ከወራት በፊት በኦሪገን በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና የማራቶን ባለ ድል የሆነው ኢትዮጵያዊ አትሌት ታምራት ቶላ ነገ በስፔን ቫሌንሲያ ማራቶን ይወዳደራል።
ታላላቅ የዓለማችን የማራቶን አትሌቶች በሚፎካከሩበት የቫሌንሲያ ማራቶን የዓለም የርቀቱ ቻምፒዮን ትልቅ የአሸናፊነት ግምት የተሰጠው ሲሆን የቦታውን ክብረወሰን ለማሻሻል እንደሚወዳደርም ታውቋል። ከዓለም ቻምፒዮና ድሉ በኋላ የመጀመሪያ የማራቶን ውድድሩን የሚያደርገው ታምራት በርቀቱ የዓለም አምስተኛው ፈጣን ሰዓት ባለቤት ሲሆን 2020 ላይ የተመዘገበውን 2:03:00 የሆነ የቫሌንሲያ ማራቶን ክብረወሰን ያሻሽላል ተብሎ ይጠበቃል።
ታምራት በርቀቱ የዓለምን አምስተኛ ፈጣን ሰዓት ያስመዘገበው የዓለም ቻምፒዮን ከመሆኑ ከአንድ አመት በፊት አምስተርዳም ማራቶን ላይ ሲሆን ሰዓቱም 2:03:39 ነበር። የዓለም ቻምፒዮን ከመሆኑ በፊት በመምና አገር አቋራጭ ውድድሮች አጭር ጊዜ ቆይታው ስኬታማ መሆን የቻለው ታምራት በኦሊምፒክና በዓለም ቻምፒዮና የብርና የነሐስ ሜዳሊያዎችን በማራቶን ማጥለቅ እንደቻለ ይታወሳል።
ነገ በቫሌንሲያ ማራቶን በሚያደርገው ፉክክርም ከአሸናፊነት በዘለለ የውድድሩን ክብረወሰን እንዲሁም የራሱን ፈጣን ሰዓት ለማሻሻል እንደሚሮጥ ተስፋ አድርጓል። “የለንደን ማራቶንን ለመወዳደር ካልቻልኩኝ በኋላ በቫሌንሲያ እንድሮጥ የቀረበልኝን ጥሪ በደስታ ነው የተቀበልኩት” በማለት ለመገናኛ ብዙሃን አስተያየቱን የሰጠው ታምራት ባለፈው ለንደን ማራቶን መወዳደር ያልቻለበትን ምክንያት እንዲህ ሲል ያስረዳል “ከዓለም ቻምፒዮናው ድል በኋላ ለ15 ቀን ማገገም ነበረብኝ፣ ይህ ማለት ደግሞ በ60 ቀናት ውስጥ በለንደን ማራቶን ለመወዳደር መዘጋጀት አለብኝ፣ ይህ ደግሞ ለንደን ላይ ጥሩ ውድድር ለማድረግ በቂ ነው ብዬ አላምንም”።
የቫሌንሲያ ማራቶን በርቀቱ ፈጣን ሰዓት የሚመዘገብበት እንደሚሆን ያለውን እምነት የገለጸው ታምራት በውድድሩ ላይ ነገሮች ጥሩ ከሆኑ የራሱን ፈጣን ሰዓትና የውድድሩን ክብረወሰን ለማሻሻል ጥረት እንደሚያደርግ አስረድቷል።
በዓለም አትሌቲክስ የወርቅ ደረጃ ከተሰጣቸው የጎዳና ላይ ሩጫዎች መካከል አንዱ በሆነው በዚህ የሩጫ ውድድር ላይ በወንዶች መካከል በሚደረገው ፉክክር ከታምራት በተጨማሪ ሌሎች የርቀቱ ከዋክብት ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ርቀቱን ከ2 ሰዓት ከ05 ደቂቃ በታች የሮጡ ሰባት ያህል አትሌቶች ተፎካካሪ እንደሚሆኑ በሚጠበቀው በዚህ ውድድር ፈጣን ሰዓት ያለው ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ጌታነህ ሞላ ነው፡፡ በርቀቱ ያለው ፈጣን ሰዓት 2:03:34 ሲሆን በዚህ ዓመት በተካሄደው የቶኪዮ ማራቶንም ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቁ ይታወቃል፡፡ 2:04:27 የሆነ ሰዓት ያለው ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ዳዊት ወልዴ ደግሞ ሶስተኛውን ፈጣን ሰዓት ይዞ በነገው ውድድር ተፎካካሪ ይሆናል፡፡
በተመሳሳይ በሴቶች መካከል በሚካሄደው ውድድርም ኢትዮጵያዊት የ10ሺ ሜትር የዓለም ቻምፒዮን በርቀቱ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደምትወዳደር ቀደም ብሎ ተዘግቧል፡፡ በ5 ሺ እና 10ሺ ሜትር እንዲሁም በ15 ኪሎ ሜትር የዓለም ክብረወሰን ባለቤት የሆነችው ለተሰንበት ግደይ በስኬታማነት ከምትታወቅበት የመም ውድድር ወደ ማራቶን ፊቷን ያዞረችበት የመጀመሪያው ውድድር ሆኗል፡፡ ባለፈው ዓመት በዚሁ የቫሌንሲያ ግማሽ ማራቶን ሮጣ 1:02:52 በሆነ ሰዓት በማግባት የርቀቱን የዓለም ክብረወሰን በእጇ ያስገባችው ለተሰንበት፣ አሁን ደግሞ በረጅሙ ርቀት የማራቶን ውድድር ልታደርግ መዘጋጀቷን ግሎባል ስፖርት ኮሙዩኒኬሽን የተሰኘው የስልጠና ቡድኗ አስቀድሞ ማሳወቁ ይታወሳል፡፡ ይህንን ተከትሎም የአትሌቷ አሰልጣኝ ኃይሌ እያሱ ከለተሰንበት ጋር ከዓመታት በፊት በ5ሺ ሜትር እና 10ሺ ሜትር እስከ ማራቶን የዓለምን ክብረወሰን መስበር የሚል እቅድ እንደነበራቸው ገልጿል፡፡ በዚህ መሰረት አትሌቷ አሁን በደረሰችበት ማራቶን ብቃት አዲስ ነገር ልታስመለክት ትችላለች በሚል ትጠበቃለች፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ኅዳር 24/ 2015 ዓ.ም