ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በጠላትነት ከመፈራረጅ ወጥተው ወዳጅነት ከመሠረቱ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ የእነዚህ አገራት ወዳጅነት መጠናከር ደግሞ በምስራቅ አፍሪካ ያለውን ዲፕሎማሲ እና ተያያዥ ሁኔታዎችን እንደቀየረ ይታመናል፡፡
«የምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ከበስተጀርባው በርካታ አካላት ያሉበትና አያሌ የዓለም ክፍሎች ፍላጎትና ሽኩቻ የሚንፀባረቅበት ነው» የሚሉት በመካከለኛው ምስራቅ የማስተርስ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት እና ፖለቲከኛው አቶ ትዕግስቱ አወሉ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ከቅኝ ግዛት ነፃ አገር ብትሆንም፤
በምስራቅ አፍሪካ ያሉት አገራት ግን የራሳቸውና የቅኝ ገዥዎቻቸው ፍላጎት የሚስተዋልበት ብሎም ከፍተኛ ሽኩቻ ያለበት ነው፡፡ ለአብነትም ኢትዮጵያ ከሞቃዲሾ ጋር ግንኙነቷን ስታጠናክር ራሳቸውን ከዋናዋ ሶማሊያ ያገለሉት ፑንትላንድ እና ሱማሌላንድ ፍላጎት መዘንጋት የለበትም፡፡ በሌላ መንገድ ደግሞ እነዚህ ሁለት ግዛቶች የቅኝ ገዥዎቻቸው የእንግሊዝ እና ጣሊያን ፍላጎት ብሎም ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖረውን ሁሉን አቀፍ ግንኙነት ማጤን ይገባል ሲሉ ያሳስባሉ፡፡
ከጅቡቲ ጋር ያለው ወዳጅነት ዘመናትን ያስቆጠረ ቢሆንም፤ ቅኝ ገዥዋ የነበረችው ፈረንሳይ ፍላጎት ግን አልከሰመም፡፡ በደቡብ ሱዳን ያለው አለመረጋጋትም በኢትዮጵያ ላይ እየፈጠረ ያለው ጫና ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም ብለዋል፡፡
ስደተኞችን መቀበል ሰብዓዊነት ቢሆንም፤ ከደቡብ ሱዳን የሚሰደዱት የኑዌር ጎሳዎች ጋምቤላ ክልል መክተማቸውና የበርካታ አገራት ስደተኞች ኢትዮጵያን መዳረሻ ማድረጋቸው በጊዜ ሂደት ጫና መፍጠሩ የማይቀር ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለቀጣናው እንግዳ የሆነው ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ያለመስፈን፣ በቀጣናው የመሰረተ ልማትና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ባለማደጉ ኢኮኖሚያዊ ሽኩቻውን ያጦዘዋል፡፡ በመሆኑም በቀጣናው የሚኖረው አሉታዊ ገፅታ፤ የበርካቶች ትኩረት በሆነችው ኢትዮጵያ ላይ የሚፈጥረውን አሉታዊ ተፅዕኖ የገዘፈ መሆኑንም ይጠቁማሉ፡፡
እንደ አቶ ትዕግስቱ ማብራሪያ፤ በዓለም ኃያላን የሆኑት እንደ ቻይና እና አሜሪካ ያሉ አገራት ደግሞ በምስራቅ አፍሪካ ጫና ለመፍጠር ትልቅ ፉክክር ውስጥ ናቸው፡፡ በሌላ መንገድ ለኢትዮጵያ የኤርትራን ወደቦች መጠቀሙ አዋጭ እንደሆነ ሁሉ፤ ከቀጣናው ፖለቲካና አዋጭነት አኳያ የመካከለኛው ምስራቅ አገራትም የኤርትራን ወደቦች ቢጠቀሙ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያስገኝላቸዋል፡፡ ሆኖም የኤርትራን ወደቦች መጠቀሙ ለኢትዮጵያ ተስፋ ቢሆንም፤ በዚህ አካባቢ ፍላጎታቸው የበዛ አገራት መበራከት ጥንቃቄ ካልታከለበት ችግሮች ሊገጥሙ ይችላሉ ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡
በመካከለኛው ምስራቅ ኃያል ሆኖ ለመውጣት በሚደረገው ሽኩቻ ሳውዲዓረቢያ እና ኢራን ዋነኞቹ ተዋናይ ሆነው መጥተዋል፡፡ የየራሳቸውን የኃይል አሠላለፍ ለማጠናከር እየተራኮቱ ነው፡፡ በምስራቅ አፍሪካም አሻራቸው ጎልቶ እንዲወጣ ትልቅ ፍላጎት አላቸው፡፡ እነዚህን ሁነቶች ደግሞ በኢትዮጵያ ሆነም በምስራቅ አፍሪካ አገራት ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው፡፡ ግብፅም ሚናዋን ለመወጣት ትልቅ ዋጋ ለመክፈል ትፈልጋለች ሲሉም ያብራራሉ፡፡
እንደ አቶ ትዕግስቱ ሃሳብ፤ ኤርትራ በዓረብ ሊግ በታዛቢነት የምትሳተፍ በመሆኑ፤ ለኢትዮጵያ የሚኖረውን አንድምታ በቅጡ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ በኤርትራ የሚፈጠረው መልካም ይሆን መጥፎ አጋጣሚም ለኢትዮጵያ ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ ስለሆነም ከኤርትራ ጋር ያለው ሁኔታ በጠንካራ መሠረት ላይ እንዲገነባ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የኢትዮጵያን የኃይል አሰላለፍና ዘላቂ ጥቅምን በሚገባ ማጥናት ይገባል፡፡ ውጭ ጉዳይ ፖሊሲም ከእነዚህ ሁኔታዎች አኳያ ሊፈተሽ ይገባል፡፡
