ስንዴን ከእንክርዳድ ለመለየት በሰፌድ ማንገዋለል እንደሚያስፈልግ ሁሉ ከመሬት ውስጥ ተቆፍሮ የወጣውን ወርቅ ከአፈሩ ለመለየት ማዕድን አውጭዎች በጎድጓዳ የብረት እቃ ውስጥ በማድረግ ውሃ በመጨመርና በእጃቸውም እያሹ በማንገዋለል ወርቁን ከአፈር ይለያሉ። ወርቁን ከአፈር የመለየቱ ስራ ውሃ በብዛት ስለሚፈልግ በአብዛኛው የሚከናወነው በወንዝ ዳርቻ ነው።
ይህን የሚያከናውኑት ሰዎች በአንዳንድ አካባቢዎች ግማሽ አካላቸው ውሃ ውስጥ ሆኖ ነው የሚሰሩት። ለጤናቸው የሚያደርጉት ጥንቃቄ የለም። ወርቁን የመለየቱ ሥራ ሰአታትን ሊወስድ ይችላል። ጊዜ ወስደው፣ ጉልበታቸውን አፍስሰው፣ ጤናቸውንም ጎድተው ቢሆን ንጹህ ወርቅ ከአፈር ለይቶ ለገበያ በማዋል የሚያገኙት ገቢ ላይ ነው ትኩረታቸው።
ወርቅ ያለበትን አፈር በቁፋሮ በማውጣት፣የወጣውን ወርቅ ደግሞ በእጥበት ከአፈር የመለየቱ ሥራ የሚወስደውን ጊዜና ድካሙን ተቋቁመው በኪሎግራም የሚያገኙት የወርቅ መጠን ልፋታቸውን የሚያካክስ ላይሆን ይችላል። የወርቅ ማዕድን ልማቱን መተዳደሪያቸው ካደረጉት ምርጫ ስለሌላቸው የየእለት ኑሮአቸው በዚህ መልኩ ነው የሚቀጥለው። የወርቅ ማዕድን ልማቱ በዚህ መንገድ ሲከናወን ዘመናት ተቆጥሯል። አሁንም በአብዛኛው ይኸው ነው።
በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለው የማዕድን ልማት ባህላዊ ነው ከሚያሰኘው አንዱ ሂደቱ ነው።የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉትም፤ የወርቅ ማዕድን ልማት አድካሚ ነው። ሀብቱ የሚገኝበትን ቦታ ለይቶ ልማቱን ለማከናወን የአንድ መንደር ስፋት ያህል ጥናት ማካሄድን ይጠይቃል። አብዛኛው የልማት ሥራ የሚከናወነው ደግሞ በባህላዊ መንገድ በመሆኑ በግምት ነው ቁፋሮ የሚካሄደው። በዚህ ሂደት ደግሞ መጠኑ ያነሰ ወርቅ ብቻ ሊገኝ ይችላል፤ ፈጽሞ ሳይገኝም ሊቀር ይችላል። የወርቅ ማእድኑ በቁፋሮ ከተገኘ በኃላ ወርቁን ከአፈር ለመለየት በሚከናወነው ሥራ የወርቅ ብክነትም ያጋጥማል። በአጠባ ወቅት ወርቁ አምልጦ ውሃ ውስጥ ሊገባም ይችላል።
በኢትዮጵያ ለማዕድን ልማት የሚውሉ ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ አለመዋላቸው ከፍተኛ የጊዜና የጉልበት ብክነት ይደርሳል፤ የስራ ጫናም ይበዛል፤ ይህ ሁሉ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳርፋል። የማዕድን ልማቱን አሰራር እንደ ድክመት በመጠቀም ገበያ ላይ መደራደሪያ አድርገው የሚጠቀሙ አንዳንድ ገዥ ሀገራት መኖራቸውም ይነገራል። ይህ ሁሉ ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ ካለመሥራት የመጣ እንደሆነም በክፍተትነት ይነሳል።
