ኢትዮጵያ የሺህ ዘመናት የአገረ መንግስት ታሪክ፣ ውብ ባህልና ማንነት ያላቸው ብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች በጋራ ተዋደውና በአንድነት ሆነው የሚኖሩባት አገር ናት:: ህዝቦቿ ለአይን ማራኪ፣ ጆሮ ገብና ተወዳጅ የሆኑ ለባዳ የሚያስቀኑ፣ ለወዳጅ ሁሌም ሃሴትን የሚያጭሩ በርካታ የባህል እሴቶች አሏት። ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦቿ ለሉአላዊነታቸው መከበር በጋራ ዘብ የሚቆሙ፣ ጠላትን በአንድነት መክተው ድባቅ የሚመቱም ናቸው።
ሁሉም ዜጎች ኢትዮጵያዊነትን ሳይለቁና የመጡበትን ማህበረሰብ ባህልና ማንነት ሳይሸራርፉ አብረው የመኖር የሺህ ዓመታት ታሪክ ባለቤትም ናቸው። የነዚህን ህዝቦች አንድነት የተፈታተኑ አያሌ አጋጣሚዎች በተለያዩ ጊዜያት ተከስተዋል፤ ይሁንና በጠንካራው አብሮነትና የተጋድሎ ወኔያቸው ችግሮቹን በጣጥሰው በማለፍ ዛሬ ላይ ደርሰዋል። የጋራ ማንነት ያላቸው ህዝቦች ንፋስ ያመጣውን ወጀብ ሁሉ ለዘመናት በገነቡት የአብሮነት ባህላዊ እሴት መክተው ውድማማችነታቸውንና አንድ መሆናቸውን አጽንተዋል::
ይህ ወንድማማችነት ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች በልዩነት ብቻ ሳይሆን በአንድነት ውስጥ ያሉ መሆናቸውን በሚገባ ያመለክታል:: ይህ ወንድማማችነትና አንድነት ይበልጥ እንዲጠናከርም ነው በመንግስት በኩል እየተሰራበት ያለው:: የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በአል መከበርም ከዚሁ አኳያም የሚታይ ነው::
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አሕመድ ሰሞኑን ለ17ተኛ ጊዜ የተከበረውን የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል አስመልክተው ባስተላለፉት መልእክት “የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል የኢትዮጵያዊነት በዓል ነው፤ ኢትዮጵያዊነት የብሔር ብሔረሰቦች የጋራና የአንድነት መገለጫ ነውና›› ሲሉ አስገንዝበዋል። ኢትዮጵያዊነት ማለት የብሔሮች ብሔረሰቦች ዕሴቶች፣ ባህሎች፣ ታሪኮች፣ ቅርሶች፣ ቋንቋዎችና ጥበቦች በአንድነት የሚገለጡበት የጋራ ማንነት መሆኑን ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በዓለም መድረክ አሸናፊ ሆነው እንዲወጡ ከፈለግን ሁላችንም አሸናፊ የምንሆንበትን መንገድ መፍጠር አለብን” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያውያን ከልዩነት ባሻገር የጋራ ማንነት ያላቸው ህዝቦች እንደሆኑ አበክሮ በሚገልፀው መልእክታቸው ላይ ደጋግመው እንዳስገነዘቡት፣ በምንም መልኩ ኢትዮጵያውያን አንዳቸው ያለ ሌላኛቸው ሊኖሩም፣ ሊያድጉም ሆነ ሊያሸንፉ አይችሉም።
‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሁሉም ሕዝቦች ሕዝቦቻችን ናቸው። ሁሉም ቋንቋዎች ቋንቋዎቻችን ናቸው። ሁሉም ባህሎች ባህሎቻችን ናቸው። ሁሉም በዓሎች በዓሎቻችን ናቸው። ሁሉም እምነቶች እምነቶቻችን ናቸው። ሁሉም ቅርሶች ቅርሶቻችን ናቸው። ሁሉም አካባቢዎች የሁላችን አካባቢዎች ናቸው። ሁሉም የተፈጥሮ ሀብቶች የሁላችንም ሀብቶች ናቸው። ለዚህም ነው በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል የጸጥታ ኃይሎቻችን ደማቸውን የሚያፈስሱት፤ አጥንታቸውንም የሚከሰክሱት›› በማለት የኢትዮጵያውያንን ጠንካራ የጋራ እሴት በማጉላት አስረድተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ያለ ዘላቂ ሰላም ዘላቂ ሰላምም ያለ ህብረ ብሄራዊ አንድነት ሊሳካ እንደማይችል አስገንዝበዋል::
