አዳማ አያቴ ጋር ለተወሰነ ጊዜ ኖሬያለሁ። ትምህርቴንም እዛው የመከታተል አጋጣሚውም ነበረኝ። ከከተማዋ ከወጣሁ በኋላም ቢሆን ቅዳሜና እሁድ ጨምሮ ትምህርት በማይኖረኝ ሰዓት እየሄድኩ ጊዜን አሳልፍ ነበር።
በዚህ አጋጣሚ አያቴ ጊቢ ካሉት ተከራዮች አንዱ ከሆነው ከባጃጅ አሽከርካሪው ጋሻውና ከቤተሰቡ ጋር ተዋውቀናል። ቤተኞች ነን ማለት ይቻላል።በተለይ ከሚስቱ ጋር በጣም እንግባባ ነበር።ስትወልድ ከማረስ ጀምሮ በተለያዩ ማህበራዊ ግንኙነቶችም ላይ አብረን ነበርን። እኔም ጋሻውን እንደ ታላቅ ወንድሜ አየው ነበር።እሱ ጋር የሚመጣና አጎቴ የሚለው አንድ ዕድሜው 60 ዓመት የሚጠጋ ታምራት የሚባል ሰውዬንም በእሱ አማካኝነት ተዋወቅሁ። ከአያቴ ጋርም ከአይን ያለፈ ትውውቅ ባይኖራቸውም ታውቀዋለች። ሰውዬው በአዳማ ከተማ ጋራዥ ያለውና የታወቀ ሀብታም ነበር። ከዚህም በላይ ልጁ የታወቀችና የተዋጣላት ተዋናይ ስለነበረች ከሀብቱ በተጨማሪ በአርቲስቷ ልጁም ጭምር ይታወቅና ይከበራል።
“ታድያ አንድ እሁድ እንደተለመደው አዳማ ሄጄ ነበር። ተከራዩ ጋሻው ነይ ዘወር ዘወር ብለን እንምጣ አለኝ።መለስ ብዬ ወደ አያቴ ቤት በመግባት ሳሎን ቁጭ ብላ ለነበረችው እናቴ መጣሁ ዞር ዞር ብዬ በማለት ነገርኳትና ባጃጅ ውስጥ ገባሁና ቁጭ አልኩ።ተሳፋሪ እየጠበቀ ምን አለ ታምራት ቢደውልልኝና ልጋብዝህ ቢለኝ አለ።ወድያው ስልኩ ጮኽ። ታምራት ነው ብሎ አነሳው። የልጁ ድምፅ እንጂ የሰውዬው ባይሰማኝም አወሩ። ህንደኬም አለች ሲለው ሰምቻለሁ። ሰውዬው ያለበት ቦታ ሄድን።መጠጥ ይዘው ቁጭ ያሉ ብዙ ሰዎች ያሉበት ነበርና ደስ እንዳላለኝ አይተው ቤት እንቀይር አሉና ወጣን።ከዚህ ቀደም ባጃጅ እንዳለው ጋሻው ሲያወራ ባልሰማም ሰውዬው ባጃጅ ይዞ ነበርና በእሱ ባጃጅ ለጾም መያዥያ ሊገባበዙ ወደ ተስማሙበት ሆቴል አመራን” ትላለች።
ሆቴል ከገቡ በኋላ የአያቷ ተከራይ ጋሻው መፀዳጃ ቤት ደርሼ ልምጣ ብሎ ሄደ።አቶ ታምራትም ህንደኬን ቁጭ አድርጎ ምግብ ልዘዝ ብሎ ተነሳ።ሁለቱም ቆየት ብለው ተመለሱ። ጋሻው ስፕራይት እንጂ ሌላ የአልኮል መጠጥ ጠጥታ እንደማታውቅ ቢያውቅም የሚጠጣ ቀይሪ ማለቱ ግን አልቀረም።
ህንደኬ ትናገራለች “ የሚጠጣ ልቀይር ብዬ ቶኒክ አልኩ። ቶኒክ መጠጥ ቁጭ ብሎ ነበር። ከፍቼ ልጠጣ ስል ታምራት ሳትበይ አትጠጪ ከበላሽ በኋላ ጠገብኩ ብለሽ ንገሪኝና ትጠጫለሽ አለኝ። የታዘዘው ምግብ እስኪመጣ ስለ ታዋቂዋ ልጁ ማውራት ጀመሩ።ጋሻው ወጣት ልጁ አባቷን እንደ አምላኳ እንደምታየውና ከፈለኩ ውጪ መሄድ እንደምችል ምናምን ሲያወሩ ቆዩ። ወድያው ምግቡ መጣና እጄን ልታጠብ ስነሳ ጋሻውን ይዘሃት ሂድ አለው።ታጥቤ ስመጣ ቶኒኩ ተቀድቶ ነበር የጠበቀኝ።በልቼ ስጨርስ አሁን ጠግቤአለሁ ልጠጣ አልኩና ከተቀዳው ቶኒክ የተወሰነ ተጎነጨሁ”።
