ኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በርካታ እምቅ የአትሌቲክስ አቅም ያላት አገር ብትሆንም መጠቀም የቻለችው ውስን መሆኑን ባለሙያዎች ሲናገሩ ይደመጣል። በተለይም ኢትዮጵያ ከረጅምና መካከለኛ ርቀት ውድድሮች ውጪ በአጭር ርቀቶችና በሜዳ ተግባራት ውድድሮች በተለያዩ አካባቢዎች ያላትን እምቅ የአትሌቲክስ አቅም አውጥታ መጠቀም አልቻለችም። የረጅም ርቀት ውድድሮች በአለም ላይ እየተመናመኑ መምጣታቸውና ያሉትም ከፍተኛ ፉክክር የሚደረግባቸው በመሆኑ ኢትዮጵያ በውጤታማነቷ ለመቀጠል ፊቷን ወደ አጭር ርቀትና የሜዳ ተግባራት ውድድሮች ማዞር ያለባት ጊዜ አሁን እንደሆነ የፌዴሬሽኑም እምነት ነው።
ለዚህ ደግሞ ትልቅ እምቅ አቅም ካላቸው አካባቢዎች አንዱ የደቡብ ኦሞ ዞን ተጠቃሽ ነው። “ታላቁ ሩጫ በትንሿ ኢትዮጵያ ጂንካ” በሚል መሪ ሃሳብና “ለሠላም እሮጣለሁ” በሚል መፈክር” በፋን ኢትዮጵያና በደቡብ ኦሞ ዞን ትብብር በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን በጂንካ ከተማ ሰሞኑን በተካሄደው የስምንት ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ላይም ዞኑ ከሃገር አልፈው በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያን ሊያስጠሩ የሚችሉ ተተኪ አትሌቶችን ለማግኘት የሚያስችል የአትሌቲክስ እምቅ ኃይል እንዳለው ማስተዋል ተችሏል።
ሕዳር 25 ቀን 2015 ዓ.ም በተካሄደው የስምንት ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በክብር እንግድነት የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጀላ መርዳሳ፣ የደቡብ ኦሞ ዞን ከፍተኛ የሆነ እምቅ የአትሌቲክስ አቅም ያለው መሆኑን መገንዘባቸውን ገልጸዋል፡፡የደቡብ ኦሞ ዞን በተፈጥሮና በባህል የታደለና ከፍተኛ የቱሪስት መስህብ ያለበት ከመሆኑም ባሻገር ከሃገር አልፈው በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያን ሊያስጠሩ የሚችሉ ተተኪ አትሌቶችን ለማግኘት የሚያስችል የአትሌቲክስ እምቅ አቅም እንዳለው መገንዘባቸውን ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም መንግሥት በዞኑ ላለው የስፖርት እንቅስቃሴ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ የሚከታተለውና አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ያመላከቱት አቶ ቀጀላ፤ የዞኑ ነዋሪዎችም የተጀመረውን የማሕበረሰብ ስፖርት ከዚህ በኋላም አጠናክረው እንዲያስቀጥሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ በበኩላቸው፤ ዞኑ በቱሪዝም ብሎም በአካባቢው ያሉትን ግዙፍ የስኳር ፋብሪካዎች ጨምሮ በግብርና ምርትም ከክልሉ አልፎ ለኢትዮጵያ ዋልታና ማገር የሚሆን ግዙፍ ሃብት ያለበት መሆኑን ጠቁመው፤ በስፖርት በተለይም በአትሌቲክሱ ትልቅ ደረጃ ሊደርስ የሚችል እምቅ ሃብት መኖሩን ተናግረዋል፡፡
