ወቅቱ ቴክኖሎጂን በሁሉም አማራጮች በመጠቀም ከዘመኑ ጋር አብሮ መዘመንን የግድ ብሎ የሚጠይቅበት ነው:: ኢትዮጵያም ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የዲጅታል ዓለምን እየተቀላቀለች ባለችበት በዚህ ወቅት በርካታ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ተግባራዊ እየሆኑ ይገኛሉ:: በተለይም የዜጎችን ሕይወት ቀለል ማድረግ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎች ከፍተኛ ትኩረትን የሚስቡ ናቸው:: ቴክኖሎጂን ከመተዋወቅ ባለፈ ተግባራዊ ለማድረግ የሚደረገው ሩጫ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም:: ዕለት ተዕለት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የመተዋወቅ ዕድል እየተፈጠረ ያለውም በዚሁ ምክንያት ነው::
ከሰሞኑም የክፍያ ሥርዓቶችን ቀላልና ለሁሉም ሰው የተመቸ እንዲሆን ማድረግ የሚያስችለው ሳንቲም ፔይ ፋይናንሻል ሶሉሽን አክሲዮን ማህበር አዲስ የክፍያ ስርዓትን ይፋ አድርጓል:: ሳንቲም ፔይ የክፍያ ስርዓት በወጣትና አንጋፋ በሆኑ ሥራ ፈጣሪዎች የተቋቋመ አገር በቀል ድርጅት ሲሆን፤ ኢትዮጵያን ወደ ዲጅታሉ ዓለም ለመቀየር የተቋቋመ የፋይናንስ ድርጅት ስለመሆኑም ተነግሯል::
አዲስ የክፍያ ስርዓትን ይዞ የመጣው የሳንቲም ፔይ ፋይናንሻል ሶሉሽን አክሲዮን ማህበር የኢትዮጵያን የዲጅታል ዓለም ከፍ ማድረግ የሚችልና ከዓለም አቀፍ ተቋማትና የፋይናንስ ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን ፍጥነት እየተሳሰረ የሚገኝ ነው:: ድርጅቱ በኢትጵያ የክፍያ ስርዓት ውስጥ ማገልገል እንዲችል ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባገኘው ህጋዊ ፈቃድ መቋቋም እንደቻለም ተጠቅሷል:: ሳንቲም ፔይ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ አህጉር ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ ከገንዘብ ንክኪ ነጻ በማድረግ የዘመናዊ ግብይትን ለማስጀመር ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ እየሠራ ያለ የገንዘብ ድልድይ ነው::
የሳንቲም ፔይ የቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው ኢትዮጵያ ቀደምት ስልጣኔ የነበራት፤ ሰፊና አኩሪ ታሪክ ያላትና ተከባብረው የሚኖሩ ሕዝቦች ባለቤት ስለመሆኗ አንስተው፤ ብዙዎቹ የዓለም አገራት መገበያያ ገንዘብ ሳይኖራቸው ኢትዮጵያ በአክሱም ዘመነ መንግሥት የመገበያያ ገንዘብ ኮይን የነበራት መሆኑን አስታውሰዋል:: ገንዘብና የገንዘብ ዝውውር ለአገር ዕድገት ዋናው ምሰሶ መሆኑም አስረድተው፤ ለአንድ ሀገር ጤናማ እንቅስቃሴና ዕድገት ገንዘብ በሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፍ ውስጥ በጥሩ ሁኔታ መዘዋወር አለበት:: ለዚህም ባንኮች በፋይናንሻል ሶሉሽን በመጠቀም ሥራቸውን እንዲያቀለጥፍ ማድረግ የሚገባቸው እንደሆነም አንስተዋል::
ዓለም በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በቴክኖሎጂ ዕለት ተዕለት በሚያስደንቅ ፍጥነት እየተቀየረች እንደሆነ ያነሱት ፕሮፌሰር ዳንኤል፤ በተቀየረውና በመቀየር ላይ ባለው ዓለም በቀደመ ጊዜ አሰራርና ልምድ መጓዝ አዋጭ እንዳልሆነ ገልጸው፤ አዋጭ ካለመሆኑም በላይ በዘመኑ የሚመጡ ችግሮችን መቋቋም አይቻልም ብለዋል:: በተለይም በዚህ ዘመን ገንዘብን በቤት ውስጥ መደበቅና ቆፍሮ ማስቀመጥ ጊዜው ያለፈበት እንደሆነ ሁሉ ገንዘብን ይዞ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስም እንዲሁ ዘመኑን የዋጀ አይደለም:: ለዚህም ሳንቲም ፔይን የመሰሉ ዘመናዊ የክፍያ ስርዓቶች ሊበራከቱ ይገባልም ብለዋል::