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሌሎች ሀገሮች ዛሬ በሚያወጧቸው ህግች ሁሉን የሚያቅፍ ስርአት መገንባት ከቻሉ እኛ ከእነሱ በተሻለ በእሴት ጭምር የመገንባት ሀገራችንን ማጽነት እንችላለን፤ የባለ ጠንካራ መሰረት ህዝቦች መሆናችንን የመዘንጋት ጊዜያችንን ይብቃ፤ ልዩነታችንን ለሚና ካወልነው አንድነታችን በእሴታችን ላይ ባማረ መልኩ ይገነባል:: አንድነት እና ልዩነት አይጣሉብን፤ ልዩነት ያልተዳፈነ ቀዳዳችንን የምንደፍንበት የስራ ስማችን ነው፤ አንድነት ደግሞ የእውቀት ጉዟችን ይሆናል፤ እናም በህብረት አንድ ላይ በመቆም ብቻ ሳይሆን በመደመር ሀይላችንን ከቁጥራችን አናብዛ›› ሲሉም በጋራ የመቆምን ፋይዳ አስገንዝበዋል::
የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ለ17ኛ ጊዜ በሲዳማ ክልል በሃዋሳ ከተማ “ህብረ ብሄራዊ አንድነታችን ለዘላቂ ሰላማችን” በሚል መሪ ቃል በተከበረበት ወቅት የተገኙ ተሳታፊዎችም የጠቅላይ ሚኒስትሩን መልእክት የሚያጠናክር ሃሳብ ተናግረዋል:: ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ልክ በአንድ ቤት በሚኖሩ የቤተሰብ አባላት እንደሚመሰሉ ነው የተናገሩት:: የማንነት ልዩነቶች የውበት እንጂ የግጭት መንስኤ ሊሆኑ እንደማይገባም አስገንዝበዋል።
በስፍራው የተገኘው የዝግጅት ክፍላችን ዘጋቢ ካነጋገራቸው ተሳታፊዎች መካከል አንዱ የሆኑት የኦሮሞ ብሄር ተወካይዋ ወይዘሮ ከድጃ አዲይ ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ጉራጌ፣ ወላይታ፣ሲዳማን የመሳሰሉ ልዩ ልዩ ማንነቶች እንዳሉ ጠቅሰው፣ እነዚህ ማንነቶች የውበት የአንድነት መገለጫ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፤ ልዩነቶች የግጭት ሰበብ ሊሆኑ አይገባም ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። ሁሉንም ኢትዮጵያውያን የሚያስተሳስሩ አያሌ የጋራ ማንነቶች እንዳሉም ጠቅሰው፣ እነርሱን ለማጉላትና የአንድነቶቻችን መሰረት እንዲሆኑ መስራት ያስፈልጋል ይላሉ።
በአፋር ክልል አርጐባ ብሄረሰብ ወክለው የተገኙት አቶ ሙክታር ኡመር፣ እኛ ኢትዮጵያውያን በአንድ ቤት ውስጥ ባለ ቤተሰብ የምንመሰል፣የተለያዩ አስተሳሰቦች አሉን ሲሉ ይገልጻሉ። እነዚህ አስተሳቦች ውበት ናቸው። አንዱ ያለአንዱ ውበትና ጥንካሬ የለውም። ስለዚህ በብዝሃነታችን ውስጥ አንድነታችን አስጠብቀን ልንጓዝ ይገባል ነው ያሉት።
የወላይታ ብሄር ተወካይዋ ወይዘሮ ጸዳለ ዱሌም ይህን ሀሳብ ይጋራሉ። በኢትዮጵያ የተለያዩ የማንነት ጥያቄዎች እንዳሉ ጠቅሰው፣ እነዚህ የማንነት ጥያቄዎች በህገመንግስቱ በዲሞክራሲያዊ መንገድ እንጂ በግጭት ሊፈቱ እንደማይችሉ ይናገራሉ። “የሚያምርብን ኢትዮጵያዊ አንድነታችን ነው። የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በአልን ሁሉም በመነፋፈቅ የሚጠብቁት ልዩ ቀን ነው” በማለትም አንድ እናት በሆነችን ኢትዮጵያ ውስጥ ተቻችለንና ተከባብረን ልንኖር ይገባል ብለዋል። ይህንን ለማድረግ የሚያስችሉ የጋራ ባህላዊና ማህበራዊ መሰረቶችም እንዳሉም ነው የሚገልፁት።
የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን የጋራ ባህላዊ እሴቶች አሁን ካለውም በላይ በእጅጉ በላቀ ማጠናከርና ማጎልበት እንደሚያስፈልግ የዘርፉ ምሁራንም ያስገነዝባሉ። ለመሆኑ “ኢትዮጵያውያን የጋራ ባህላዊ እሴቶች አሏቸው። እነርሱን ማልማት፣ ማጠናከር፣ ለወንድማማችነትና አንድነት መሰረት እንዲሆኑ ማድረግ ላይ መስራት ያስፈልጋል” ሲባል ምን ማለት ይሆን?