የደቡብ ኦሞ ዞን በምስራቅ አፍሪካ በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ርቀቶች በርካታ ስመ ጥር ተወዳዳሪዎች መፍለቂያ ከሆነው ሰሜን ኬኒያ ጋር የቅርብ ጎረቤት በመሆኑ “ትኩረት ሰጥተን ከሠራንበት በእኛም ሃገር በዘርፉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ አያሌ አትሌቶችን ለማፍራት የሚያስችል ዕድል አለ” ብለዋል፡፡ ዞኑ በተለይም የሰሜን ኬኒያ አጎራባች ከሆኑት በእኛንጋቶም፣ ከዳሰነች፣ ከሐመር፣ ከቦዲ፣ ከሙርሲ በአጭርና በመካከለኛ ርቀት ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊያስጠሩ የሚችሉ በርካታ አትሌቶችን ለማፍራት ትልቅ አቅም ያለው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በሩጫም ብቻ ሳይሆን በጦር ውርወራ፣ በውሃ ዋና፣ በእርምጃና በሌሎችም የስፖርት ዓይነቶች ጭምር ከፍተኛ እምቅ ሃብት የሚገኝበት መሆኑንም ዋና አስተዳዳሪው አመላክተዋል፡፡ በመሆኑም ከፋን ኢትዮጵያ ጋር ከተካሄደው ከዚህ ውድድር ጀምሮ የዞኑን ብሎም የሃገርን እምቅ የአትሌቲክስ ሃብት ለመጠቀም የሚያስችል ወርቃማ በር መከፈቱን ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ከፍተኛ እምቅ ሃብት ባለበት የአትሌቲክስ ዘርፍም ሆነ በሌሎችም አትራፊ የሆኑ የዞኑ ሃብቶች ሁሉ ኢንቨስት ማድረግና ሃገርን መጥቀም የሚፈልግ ሃገር ወዳድ ባለ ሃብት ሁሉ ወደዞኑ በመምጣት ኢንቨስት እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ለዚህም ዞኑ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግና ኢንቨስት ማድረግ ከሚፈልጉ ባለሃብቶች በሙሉ ትብብር ለመሥራት በቁርጠኝነት ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል፡፡
የፋን ኢትዮጵያ መሥራች አትሌት ፋንቱ ሚጌሶ በበኩሏ፤ ፋን ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ተመሳሳይ የጎዳና ላይ ሩጫ ሲያካሂድ መቆየቱንና ታች ሕብረተሰቡ ድረስ ወርዶ በመሥራት በአጭር ጊዜ ውስጥ በዘርፉ እምቅ አቅም ላላቸው በርካታ ወጣቶች ዕድል መፍጠሩን ተናግራለች፡፡ አሁን ደግሞ ለሰባተኛ ጊዜ ከአስራ ስድስት በላይ ብሔር ብሔረሰቦች ተፈቃቅረውና ተከባብረው በሰላም በሚኖሩባት የደቡብ ኦሞዋ ፈርጥ ትንሿ ኢትዮጵያ ጂንካ ከተማ ከሰላሳ ሺ በላይ የከተማዋንና የአካባቢዋን ነዋሪዎች በመሳተፍ በደማቅ ሁኔታ መካሄዱን ገልጻለች።
ሩጫው በዞኑ ያለውን እምቅ የአትሌቲክስ አቅም በመጠቀም እንደ ፈር ቀዳጁ ታላቅ አትሌት አበበ ቢቂላና ምሩጽ ይፍጠር፣ እንዲሁም ጥሩነሽ ዲባባ የመሳሰሉ ታላላቅ አትሌቶችን የማፍራት ዓላማ ያለው መሆኑን አትሌት ፋንቱ ጠቁማለች። ከዚህ በተጨማሪም በጂንካ ከተካሄደው ከዚህ የጎዳና ላይ ሩጫ ጀምሮ ውድድሩን ለሚያሸንፉና ጥሩ ሰዓት ለሚያስመዘግቡ አትሌቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ መሳተፍ የሚችሉበት ፍቃድና ዕድል የሚመቻችላቸው መሆኑንም አመላክታለች፡፡ ለአንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ከአሁን በኋላ በቀጣይም በየአመቱ በተከታታይ ተመሳሳይ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድሮችን ለማካሄድና በዞኑ ያለውን እምቅ የአትሌቲክስ አቅም ለሃገር ጥቅም ለማዋል መታቀዱንም አትሌት ፋንቱ አስረድታለች፡፡
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን ኅዳር 28/ 2015 ዓ.ም