የሚገርመው ነገር ግን የንጉሣውያኑ ቤተሰቦች በዚህን ያህል ስራዎቻቸውን ወደውት ”ስሪልን” ይበሏቸው እንጂ ገንዘብ መቀበል ነውር ስለነበር በነጻ ነበር የሚሰጧቸው። “… በገንዘብ ሳይሆን በነጻ እሰራ ነበር። በኋላ ግን የሰው ፍላጎት እየጨመረ ሲመጣ ቤቴ መስራት ጀመርኩ፤ ግን ’ቤት መስራት አይቻልም’ በመባሉ እንደምንም ሱቅ ከፍቼ መስራት ጀመርኩ”።
“………. በወቅቱ ሴት ልጅ ከቤቷ ወጥታ አደባባይ ሱቅ መቆም በራሱ አስቸጋሪ የነበረ በመሆኑ ብዙ ተቸግሬያለሁ። ግን ደግሞ የነገስታቱ ቤተሰቦች እኔ እንዳላፍ? እንድበረታታ እኔ ጋር ቁጭ ብለው ይውሉ ነበር። ከዛ በኋላ ግን ሰውም እየለመደው እኔም መስራቱ ሱስ እየሆነብኝ፤ ሱቅ ከፍቶ መቀመጥም ነውር እንዳልሆነ ተረድቼ ስራዬን መስራት ቀጠልኩ” በማለት መናገራቸው ይታወሳል።
እማማ ጽዮን ባለቤታቸውም ዲፕሎማት ስለነበሩ ለውጪው ዓለም ቅርብ ነበሩ። አጋጣሚውንም በመጠቀም ፈረንጆች ባህላዊ ልብሳችንን እንዲያውቁ የላቀ ጥረት አድርገዋል። በዚህም ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ አሳውቀዋታል።
እማማ ጽዮን “…….. ፈረንጆች የእሱን ልብስ ዓለም ይለብሰዋል፤ የእኛ ግን ከሁሉም ይለያል። እኔ ለብሼ ሲያዩኝ ከፍ ባለ የደስታ ስሜት ውስጥ ገብተው ይገዙኛል፤ ይለብሳሉ፤ እኔም በፋሽን እሰፋለሁ” በማለት ነበር ሁኔታውን የገለፁት።
በተደጋጋሚ ቃለ ምልልስ ያደረገችላቸው የቀድሞ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ባልደረባ ስንዱ ሃይሌ ሞታቸውን ተከትሎ በማህበራዊ ገጿ ላይ እንዳሰፈረችው “… በውጭ አገር እያሉ ለቤተክርስቲያን የሚያገለግለውን፣ የሚያብለጨልጨውንና ዳር ዳሩ ዘርፍ ያለበትን ጥላ አጥልቼና ራሴ ዲዛይን ያደረኩትን የተለያየ የአገር ባህል ልብስ ለብሼ ስወጣ ’ዛሬ ደግሞ ንግሥት መስላለች’ ይሉኝ ነበር” ማለታቸውን ታስታውሰናለች።
በሌላ ቃለ ምልልሷ ደግሞ «የሚገርምሽ ጥላውንም እንደ ባህሌ መገለጫ አይቼ እንጂ ከቤተክርስቲያን ውጭ እንደማይያዝ አላውቅም ነበር።» እንዳሏት አካፍላናለች። ስንዱ ስለእማማ ጽዮን ስትገልጽ “…. ሰው ወዳድ፣ ሳቂታ፣ አንደበታቸው እንደ ሕጻን ልጅ የሚጣፍጥ፣ ሁሉን ተቀባይ ናቸው። በተደጋጋሚ ላም በረት አካባቢ ወደ’ሚገኘው ቤታቸው ሄጃለሁ። ከእማማ ጽዮን ጋር የነበሩኝ ቆይታዎች ዛሬን የሆኑ ያህል እንደ ስዕል ይታዩኛል። የአገር ልብሳቸውን ለብሰው፣ ነጠላቸውን አጣፍተው ልብስ ሲሰፉ፣ «ምክንያት ካልሆነ በስተቀር የአገር ልብስ ለሥራ አይመችም የምትሉ ወጣቶች ትክክል አይደላችሁም። ይኸው እኔ ለብሼ እየሠራሁ፤ እያየሽኝ አይደል?» እያሉ በተግባር እውነታውን ሲያሳዩኝ የምመልሰው አልነበረኝም። ያኔ እንደነገሩኝ ከአገር ልብስ ውጪ በቤት ውስጥም ሆነ ውጭ ሌላ ልብስ አልለበሱም። የላቸውምም። ማየት ማመን አይደል፤ ነጭ ልብስ ብቻ የሞላውን ቁም ሳጥናቸውን ከፍተው ሲያሳዩኝ ዓይኔንም፣ አፌንም ከፍቼ ቀርቻለሁ። ከአግራሞቴ የመለሱኝ ያቺ ደስ የምትል ቀጭን ሣቃቸው ነበረች። በወቅቱ ልብስ ከሚሰፉበት ከቤቱ ጀርባ ካለው ክፍል ዳር ላይ ሸማኔዎችም አብረዋቸው እንደሚሠሩ አስጎብኝተውኛል” ትላለች።