በወቅቱ የጠጣችው ቶኒክ ከምታውቀው ጣዕም የተቀየረ ስለመሰላት ብዙ መጠጣት አልቻለችም፤ ወዲያው ታምራት ከቀረበው ምግብ ቢያጎርሳትም እሱም ሳይጥማት ቀረና ተወችው። ከዚህ በኋላ ግን ህንደኬ የሆነውን ነገር ማስታወስ አትችልምⵆ
“ በወቅቱ ራሴን ስለሳትኩ የሆነውን አላስታውስም።ወደ አልጋ እንዴት እንደተወሰድኩ የማውቀው ነገር የለም።ራቁቴን ከአልጋ ላይ ያገኘሁት እኩለ ሌሊት ላይ ነው።አስገድዶ መድፈር ተፈፅሞብኝ ነበር።በዚህ የተነሳ ከፍተኛ ህመም እየተሰማኝ ነው።ሰውነቴ ደክሞ ከአልጋው ላይ መነሳት ሁሉ ተስኖኝ ነበር” በማለት ከደነዘዘችበት ስትነቃ የገጠማትን ትናገራለች።
አሁን እኩለ ሌሊት ነው ክፍሉን ስታየው አታውቀውም። ራሷን ስታይም ራቁቷን ናት ቀን ከጋሻው ጋር ስትገናኝ የለበሰቻቸው ልብሶች መሬት ላይ ተዝረክርከዋል። የታምራት ልብሶች ግን ወንበር ላይ በክብር ተቀምጠው ነበር። ታምራት ደግሞ ከጎኗ ተኝቷል።እሷ ግን አልጋው ላይ መተኛት ቀርቶ መቀመጥ በጣም ነበር የቀፈፋት። ከአልጋው እንደምንም ወርዳ ሱሪዋን ስታነሳ ስልኳን አገኘችው። እንዳያገኝባት በመደበቅ ወደ መታጠቢያ ቤት ለመግባት ስትነሳ ሰምቶ ምን እንደሆነች ጠየቀ። በዚህ ጊዜ ህንደኬ በህመም እጅግ በመረረ ሃዘን ውስጥ በመሆኗ መልስ እንኳን ለመስጠት አልፈለገችም፤ ከቻለ እንደውም ክፍሉን ለቆ እንዲወጣላት ጠየቀችው።
እሱ ግን ምንም እንዳልተፈጠረ የኔ ውድ እያለ ሊያቆላምጣት ሞከረ። ህንደኬ ግን በቀላሉ የምትመለስ አለመሆኗን ሲረዳም ክፍሉን ለቆ ወጣ። እሷም ለአክስቷ ልጅ በመደወል የሆነችውን ልትነግራት ስጀምር እሷ ግን በምላሹ እየቃዠች መስሏት ስልኩን ዘጋችባት።ደግማ በመደወል ቅዠት አለመሆኑን ከቻለች እንድትረዳት ጠየቀቻት፤ ይህንን ጊዜ የአክስቷ ልጅ በመደናገጥ የት እንዳለች ጠየቀቻት እሱንም ለመመለስ ቦታውን በትክክል ማወቅ ያስፈልግ ነበር። ነገር ግን ሁኔታው ከመከሰቱ በፊት ያየችውን የምትገምተውን ምልክት ነገረቻት።
የቀድሞዋ የትምህርት ቤት ጓደኛዋ ርብቃ ጋር እንደምታድር በሰው ተደውሎ የተነገራቸው እናቷም ስለደረሰባት ነገር ሰሙ፤ አሁን ያለችበትን ቦታ ማፈላለጉ ቀጠለ። ከብዙ ጥረት በኋላም ያለችበት ቦታ ተገኘ።
“ጋሻው ያለሁበትን አልቤርጎ ሊያሳይ እየመጣ እንደሆነ በመስኮት አየሁት ልክ ለእሱ በሩን እንደከፈትኩለት ጥቃቱ አዳክሞኝ ነበርና ራሴን ስቼ ወደኩ።ጋሻው በኋላ ላይ ፈፅሞ እንዳላገኘኝና ለታምራት አሳልፎ እንዳልሰጠኝ ሊክድና ታምራትን ሊያስመልጠው ቢሞክርም አልተሳካለትም ።ደፋሪዬ ታምራትም እጅ ከፍንጅ ለመያዝ በቃ። እኔም ለምርመራ ወደ ሆስፒታል ተላኩ። ሕክምና ምርመራ የመጣሁት የተደፈርኩበትንና የለበስኩትን ልብስ እንዳደረኩ ነበር። ሰውነቴን አልታጠብኩም። በመሆኑም የገዛ ሰውነቴ እጅግ ቀፈፈኝ። ሴትነት በጾታ ያጋመደን እህቶቼ ሆይ ራሴን በራሴ ተጠየፍኩት”።
