ኢትዮጵያ በታላቁ የኦሊምፒክ መድረክ በታሪክ ማህደራቸው ካሰፈረቻቸው ደማቅ ታሪኮች ጎልቶ የሚጠቀሰው የአትሌቲክስ ስፖርት ስኬታማ ነው። ኦሊምፒክ ከውጤት ባሻገር ተሳትፎም ትልቅ ቦታ ይሰጠዋልና በዚያ ረገድ ያሉ ታሪኮችን ካገላበጥን የቦክስ ስፖርት በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ተሳትፎ ትልቅ ታሪክ አለው። ኢትዮጵያ በቦክስ ስፖርት ስምንት በሚሆኑ ኦሊምፒኮች ላይ ተካፋይ በመሆን ስፖርቱ በታላቁ መድረክ ተሳትፎ ለኢትዮጵያ ከአትሌቲክስ በመቀጠል ሁለተኛ ደረጃን ይይዛል።
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ የቦክስ ስፖርት የተሳትፎ ታሪክ የሚጀምረው በሜክሲኮ ኦሊምፒክ ሲሆን፤ በሙኒክ፣ ሞንትሪያል፣ ሞስኮ፣ ባርሴሎና፣ አትላንታ፣ ሲድኒ፣ አቴንስ እና ቤጂንግ ኦሊምፒኮች በተከታታይ መሳተፍ ተችሏል። በዚህ ሁሉ የተሳትፎ ታሪክ ውስጥ ግን ኢትዮጵያ በውጤታማነት አገሯን ማስጠራት አልቻለችም። ይልቁንም ስፖርቱ ሲነሳ በሄዱበት አገር ስለሚጠፉ ቦክሰኞች የሚወሳው ታሪክ ያመዝናል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ ለሶስት የኦሊምፒክ ዓመታት ከቦክስ ስፖርት ተሳትፎ መራቅ በኋላ በመጪው የፓሪስ ኦሊምፒክ ዳግም በመድረኩ ለመሳተፍ ስለሚቻልበት ሁኔታ ከወዲሁ ማሰብ ተገቢ እንደሚሆን ይታመናል። በሲድኒ ኦሊምፒክ በስፖርቱ አገራቸውን ከወከሉ 4 የቡድኑ አባላት መካከል በብቸኝነት ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰውና በአሁኑ ወቅት በፌዴሬሽኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆነው ኮማንደር ጸጋስላሴ አረጋይ ነው። የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የቡጢ ተፋላሚው ፀጋስላሴ ታዳጊ ሳለ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በርካታ የቦክስ ክለቦች መኖራቸውንና ጥቂት የማይባሉ ውድድሮች በስፖርቱ ይዘጋጁ እንደነበር ያስታውሳል። ወደስፖርቱ ከገባበት ጊዜ አንስቶ እስከ ሲድኒ ኦሊምፒክ ድረስ በተሳተፈባቸው 102 ውድድሮች ላይ 100 በሚሆኑት ላይ በማሸነፍ 26 የወርቅ ሜዳሊያ 2የብር ሜዳሊያ፤ በግብጽ በተካሄደ የዞን 5 ጨዋታ የወርቅ እንዲሁም 7ኛው መላ አፍሪካ ጨዋታ የብር ሜዳሊያ በማግኘት በሲድኒ ኦሊምፒክ ለመሳተፍ መቻሉንም ይጠቁማል።
ይህ ኦሊምፒያን እንደሚናገረው፣ ኦሊምፒክን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ የሚደረግ ተሳትፎ ቁርጠኝነት፣ የአገር ፍቅር ስሜት እንዲሁም በርካታ አዳዲስ ባህሎችንና ልምዶችን ያስገኛል። በመሆኑም ስፖርቱ በዋናነት የሚያስፈልገው ትኩረት ነው፤ እንደ አገርም ሆነ እንደ ክለብ ከፍተኛ ገንዘብ ወጥቶባቸው ከሚከናወኑ ስፖርቶች መካከል ቦክስ የለበትም። ነገር ግን ቦክስ በጥቂት ወጪ ውጤት ሊገኝበት የሚችል ስፖርት ነው። በመሆኑም ስፖርቱ አቅም አግኝቶ ቦክሰኞቹንም ወደ ውጤታማነት እንዲመራ እንዲሁም አስፈላጊውን ነገር ለማድረግ እንደ ስራ አስፈጻሚ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ ያብራራል። ለዚህ ደግሞ መንግስታዊው አካልም ሆነ ስፖርቱን ማገዝ የሚችሉ ሁሉ ከጎኑ እንዲሆኑም ጥሪውን አቅርቧል።