በሀገራችን አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው ወርቅን ጨምሮ የማዕድን ዘርፉ አኪኖሚውን በማሳደግ ከሚጠቀሱ አንደ ቡና፣ የቅባት እህሎችና ሌሎች የግብርና ውጤቶች እኩል ኢኮኖሚው ውስጥ ድርሻ እንዲኖው በትኩረት እየተሰራበት ይገኛል። የወርቅ ልማቱ በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን በሚደረገው ጥረት ግለሰቦችም በልምድና በትምህርት ያገኙትን አውቀት በመጠቀም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ።
ቴክኖሎጂ ሲታሰብ የብዙዎች አእምሮ ወደ ውጭ ነው የሚሄደው። የሀገር ውስጥ ቴክኖሎጂ አፍላቂዎች ደግሞ እኛ አለን ተመልከቱን እያሉ ናቸው። በተግባርም አሳይተው ውጤት ያስገኙ ኢትዮጵያውያንንም እያየን ነው። በተለይም የማዕድን ዘርፉን የሚያግዝ ቴክኖሎጂ በግለሰቦችና በማህበር በተደራጁ ወጣቶች ጭምር በተለያየ ደረጃ ተመርቶ ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል።
ቴክኖሎጂውን በማሻሻል ጭምር ዘርፉን እያገዙ በሚገኙ ዜጎች ጥቅም ላይ እየዋለ በሚገኘው የወርቅ ማዕድን ማጠቢያ ማሽን ቴክኖሎጂ ከተጠቀሙት መካከል በደቡብ ክልል ሚዛን ቴፒ ዲማ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በወርቅ ማዕድን ልማት የተሰማሩት አቶ አቻምየለህ አዲሱ አንዱ ናቸው። አቶ አቻምየለህ በአካባቢው የሚገኘው ወርቅ ደቃቅ በመሆኑ ባህላዊ የወርቅ ማዕድን አልሚዎች በአጠባ ወቅት ወርቁ አምልጦ ውሃ ውስጥ እንዳይገባባቸው በጥንቃቄ ሲሰሩ ማስተዋላቸውን ይገልጻሉ። ሥራው ድካም ያለው መሆኑንም ታዝበዋል።
እናም የወርቅ ማጠቢያ ማሽን ለዲማ አካባቢ አስፈላጊ ሆኖ አገኙት። በማሽኑ የሚከናወነው አጠባ በአይን እየታየ መሆኑንም ጠቅሰው፣ አልሚውን አትራፊ ያደርገዋል ነው ያሉት። አቶ አቻምየለህ የወርቅ ማጠቢያ ማሽንን ጥቅም በተግባር ካረጋገጡ በኃላም እየተጠቀሙበት ያለውን የወርቅ ማጠቢያ ማሽን ‹‹ራሱ ወርቅ ነው››ሲሉ ገልጸውታል።
በወርቅ ማጠቢያ ማሽኑ መጠቀም ከጀመሩ አንድ አመት የሆናቸው አቶ አቻምየለህ፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ በአጠቃቀምም ሆነ ሌላ ችግር እንዳላጋጠማቸው ነው ያስረዱት። በሀገር ውስጥ ተመርቶ መቅረቡንም እንደ ስኬት ተመልክተውታል።
በሀገር ውስጥ ቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች መቅረቡ አገልግለቱን ለሚፈልገው ብቻ ሳይሆን ጥቅሙ ለሀገርም ነው ይላሉ። የውጭ ምንዛሪ ወጭ በማዳን ሀገርንም ተጠቃሚ ያደርጋል የሚል እምነት አላቸው። በሀገሪቱ ተመርቶ ለገበያ ሲቀርብ ገዥዎች በፈለጉ ጊዜ ለማግኘት ያስችላቸዋል በዋጋ ተመጣጣኝ እንዲሆን ያደርገዋል ይላሉ ። እርሳቸው በገዙበት ወቅት ዋጋው ዘጠኝ መቶሺ ብር እንደነበር ያስታውሳሉ። የወርቅ ማዕድን ልማቱ በቴክኖሎጂ መታገዙ በጥራትና በመጠን እንዲሁም ጊዜ ቆጣቢ የሆነ ሥራ ለመሥራት የሚያስችል በመሆኑ በሥራው ላይ ያለውን አልሚ ከማበረታታቱ በተጨማሪ አዲስ ኢንቨስትመንትንም እንደሚስብ ነው ያስረዱት።