የሕክምናው ጠበብቶች እንደሚሉት የሴቶች ድንግል ሦስት ዓይነት ነው። አንደኛው በተፈጥሮ ድንግልና የሌላቸው ሴቶች ያሉበት ነው።ሁለተኛ ከባድ ዕቃዎችን በማንሳት ምንም ሳይሆን በራሱ በተፈጥሮ የሚሄድ ድንግልናም አለ።ሦስተኛ በሕክምናው በተደፈረችበት ሰዓት ሳይሆን ከተደፈረች በኋላ በሦስተኛው ቀን የሚጠፋ (ብሊድ የሚያደርግ) ድንግልና ነው።በዚህ ምክንያት እያንዳንዱ የሕክምና ሂደት ለእኔ አድካሚና አሰልቺ ነበር በማለት ያለፈችበትን መንገድ ትናገራለች።
እያንዳንዱ ሂደት ከሕክምና ማስረጃ ጋር ተያይዞ ነው የሚከናወነው። ይሄን ለማወቅ በርካታ ጥያቄዎች ይደረጋሉ ። ፍቅረኛ አለሽ የለሽም? የሚሉና ብዙ ብዙ በዛን ሰዓትና ሁኔታ በፍፁም መጠየቅ አለበት ተብሎ የማይጠበቁ ጥያቄ ይነሳሉ። ለምሳሌ ፍቅረኛ አለሽ የለሽም? ተብሎ መጠየቅ አግባብ አለው ብዬ አላምንም የምትለው ህንደኬ ለዚህ ምክንያቷ ደግሞ አለኝ ከተባለ መርማሪዎቹ ከዛ በፊት የነበረ የጾታ ግንኙነት ታሪክ አለ ለማለት ይጠቀሙበታል።የወሲብ ልምምድ ስላላት በተከሳሹ ተደፍራለች ወይም ድንግልናዋን በመደፈር አጥታለች ብለው ስለማይገምቱ ስለመሆኑም ታብራራለች ።በተለይ የመደፈር ጥቃቱ የደረሰው ዕድሜዋ ከ18 ዓመት በላይ የሆነች ሴት በህግ በኩል ምታገኘው ውጤት ብዙም አመርቂ አለመሆኑንም በቅሬታ ታነሳለች ።
“እኔ ስደፈር 18 ዓመቴ ነበር። በዚህ የተነሳ ይሁን በሌላ በማላውቀው ምክንያት ሰውዬው ከቤርጎው ሳይወጣ እጅ ከፍንጅ ቢያዝም የክስ ሂደቱ ከአራት ወራት በላይ ፈጅቷል። በእሱም ብሶ በዚህ ጊዜ ውስጥ ሁሉ ድርጊቱን እሱ ሳይሆን ሌላ ሰው እንደፈፀመው ሁሉ ቆይ እስቲ እናያለን እያለ ይዝት ነበር። ዛቻ ብቻ ሳይሆን ዕድሜዬን ከፍ ለማድረግና ራሱን ከጥፋተኝነት ለማዳን ብዙ ሙከራዎችን አድርጓል። የተወለድኩበት ሆስፒታል፤እንዲሁም የአንደኛ ደረጃ ትምህርቴን እማርበት የነበረ ትምህርት ቤት ድረስ በመሄድ ዕድሜዬን ከፍ አድርጎ ለማስወጣት ጥሯል።ፋይል ለማስጠፋትም በእጅጉ ተግቶ ነበር” በማለት የደረሰባትን ትናገራለች።
በሌላ በኩልም ትላለች ህንደኬ በፍርድ ቤት ሂደት ላይ መጓተት እንዲፈጠር እሷም ተሰላችታ ሁኔታውን እንድትተወው በሚመስል መንገድ ሰውዬው አማርኛና ሌሎች ቋንቋዎች እየቻለ አማርኛ እንደማያውቅ በአስተርጓሚ ሀሳቡን የሚገልፅበት ሁኔታ እንደነበር ትናገራለች።
ይህ ሁሉ አሰልቺ ሂደት ቢታለፍም ህንደኬን የደፈረውም ሆነ ሁኔታውን ያመቻቸለት ጓደኛው ስምንት ዓመት ከአምስት ወር ተፈርዶባቸዋል።ግን በተፈረደባቸው አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሁለቱም ከእሥር ቤት ወጡ። ይህንን የተመለከተችው ህንደኬም ሆነች ቤተሰቦቿ ለምን ሲሉ ለመጠየቅ እንኳን ጊዜ ሳያገኙ አጥፊዎቹ ከሀገር ወጥተው ማምለጣቸውን ሰሙ።