ደስታ ሎሬንሶ በአንትሮፖሎጂ የትምህርት መስክ ሶስተኛ ዲግሪያቸውን እየሰሩ ያሉና በባህል ልማትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በርካታ የጥናት ውጤቶችን ይፋ ያደረጉ ምሁር ናቸው። እርሳቸው ኢትዮጵያውያን በአገር ላይ ጠላት ሲመጣ በጀግንነት የሚመክቱበት እሴት በሌላው ዓለም ላይ የሌለና ብቸኛው የማንነታቸው መሰረት መሆኑን ይገልፃሉ። ከዚህ ባለፈ ፍቅር፣ ብሄርን ሳይሆን ሰውነትን ያስቀደመ መተሳሰብና ትብብር የኢትዮጵያውያን መገለጫና የጋራ ባህላዊ እሴታቸው መሆኑንም ይናገራሉ። በነዚያ የድል ወቅቶች መላው ብሄረሰቦች ልዩነታቸውን ወደጎን ትተው ከሁሉም የአገሪቷ ክፍሎች በርካታ ኪሎ ሜትሮችን በማቋረጥ ሉአላዊነታቸውን ያስከበሩበት ዋንኛ ምክንያትም የጋራ እሴቶች ስላሏቸው እንደሆነ ነው አስረግጠው የሚናገሩት።
ይህንንም በወጣቱ ዘንድ ማስረጽ እንደሚገባ አስገንዝበው፣ በስርአተ ትምህርቱ ውስጥ በማካተት ማሳደግና እሴቶቹን ማጎልበት እንደሚያስፈልግ ነው የሚያስረዱት። መረዳዳት፣ ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓት እና ሌሎችም መሰል ማንነቶች የኢትዮጵያዊነት መገለጫና የጋራ እሴት መሆናቸውን ይጠቅሳሉ።
“ሁሉም ሰው ስለ ጋራ እሴት ሊያወራ ይችላል። ይሁን እንጂ ይህ ማንነት ተቋማዊ በሆነ መንገድ ተጠንቶና ታትሞ ለትውልድም ሆነ ለትምህርት ተቋማት እየተላለፈ አይደለም” የሚሉት ምሁሩ ፤ በተለይ በመንግስት ስር ያሉ በባህልና በብሄር ብሄረሰቦች ጉዳይ ላይ የሚሰሩ እንደ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴርና የፌዴሬሽን ምክር ቤትን የመሳሰሉ ተቋማት በተደራጀ መንገድ በስትራቴጂ ተደግፈው የጋራ እሴቶችን ለማጎልበት እየሰሩ እንዳልሆነ ነው የሚያምኑት።
ከዚህ በመነሳትም “የኢትዮጵያውያን የጋራ ባህላዊ እሴት ግንባታና ጥናትና ምርምር ተቋም ማቋቋም ያስፈልጋል” የሚል ጠንካራ አቋም ያራምዳሉ። ይህንን ሃላፊነት መንግስት ሊወጣና በፖሊሲ፣ ህግና በተግባር መሬት ላይ የሚተረጎምበት መንገድ መፈለግ እንዳለበትም ይናገራሉ። በተለይ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚቀነቀኑ “መደመርን”ና “ወንድማማችነት” የመሰሉትን የጋራ እሴቶችን የሚያጎለብቱ ሃሳቦች ከቃላት ባለፈ መሬት ላይ ወርደው በጥናት፣ ፖሊሲ ተቀይረው ማህበረሰቡ ውስጥ ዘልቀው እንዲገቡ በማድረግ የባህል አብዮት ሊያመጡ በሚችሉበት መንገድ ላይ ሊሰራ ይገባል የሚል ጠንከር ያለ መልእክት ያስተላልፋሉ።
እንደ መውጫ
የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች የየራሳቸው ማንነት ፣ ባህል፣ ቋንቋና ታሪክ አላቸው። ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ኢትዮጵያዊነት ናቸው:: እነዚህን ማንነቶች በግል ወይም በተናጠል ማሳደግ ወይም በትይዩ (parallel) የጋራ ዕሴቶቻችን ማስተሳሰር፣ መገንባት እና ኢትዮጵያዊ ማንነትን ማጠናከር ያስፈልጋል:: ኢትዮጵያዊ ማንነት ወይም ሀገራዊ አንድነት እና ሉዓላዊነት የወቅቱ ትልቁ የሀገሪቱ አጀንዳ ነው:: በዚህ ሀገራዊ ማንነት ላይ መሰረት ጥለን የኢኮኖሚ ዕድገት እና ብልጽግናን እንዲሁም ዘላቂ ሰላምን በተባበሩ የኢትዮጵያ ህዝቦች ማረጋገጥ ይቻላል::