‹‹በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገራት በሚኖር እንቅስቀሴ ሁሉ ገንዘብ በእጅ ይዞ መንቀሳቀስ ጊዜው አይደለም›› ያሉት ፕሮፌሰር ዳንኤል፤ በአሁን ወቅት ዓለም በሙሉ ካርድ እየተጠቀመ እንደሆነ በመጥቀስ ለአብነትም ማስተር ካርድ፣ ቪዛ ካርድ፣ ዩኒየን ፔይ፣ አሜሪካን ኤክስፕረስና ሌሎችም የሚገኙበት እንደሆነ አስረድተው፤ ይህም ገንዘብ ሳይሆን ቴክኖሎጂ መሆኑን አንስተዋል:: ዓለም ተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የገንዘብ ዝውውር በማድረግ ግብይት መፈጸም ደረጃ ላይ ደርሷል:: ኢትዮጵያም ከዚህ ውጭ መሆን አትችልም በማለት ሲያስረዱ፤
ዓለም በፈጣን የስልጣኔ ጎዳና ላይ በመሆኗ ኢትዮጵያም ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የቴክኖሎጂ ስርዓት ብቁ መሆን ይኖርባታል:: ይህ ካልሆነና ዛሬም በድሮ አሰራር እንስራ ካልን ከዓለም ገበያ ውደድር የሚያስወጣት ይሆናል:: ከዚህ በተጨማሪም የገንዘብ ኖቶች ህትመት ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ ጫናው ይበረታል:: ስለሆነም መሰል የቴክኖሎጂ ውጤቶችን መጠቀም የግድ በመሆኑ የውጭ ዜጎች የሰሩትን ኢትዮጵያውን ለምን አይሰሩም በሚል ቁጭትና በይቻላል መንፈስ ሳንቲም ፔይ ፋይናንሻል ሶልሽንን ማቋቋም ተችሏል::
ድርጅቱ በኢትዮጵያውያን ወጣቶች የተሰሩ የተለያዩ ሶፍትዌሮችን ማበልጸግ የቻለ ሲሆን በተጨማሪም ባንኮች ለፖስና ለሶፍትዌር ግዢ የሚያወጡትን ከፍተኛ ወጪ መቀነስ አስችሏል:: በቀጣይም ለባንክ የሚሆኑ የተለያዩ ሶፍትዌሮችን በመሥራት ባንኮች ከከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ መዳን እንዲችሉ ያደርጋል:: በአሁን ወቅትም ባንኮች ለፖስ የሚወጡትን ዋጋ 20 ጊዜ በመቀነስ በተሻሉ የፖስ ማሽኖች በመተካት የውጭ ምንዛሪን ማዳን ተችሏል:: ከውጭ ባንኮች ጋር መሥራት የሚያስችል መደላድልም ተፈጥሯል:: ከአገር ውጭ ባሉ ከጎረቤት ሀገራት ጭምር መሥራት የሚችል በመሆኑ በቅርቡም ከአውሮፓ ባንኮችና አስር ሺህ ከሚደርሱ የአሜሪካን ባንኮች ጋር መሥራት የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እየሠራ እንደሆነም አስረድተዋል::
የኢፌዴሪ ኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሀሚድ በኩላቸው፤ የሳንቲም ፔይ ፋይናንሻል ሶሉሽን አክሲዮን ማህበር በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘረፉን ለማሻሻልና አጋዥ የሆኑ ሥራዎችን ከስድስት ባንኮችና ከቴሌ ብር ጋር በመተባበር ሥራውን የጀመረ መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ የዲጅታል ምህዳሩንና ቴክኖሎጂን በመጠቀም የበለጸገ ማህበረሰብን መፍጠር የሚያስችላትን ከፍተኛ አቅም መገንባት ባትችልም በዲጅታል ምህዳሩ አቅም በመፍጠር፣ የተለያዩ ዕውቀቶችንና ክህሎቶችን በማደራጀት ላይ የምትገኝ እንደሆነ ጠቅሰዋል::
