በመም ውድድሮች ጠንካራና ውጤታማ የሆኑ በርካታ ሴት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፊታቸውን ወደ ማራቶን ውድድሮች አዙረው የአርባ ሁለት ኪሎ ሜትር ፉክክሩ ላይ ጎልተው እየወጡ ይገኛሉ። በመም ውድድሮች ብዙ ስኬት የሌላቸውና መነሻቸውም ማራቶን የሆነ በርካታ ሴት አትሌቶችም በታላላቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ብዙ ድሎችን ሲያስመዘግቡ ታይተዋል።
ከሌሎች ውድድሮች በተለየ ለግምት እንኳን አስቸጋሪ በሆነው የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያውያን ሴት አትሌቶች በተለያዩ አለም አቀፍ ውድድሮች በስኬት የተንበሸበሹበት አመት ቢኖር የዘንድሮው በጉልህ መጠቀሱ የግድ ነው። እንስቶቹ ኢትዮጵያውያን በርቀቱ በርካታ አለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ከማሸነፍ በዘለለ ፈጣን ሰአቶችን ማስመዝገብ መቻላቸው ወርቃማ የማራቶን ዘመናቸው ላይ እንደሚገኙ ማሳያ ነው።
ባለፈው ክረምት በፖርትላንድ ኦሪገን ከተካሄደው የአለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ጀምሮ ኢትዮጵያውያን ሴት አትሌቶች በርካታ የማራቶን ድሎችን አስመዝግበዋል። የ27 አመቷ ድንቅ አትሌት በአለም ቻምፒዮናው ስታሸንፍ የቻምፒዮናውን ክብረወሰን በ2:18:11 በማሻሻል ጭምር ነበር። ከዚህ ታላቅ ስኬት በተጨማሪ ባለፉት ስምንት ወራት ብቻ የኢትዮጵያ ሴቶች የማራቶን ክብረወሰን ሶስት ጊዜ በተለያዩ አትሌቶች ተሻሽሏል።
ባለፈው ሚያዝያ በሃምቡርግ ማራቶን አትሌት ያለምዘርፍ የኋላው ከ2019 ወዲህ የኢትዮጵያን የማራቶን ክብረወሰን በ2:17:23 አሻሽላለች። ይህም በርቀቱ የአለም ሁለተኛው ፈጣን ሰአት ሆኖ ተመዝግቧል። ባለፈው መስከረም መጨረሻም ይህ የኢትዮጵያ የርቀቱ ክብረወሰን በአትሌት ትእግስት አሰፋ በርሊን ማራቶን ላይ ከሁለት ደቂቃ በበለጠ ሊሻሻል ችሏል። 2:15:37 የሆነው ሰአት የኢትዮጵያ አዲስ ክብረወሰን ከመሆኑ በዘለለ የአለም ሁለተኛው ፈጣን ሰአትም ነበር።
በበርሊን የተመዘገበው ይህ የኢትዮጵያ የማራቶን ክብረወሰን ከሁለት ወር በኋላም ከትናንት በስቲያ ቫሌንሲያ ማራቶን ላይ እንደገና ተሻሽሏል። የክብረወሰኑ ባለቤት የሆነችው የ31 አመቷ አትሌት አማኔ በሪሶ 2:14:58 በሆነ ሰአት ስታሸንፍ ሁለተኛው የርቀቱ የአለም ፈጣን ሰአት ሆኗል። ይህ ሰአት አትሌቷ የራሷንና የቫሌንሲያ ማራቶን ክብረወሰንን ከአምስት ደቂቃ በበለጠ ያሻሻለችበት ሲሆን በኬንያዊቷ የኦሊምፒክ ቻምፒዮን ፕሬስ ጂፕቺርቺር ከተያዘው የአለም ክብረወሰንም በ54 ሰከንዶች ብቻ የዘገየ ነው።
በዚሁ ውድድር ትልቅ ትኩረት አግኝታ የነበረችው የአለም የ10ሺ ሜትር ቻምፒዮኗ አትሌት ለተሰንበት ግደይ በማራቶን የመጀመሪያዋን ፉክክር አድርጋ ሁለተኛ ነው ያጠናቀቀችው። ያስመዘገበችው 2:16:49 ሰአት ግን በመጀመሪያ የማራቶን ውድድር ከተመዘገቡ ሰአቶች ፈጣኑ በመሆን አትሌቷ ወደ ፊት በርቀቱ ትልቅ ታሪክ መስራት እንደምትችል ፍንጭ የሰጠ ነው።
ለተሰንበት በመጀመሪያ የማራቶን ውድድር ተሳትፎ በታሪክ ፈጣኑን ሰአት ቫሌንሲያ ላይ ከማስመዝገቧ ከሶስት ሳምንታት በፊትም ኢትዮጵያዊቷ የኦሊምፒክና የአለም ቻምፒዮና የ10 ሺ ሜትር ባለ ድል አልማዝ አያና ተመሳሳይ ታሪክ መስራት እንደቻለች ይታወሳል። አልማዝ ከሶስት ሳምንት በፊት በአምስተርዳም ማራቶን በርቀቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ተወዳድራ 2:17:20 በሆነ ሰአት ስታሸንፍ ያስመዘገበችው ሰአት በርቀቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በተፎካከረች አትሌት የተመዘገበ ፈጣኑ ሰአት ነበር። በመም ውድድሮች ብርቱ ተፎካካሪዋ የሆነችው አትሌት ገንዘቤ ዲባባም በርቀቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ተወዳድራ አልማዝን ተከትላ ሁለተኛ ስታጠናቅቅ ያስመዘገበችው 2:18:05 ሰአት በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
እንደ አጠቃላይ ከአለማችን ሃያ ፈጣን የሴቶች ማራቶን ሰአቶች አስሩ የተመዘገቡት በኢትዮጵያውያን አትሌቶች ነው። ከነዚህ አስር ፈጣን ሰአቶች ውስጥ ስድስቱ የተመዘገቡት ደግሞ በ2022 የውድድር አመት ነው። ቀዳሚ ሆነው የተቀመጡት ሁለት ፈጣን ሰአቶች በኬንያውያን አትሌቶች የተመዘገቡ ቢሆንም አንዱና ዋነኛው የአለም ክብረወሰን ከሶስት አመት በፊት ነው የተመዘገበው። ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዚህ የውድድር አመት የማራቶን ወርቃማ ጊዜ እያሳለፉ ይገኛሉ ቢባል አልተጋነነም። ይህም በቅርብ ርቀት እየተከተሉት የሚገኘውን የአለም የማራቶን ክብረወሰን ለመስበር ብዙ ጊዜ ላይፈጅባቸው እንደሚችል ተስፋ የሰጠ ሆኗል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ኅዳር 27/ 2015 ዓ.ም