የቦክስ ስፖርት ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ስንታየሁ ተስፋዬ፤ የቦክስ ስፖርት ከኦሊምፒክ መራቁ ትልቅ ቁጭት እንደሆነ ይጠቁማሉ። የኢትዮጵያን የቦክስ ስፖርት ታሪክ ለማስቀጠልም ዘንድሮ አዳዲስ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል። የስፖርቱ ትልቁ ችግር የነበረው የገንዘብ እና የውድድር እድል ነው። በመሆኑም በተያዘው ዓመት እንዲሁም በ2016 ዓ.ም በዚህ ረገድ የተሻለ በመሆን ስፖርቱን ለማሳደግ ፌዴሬሽኑ ጠንክሮ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። በተለይም ፌዴሬሽኑ ቋሚ የሆነ እና አቅም ያለው ስፖንሰር በማፈላለግ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ ይህ ከሆነ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ተሳትፎ ላይ እክል የሆነውን የገንዘብ ችግር መቅረፍ ይቻላል ባይ ናቸው። ከዚህ ባሻገር ኢትዮጵያውያን ቦክሰኞች የቴክኒክ እና የአቅም ችግር የሌለባቸው እንደመሆኑ የውድድር ልምድ እንዲያገኙ በማድረግ ወደ ተሻለ ደረጃ መድረስ እንደሚቻልም እምነታቸውን ገልፀዋል።
ከዚህ ቀደም ፌዴሬሽኑ በዓለም አቀፍ ግንኙነቱ ላይ ችግሮች ሲስተዋሉ የቆዩ ሲሆን፤ ይህን በመቅረፍ በአሁኑ ወቅት መልካም በሚባል እንቅስቃሴ ላይ የሚገኝ መሆኑንም የፅህፈት ቤት ተወካዩ ያብራራሉ። የአፍሪካ ቦክስ ፎረም በቅርቡ በአዲስ አበባ ያዘጋጀው ፌዴሬሽኑ፤ በቀጣይም አዲስ አበባ ውስጥ የቦክስ ውድድሮችን፣ ጉባኤዎችን እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮችን ስለማከናወን ንግግር አድርጓል። በመሆኑም በዚህ መሰረት እንቅስቃሴው ከቀጠለ ስፖርቱ ሊያድግ የሚችልበት ወቅት ሩቅ እንደማይሆን አብራርተዋል።
ይሁንና የአገሪቷን ስፖርት በበላይነት የሚመራው የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ከሚያደርገው ድጋፍ ጋር በተያያዘ ክፍተት መኖሩን ኃላፊው ይጠቅሳሉ። ባለፈው ዓመት በቱርክ በተካሄደው የሴቶች የቦክስ ዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ ፌዴሬሽኑ አስፈላጊውን ዝግጅት ቢያደርግም መሳተፍ ግን አልቻለም። በተመሳሳይ ሁኔታ ዘንድሮም በስፔን በተካሄደ የታዳጊ ወጣቶች ቻምፒዮና ላይም መሳተፍ አልተቻለም። ለዚህ ዋነኛው ችግር ደግሞ በጀት ነው። በጥቂት ስፖርተኞችም ቢሆን አገርን መወከል ውጤታማ ያደርጋል፤ በመሆኑም ድጋፍ አስፈላጊ ነው። መንግስት እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት እገዛ ማድረግ ከቻለም እአአ በ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ ወደ መድረኩ መመለስ እንደሚችል ኃላፊው ያላቸውን ተስፋ ተናግረዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 5 /2015