የዓለም አትሌቲክስ ከሚያዘጋጃቸው ትልልቅ ዓመታዊ ውድድሮች መካከል አንዱ በመም ሩጫዎችና በሜዳ ተግባራት (32 የውድድር ዓይነቶች) የዓለም አትሌቶች የሚፎካከሩበት ዳመንድሊግ ነው:: እአአ 1998 ጀምሮ ይካሄድ የነበረውን ጎልደን ሊግ ውድድርን ተክቶ እአአ ከ2010 ጀምሮ እየተከናወነ የሚገኘው ይህ ውድድር 14 ዙሮች ያሉት ሲሆን፤ በተለያዩ የዓለም ከተሞች በመዘዋወር ይካሄዳል::
ኢትዮጵያዊያን ወጣትና በስፖርቱ ትልቅ ስኬት ላይ የደረሱ አትሌቶችን ጨምሮ በመላው ዓለም የሚገኙ አትሌቶች የሚካፈሉበት የዳይመንድሊግ ውድድር የተለያዩ የዓለም ክብረወሰኖች እንዲሁም ፈጣን ሰዓቶች የሚመዘገቡበትና ከፍተኛ ፉክክር የሚስተዋልበት በመሆኑ ትልቅ ትኩረት ይሰጠዋል::
በመጠናቀቅ ላይ በሚገኘው የፈረንጆቹ ዓመት በተካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር በርካታ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ሲሳተፉ የቆዩ ሲሆን፤ የዓለም የ3ሺ ሜትር የብር ሜዳሊያ አሸናፊዋ አትሌት የወርቅውሃ ጌታቸው የዚህ ዳይመንድሊግ አጠቃላይ አሸናፊና የዋንጫ ተሸላሚ መሆና ይታወሳል:: የ3ሺ ሜትር መሰናክል አትሌቷ በሞናኮ እና ዙሪክ ባካሄደችው ውድድር ውጤታማ ልትሆን እንደቻለች አይዘነጋም:: ወጣቷ አትሌት በአሜሪካው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በርቀቱ የብር ሜዳሊያ ካጠለቀች ጥቂት ጊዜያት በኋላ ዳግም በዳይመንድሊግ ባለድል መሆኗ ደግሞ በአትሌቲክስ ቤተሰቡ ዘንድ አድናቆትን አትርፎላታል::
ከአንድ ወር በኋላ በሚመጣው አዲሱ የፈረንጆች ዓመት የሚካሄደው የ14ኛው ዳይመንድ ሊግ መርሃ ግብርም ከወዲሁ ይፋ የተደረገ ሲሆን በርካታ የዓለማችን አትሌቶችም በጉጉት እየጠበቁት ይገኛሉ::
የ2023 የዳይመንድሊግ ውድድር አዳዲስ ጉዳዮች የተካተቱበት መሆኑን የዓለም አትሌቲክስ ይፋ ያደረገው መረጃ የሚጠቁም ሲሆን በመጪው የፈረንጆቹ ዓመት 2023 ግንቦት ወር ላይ ይጀመራል:: መነሻውን በኳታሯ ዶሃ የሚያደርገው ይህ ውድድር ከአምስት ወራት በኋላ በአሜሪካዋ ዩጂን መደምደሚያውን ያደርጋል:: ይህም ያልተለመደ ሁኔታ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም ይታወቅ የነበረው ውድድሩ ዙሪክ እና ብራሰልስ ላይ በሚኖረው ደማቅ መርሃ ግብር ይጠናቀቅ ነበር::
ውድድሩ በ12 ሃገራት 15 ከተሞች ላይ ሲከናወን እያንዳንዳቸው ከተሞች የአንድ ቀን መርሃ ግብር ያሰናዳሉ:: ከውድድሮቹ የሚልቁት በአውሮፓ አህጉር የሚዘጋጁ ሲሆን፤ በዓመቱ 10 የአውሮፓ ከተሞች የማስተናገድ እድል አላቸው:: ታላቋ አህጉር እስያ ሶስት ውድድሮች ሲካሄዱባት አፍሪካ እና አሜሪካ አንድ አንድ ከተሞቻቸው ውድድሩን ያከናውናሉ:: ማጠቃለያው የሚደረግበት ዩጂን ደግሞ የሁለት ቀናት ቆይታ ይኖረዋል:: እአአ የ2024 ዳይመንድ ሊግ መዝጊያ ብራሰልስ ስታዘጋጅ የ2025ቱን ደግሞ ዙሪክ ትሆናለች:: ቀጣዮቹን ሁለት ዓመታትም በተመሳሳይ አውሮፓዊያኑ ከተሞች በመፈራረቅ የመዝጊያ ስነስርዓቱን እንደሚያካሂዱም የተያዘላቸው መርሃ ግብር ያሳያል::
በመጪው የዳይመንድ ሊግ ውድድር ላይ አዳዲስ ውድድሩን የሚያስተናግዱ ከተሞች የተካተቱ ሲሆን፤ ላለፉት አራት ዓመታት አዘጋጅነቷን አቋርጣ የቆየችው ለንደንም በድጋሚ ወደ አዘጋጅነተ መመለሷ ታውቋል:: እአአ ከ2010-2019 ባሉት ዳይመንድሊግ ውድድሮች ተሳታፊ የነበረችው ለንደን አይረሴ የሆኑ ክስተቶችን አስተናግዳለች:: ከወራት በኋላም በንግስት ኤልሳቤት ኦሊምፒክ ፓርክ ዳግም ዳይመንድ ሊግን ለማስተናገድ ዝግጅቷን አጠናቃለች:: በተጨማሪም ሌላኛዋ የአውሮፓ ሃገር ፖላንድ ውድድሩን የሚያሰናዱን መቀላቀሏ ታውቋል:: ለመጀመሪያ ጊዜ ዳይመንድ ሊግ እንዲካሄድበት የተመረጠው የፖላንድ ከተማ ደግሞ ሲሊዚያ የሚሰኝ ነው:: በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ውድድሩን ማስተናገድ ያቆሙት ቻይናዊያኑ ከተሞች ሻንጋይ እና ሺንዚንም በ2023ቱ ዳይመንድ ሊግ ወደ አዘጋጅነታቸው ተመልሰዋል:: አራት ወራትን ይፈጅ የነበረው ዳይመንድ ሊግ በመጪው ዓመት የተለያዩ መዳረሻዎችን በመጨመሩ ምክንያት የሚፈጀው ጊዜም ወደ አምስት ወራት ማደጉ ተጠቁሟል::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 1 /2015