ይህ ሁኔታ ደግሞ ከተፈጠረባት የአስገድዶ መድፈር ወንጀል በላይ ጎዳት።ስቃይዋን አበረታው። ጥቃት ፍትህ ተፈፃሚ ያለመሆኑ በደል ፤በሀብታሞችና በድሆች ሰዎች መካከል ያለው ፍትህ የማግኘት ልዩነት ህንደኬን ከፍ ወዳለ የስነ ልቦና ችግር ውስጥ አስገባት።
“ዳግም ላይጠገን ልቤ ተሰበረ። በእጅጉ ደማ፤ ቆሰለ። በሰፈር፤ በትምህርት ቤት፤ በቤት ውስጥ ከቤተሰብ ጋር የነበረኝ ማህበራዊ መስተጋብር ውሃ የተቸለሰበት ያህል ሙሉ በሙሉ ቀዘቀዘ።ሳቂታና ተጫዋችነቴ ጠፋ። ራሴን የምረሳበት መንገድ እፈልግ ነበር።ለወንድ የነበረኝን ዕምነት አጣሁ።እንኳን አጠገቤ ላስጠጋቸው ከሩቅ ሳያቸው እሸሻለሁ። የ11ኛ ክፍል ትምህርቴን ደግሜ ለመማር ትምህርት ቤት ገብቼ ነበር።ሆኖም ከጓደኞቼ እኩል መሄድ አልቻልኩም። ልቤ በራሴ ችግር ጭልጥ ብሎ እየሄደ በድኔ ብቻ ቁዝም ብሎ መቀመጥ ሆነ።ማንም እንደማይረዳኝ አስብ ነበር። በነዚህና ራሴን እየሳትኩ በመውደቄ፤ ደጋግሜ በመታመሜ መዝለቅ አልቻልኩም።እናም በደረሰብኝ ተገዶ መደፈር መዘዝ ለሁለት ዓመታት ትምህርቴን አቋረጥኩ” ትላለች።
ህንደኬ ከጥቃቱ በፊት ዓላማ ፣ራዕይና ግብ ያላት ጎበዝ ተማሪ ነበረች። በዕድሜ በአንድ ዓመት ከሚበልጣት ወንድሟ ጋር ደረጃቸው አንድ እየሆነ ወላጆቻቸውና የሚማሩበት ትምህርት ቤት ለመሸለም ይቸገሩ ሁሉ ነበር ፤ ግን ጥቃቱ ከደረሰባት በኋላ ይሄ ሁሉ ጥንካሬና ብርታቷ ጠፍቶ ባዶ ቀረች። በጣም ስለተጎዳችም አንዳንድ ስም የሚጠየቅባቸው ቦታዎች ላይ ስትሄድ ራሱ ጭልጥ ብላ ስለምትጠፋ የገዛ ስሟ ይጠፋት ነበር።
የሕክምናው ሙያ እና ሕጉ ይሄን ሁሉ የተጠቂዋን የስነ ልቦና በደል የሚያገናዝብ አለመሆኑ አሁንም እንደሚንበለበል እሳት ያቃጥላታል።
ዛሬ ላይ በፈጣሪ እርዳታ በእናቷ ብርታት ወደ ራሷ ተመልሳለች ።”ነገሮች ከብደው ሲመጡ እንዴት ማቅለልና መቋቋም እንደሚቻል ከእናቴ ተምሬያለሁ። አርአያነቷ ወደ ራሴ እንድመለስ አድርጎኛል።መቼም ከጎኔ ተለይታኝ የማታውቀው ጓደኛዬም ለእኔ መለወጥ ድርሻዋ ብዙ ነው። ዛሬ ላይ 21 ዓመቴ ነው። 22ኛዬን ለመያዝም የጥቂት ወራት ናቸው የሚቀሩኝ።ትምህርቴን በጥቃቱ ካቋረጥኩ ከሁለት ዓመት በኋላ ቀጥዬ 12ኛ ክፍል አጠናቅቄያለሁ። ወደከፍተኛ ትምህርት ተቋምም ገብቼ ዘንድሮ የሶስተኛ ዓመት የነርሲንግ ተማሪ ነኝ” በማለት ከወደቀችበት መነሳቷን ትናገራለች።
አሁን ላይ ህንደኬ ሴቶችና ህፃናት ያልተገባና ሰዋዊ ባልሆነ ባህርይ ባላቸው ሰዎች እንዳይጠቁ የሚያግዝ መከርቻ ቻሪቲ ኦርጋናይዜሽን (MEKRECHA CHARITABLE ORGANIZATION) የተሰኘ ሴት ህፃናትን ብቻ ሳይሆን ወንዶችንም አስገድዶ ከመድፈርና ከተለያዩ ጥቃቶች የሚከላከል ድርጅት በመመስረትና ስራ አስኪያጅ በመሆን እየሰራች ትገኛለች።
