
ዜና ሐተታ
ኢትዮጵያ ካላት የሕዝብ ቁጥር 70 በመቶ የሚሆነው ወጣት ትውልድ እንደሆነ በተለያየ መልኩ ይገለጻል፤ ወጣትነት ለመሥራት፤ ለመገንባት እንዲሁም፤ ሀገርን ለመጠበቅ ትልቅ አቅም እና ግለት ያለበት የእድሜ ደረጃ እንደመሆኑ፤ ከአጠቃላይ ሕዝብ ብዛት አንጻር ትልቁን ድርሻ መያዙ በሁሉም ዘርፍ ፈጣን ውጤት ለማምጣት በእጅጉ ያግዛል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት፤ ‹‹ወጣቶች የለውጥ አንቀሳቃሽ ኃይል ናቸው፡፡ ወጣትነት ውስጥ እሳትና ከባድ ግለት አለ፡፡ ይህንን እሳት ብረት አቅልጡበት፤ ወንዝ ጥለፉበት፤ ተራራ ናዱበት፤ ፋብሪካ ገንቡበት፤ ድልድይ አንጹበት፤ ከምንም በላይ ደግሞ፤ ይህን እሳት ሕይወት ለማዳን ተገልገሉበት›› ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።
እሳት በአግባብ ካልተጠቀሙበት አጥፊ እንደመሆኑ ሁሉ፤ ወጣትነትም በሥነ-ምግባር ካልታነጸ ጉዳቱ የከፋ ይሆናል። ከዚህ አንጻር ወጣቱ ግንዛቤ ኖሮት ለሀገር ግንባታ እና ሰላም ዘብ እንዲቆም ያለመ ውይይት ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከተውጣጡ ወጣቶች ጋር ባለፈው ወር ውይይት ተካሂዷል። ይህን ሀገራዊ መድረክ መነሻ በማድረግ በሀገር ግንባታ ሂደት የወጣቱ ሚና ምን መሆን አለበት? በሚል አዲስ ዘመን ጋዜጣ ወጣቶችን አነጋግሯል።
ሁሉንም የልማት ሥራ መሥራት የሚቻለው ሀገር ሰላም ስትሆን ነው የሚለው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ የወጣቶች ክንፍ ምክትል ሰብሳቢ ወጣት ሞርካ ጉሬ፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ ለሀገር ግንባታ እና ሰላም መስፈን የወጣቶች ሚና እጅግ በጣም ወሳኝ ነው ይላል።
ከዚህ በፊት ወጣቱ ለሀገር ሰላም ዋጋ ሲከፍል እንደቆየ አስታውሶ፤ በአሁኑ ዘመንም የሀገር ሰላም እንዲቀጥል ወጣቱ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ለሚናፈሱ ሐሰተኛ ወሬዎች ጆሮውን ሳይሰጥ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር ለሀገሩ ሰላም መሥራት እንዳለበት ይገልጻል። የኢትዮጵያ ሰላም የማይፈልጉ አካላት መኖራቸው ጠቅሶ፤ ወጣቱ እነዚህን ኃይሎች በጋራ ሊታገል ይገባል ሲል ያስረዳል።
መንግሥት በርካታ የልማት ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል የሚለው ወጣት ሞርካ፤ ወጣቱም እነዚህን ሥራዎች የማገዝ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ይላል፤ የወጣቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑ ታምኖበት መንግሥት በአመራር ደረጃ ወጣቶች ሰፊ ድርሻ እንዲኖራቸው በተለያዩ ቦታዎች ላይ እንዲያገለግሉ አድርጓል፤ ወጣቶች በሀገራቸው ሰላምና ልማት ከመንግሥት ጎን መቆም እንዳለባቸውም ይጠቁማል።