መንግሥት ቴክኖሎጂ የመጪው ጊዜ ወሳኝ መወዳደሪያ መሆኑን በማመን መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ እና ልዩ የፈጠራ ችሎታ ላላቸው እንዲሁም ቁርጠኛ ለሆኑ ግለሰቦች አዳዲስ ቢዝነሶችንና አገልግሎቶችን እንዲጀምሩ አስቻይ ሁኔታዎችን እየፈጠረ መሆኑን አንስተዋል:: ሳንቲም ፔይ ፋይናንሻል ሶሉሽን አክሲዮን ማህበርም መንግሥት የክፍያ ሰርዓት ላይ ያደረጋቸውን የፖሊሲ ማሻሻያዎች እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ወደ ምህዳሩ የገባ የክፍያ ስርዓት እንደሆነ ገልጸው፤ ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር ወደ ተግባር የሚያስገባው የቴክኖሎጂ ስርዓት በኢትዮጵያ የዲጅታል ዘርፉ ላይ የተፈጠረውን ክፍተት የሚሞላ በመሆኑ የሚበረታታ ነውም ብለዋል::
‹‹መንግሥት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአሁን ወቅት የቁጥጥር ስርዓትን ማሻሻል ችሏል›› ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዲጅታል የፋይናንሻል አገልግሎት ሰጪዎችን በማካተትና አዋጁን በማሻሻል በዘርፉ አቅም ያላቸው የዲጅታል የክፍያ ስርዓትን የሚያቀርቡ ተቋማት እንዲበራከቱ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል:: ይህም የአገሪቱን የፋይናንስ ስርዓት የዘመነ በማድረግ ማህበረሰቡም ለዘርፉ ምቹና ቀልጣፋ የሆነ አገልግሎት እንዲያገኝ ያደርጋል:: ሳንቲም ፔይ በአገሪቱ ያለውን የዲጅታል ፋይናንሻል ግብይት ተጠቃሚ የሆነ ማህበረሰብን ለመፍጠር የሚያግዝ ሥርዓት ነው:: ከዚህም በተጨማሪ የክፍያ ስርዓትን በማዘመን የተለያዩ የፋይናንሻል መድረኮች ማለትም ባንኮችና የክፍያ ሞባይል ዋሌት መተግበሪያዎች መካከል የክፍያ ስርዓትን ለመፍጠር የመጣ በመሆኑ በዘርፉ ያለውን እጥረት በከፍተኛ መጠን ሊቀርፍ እንደሚችል ገልጸዋል::
ድርጅቱ ሀገሪቷ ለፖስ ማሽኖች መግዣ በየዓመቱ የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚቀንስ እንደሆነ የታመነበት ሲሆን፤ ከዚህም ባለፈ ቴክኖሎጂው በኢትዮጵያ ውስጥ በጥሬ ገንዘብ ላይ ያልተመሰረተ ዘመናዊ የገንዘብ ዝውውር እንዲመሰረት ያደርጋል:: የገንዘብ ዝውውሮችን ምቹና ቀልጣፋ እንዲሁም ከማጭበርበር የጸዳ እንዲሆንም ያስችላል:: መንግሥት ለጥሬ ገንዘብ ህትምት የሚያወጣውን የውጭ ምንዛሪ በእጅጉ ከመቀነስ ባሻገር አገሪቷ የያዘችውን የዲጅታል ኢትዮጵያ የ2025 ስትራቴጂ ዕቅድ ከማሳካት አንጻር ሳንቲም ፔይ የራሱን አሻራ ማኖር የሚችል ነው ያሉት ምክትል ዳይሬክተሯ፤ ማህበረሰቡም በፋይናንስ ዘርፍ ያለውን የኋላ ቀር አሰራር ቀልጣፋ፣ ጊዜ ቆጣቢና ከጥሬ ገንዘብ ንክኪ ነጻ የሆነውን ፋይናንሻል ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የራሱን ሚና እንዲወጣም አሳስበዋል::
የኢትጵያን የዲጂታል ዓለም ከፍ ማድረግ ያስችላል የተባለውና በኢትዮጵያውያን ተመስርቶ ይፋ የሆነው የሳንቲም ፔይ ፋይናንሻል ሶሉሽን አክሲዮን ማህበር አገር በቀል እንደመሆኑ ተደራሽነቱም ሰፊ ነው በማለት ያስረዳው የድርጅቱ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ወጣት ትንሳኤ ደሳለኝ ነው:: እንደ ወጣት ትንሳኤ ገለጻ፤ የክፍያ ሥርዓቶችን ቀላልና ለሁሉም ሰው የተመቸ ለማድረግ እየሠራ ያለ ተቋም ሲሆን በወጣትና አንጋፋ በሆኑ ሥራ ፈጣሪዎች የተቋቋመ አገር በቀል ድርጅት እንደሆነም ገልጿል::
ድርጅቱ በኢትዮጵያ የክፍያ ስርዓት ውስጥ ኦፕሬተር ሆኖ እንዲያለማ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ፍቃድ አግኝቶ በሐምሌ ወር 2014 ሥራ መጀመሩን አንስተው፤ ሳንቲም ፔይ ፋይናንሻል ሶሉሽን አክስዮን ማህበር፤ ሦስት አይነት የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቶችን ይዞ መምጣቱንም አስረድቷል።
