ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ ታኅሳስ 01/2015 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ በአስራ አንደኛ ሳምንት መርሃ ግብር በተከናወኑ ጨዋታዎች ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን የዲሲፕሊን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ የተለያዩ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
በዚህም የተለያዩ የቅጣት ውሳኔዎች እንደተላለፉ ተገልጿል። የቅጣት ውሳኔ ከተወሰነባቸው ተጫዋቾች መካከል የሐዋሳ ከተማው ተጫዋች ተባረክ ሔፋሞ ክለቡ ከመቻል ጋር ባደረገው የ11ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ጨዋታ በ77ኛ ደቂቃ ላይ ከባድ የአጨዋወት ጥፋት ከጨዋታ ሜዳ የተወገደ ሲሆን ለፈፀመው ጥፋት የዲሲፕሊን ርምጃ ተወስዶበታል። በዚህም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት ሶስት ጨዋታ እንዲታገድ እና በተጨማሪም የሶስት ሺ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍል ተወስኖበታል።
ወልቂጤ ከተማው ቡድን መሪ አቶ ጌታቸው ታዳሙ ክለቡ ከኢትዮጵያ መድን ጋር በነበረው የ11ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ጨዋታ ቅድመ ስብሰባ ወቅት ከ15 ደቂቃ በላይ ዘግይተው ስለመምጣታቸው ሪፖርት የቀረበባቸው ሲሆን ለፈፀሙት ጥፋት በፕሪምየር ሊጉ የውድድር ደንብ መሰረት አንድ ሺ ብር እንዲከፍሉ ወስኗል።
ሀዲያ ሆሳዕና በሳምንቱ ጨዋታ የክለቡ አምስት ተጫዋቾች በተለያዩ ጥፋቶች ካርድ የተመዘዘባቸው በመሆኑ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት ክለቡ የአምስት ሺ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍል ተወስኖበታል። ድሬዳዋ ከተማ ከፋሲል ከነማ ጋር በነበረው የ11ኛ ሳምንት ጨዋታ የአፄዎቹ ደጋፊዎች አፀያፊ ስደብ ስለመሳደባቸውና የተቃራኒ ቡድን ተጫዋች ላይ ቁሳቁስ ስለመወርወራቸው ሪፖርት የቀረበ ሲሆን በዕለቱና ከዚህ በፊት የክለቡ ደጋፊዎች ተሳድበው በተቀጡት ቅጣት ሊታረሙ ባለመቻላቸው በፌዴሬሽኑ የዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት ሰባ አምስት ሺ ብር እንዲሁም የተቃራኒ ቡድን ተጫዋች ላይ ቁሳቁስ በመወርውራቸው ሃያ አምስት ሺ ብር በድምሩ ብር የአንድ መቶ ሺ እንዲከፍል ወሳኔ መተላለፉ ተገልጿል።
በ2015 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 11ኛ ሳምንት በተካሄዱ ሰባት ጨዋታዎች አምስት ጨዋታዎች በመሸነፍ ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። በዚህም አስራ ስድስት ግቦች በተለያዩ አስራ አራት ተጫዋቾች ከመረብ አርፈዋል። ከነዚህ ግቦች መካከል ሁለቱ ግቦች በፍጹም ቅጣት ምት ሲቆጠሩ ቀሪዎቹ በጨዋታ የተቆጠሩ ናቸው። በሳምንቱ መርሃ ግብር ሰባት ጨዋታዎች ሰላሳ ዘጠኝ ተጫዋቾችና የቡድን አመራሮች የቢጫ ካርድ የተመዘዘባቸው ሲሆን አንድ ተጫዋች በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።
በተያያዘ ዜና በፕሪሚየር ሊጉ እየተሳተፈ የሚገኘውና በውጤት ማጣት መነሻነት አሰልጣኞቹን የጠራው የለገጣፎ ለገዳዲ ክለብ ቦርድ የስንብት እና የማስጠንቀቂያ ውሳኔዎችን እንደተሰጡት ታውቋል። በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እየተሳተፈ የሚገኘው ለገጣፎ ለገዳዲ የመጀመሪያ ጨዋታውን ሀዋሳ ከተማን በመርታት በድል በመጀመር ብዙዎችን አስደንቆ ነበር። ሆኖም እንደ አጀማመሩ መዝለቅ ባለመቻሉ በሁለት ጨዋታ ነጥብ ከተጋራ በኋላ በሰባት ጨዋታ ሽንፈት አስተናግዶ በደረጃው ሠንጠረዡ ግርጌ ለመቀመጥ ተገዷል።
በዚህ ሒደት ደስተኛ ያልሆኑ የክለቡ የቦርድ አመራሮች ቡድኑ ከአዳማ ከተማ በተረታበት ጨዋታ በአካል ተገኝተው ከተከታተሉ በኋላ በውጤቱ ደስተኛ ባለመሆን እና በቀጣይ ክለቡ በሚስተካከልበት ጉዳይ ላይ ለመምከር የቡድኑ የአሰልጣኝ አባላት ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ በማድረግ ውይይት አድርገው የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፈዋል።
በዚህም መሠረት ረዳት አሰልጣኝ የሆኑትን ዳዊት ይፍሩ፣ እዮብ ዋቢ እና ድሪባ ጃንቦ ሦስቱንም ማሰናበታቸው ሲታወቅ ውጤት የማሻሻል ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው አሰልጣኝ ጥላሁን ተሾመ እና የግብ ጠባቂ አሰልጣኙ ፍቃዱ ገብሩ ለቀጣይ ጨዋታ ቡድኑን ለማዘጋጀት ወደ ድሬዳዋ ተመልሰዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 4 /2015