እማማ ጽዮን፣ ቀደም ሲል ይሠሯቸው የነበሩ በሙሉ ጥበብ የተሰሩ ቀሚሶች የሚያምሩ ቢሆኑም፣ «ሙሉ ጥበብ ቀሚስ የእኛ አይደለም። ያኔ ስህተት ሠርቻለሁ። የእኛ አገር ልብሶች በነጩ ፈትል ላይ ታቹ ጥበብ የሚሠራበት ነው» ሲሉ ሌሎችም ሙሉውን ጥበብ የሆነ ቀሚስ እንዳይሠሩና ያ ከሆነ ኢትዮጵያዊ የባህላዊ ልብስ እንዳልሆነ መክረው ነበር። የአገር ልብስ ነጠላ ከሌለው ጎዶሎ ባህልም እንደሆነ ነው በተደጋጋሚ ሲገልጹ የነበረው።
እማማ ጽዮን እድሜ ልካቸውን ለጤናቸው ተስማሚ የሆነ ምግብን የሚያዘጋጁት ራሳቸው ነበሩ። በ80ዎቹ እድሜ ክልል ሆነው መኪናቸውን (ቀይዋን) ሲያሽከረክሩም ለተመለከታቸው ያስገርማሉ። የእስር ቤት ታሪካቸውንና የወንድማቸውን አገዳደል ደጋግመውም ያነሳሉ። ለንጉሡ ካባ ወስደው ሽልማት እንኳ እንዳልሰጧቸውም እንደዚያው።
እማማ ጽዮን ከፋሽን ዲዛይነርነታቸው ባሻገር የሴቶች መብት ተሟጋችም ነበሩ። ስለሴቶች ጉዳይ ብዙ ቢሉም “ሴት ዘውዷ ቤቷና ቤተሰቧ ነው። ሴት ቤት ትሰራለች። ወንድ ወጥቶ ገንዘብ ያመጣል። ቤቱን የምታስተዳድረው ሴት ናት። ነገር ግን አሁን ላይ የወንዶችን ቦታ እየያዙ ነው ሰርተውም ገንዘብ እያገኙ ነው፤ ይህ ደግሞ ሴቶች በወንድ እጅ ተዳዳሪ እንዳልሆኑ ያሳየ በመሆኑ እኩልነቱ ጥሩ ነው። ተጋግዘን ቤተሰባችንን እንምራ ማለትም ክፋት የለውም። ነገር ግን ሴቶች ውጪ ውጪውን እያሉ ቤታቸውን፣ ልጆቻቸውን መርሳት አይገባም” ሲሉም መክረው ነበር።
እማማ ጽዮን በደርግ ጊዜ ለሰባት ዓመታት በእስር ለማሳለፍ ተገደው ነበር። “…. መጀመሪያ እስር ቤት ስገባ ተደናግጬ ነበር፤ ኋላ ላይ ግን ሁሉንም ለመድኩት፤ እንደውም 20 ልጆችን አስተማርኩ፤ አሳደኩ። “… ሴቶች ወደ እስር ቤት አርግዘው ይመጣሉ፤ እዛው ይወልዳሉ፤ ሁኔታው ደግሞ ልጆችን ለመንከባከብ ምቹ አልነበረም፤ እኔም ልብሴን እየቀደድኩ ለህጻናቱ ልብስ እየሰፋሁ እያለበስኩ ቆየሁ። ይህንን የሰሙ በውጭ ያሉ ሰዎች ደግሞ ጨርቅ ይልኩልኝ ጀመር፤ ይህ ደግሞ በእስር ላይ ያሉ ሴቶችን የልብስ ስፌት ሙያ እንዳስተምር በር ከፈተልኝ። በሌላ በኩልም እስር ቤት መግባቴም ብዙ ሰው እንዳውቅ። የተለያዩ ባህርያትን እንድለምድ ስላስቻለኝ እስር ቤቱ ለእኔ ጥሩ የደስታ ቤቴ አደረኩት” በማለት ተናግረውም ነበር።
እማማ ጽዮን በእሌኒ ባርተን አማካይነት ወደ ቀይ መስቀል ስራም ገብተዋል። የመጀመሪያውን የበጎ አድርጎት ድርጅትም በማቋቋም ለብዙዎች ተምሳሌት የሆኑም ሴት ነበሩ።
ስለ እማማ ጽዮን ሚካኤል አንዶም ተናግሮ፣ በደርግ ዘመን የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ስለነበሩት ታናሽ ወንድማቸው፣ አማን ሚካኤል አምዶም አለመናገር ከባድ ነው።