“ህፃናት እንዲሁም ሴቶች ለጥቃት እንዳይጋለጡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እየሰራሁ ያለሁት ከታናሽ እህቴ ጋር ነው። ለዚህ ዋናው ምክንያቴ ደግሞ እኔ ላይ የደረሰው ጉዳት ነው። በግሌ ጾታዊ ጥቃቱ ከደረሰብኝ በኋላ ወንድ ልጅ ከሴት ልጅ ገላ የዘለለ አመለካከት እንዳለው ያየሁበትም አጋጣሚ አለ።የደፈረኝ ወንድ የመሆኑን ያህል አሁን ላይ ድርጅቴ ራሱን ችሎ በሁለት እግሩ እንዲቆም በማድረጉ ረገድ በከፍተኛ ሁኔታ እያገዘኝ ያለውም የሥራ አጋሬ ወንድ ነው።ያልሆኑ ወንዶች እንዳሉ ሁሉ መልካም ወንዶችም አሉ”ትላለች። የእሷን ድርጅት ጨምሮ በርካቶች በሴቶች ጥቃት ላይ ብዙ ስራ እየሰሩ ቢሆንም ዛሬም በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት አልቆመም እንደውም ተባብሶ ቀጥሏል። ድብደባ፤መደፈር አንዳንድ ባሎችና የወንድ ጓደኞች የትዳር አጋራቸውን እስከመግደል የደረሰ ኢ ሰብዓዊ ድርጊት ሁሉ እየፈጸሙ ነው። ሆኖም በሕግ የሚጣለው ቅጣትም ሆነ በሌላ አካላት የሚወሰደው እርምጃ አስተማሪነቱ ላይ የብዙዎች ጥያቄ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ጥቃት የደረሰባቸውም ሆኑ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እንዲሁም ሌሎች የችግሩን አሳሳቢነት የተረዱት አይመስልም ምክንያቱም አንድ ሰሞን ሆይ ሆይ ይባልና ሁሎም ነገር ይረሳል።ይህ ደግሞ ችግሩ ተዳፍኖ እንዲቀር ቀን እየጠበቀ እዚህም እዚያም እንዲፈነዳ እያደረገው ነው ትላለች ህንደኬ።
“እሳት በአንድ እንጨት ሳይሆን በብዙ እንጨት ጥምረቶች እንደሚነድ ሁሉ ጥቃቱን በጋራ ትግል ማስቆም ይገባል። ግለሰብ፤ቤተሰብ፤ የሕግ አካላት፤የሃይማኖት ተቋማት፤መምህራን ፤የነቃ ተሳትፎ ማድረግ አለባቸው።በግሌ እንዲህ ራሴን አሳልፌ እስከመስጠት በመድረስ ታሪኬን አርአያ አድርጌ እየታገልኩ እገኛለሁ።ሆኖም ትግሉ ቀላል አይደለም።በርካታ ባለሀብቶች፣ አንቱ የተባሉ ሰዎች ከጾታዊ ጥቃት ተነካክተዋል። በመሆኑም በሃሳብም ሆነ በገንዘብ መደገፍ አይፈልጉም። ማህበሩ በ2012 ዓ.ም ቢመሰርትም ድጋፍ አግኝቼ ቢሮ የከፈትኩት በቅርብ ነው” በማለት በዘርፉ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች እየተገኙ ያሉ ድጋፎችም አመርቂ አለመሆናቸውን ትናገራለች።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ኅዳር 27/ 2015 ዓ.ም