ሳንቲም ፔይ ይፋ ያደረጋቸው፤ ፖስ (ተንቀሳቃሽ የክፍያ መተግበሪያ)፣ ዩኒፋይድ ፔይመንት ኢንተርፌስ (ዩ ፒ አይ) (ባንኮችን የሚያስተሳስር የክፍያ ስርዓት) እና ፔይመንት ጌትዌይ (በኢንተርኔት የሚደረጉ ክፍያዎችን የሚያስተሳስር) የተባሉ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቶችን ነው። እነዚህን የክፍያ ሥርዓቶች ከስድስት አጋር ባንኮች ማለትም ከአቢሲንያ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንከ፣ ቡና ባንክ፣ አዋሽ ባንክ አማራ ባንክ፣ ብርሃን ባንክ፣ ይሙሉ እና ከቴሌብር ጋር በመተባበር ተግባራዊ ማደረግ ተችሏል።
ይህ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓትም በኢትዮጵያ ደህንነት መረብ ኤጀንሲ የደህንነት ምርመራ ሰርተፊኬት ያገኘ ሲሆን፤ በዓለም አቀፍ ደረጃም፤ በፒሲ አይ ኤስ ኤስ ሲ (PCSSC PAYMENT CARD INDUSTRY SECURITY STANDARDS COUNCIL) በኩል ደህንነቱ መረጋገጡን የቦርድ ሰብሳቢው ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው ሲያስረዱ፤ ሳንቲም ፔይ ከገንዘብ ንክኪ ነጻ የሆነ ዲጂታል እና የዘመናዊ ግብይት ተጠቃሚ የሆነ ማህረሰብን ለፍጠርና፤ የክፍያ ሥርዓትን ለማዘመን እየሠራ የሚገኝ ነው ብለዋል:: በዚህም መሠረት ሀገራዊ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቱን ለማፋጠን ፖስ ማሽኖችን ጨምሮ ሦስት አዳዲስ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቶችን በማምጣት የዲጂታል ፋይናንስ ኢንዱስትሪውን መቀላቀል እንደቻለም ገልጸዋል።
ተንቀሳቃሽ ፖስ ማሽኖቹ ለነጋዴዎች ምቹና ከተለያዩ የክፍያ ሥርዓቶች ጋር የተገናኙ መሆናቸውን የገለጸው ዋና ሥራ አስኪያጁ ወጣት ትንሳኤ፤ ኔትወርካቸውም አሁን ካሉት ፖስ ማሽኖች 65 በመቶ ድረስ የተሻሉ መሆናቸውን አስረድቷል። በተጨማሪም በላያቸው ላይ በተገጠሙላቸው የፖስ መቆጣጠሪያ መሳሪያ አማካኝነት፤ ችግሮች ሲከሰቱ ከቢሮ ሆኖ ማወቅና ማስተካከል ስለሚቻል የጥገና ጊዜና ወጪን ከመቀነስ አንጻር ጠቀሜታቸው ከፍተኛ እንደሆነም አስረድቷል። ባንኮችም ለፖስ የሚያወጡትን ዋጋ በ20 በመቶ በማሳነስ ትልቅ የውጭ ምንዛሪ ወጪን ማዳን እንደሚያስችል ተናግሯል።
ተንቀሳቃሽ ፓስ ማሽኖቹ የውጪ ሀገራት የክፍያ ካርዶችን የሚቀበሉና ማስተናገድ የሚችሉ መሆናቸውን ያነሳው ወጣት ትንሳኤ፤ በቅርቡም ከአውሮፓ ባንኮች እንዲሁም ከ10 ሺ በላይ የሆኑ የአሜሪካን ባንኮች ወደ ሥርዓቱ የሚገቡበት ሁኔታ ስለመፈጠሩና አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ ስለመሆናቸው አስረድቷል። በተጨማሪም ዩኒፋይድ ፔይመንት ኢንተርፌስ (ዩ ፒ አይ) ባንኮችን የሚያስተሳስር የክፍያ ስርዓት ሲሆን፤ የሁሉም ባንክ ተጠቃሚዎችን በአንድ ቦታ ፈጣን አገልግሎትን እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን ተገልጿል:: ፔይመንት ጌትዌይ ደግሞ በኢንተርኔት የሚደረጉ ክፍያዎችን የሚያስተሳስርና፤ የኦን ላይን ክፍያዎችን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው እንደሆነም ተነግሯል።
የሳንቲም ፔይ ፖስ ማሽኖችን በመጠቀም የታክስ፣ የአገልግሎቶች፣ የኢንተርኔት፣ ትራፊክ፣ DSTV እና የአየር መንገድ ክፍያዎችን ማከናወን የሚቻል ሲሆን፤ በቀጣይ ሁለት ዓመት ውስጥም ሳንቲም ፔይ ፋይናንሻል ሶሉሽን 70 ሺ የፖስ ማሽኖችን በመላው ሀገሪቱ ለማሰራጨት ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል:: በዚህም ከ250 ሺ በላይ ተገልጋዮች ይጠቀሙበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ኅዳር 28/ 2015 ዓ.ም