እንደ አቶ አቻምየለህ ገለጻ፤ ልማቱ በቴክኖሎጂ መታገዙ በራሱ ብቻውን ግብ አይደለም። የሥራ ባህልም መሻሻል አለበት። አሁን ባለው አሰራር በትርፍ ክፍያ እንኳን ለማሰራት ቢፈለግ ፍቃደኛ አይገኝም ። እርሳቸው በተሰማሩበት አካባቢ በወርቅ ማዕድን ልማት ላይ የተሰማሩ የውጭ ኩባንያዎች ውሎአቸውንም አዳራቸውንም በማዕድን ልማቱ ሥፍራ በማድረግ ነው ለሥራቸው ትኩረት ሰጥተው የሚሰሩት። ጠንካራ የሥራ ባህል ዳብሮ ሥራን በሚያቃልል ቴክኖሎጂ መጠቀም ከተቻለ የማዕድን ልማቱ ትርፋማ እንደሚያደርግ ይገልጻሉ።
አልሚውም፣በሀገር ውስጥ ቴክኖሎጂ ለማቅረብ እየተነሳሳ ያለውም በጋራ በመሆን እንደሀገር የተያዘውን በኢኮኖሚ የማደግ እቅድ ለማገዝ የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለበቸው ነው መልእክት ያስተላለፉት።
እሳቸው በግላቸው ልማቱን በማጠናከርና ድርጅታቸውን ወደ ኩባንያ በማሳደግ የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት ተዘጋጅተዋል። ተጨማሪ የወርቅ ማጠቢያ ማሽን ለመግዛትም አቅደዋል። አሁን እያለሙ ያሉት በአካባቢው በማህበር ተደራጅተው ለወርቅ ማዕድን ልማት ቦታ ከወሰዱ ወጣት ማህበራት ላይ በኪራይ በወሰዱት ቦታ ላይ ሲሆን፣ አነስተኛ የወርቅ ማዕድን አልሚ ናቸው።
አቶ አቻምየለህ ሀገር ውስጥ ገዝተው ጥቅም ላይ ያዋሉት የደለል ወርቅ ማጠቢያ ማሽን በአቶ አብረሃም ተስፋዬ የተመረተ ነው። አቶ አብረሃም ስለማሽኑ አሰራር፣አጠቃቀም፣አገልግለቱ እንደነገሩን፤ማሽኑ ከደ ለል የለየውን ወርቅ አቅልጦ በአንድ ላይ ጠፍጥፎ ያወጣል። ብክነት አይኖርም። ማሽኑ በግዥ በገቡ ግብአቶች በጥንቃቄ የተሰራ በመሆኑ በዓለምአቀፍ ከሚቀርቡ ማሽኖች ደረጃ እኩል ነው። በውጭ ከሚመረተው የተለየ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል።
ከውጭ የሚመጣው የወርቅ ማጠቢያ ማሽን ተገጣጣሚ ባለመሆኑ ለማጓጓዝ ምቹ አይደለም።በማጓጓዝ ሂደትም ጉዳቶች ያጋጣማሉ። በሀገር ውስጥ በተመረተው ማሽን በዚህ በኩል ያለውን ችግር ለማስቀረት ተችሏል። ሌላው በአጠባ ወቅት ለደቃቅና አንኳር ወርቅ የሚለቀቀው ኃይል እኩል እንዳይሆን በማድረግ ብክነትን ማስቀረት ተችሏል። የውጭው ማጠቢያ ግን እንዲህ ያለ ባለመሆኑ ለደቃቅ ወርቅ ምቹ አይደለም።
በአጠባ ወቅት የሚያመልጥ ወርቅ እንዳያጋጥም በስድስት ደረጃ ለመቆጣጠር የሚያስችል በመሆኑ ከሥጋት ነጻ ያደርጋል። በአጠቃላይ እንደ ወርቁ መጠን ከፍና ዝቅ ባለ የኃይል ቁጥጥር ዘዴ እንዲያግዝ ተደርጎ ነው የተሰራው። ማሽኑ በሰአት 50 ቶን አፈር ማጠብ እንዲችል ተደርጎ ነው የተሰራው፤ ክብደቱም 50ኪሎ ግራም ይመዝናል። በቀላሉ ከቦታ ቦታ በማንቀሳቀስ ነው ጥቅም ላይ የሚውለው።
