በአገሪቷ እየታየ ያለውን የስኳር እጥረት ተከትሎ መንግስት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለሸማቾች የሚያቀርበውን ስኳር መጠን እየቀነሰ ይገኛል። በገበያ ላይ ያለው የስኳር ዋጋም አልቀመስ እያለ ነው። በአዲስ አበባ ከተማ ለአንድ ስኒ ቡና እንዲሁም ለአንድ ብርጭቆ ሻይ እየተጠየቀ ያለው ዋጋም የስኳር ገበያው ችግር ውስጥ መሆኑን ያመለክታል። አስር ብር ይሸጥ ለነበረው አንድ ስኒ የጀበና ቡና አሁን ከ15 እስከ 20 ብር እየተከፈለ ይገኛል፤ የአንድ ብርጭቆ ሻይ ዋጋም በተመሳሳይ ከ10 እስከ 15 ብር ነው ሲሉ ሸማቾች ይጠቁማሉ። የዚህ ምክንያቱ የስኳር አቅርቦት እጥረትና ዋጋ መናር መሆኑን ነው የሚገልጹት።
በቅርቡ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የ2015 ዓ.ም የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸሙን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅት በ2015 ዓ.ም ከውጭ ተገዝቶ መግባት የነበረበት የስኳር ምርት ወደ አገር ውስጥ አለመግባቱን አስታውቋል፤ በመንግሥት መጋዘኖች ለመጠባበቂያ የሚሆን የስኳር ምርት አለመኖሩንም ገልጾ፣ ይህ ሁሉ በአገሪቱ እየታየ ላለው የስኳር እጥረትና የገበያ ችግር እንደ ምክንያት እንደሚጠቀስ ተጠቁሟል።
መንግሥት በሩብ ዓመቱ ከ835 ሺ በላይ ኩንታል ስኳር ለማሠራጨት አቅዶ እንደነበረ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ አቶ ገብረ መስቀል ጫላ አስታውቀው፣ ያሰራጨው ግን 284 ሺ ኩንታል ብቻ መሆኑን ተናግረዋል። በሌላ በኩል በፍራንኮ ቫሉታ ከታክስና ከቀረጥ ነፃ አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ወደ አገር ውስጥ እንደገባም ተጠቅሷል።
ይሁን እንጂ መንግሥት ለማህበረሰቡ የሚያቀርበው የስኳር መጠን በአሁኑ ወቅት እጅግ ያነሰ መሆኑን ተከትሎ ከፍተኛ የስኳር እጥረት ተከስቷል፤ በሸማቾች ማህበራት አማካይነት ለማህበረሰቡ እየቀረበ ያለው የስኳር መጠን በእጥፍ መቀነሱ ይታወቃል። ከሸማቾች ማህበራት መደብሮች ውጭ ባለው ገበያም አንድ ኪሎ ስኳር ከ120 ብር እስከ 130 ብር እየተሸጠ ነው።
በስኳር አቅርቦት እጥረቱና እየታየ ባለው የዋጋ ጭማሪ ዙሪያ ያነጋግርናቸው የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዶክተር ተሾመ አዱኛ በቅድሚያ ስለገበያዎች የተለያየ ባህሪ አብራርተዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ ገበያዎች የተለያየ ባህሪ አላቸው። ነጻ የኢኮኖሚ ገበያ፣ ሞኖፖሊ ገበያና መሐል ላይ ያሉ የገበያ አይነቶች አሉ።
ገበያዎች በራሳቸው የሚንቀሳቀሱ አይደሉም። የተለያዩ አካላት ከጀርባቸው አሉ። እነዚህ አካላት አቅራቢዎችና ሸማቾች ሲሆኑ፣ የገበያውን ውጤት መወሰን የሚችሉ ናቸው። የሸማቾችና የአቅራቢዎች ባህሪ ደግሞ የገበያዎችን ውጤት እንደሚወስን ዶክተር ተሾመ ጠቅሰው፣ ገበያ ውስጥ ያሉ ሸማቾች መጠንና የአቅራቢዎች መጠንም እንዲሁ ገበያውን መወሰን እንደሚችሉ ነው ያብራሩት።
በኢትዮጵያ ያለው የገበያ ሁኔታም ይህንኑ እንደሚያመለክት ነው የተናገሩት፣ ለስኳር አቅርቦት እጥረቱ እንዲሁም ለዋጋው መናር ምክንያቱ ገበያው የሚመራበት ስርዓት የሌለው ከመሆኑ ጋር እንደሚያያዝ አስታውቀዋል።