የጋራ ባህላዊ ትስስር የኢኮኖሚ ማህበራዊ ትስስር፣የፖለቲካ መረጋጋት፣ ሰላም እና ደህንነት ለማረጋገጥ ዋስትና ይሰጣል። ከዚህም በተጨማሪ የኢኮኖሚ መስተጋብር እና የንግድ ልውውጥ (shared values) ይፈጥራል:: ጠንካራ ሀገር በጋራ እሴት ውስጥ እንደሚገነባም መገንዘብ ያስፈልጋል::
በዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሳይንሳዊ ምርምር ያደረጉ ምሁራን ህዝቦች ወንድማማችነትን የሚያጎለብቱት የጋራ እሴቶቻቸውን ለይተው ትኩረት ሰጥተው ሲሰሩ መሆኑን ነው የሚያምኑት:: ማህበራዊ ትስስር እና የጋራ እሴቶች ሲላሉ ለእርስ በእርስ ግጭት (civil war) መነሻ እንደሚሆኑ እነዚህ ምሁራን ያስረዳሉ። ይህ እሴት የማይዳብር ከሆነ ህዝቦች ሀገርን አናውቅም፣ ትስስር የለንም ማለታቸው እንደማይቀርም ነው የሚያስረዱት:: በዚህ ምክንያትም ጥላቻ ይሰፍናል፣ ለጠላቶቻቸውም መግቢያ ቀዳዳዎች ይፈጠራሉ፤ ኢኮኖሚ ይወድማል፣ የሀገር ጸጥታ ይናጋል፤ ገጽታ በእጅጉ ይበላሻል:: ህዝቦች በስጋት ይኖራሉ፣ የህዝቦች ጥርጣሬ እና አለመተማመን ለልማትም አብሮ ለመኖርም ጸር ነው:: ኢትዮጵያ አንድ ሀገር ደግሞም የብዙ ህዝቦች የጀግንነት እና ሉዓላዊነት ውጤት ነች። የጋራ ባህላዊ ዕሴት መገንባት ለሀገሪቷ ቀደምት ታሪክ፣ የጀግንነት፣ የሉዓላዊነት፣ የመተባበር፣የመረዳዳት ዕሴቶች ዕውቅና መስጠት ነው::
ሰሞኑን የተከበረው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓልም አንድነትንና ወንድማማችነትን በሚያጠናክሩ እሴቶች ተሞልቶ ተከብሮ ማለፉን መረጃዎች ያመለክታሉ። ሁሉም ዜጎች እንደየ ባህላቸውና የእሴት መሰረታቸው ማንነታቸውን በሚገልፁ ተወዳጅ አለባበሶች፣ ባህላዊ ስርአቶች፣ አመጋገቦችና ሌሎች የሽምግልናና መሰል ሃብቶች ደምቀው ማሳለፋቸውም፣ ቀኑን የተመለከቱ መድረኮች መካሄዳቸውም እሴቶቹን ለማጠናከር ፋይዳቸው ከፍተኛ ነው።
እሴቶቹን ለማጎልበትና በህዝቡ ዘንድ እንዲሰርጹ ለማድረግ ከዚህም በላይ መሰራት ይኖርበታል:: ከባህልና ከመሳሰሉት ጋር የሚሰሩ ተቋማት በእዚህ በኩል ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው:: የብሄሮች ብህረሰቦችና ህዝቦች ባህሎችና ሌሎች እሴቶች የመላ ኢትዮጵያውያን እሴቶች መሆናቸው ላይ አበክረው መስራት አለባቸው::
የአንትሮፖሎጂ ምሁሩ አቶ ደስታ ሌሬንሶ እንዳሉትም፤ ወንድማማችነትንና አንድነትን የሚያጠናክሩትን እነዚህን የጋራ እሴቶች/ ሀብቶች/ ዜጎች ይበልጥ እንዲገነዘቧቸውና የራሳቸው አድርገው እንዲመለከቷቸው አልፎም ተርፎ ለልማትና ለዴሞክራሲ ስርአት ግንባታው እንዲያውሏቸው ለማድረግ እሴቶቹን በተቋማዊ አሰራርና አደረጃጀት ማጎልበትና ማስረጽ ላይ በስፋት መስራት ያስፈልጋል። ይህን ማድረግ ሲቻል የሚነፍሰውን የጥፋት ነፋስ እና ወጀብ በራሳችን እሴቶች ከመቆጣጠርና የአንድነት መሰረትን ከማጠናከር ባሻገር ለትውልድ የሚሻገር ተግባር ማከናወን ይቻላል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 2 /2015