ከውጭ በግዥ የሚገኝ ማሽን ለባለሙያ ተጨማሪ ወጭ የሚያስወጣ እንደሆነ የገለጹት አቶ አብርሃም፣ እርሳቸው ማሽኑን ተክለው፣ስልጠናም ሰጥጠው ችግርም ሲያጋጥም በቦታው ተገኝተው በማስተካከል ጭምር አገልግሎት እንደሚሰጡ በማብራራት የማሸኑኑን በሀገር ውስጥ መሰራት ፋይዳ ገልጸዋል።
ከውጭ ተገዝቶ አገልግሎት ላይ የሚውለው ግን ተጨማሪ ወጭ እንደሚጠይቅ ነው አቶ አብርሃም የጠቆሙት። በሀገር ውስጥ የተመረተው ተመሳሳይ ቴክኖሎጂ በዚህ ወቅት ሁለት ሚሊየን ስድስት መቶ ሺ ብር እንደሚሸጥና ከውጭ የሚገባው 12ሚሊየን ብር እንደሚፈልግ ተናግረዋል።
አቶ አብርሃም ለድንጋይ ወቅር ማዕድን ልማትም ከመፍጫ፣እስከ ወርቅ ማቅለጫ ያለውን ሂደት በማከናወን የሰው ጉልበትን ተክቶ የሚሰራ ማሽን ሰርተው በማቅረብ በባህላዊ መንገድ የሚሰራን የማዕድን ልማት ማገዝ ችለዋል። በሀገር ውስጥ ተመርቶ የሚቀርበው የድንጋይ ወርቅ ማሽን በዋጋ ከሶስት ሚሊየን ብር በላይ ነው የሚያወጣው።እንደ ደለል ወርቅ ማጠቢያው ተንቀሳቃሽ አይደለም።የወርቅ ማድኑ በሚገኝበት አካባቢ ነው የሚተከለው።
አቶ አብረሃም ለማዕድን ልማቱ የሚሆኑ መሣሪያዎችን ማምረት የጀመሩት ለራሳቸው ሲሉ ነበር፤ በእርሻ ኢንቨስትምንት ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተሰማሩበት ወቅት ባገኙት አጋጣሚ ለግንባታ በሚውል የእምነበረድ የማዕድን ልማት ላይ ይሰማራሉ። በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥራ ለመሥራት መሰርሰሪያ፣ መቁረጫ፣ ማጠቢያ ማሽንና ሌሎችንም መሳሪያዎች በራሳቸው አምርተው ጥቅም ላይ በማዋል ሥራቸውን ለማቃለል ችለዋል።
ቆይተውም ማሽኖችን ለገበያ በማዋል ገቢ ማግኘት ጀመሩ። በቤንሻንጉል ክልል የወርቅ ማዕድን ሀብቱ እንደሚገኝ ካረጋገጡ በኃላም ሥራውን ለማቃለል የሚያግዘውን የወርቅ ማጠቢያ ማሽኑን ለመሥራት ተነሳሱ። የደለል ወርቅና የድንጋይ ወርቅ ማጠቢያ ማሽኖችን ሰርተው ሸርቆሌ አካባቢ ለአልሚዎች ለገበያ ማቅረብ ችለዋል።
በደቡብ ክልል ዲማ አና በጋምቤላ ክልል በወርቅ ማዕድን ልማት ለተሰማሩም ምርታቸውን በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርገዋል። የወርቅ ማጠቢያ ምርታቸውን በመጠቀም በኦሮሚያ ክልል ሻኪሶ ላይ የሚገኙ የወርቅ ማዕድን አልሚዎች ደንበኞቻቸው ናቸው። መንግሥት ለዘርፉ የብድር አገልግሎት እንዲመቻች በማድረግ በተለያየ መንገድ እገዛ ቢያደርግላቸው የበለጠ እንደሚሰሩ የገለጹ ሲሆን፣ የአቶ አብርሃም ምኞትና እቅድ ማሽኖቹን በስፋት በማምረት የሀገራቸው የማዕድን ልማት በቴክኖሎጂ የታገዞ ሆኖ ማየት ነው።