በአገር ውስጥ የሚገኙ ስኳር አቅራቢዎች ጥቂት እንደሆኑም ዶክተር ተሾመ ጠቅሰው፣ ውስን በመሆናቸው ሰው ሰራሽ የዋጋ ንረት ለመፍጠር የተጋለጡ መሆናቸውን ይናገራሉ። ይህም የተዛባ ስርጭት እንዲኖር ማድረግ ያስችላቸዋል ይላሉ። ከዚህ ባለፈም ተጠቃሚው ለገበያ የሚሰጠው ምላሽ ወይም የሚያሳየው ባህሪ ገበያው እንዲበላሽ የሚያደርግ መሆኑንም ይጠቁማሉ።
የኢትዮጵያ ሸማች ወይም ደንበኛ ዋጋ ይጨምራል በሚል ስነልቦና የተገነባ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከዚህም ባለፈ ዋጋው ቢጨምርም እገዛዋለሁ እንጂ፤ እተወዋለሁ የሚል ስነልቦና እንደሌለው ያስረዳሉ። በመሆኑም አቅራቢው ውስን በመሆኑ ከሚፈጥረው ሰው ሰራሽ የዋጋ ንረት በተጨማሪ በሸማቹ ማህበረሰብ ዘንድ ያለው ስነልቦና ዋጋ ይጨምራል የሚልና ቢጨምርም እገዛዋለሁ የሚል መሆኑ ተዳምሮ አቅርቦት ቢኖርም ዋጋ የሚጨምርበት ሁኔታ እንዳለ ነው ያብራሩት።
ሌላው የምጣኔ ሃብት ባለሙያ አቶ ወሰንሰገድ አሰፋ የስኳር እጥረትና ዋጋ መወደድን አስመልክቶ ያነሱት ሀሳብ የዶክተር ተሾመን ሃሳብ የሚያጠናክር ነው፤ አሁን በስኳር ምርት ላይ እየታየ ያለው የዋጋ ንረት ከምርት እጥረት ጋር ተያይዞ የመጣ ነው ለማለት እንደሚያስቸግር አቶ ወሰንሰገድ ይገልጻሉ። እጥረት ስለመኖር አለመኖሩ ለማወቅ ጥናት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፣ ገበያው ግን ሰው ሰራሽ በሆነ እጥረት እየተረበሸ ስለመሆኑ አመላካቾች መኖራቸውን ይጠቅሳሉ። አንድ ነገር የእውነትም እጥረት ሲገጥመውና ሳይኖር ሲቀር የሚፈጠር እጥረትና ምርቱ እያለ ሰው ሰራሽ በሆነ ችግር ምክንያት የሚፈጠር እጥረት ስለመኖሩም አስረድተዋል።
እጥረቱን ለማብራራትም በአገሪቱ እየተባባሰ የመጣውን የሲሚንቶ እጥረት በአብነት ይጠቅሳሉ፤ የሲሚንቶ እጥረት እየተከሰተ ያለው በአገሪቱ ሲሚንቶ እየተመረተ ባለበት ሁኔታ መሆኑን ይጠቅሳሉ። አንድን ምርት የተወሰኑ ሰዎች በብዛት ያከማቹትና ገበያ ውስጥ ሰው ሰራሽ እጥረት ሲከሰት ጠብቀው ያወጡታል። ሰው ሰራሽ እጥረቱ ደግሞ ዋጋው እንዲንር ያደርጋል። በዚህም ህዝቡን ይበዘብዙታል ሲሉ አቶ ወሰንሰገድ ያብራራሉ። ምናልባትም በተመሳሳይ በስኳር ላይ ሰው ሰራሽ እጥረት ተከስቶ ሊሆን እንደሚችልና ገበያ ላይ እየታየ ያለውም ተመሳሳይ ነገር ስለመሆኑ አመላካቾች እንዳሉ ይጠቁማሉ። በሲሚንቶ ላይ ሰው ሰራሽ ችግር እንደተፈጠረ ሁሉ በስኳር ምርት ላይም ህገወጥ ንግድ እየተካሄደበት እንደሆነ በመረጃ ባይደገፍም አመላካች ነገሮች እንዳሉ በመጥቀስ፣ ችግሩን መለየትና መፍትሄ ማስቀመጥ ይገባል ብለዋል።
ዶክተር ተሾመም ችግሮቹን መለየት አስፈላጊ መሆኑን ነው ያመለከቱት፤ በስኳር ምርትና የገበያ ሂደት ላይ ያለውን ችግር ለመፍታት በቅድሚያ መረጃን መሰረት ባደረገ መልኩ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ችግሩን ማጥናት እንደሚገባ ያመለክታሉ። ገበያውን መክፈትና ነጻ ማድረግም ያስፈልጋል ባይ ናቸው። ገበያው ነጻ መሆን አለበት ሲባልም አዳዲስ ስኳር ማምረቻ ፋብሪካዎችን ከመክፈት ባሻገር አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የውጭ አገር ኢንቨስትመንትም መግባት እንዲችል መፍቀድ ያስፈልጋል ሲሉ አብራርተዋል።
ዶክተር ተሾመ እንደሚሉት፤ የስኳር ማምረቻ ቴክኖሎጂ በጣም ትልቅ ቴክኖሎጂ ነው፤ የስኳር ምርት በባህሪው ከተለያዩ የእሴት ሰንሰለቶች ጋርም ይገናኛል። ለአብነትም ስኳር ለማምረት አስቀድሞ ሸንኮራ አገዳ መትከል ያስፈልጋል፤ ይህም ከመሬት ጋር ይገናኛል። ስኳር ከፍተኛ ቴክኖሎጂ የሚጠይቅ እንደመሆኑ ይህንኑ መሰረት ያደረገ የውጭ አገርና የአገር ውስጥ ኢንቨስትመንት እንዲገባ መፍቀድን ይጠይቃል።