“እኛ ወጣቶች እንደ ሀገር ከፍተኛውን ቁጥር የምንይዝ እንደመሆናችን ለሀገር ሰላምና ለፖለቲካ መረጋጋት ትልቅ ሚና መጫወት አለብን፤ ምክንያቱም ቀጣይ ሀገር ተረካቢ እንደመሆናችን የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ኃላፊነታችንን መወጣት አለብን” የምትለው ደግሞ፤ ከሲዳማ ክልል የመጣችው ወጣት ራሔል ማቴዎስ ናት።
‹‹ኢትዮጵያ ሰፊና በርካታ ባህልና ማንነት ያላት ሀገር እንደሆነች የምታነሳው ወጣት ራሔል፤ ሁሉም ባለበት አካባቢ ለግጭት የሚያነሳሱ ጉዳዮች ሲያጋጥሙት ሰከን ባለ መንፈስ ተወያይቶ፤ በሰላማዊ መንገድ ችግሩን በመፍታት ሰላሙን ሊጠብቅ ይገባል፤ እንደዚህ ዓይነት ልምድ እየጎለበተ ሲመጣ ሀገር ሰላም ትሆናለች›› ስትል ትናገራለች።
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 የወጣት ክንፍ ሰብሳቢ የሆነው ወጣት ቶኩማ መገርሳ በበኩሉ እንደሚናገረው፤ ‹‹ወጣቶች ለሰላም ዘብ በመቆም የሀገራቸውን ደኅንነት ለማስጠበቅ ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ። ከዚህ አንጻር ሁሉም ወጣት ከራሱም አልፎ እስከታች ድረስ በመወረድ ማኅበረሰቡ ለሰላም ዘብ እንዲቆም የማድረግ ኃላፊነት አለበት ›› ይላል።
በማኅበራዊ ሚዲያ የሀገርን ሰላም የሚያፈርሱ ሐሰተኛ ወሬዎች ብዙ ጊዜ ይሰራጫሉ። በዚህ መልኩ የሚሰራጩ ሐሰተኛ እና የአሉባልታ ወሬዎች የሀገርን ሰላም ያበላሸሉ የሚለው ወጣት ቶኩማ፤ ይሁንና ወጣቱ ሀገርን ለማፍረስ የሚለቀቁ ሐሰተኛ መረጃዎችን በመለየት ለሀገር ሰላም መሥራት እንዳለበት ይመክራል።
የወጣቶች ሚና እንደ ሀገር የሚታዩ ውስጣዊ እና ውጫዊ ችግሮችን በማስተዋል ለመፍትሔ በጋራ መቆም፤ በተነሳሽነት እና በሥነ ምግባር ሥራ መሥራትን ባህል ማድረግ ከወጣቱ የሚጠበቅ እንደሆነ ከትምህርትና ምዘና አገልግሎት የመጣችው ወጣት እየሩስ ይመር ትናገራለች።
ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔሮች እና ሃይማኖቶች መኖሪያ ናት የምትለው፤ ወጣት እየሩስ ፤ ከዚህ አንጻር ወጣቱ ዜጋ ልዩነቶችን ተረድቶና ብዝኃነትን አክብሮ በሰላም ቢኖር መልካም እንደሆነ አስረድታ፤ ከዛም ባለፈ የተሰማራበት የሥራ ዘርፍ ገቢ የሚያስገኝለት እንደሆነና ሕጋዊ እና ማኅበራዊ ዕሴትን የጠበቀ መሆኑን አረጋግጦ መሥራት ይኖርበታል ብላለች።
ያለፉት አባቶች በገባቸው ልክ ሠርተው ሀገርን ለዛሬ ትውልድ አድርሰዋል። የአሁኑ ትውልድም ነገ አዛውንት ሆኖ ታሪክ ጠቃሽ እንደሆነ በማንሳት፤ ወደፊት የተቃና ነገር እንዲኖር ነገሮችን ሥነ ምግባር በተሞላበት መልኩ ሊከውን ይገባል ስትል ታስረዳለች።
በዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን እሁድ ሐምሌ 6 ቀን 2017 ዓ.ም