አቶ አብረሃም የተወለዱትም ያደጉትም በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ በግ ተራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው። የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኃላ በቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋም ውስጥ በሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ተምረው ተመረቀዋል። በሥራ ዓለም ደግሞ የእርሻ መሣሪያዎችን ከውጭ በማስመጣት ለግብርናው ሥራ ከሚያቀርቡ የጣሊያን ዜግነት ካላቸው ጋር የመሥራት ዕድሉን አገኙ።
ከውጭ የሚገባ እንጂ በሀገር ውስጥ በሀገር ባለሙያ ተመርቶ ለገበያ የሚቀርብ የምርት አገልግሎት አለማየታቸው በውስጣቸው ቁጭት ይፈጥርባቸዋል። አቶ አብረሃም በቁጭት አልቀሩም፤ ትምህርታቸውንና የስድስት አመት የሥራ ልምዳቸውን ተጠቅመው የራሳቸውን የእርሻ መሣሪያ መሥሪያ (ዎርክሾፕ) ከፈቱ።
ከውጭ የሚመጡትን የተለያዩ የእርሻ መሣሪያዎች በሥራው አጋጣሚ ያውቋቸው ስለነበር ተመሳሳይ የሆኑ መሳሪያዎችን አምርተው ለማቅረብ አልተቸገሩም። በዚህ የተጀመረው ሙያ ነው ለማዕድን ዘርፉ የሚያግዘውን የወርቅ ማጠቢያ ማሽን ለመሥራት ያነሳሳቸው።
ለውጤት የበቁት ነገሮች አልጋ በአልጋ ሆነውላቸውም አልነበሩም። ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፈዋል። አቶ አብረሃም ሥራቸው በድካም ውስጥ ያለፈ ቢሆንም ጥቅም ላይ ውሎ ማየታቸው ድካማቸውን እንዲረሱት አርጓቸዋል።
የሰሯቸውን ማሽኖች የኢትዮጵያ ምርት ብለው ስለሚለጥፉበት እንጂ በሀገር ውስጥ የተመረተ ስለመሆኑ የሚለየው ሰው አላጋጠማቸውም። ከውጭ ሀገሮች በሚመጡ ቴክኖሎጂዎች ላይ ብቻ እምነት ይጥል በነበረ ማህበረሰብ ክፍል ውስጥ ሆነው በራስ መሥራት እንደሚቻል ማሳየት በመቻላቸው ኩራት አሳድሮባቸዋል። ለሌሎችም አርአያ እንደሆኑ ያስባሉ። ፍላጎታቸውም አርአያ ሆነው ብዙዎች እንደርሳቸው አምርተው በገቢ ተጠቃሚ ሲሆኑ፣ምርቱም ኢትዮጵያ ውስጥ ሲመረት ማየት ነው።
ከእሳቸው ጋር ባደረግነው ቆይታ ያላቸውን የሥራ ትጋት ከገጽታቸው ለመገንዘብ ችያለሁ። ማዕድን ሚኒስቴር በያዝነው ወር መጀመሪያ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ ባካሄደው የማዕድንና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ ላይ የማዕድን ዘርፉን የሚያግዝ የቴክኖሎጂ ውጤቶቻቸውን ይዘው ከቀረቡት መካከል አቶ አብረሃም ተስፋዬ አንዱ ነበሩ።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ዓርብ ኅዳር 30 ቀን 2015 ዓ.ም