ዶክተር ተሾመ ችግሩን ለመፍታት የገበያውን ሂደት ተጠያቂነት ባለበት መንገድ መምራት እንደሚያስፈልግ ያመለክታሉ። አሁን ያለው የገበያ ሁኔታ እኛ ገበያውን መምራት ሲገባን በተቃራኒው ገበያው እኛን እየመራ መሆኑን የሚያመለክት ነው ይላሉ። ይህ በሁሉም አካባቢ መስተካከል እንደሚገባውም ተናግረዋል። ለዚህም የገበያ መረጃዎችን ማስተካከል፣ የገበያ ማእከላትን ማስፋፋት እንደሚያስፈልግ፣ የስኳር አቅራቢዎች መጠናከር እንዳለባቸውና በስኳር አቅርቦት ስም የሚታዩ የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባራት ሊወገዙ እንደሚገባ አመላክተዋል። እንደ መድሃኒትና መሰል ምርቶች ሁሉ ለስኳር ዋጋ ተመን ቢወጣለት የተሻለ እንደሆነም አስገንዝበዋል።
በአምራችና በተጠቃሚው መካከል ያለው ልዩነት መጥበብ እንዳለበትና በአምራቹና በተጠቃሚው መካከል ያሉትን አካላት ማስወጣት ሌሎች መፍትሔዎች መሆናቸውን የጠቆሙት ዶክተር ተሾመ፤ እነዚህና መሰል ችግሮችን በማስወገድ ስኳሩ ከአምራቹ ወደ ተጠቃሚው በቀጥታ መድረስ እንዲችል ማድረግ ከተቻለ በአገሪቱ እየታየ ያለውን የስኳር አቅርቦት እጥረት መፍታትና ገበያውን ማረጋጋት እንደሚቻል ያብራራሉ።
ሌላው በዘርፉ ያለው የቅንጅት ችግር መሆኑንም ይጠቅሳሉ። ወደ ማምረት ስራ ይገባሉ የተባሉ የስኳር ማምረቻ ፋብሪካ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ መጠናቀቅ አለመቻላቸው አንዱ የቅንጅት ችግር መሆኑን በአብነት ይጠቅሳሉ። በተቀናጀ መንገድ አለመስራትና የግብዓት አቅርቦት ችግር እንዳለም ገልጸው፣ የአገር ውስጥ ባለሃብቶች አቅም ማነስና ወደ ዘርፉ አለመግባት በዚህ ላይ ተደማምሮ አቅራቢ የተባሉት የተወሰኑ አካላት ዋጋውን እንደፈለጉ ማውጣት እንዲችሉ መንገድ ከፍቷል ይላሉ።
በአገሪቱ ስኳር የሚቀርበው በመንግሥት እና በነጋዴ መሆኑን ጠቅሰው፣ ነጋዴው መንግሥት ከሚያቀርበው በእጥፍ እየሸጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ሸማቹ ከመንግሥት ያላገኘውን አንድ ኪሎ ስኳር ከ120 እስከ 130 ብር ከነጋዴው የሚገዛበትን ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸው፤ ይህም ገዢ ስላለ መሆኑን አስረድተዋል። ነጋዴው ስኳሩን በየትኛውም መንገድ ወደ አገር ውስጥ ገበያ የሚያስገባው የነጋዴው ባህሪ እንዳለ ሆኖ አንድ ኪሎ ስኳር በ130 ብር ለመግዛት ፈቃደኛ የሆነ ሸማች በመኖሩ መሆኑን ያብራራሉ። ይህ መሆን አልነበረበትም፤ ችግሩ ያለው ሸማቹና አቅራቢው ዘንድ ነው ብለዋል።
ይህን አይነቱን የገበያ ሁኔታ መንግሥት ማስቀረት እንደማይችልም ዶክተር ተሾመ አመልክተው፣ ለእዚህ ምክንያቱ ደግሞ በመንግሥት በኩል ብዙ ስርዓቶች አለመኖራቸው ነው ይላሉ። በመንግሥት በኩል ያለው ስርዓት አድርግ አታድርግ የሚል አስተዳደራዊ ስርዓት መሆኑን ገልጸው፣ በገበያው በኩል ግን ገበያውን ሊያስተካክሉም ሆነ ሊያበላሹ የሚችሉ የተለያዩ ስርዓቶች እንዳሉ ይናገራሉ።