እነዚህ ውጫዊ ሁኔታዎችን በየጊዜው መፈተሽ ተገቢነቱ እንዳለ ሆኖ፤ ከምንም በላይ ግን ውስጣዊ ችግሮችን መቋቋም ከተቻለ የውጭውን ጫና ለመቋቋም ትልቅ አቅም ይፈጥራል፡፡ ይሁንና በአሁኑ ወቅት የሚስተዋለው ውስጣዊ ጡዘት መፍትሄ ካልተበጀለት ለውጭ ጣልቃ ገብነት በር ይከፍታል፡፡ ወደ አገር ውስጥ የገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የቀድሞ መሰረታቸው በኤርትራና ሌሎች አገራት ስለነበር፤ አሁን ካለው አካሄድ ጋር በጥልቀት መገምገም ያስፈልጋል፡፡ በአጠቃላይ በምስራቅ አፍሪካ የሚዘወረው የፖለቲካ ምህዋር ከኢትዮጵያ ጥቅም አኳያ በሚገባ መተንተን እንዳለበት ይመክራሉ፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት ሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ አቶ ሄኖክ ተስፋይ፤ የምስራቅ አፍሪካ የፖለቲካ የልብ ትርታ ዋነኛ መሰረቱ ኢትዮጵያ መሆኗ መዘንጋት እንደሌለበት ይጠቅሳሉ፤ በዚያው ልክ የበርካታ አገራት ፍላጎትና የጥቅም ሽኩቻ በቀጣናው መኖሩን ያብራራሉ፡፡
አቶ ሄኖክ እንደሚሉት፤ የምስራቅ አፍሪካ ሁኔታ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የቀይ ባህር አካባቢ ያለው እንቅስቃሴ ዓረቡን ዓለም ሽኩቻ ውስጥ የከተተ ሲሆን፤ የኃይል አሠላለፉም በተለያዩ አካላት ጡንቻ ማሳያ እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡ በምስራቅ አፍሪካ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ወዳጅነት መፍጠር ሁለቱን አገራት በእጅጉ የሚጠቅም ቢሆንም ካለው ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ አኳያ ግን፤ ጥንቃቄ የተሞላበት አካሄድ ያስፈልጋል፡፡ በተለይም ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት ስትጠቀምባቸው የነበሩት የጅቡቲ ወደቦች ትኩረት መነፈግ እንደሌለበትና በዚያው ልክ የኤርትራ ወደቦች በአግባቡ መጠቀም ሊታሰብበት ይገባል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት በኤርትራ ላይ ጥሎት የነበረው ማዕቀብ እንዲነሳ መወሰኑ የበርካታ አገራትን ቀልብ እንደሚስብና በዚያው ልክ ወዳጅነት ለማጠናከር የሚታትሩ አገራት በርካታ እንደሚሆኑ የሚናገሩት አቶ ሄኖክ፤ እነዚህ አካሄዶች ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ያላትን የጎላ ሚና እንዳያሳንሰው አፅንኦት መስጠትና ከሁኔታዎች ጋር የሚጣጣም ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ አካሄድ መከተል ያስፈልጋል ይላሉ፡፡
በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል በነበረው አለመግባባትና ጦርነት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ለእልቂት ተዳርጓል።ለሁለት አሥርት ዓመታትም የሁለትዮሽ ግንኙነታቸው ተቋርጦ ቆይቷል፡፡ ኤርትራም በኢትዮጵያ፣በጅቡቲ እና ሌሎች የቀጣናው አገራት ትከተለው በነበረው የፀብ አጫሪነት ፖሊሲ በተባበሩት መንግሥታት ማዕቀብ ተጥሎባት መቆየቷ ይታወሳል፡፡ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካዊ አካሄድ እየተለወጠ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ምሁራኑ እንደሚሉት፤ የምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መዘውሮች ለኢትዮጵያ የሚኖራቸው ፋይዳ እና ጉዳት ከውስጣዊ ጥንካሬ የሚነሳ ይሆናል፡፡ከአካባቢያዊ ፖለቲካ አኳያ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ወዳጅነት ከፍተኛ ጠቀሜታ ቢኖረውም፤ ግንኙነቱ ገና መሠረት የያዘ ባለመሆኑ አገራቱ በሚገባ ሊሠሩበት ይገባል፡፡ውስጣዊ መከፋፈሎችና ሽኩቻዎች ለውጭ አገራት ጣልቃ ገብነት በር የሚከፍት በመሆኑ በምስራቅ አፍሪካ የሚኖራትን ተፅዕኖ በእጅጉ ያኮስሳል፡፡
በሌላ ጎራ ደግሞ ጠንካራ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እና ውስጣዊ ጥንካሬ ሲኖር አገራት የራሳቸውን ፍላጎት የማስቀደም ሳይሆን በጋራ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ ለመከተል ይገደዳሉ፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ያላትን ሚና ለማስቀጠል ሁኔታዎችን በጥልቀት መተንተንና ከብሄራዊ ጥቅም አኳያ የኃይል ሚዛን ጠብቆ መጓዝ ያስፈልጋል፡፡ በምስራቅ አፍሪካ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነት የበርካታ አገራትን ፖሊሲና አቋም የሚፈትሽ ሲሆን፤ በቀጣይ በምስራቅ አፍሪካም አዳዲስ ክስተቶችን ሊያስከትል ይችላል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 24/2011
በክፍለዮሐንስ አንበርብር