… አማን ሚካኤል አምዶም (ኮዳ ትራሱ) በመባል የሚታወቁት የጦር ጀግና ወደ ካርቱም ለትምህርት ቢላኩም ከጣሊያን ጋር በነበረው ጦርነት ከብሪቲሽ ኮመንዌልዝ ጦር ጋር በ1933 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ። ውትድርናን የመረጡት አማን በውትድርና አገልግሎታቸው በፍጥነት በማደግ ኮርያና ኮንጎ ከመዝመት አልፎ በሀረር የሚገኘው የሶስተኛው ክፍለ ጦር (ዕዝ) አዛዥ እስከመሆን ደርሰዋል። ከሶማሌ ጋር በኦጋዴን በተደረገው ጦርነት ጀግንነታቸው የተመሰከረው አማን በወታደሮቹ ”የኦጋዴኑ አንበሳ” እየተባለ ይጠሩ እንደ ነበር በሰዋሰው ድረ-ገፅ ላይ ሰፍሮ ይገኛል።
አንዳንዶች ቢቃወሙትም … ተራማጅ የነበሩት አማን የኢትዮ-ኤርትራ አንድነት አቀንቃኝ ነበሩ። ንጉሱ የእንዳልካቸውን ካቢኔ አፍርሰው ልጅ ሚካኤል እምሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ሲያደርጉ አማን የመከላከያ ሚኒስቴር ሆኑ። ይሁን እንጂ፣ የደርግ አባል ባይሆኑም ደርግ ሲመሰረት ከአባላቱ ጋር ግንኙነት እንደነበራቸው ይነገራል።
በኤርትራ አማጽያንና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል የነበረው አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ይመኙ የነበሩት አማን ባለ 19 ነጥብ እቅድ አቅርበውም እንደ ነበረም ድርሳናት ያመለክታሉ።
… መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ደርግ ንጉሱን ከስልጣን አውርዶ ስልጣን ላይ ሲወጣ አማንን የደርጉ ዋና ሊቀመንበር አድርጎ ሾመ። አማንም ከዚያ በፊት የነበረውን የኤርትራና የኢትዮጵያን ጉዳይ በሰላም የመፍታት ጥረት አጠናክሮ ገፋበት፤ በዚህ ምክንያትም የኤርትራ ጉዳይ የሚፈታው በወታደራዊ ርምጃ ብቻ ነው ብሎ ከሚያምነው መንግሥቱ ኃይለማርያም ጋር ግጭት ውስጥ ገቡ። ይህ ሁኔታ ያልተዋጠላቸው አማን በተሾሙ በሁለት ወሩ ከደርግ ዋና ሊቀመንበርነቱ ለቀቁ።
… በመጨረሻም በአሰቃቂዋ ህዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም ደርግ መኖሪያ ቤቱ ድረስ ታንክ ጭምር በመላክ የስልሳዎቹ ከፍተኛ ባለስልጣናትና ሌሎች በርካታ ወገኖች እልቂት ማሟሻ ሆኑ።
በዚህ አሰቃቂ ግድያም ምክንያት ታላቅ እህቱ እማማ ጽዮን የከፋ ሃዘን ውስጥ ገብተው እንደነበርና ከሀዘኑም አገግመው ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ለመመለስ ብዙ ጊዜን እንደወሰደባቸው በቅርብ የሚያውቋቸው ይናገራሉ።
እማማ ጽዮን ሚካኤል አንዶም የአገር ባለውለታ ቢሆኑም ህዳር 29 ቀን 2015 ዓ.ም አንድ ክፍለ ዘመን ሸምግለው በ100ኛ ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ነፍሳቸው በሰላም ትረፍ።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 5 /2015