አቶ ወሰንሰገድ ለስኳር ዋጋ መናር አንደኛው ምክንያት የፍላጎት መጨመር መሆኑን ይጠቅሳሉ። ከዚህ ቀደም ማህበረሰቡ ስኳር የሚጠቀመው ለሻይ እና ለቡና እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን ማህበረሰቡ ስኳርን በተለያዩ ምግቦች ላይ መጠቀም መጀመሩ ለእጥረቱ አንድ ምክንያት እንደሆነ ያመለክታሉ። ይህም ፍላጎቱ እንዲጨምር የራሱ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል። በአገሪቱ ያለው አቅራቢ በማምረት ሳይሆን በዋጋ ከፍተኛ ጥቅም ማግኘት የሚፈልግ መሆኑም የስኳር ዋጋ የተጋነነ ዋጋ እንዲኖረው ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
እንደ አቶ ወሰንሰገድ ገለጻ፤ አቅራቢው ምርት ላይ ሳይሆን ዋጋው ላይ ነው ትኩረት የሚያደርገው። ይህም ሰው ሰራሽ የዋጋ ንረት እንዲፈጠር አድርጓል። ብዙ ሰዎች ደግሞ ዋጋ ሲጨምር የምርት እጥረት እንዳለ ታሳቢ በማድረግ በስፋት ለመግዛት ጥረት ያደርጋሉ።
የዚህ አንዱ መፍትሄም ማህበረሰቡ ዋጋ የሚጨምረው የግድ እጥረት ስላለ አለመሆኑን በመገንዘብ እጥረት ሳይፈጠር ዋጋ የሚጨምሩ አካላት እንዳሉ በመገንዘብ በተጋነነ ዋጋ ከመግዛት መቆጠብ አለበት ሲሉ ያስገነዝባሉ። አቅራቢውም ዋጋ ላይ ሳይሆን ምርት ላይ ትኩረት አድርጎ ቢሰራ ሰው ሰራሽ የዋጋ ንረትን ማስወገድ ይቻላል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ የኮርፖሬት ጉዳዮች ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዘመድኩን ተክሌ በቅርቡ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፤ ከስኳር ጋር የተያያዘው ችግር መከሰት የጀመረው ከ2003 ዓ.ም አንስቶ መሆኑን ይገልጻሉ። ችግሩ እየተንከባለለ ባለፈው ዓመት አስደንጋጭ ደረጃ ላይ መድረሱን ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚው ጠቅሰው፣ በዚህ ዓመትም የስኳር ችግሩ ተባብሶ መቀጠሉን አስታውቀዋል። ለችግሩ መባባስም ፋብሪካዎች በየዓመቱ ምርታቸው እየቀነሰ መምጣቱ አንዱ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል። ከፍተኛ የስኳር መጠን ያመርት የነበረው ፊንጫ ስኳር ፋብሪካ በፀጥታ ችግር ማምረት አለመቻሉ ሌላው ምክንያት ነው ብለዋል። በተያያዘም መተሐራ ላይ አንድ ሺ ሄክታር የአገዳ ማሳ በጎርፍ መጥፋቱ ሌላው ችግር እንደሆነ መጥቀሳቸው ይታወሳል።
በአገሪቱ እየታየ ካለው የስኳር አቅርቦትና ፍላጎት ከፍተት ችግርን ለመፍታት በ2020 ዓ.ም ከውጭ የሚገባውን ስኳር ሙሉ ለሙሉ በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት ስትራቴጂ ተነድፎ እየተሰራ መሆኑንም ኮርፖሬቱ ማስታወቁ ይታወሳል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በእድገትና ትራንስ ፎርሜሽን ሁለት የእቅድ ዘመናት 10 የስኳር ፋብሪካዎችን በመገንባት በነባሩቹም ላይ ማስፋፊያዎችን በማድረግ የአገሪቱን የስኳር ፍላጎት ከማሟላት ባሻገር ስኳር ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ ግንባታዎች ተጀምረው እንደነበር ይታወቃል። የአዳዲሶቹ ፋብሪካዎች የግንባታ መጓተት አጋጥሟቸው እንደነበር ይታወሳል፤ የለውጡ መንግስት ግንባታቸውን ለማጠናቀቅ ባደረገው ጥረት የተወሰኑት ወደ ማምረት ገብተዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ መንግስት አንዳንድ ስኳር ፋብሪካዎችን ለግሉ ዘርፍ ለማስተላለፍ እየተሰራ ይገኛል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 5 /2015